Monday, July 11, 2016

ዜጎችን ማፈናቀል መግደልና ማሰደድ የህወሃት አይነተኛ መግለጫዎች ናቸው

ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ በአገራችንና በህዝባችን ላይ ሲፈጽም የቆየውና እየፈጸመ ያለው ግፍና ስቃይ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደልም። አፈና፣ እስር፣ ግድያና ዜጎችን ማፈናቀል አይነተኛ መግለጫዎቹ የሆነው ይህ የህወሃት አገዛዝ፣ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችንና የከተማ ቦታዎችን በመቸብቸብ ሃብት ለማካበት ባለው ዕቅድ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን እትብታቸው ከተቀበረበት ቀዬና የትውልድ መንደሮቻቸው በግፍ እንዲፈናቀሉ አድርጎአል። አሁንም እያደረገ ነው። ሰሞኑን በአዲስ አበባ በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ቀርሳና ኮንቶማ በተባሉ ቀበሌዎች ከ30 ሺ በላይ የሚገመት ህዝብ ለአመታት ከኖረበት መኖሪያ ቤቶች በሃይል ተገፍትረው በመውጣት ጎዳና ላይ እንዲበተኑ ተደርጎአል። በዚህም እርምጃ ምክንያት አቅመደካማ የሆኑ አዛውንቶች፤ ነፍሰጡሮችና ከወለዱ ገና ሳምንታት ያልሞላቸው እመጫቶች፤ የሚያጠቡ እናቶች፤ ህጻናትና ለጋ ወጣቶች ለከፋ ችግር ተዳርገው ለቅሶና ዋይታ በማሰማት ላይ ናቸው። በስንት ልፋትና ድካም ከሰሩዋቸው ቤቶች ተለዋጭ ቦታ ሳይሰጠን ወይም ካሳ ሳይከፈለን አንወጣም በማለት ለማንገራገር የሞከሩ 10 ሰዎች በፖሊስ ጥይት ተገደለዋል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ለእስር ተዳርገዋል። ህወሃት እንዲህ አይነት የጭካኔ እርምጃ እየወሰደ ያለው በክፍለ ከተማው የሰፈሩት ሰዎች “ህገወጦች ናቸው” በሚል ሰበብ ነው። ትናንት ባዶ እግራቸውን ነፍጥ አንግበው ቤተመንግሥቱን የተቆጣጠሩና ጄሌዎቻቸው ከመሃል ከተማው ዜጎችን እያፈናቀሉ ቪላና ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ሲገነቡ ህገወጥ ያልተባሉት ሰዎች፣ አረብ አገር ድረስ ተጉዘው በግርድና ሥራ ሳይቀር በመሥራት ባገኙት ገንዘብ በአገራቸው መሬት ላይ ጎጆ የቀለሱ ለምንድነው ህገወጥ የሚባሉት የሚለውን ለታሪክ ፍርድ እንተወውና እነዚህ ህገወጥ የተባሉ ሰዎች በመንግሥት ይዞታ ሥር ካሉ የአገልግሎት ድርጅቶች ጋር ተዋውለው መብራትና ውሃ አስገብተው ሲጠቀሙ መኖራቸው፤ ገንዘብ በማዋጣት መንገድ፤ ጤና ጣቢያዎችንና ትምህርት ቤቶችን በከተማው አስተዳደር ድጋፍ ማስገነባታቸው፤ የህወሃት የንግድ ድርጅቶች በሚሊዮኖች የሚቆጠር ትርፍ ለሚዝቁበት የአባይ ግድብ ቦንድ በየመኖሪያቤታቸው ቁጥር ሲሸጥላቸው የነበረና የምዕራቡን አለም ለማደናገር በየአምስት አመቱ የሚደረገውን የምርጫ ድራማ ለማድመቅ በግዳጅ እንዲመዘገቡና ድምጽ እንዲሰጡ ሲደረጉ መቆየታቸው ብቻውን አገዛዙ ሲመቸው እውቅና ሰጪ ሳይመቸው ደግሞ እውቅና ነሺ መሆኑን የሚያሳይ፣ ለፍትህና ለርእትዕ የማይሰራ የዘራፊዎች ቡድን በመሆኑ፣ የድሆችን ቤቶች ለማፍረስ የወሰደው እርምጃ በየትኛውም መስፈረት ተቀባይነት የሌለው ህገወጥ ድርጊት ነው። ለነገሩ ህገወጥ ከሆነ ቡድን ህጋዊነትን መጠበቅ አይቻልምና ወያኔ በህግ ሽፋን የሚወስዳቸው እርምጃዎች ሁሉ ህገወጥነታቸውን አይለውጠውም።
አባቶቻችን አገራቸውን ከባዕድ ወረራ ለመከላከል ደማቸውን ያፈሰሱትና አጥንታቸውን የከሰከሱ መጪው ትውልድ በአገሪቱ አንገት ማስገቢያ ጎጆ እንዲኖረው በማሰብ እንጅ፣ በደምና በአጥንት የተገዛው መሬት ለውጭ አገር ዜጎች እንዲቸበቸብ ወይም በመንግስት ስም የተደራጁ ሽፍቶች እንዲዘርፉት አልነበረም።
ሌላው አስገራሚና አሳዛኙ ነገር እንዲህ አይነት ሰቆቃ የተፈጸመባቸውና በዚህ ክረምት ወቅት ቤቶቻቸው ፈርሶና ንብረቶቻቸው ወድሞ ወደ ፍጹም ድህነት እንዲገቡ በተደረጉት ዜጎች መሬት ላይ፣ ህወሃት ኮንዶሚኒዬሞችን ገንብቶ ለዲያስፖራ ለመቸብቸብ ዕቅድ ያለው መሆኑ ነው። ዲያስፖራው አገዛዙ በወገኖቹ ላይ የሚፈጽማቸውን ሰቆቃና ግድያ በማጋለጥ ሥራ ላይ በመጠመዱ የህወሃት መሪዎች እረፍት አጥተዋል። በተለይ ከምርጫ 97 ወዲህ አጋዚ የተባለው ሃይል በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል የቀን ጉዳይ ካልሆነ በቀር በአለም አቀፍ ወንጀል እንደሚያስጠይቅ ወያኔ ይረዳል። ይህንን ስጋት ለማስቆም የዲያስፖራን እንቅስቃሴ ማዳከም እንደስትራቴጂ ነድፎ መንቀሳቀስ የጀመረው የነ ቴዎድሮስ አድሃኖም አገዛዝ፣ ዲያስፖራውን በጥቅም በመከፋፈል ስጋቱ ይቀነሳል ብሎ ያምናል። ከዚህም በተጨማሪ አገር ውስጥ የሚደረገውን አልገዛም ባይነት ትግል ለማጠናከር የዲያስፖራው እምቅ ሃይል የሚፈጥረውን ተአምር ህወሃት አውቆታል። ላፍቶ ክፈለ ከተማ 40 በ 60 በተባለው ፕሮጄክት የኮንዶሚኒዬም ባለቤት በመሆን የአገራቸውንና የወገኖቻቸውን ስቃይ ለማራዘም ላኮበኮቡ የዲያስፖራ አባላት እየተመቻቸች ያለ ሰፈር ነው። ከውስጧ እየተሰማ ያለው ለቅሶና ዋይታ የማይቆረቁራቸው ፤ ኮንዶሚኒዬም ቤት የሚያማልላቸው ዲያስፖራዎች አይኖሩም አይባልም።
አርበኞች ግንቦት 7 የህወሃት አገዛዝ ዜጎችን በመግደልና በማሰር ከቀያቸውና ከመኖሪያቤታቸው በሚያፈናቅለው የከተማም ሆነ የገጠር መሬት ላይ ማንም ሰው በህግ ፊት በዘላቂነት የሚጸና መብት ሊያገኝ ይችላል ብሎ አያምንም። ህወሃት በሚወረውርላቸው የጥቅም ፍርፋሪ የወጎኖቻቸውን ስቃይና መከራ ዕድሜ እያራዘሙ ያሉ ከየማህበረሰቡ የተገዙ ስላሉ በተለመደው ርካሽ ዋጋ በንጽጽር ደህና መኖር እየቻለ ካለው የዲያስፖራ ማህበረሰብ ሰዎችን መሸመት እችላለሁ ብሎ ህወሃት እየተንቀሳቀሰ ነው። በቴዎድሮስ አድሃኖም ጽ/ቤት ተዘጋጅቶ በተግባር እንዲተረጎም በውጪ አገር ባሉ የወያኔ ኤምባሲ ሁሉ የተበተነው የዲያስፖራ ፖሊሲ አላማ ይሄ ነው። ቀርሳና ኮንቶማ በእንዲህ አይነት ርካሽ ጥቅም የሚሸመቱ የዲያስፖራ አባላትን ለማሰባሰብ እየተዘጋጀ ያለ ሰፈር ነው። አርበኞች ግንቦት 7 የሶስት ቀን አራስ በተገደለችበት፤ በርካታ እናቶች፤ አቅመደካማ አዛውንቶችና ታዳጊ ህጻናት ተፈናቅለው ለጎዳና ተዳዳሪነት በተዳረጉበት ቦታ ላይ የሚገነባውን ኮንዶሚኒዬም፤ ለተለያዩ አገልግሎት የሚሆኑ ህንጻዎች ወይም ሌላ ኢንቬስትመንት ባለቤት ለመሆን በየዋህነት ያሰፈሰፉ ካሉ ውሳኔያቸውን ቆም ብለው እንዲያጠኑት ይመክራል። ከቤታቸው ተፈናቅለው እንባቸውን እያፈሰሱና በየሜዳው ተበትነው የሚንከራተቱ ወገኖቻችን እንባ ሳይደርቅ ህወሃት ወደ መጨረሻው ከርሰመቃብር ይወርዳል። ይህ ምኞት ሳይሆን የቆምንለትና እየሞትንለት ያለው ትግል ውጤት ነው።
ወያኔ ሃብት ለማካበት በሚያጧጡፈው የመሬት ንግድ የሚፈናቀሉ ወገኖቻችን ህይወት ሁላችንንም ይመለከታል። የአገሪቱን ዜጎች ለጎዳና ተዳዳሪነት በመዳረግ የሚገነቡ አዳዲስ ህንጻዎችና መንገዶች ልማት ሳይሆን ማህበራዊ ቀውስ በመፍጠር ህብረተሰቡን ለከፍተኛ ችግር የሚዳርግ አደጋውም ለአገር የሚተርፍ ነው። አልጠግብ ባይ ጥቂት የህወሃት አመራሮች ህዝባችንን ሲያፈናቅሉትና አገር አልባ ሲያደርጉ ዝም ብሎ መመልከት ችግሩ እንዲባባስና እያንዳንዳችን የጥቃቱ ሰለባ እንዲንሆን መጋበዝ ነው። አርበኞች ግንቦት 7 ይህንን የህወሃት ዜጎችን የማፈናቀል እርምጃ ለማስቆምና በግፍ ለተገደሉ ወገኖቻችን በህግ ለመፋረድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በያለበት ጸረ ወያኔ ትግሉን እንዲያፏፉምና ትግሉን እንዲቀላቀል ወገናዊ ጥሪውን ያቀርባል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!

Monday, May 23, 2016

ዛሬ በመርካቶ አሜሪካን ጊቢ አካባቢ የበርካታ ድሆች ቤት እየፈረሰ ነው


(ዘ-ሐበሻ) ካለምንም በቂ ካሳና ካለምንም የሕዝብ ይሁንታ በመርካቶ አካባቢ በተለምዶው አሜሪካን ጊቢ አካባቢ በርካታ የድሆች መኖሪያ ቤቶች  እና የንግድ ቤቶች በልማት ሰበብ ዛሬ እንደፈረሱ ከስፍራው የደረሱን መረጃዎች አመለከቱ::
እነዚህ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ለረዥም ዓመታት የኖሩት ወገኖች የሚኖሩበት ቤት ለሃብታሞች በሚሊዮኖች ብር ስር ዓቱ እየቸበቸበው ሲሆን ለነዋሪዎቹ በቂ የሆነ ካሳ አለመከፈሉ ብዙዎችን እያስቆጣ ነው::
ዛሬ ከፈረሱት መኖሪያ ቤቶች በተቸማሪ የተለያዩ የንግድ ድርጅቶችም እንደፈረሱ ያስታወቁት ምንጮች ሕዝቡ መሬቱ ለሃብታሞች ሲሰጥበት በቁጭት እየተምከነከነ መሆኑን አስረድተዋል::

Monday, May 9, 2016

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያልተወራረደና የተበላሸ ብድሩ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል።

ሚያዚያ ፩(ግንቦት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በየአመቱ በሚያወጣቸው የሂሳብ አያያዝ መግለጫዎቹ ከፍተኛ ትርፍ እንዳገኘ ሲናገር የቆዬው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2006 እና 2007 ዓም ባሉት 2 ዓመታት ብቻ 11 ቢሊዮን 273 ሚሊዮን ብር ያላወራረደው ገንዘብ ሲኖር፣ 1 ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ብር ደግሞ የተበለሻ ብድር እንዳለው ሰነዶች አመለከቱ።
በአውሮፓውያን አቆጣጠር እስከ ሰኔ 30፣ 2014 ድረስ የተለያዩ የድርጅቱ ቅርንጫፍ ባንኮች 3 ቢሊዮን 590 ሚሊዮን ከ30 ሳንቲም ፣ በ2013 ደግሞ 6 ቢሊዮን 956 ሚሊዮን ከ20 ሳንቲም ያላወራረዱት ገንዘብ መኖሩን ከንግድ ባንኩ ሰራተኞች የተገኘው የሂሳብ መዝገብ ያሳያል።
ብድር ወስደው መክፈል ያልቻሉት ድርጅቶችና ብድራቸው በተበላሸ ብድር መዝገብ ከሰፈሩት መካከል፣ ሳይጀን ዲማ ቴክስታይል ፋብሪካ 437 ሚሊዮን ብር፣ ሙሉነህ ካካ ላኪ ድርጅት 94.2 ሚሊዮን ብር፣ አኪር ግንባታ 87.1 ሚሊዮን ብር፣ ካራቱሬ እርሻ ደርጅት 55.3 ሚሊዮን ብር፣ ባዘን እርሻ እና ኢንዱስትሪ ልማት የግል ማህበር 42.1 ሚሊዮን ብር፣ የጌታ ትሬዲንግ 39.3 ሚሊዮን ብር፣ ማሜ ብረታብረት ፋብሪካ 39.2 ሚሊዮን ብር፣ የገነት ላኪና 62 ሚሊዮን ብር፣ ሸበሌ ትራነስፖርት 17.2 ሚሊዮን ብር፣ ፍጹም ዘአብ አስገዶም 14.2 ሚሊዮን ብር ቤድፋም ኢንተርናሽናል 21 ሚሊዮን ብር ይገኙበታል።
ባንኩ በ2013/14 በጀት አመት 17.2 ቢሊዮን ብር እንዳተረፈ ቢገልጽም፣ የባንኩ ሰራተኞች እንደሚሉት ግን የተበላሸው ብድርና ያልተወረራደው ገንዘብ ግምት ውስጥ ሲገባ ባንኩ ያተረፈው ከ5 ቢሊዮን ብር አይበልጥም።

Wednesday, April 27, 2016

የቀድሞ የጋምቤላ ፕ/ት 9 ዓመት ተፈረደባቸው (በእጅ ጽሁፋቸው የጻፉትና ምስጢር የያዘው የክስ መቃወሚያቸው እጃችን ገብቷል)

(ዘ-ሐበሻ) የኖርዌይ ዜግነት እንዳላቸው የሚነገርላቸውና ደቡብ ሱዳን ላይ ታፍነው ተወስደው የታሰሩት የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦኬሎ አኳይ “አገርን ለመገንጠል” በሚል በቀረበባቸው ክስ የ9 ዓመት እስራት ተፈረደባቸው:: ኦኬሎ ከፍርድ በፊት ለሚዲያ ይድረስልኝ በሚል የላኩትና ለፍርድ ቤቱም በእጅ ጽፉፋቸው አስገብተውት የነበረው የክስ መቃወሚያ ዘሐበሻ እጅ ደርሷል:: ይዘነዋል::
ከኦኬሎ ጋር በተባባሪነት የተቀሰሱት ዴቭድ ኡጁሉ 9 ዓመት; ኡቻን ኦፔይ 7 ዓመት; ኡማን ኝክየው 7ዓመት; .ኡጁሉ ቻም 7ዓመት; ኦታካ ኡዋር 7ዓመት እና ኡባንግ ኡመድ 7 ዓመት ተፈርዶባቸዋል::

Wednesday, April 13, 2016

በጅንካ የመከላከያ ሰራዊትና ልዩ ሃይል አባላት ከፍተኛ ቅኝት እያደረጉ ነው

 የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት በደቡብ ኦሞ በጅንካ ከተማና አካባቢዋ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከልዩ ሃይል አባላት ጋር በመሆን፣ በተለይ ከምሽቱ 2 ሰአት ጀምሮ በመኪኖች ላይ መትረጊስና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎችን ደግነው ቅኝት በማድግ ላይ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ የወጣቶች ነጻ እንቅስቃሴ የተገደበ ሲሆን፣ ነዋሪዎችም ጭንቀት ውስጥ ገብተዋል፡፡
ክትትሉ የተጀመረው በአካባቢው ከፍተኛ እውቅና ያላቸው የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት ም/ሊቀመንበርና የዞኑ ጽ/ቤት ቤት ኃላፊ አቶ ዓለማዬሁ መኮንን፣ አቶ አብረሃም ብዙነህ እና አቶ ስለሺ ጌታቸው መጋቢት 17፣ 2008 ዓም መታሰራቸውን ተከትሎና ፓርቲያቸው መሪዎቹና አባሎቹ ካልተፈቱ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚጠራ መግለጫ ማውጣቱን ተከትሎ ነው፡፡
እነ አቶ አለማየሁ መኮንንን በሽብር ወንጀል ለመክሰስ የተደረገው ሙከራ ፣ ለምስክር የተዘጋጁ ሰዎች በሃሰት አንመሰክርም በማለታቸው ላይሳካ እንደሚችል ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቶአል፡፡
ለምስክርነት በቅድሚያ የታጩት የታሳሪዎች መኖሪያ ሲፈተሸ የነበሩ ስድስት ሰዎች ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል አቶ መስፍን እርገጤ፣ አቶ ዓሊዬ ይታ፣ እና ወጣት ሃና ‹‹ከታሳሪዎች ቤት ክላሽንኮቭ ጠመንጃና ቦምብ በፍተሻ ሲገኝ አይተናል ›› ብላችሁ ከመሰከራችሁ ‹‹አዋሳ ወስደን ከመዝናናችሁ በተጨማሪ ለመቋቋሚያ የሚሆን ለእያንዳንዳቸው ብር 50 ሺህ፣ ይሰጣችኋል ››ቢባሉም የሃሰት ምስክርነቱን ኃሳብ ውድቅ ማድረጋቸውን ፣ ጉዳዩን በቅርብ ከሚከታተሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለማወቅ ተችሎአል፡፡
መስካሪዎች ‹‹ ከጂንካ ከተማ ህዝብ ጋር ከምንጋጭ ከነድህነታችን ከህዝብ ጋር መኖር እንፈልጋለን ›› ማለታቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ መስካሪዎቹ አዋሳ ለመሄድ ፈቃደኛ ያለመሆናቸውንና የዕለት ሥራቸውን ሰርተው ማደር እንደሚፈልጉ የገለጹ ሲሆን፣ ይህ ሳይሆን አዋሳ በግዳጅ ብንሄድ የተለየ እንደማንመሰክርና እየደረሰብን ያለውን ጫና ለህዝብ በአደባባይ ለማሳወቅ እንገደዳለን ማለታቸው ታውቆአል፡፡
በደቡብ ኦሞ መሬት ከወሰዱት ባለሃብቶች መካከል ከ98 በመቶ በላይ የሚሆነውን መሬት የወሰዱት የህወሃትና ከህወሃ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች መሆናቸውን የሚያመለክት ጥናት በወጣ ማግስት እነ አቶ አለማየሁ መታሰራቸውን ኢሳት መዘገቡ ይታወቃል፡፡
መረጃው ከወጣ በሁዋላ የአካባቢው ነዋሪዎች በስፋት እየተነጋገሩበት ሲሆን፣ የዞኑ መስዳደርም ሆነ ክልሉ በጉዳዩ ዙሪያ ለህዝቡ ጥያቄ መልስ አልሰጡም፡፡
ሚያዚያ ፬( አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :

Friday, April 8, 2016

ትግሉ ሰፊ የምሁራን ተሳትፎ ይሻል!

April 8, 2016
def-thumbኢትዮጵያ በበብዛትም ይሁን በጥራት በውጭው አለምም ይሁን በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ምሁራን ያፈራች ሀገር ነች። በጅጉ የሚያሳዝነው ግን በሀገሪቱና በሕዝቧ ችግር ላይ ሀሳብ ሲሰጡ ፣ ባደባባይ ሲከራከሩና ሲታገሉ የሚታዩት በጅጉ ጥቂቶች ናቸው። ርግጥ ነው ተከታታይ መንግስታት በምሁራን ላይ ያደረሱት ጥቃትና ማግለል ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት ብዙዎች መከራን ከህዝብ ጋር ከመጋፈጥ ይልቅ አጎንብሶ ማሳለፈን የመረጡበት ሁኔታ አለ። ቁጥራቸው ጥቂት ያልሆኑም ለግል ጥቅማቸው ቅድሚያ በመስጠት ከጨቋኝ ገዥዎች ጋር በመተባበር የሚሰሩ መኖራቸውም አይካደም። አብዛኛው ምሁራን በተለይም በብዙ የሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ጠለቅ ያለ እውቀት ያላቸው ጭምር ሀገሪቱን ከገባችበት ማጥ ለማውጣት በሚደረገው ትግል ውስጥ እየተሳተፉ አይደለም። ይህ ዛሬ ባለው ችግርም ይሁን በታሪክ ፊት አሳዛኝ ነው።
ሀገራችን ዛሬ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነች። የተማሩ ልጆቿ መላ እንዲመቱ በመጠየቅ ላይ ትገኛለች። ይልቁንም በሀገራችን ያለው ችግርና ሀገሪቱ እየሄደች ያለችበት መንገድና አቅጣጫ በተለይ ምሁራንን እንቅልፍ ሊነሰ ይገባል። ዕውነታው ከዚህም አልፎ የሀገሪቱን አሳዛኝና አደገኛ ሁኔታ ለመቀየር በሚደረገው ትግል ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ግድ ይላል። የመንግስት ግፍና ሰቆቃ በበዛበትና የሀገራችን ሕልውና አደጋ ላይ በወደቀበት በአሁኑ ሰዓት ምሁራን ላለመሳተፍ ምክንያት ማቅረብ የማይችሉበት ወቅት ላይ ደርሰናል። እንደማንኛውም ሀገር ምሁራን የኢትዮጵያ ምሁራን በሀገራችን ውስጥ ሰላምና ዲሞክራሲ እንዲሰፍንና ፍትሕ የሰፈነበት ስርዓት እንዲመሰረት ሊሸሹት የማይገባ ትልቅ ሚና አላቸው።
ዛሬ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ ዜጎች መንግስት በልማትና በልማት እያመካኘ የሚያካሂደውን ሰፊ ዝርፊያ እንዲሁም ወያኔ ሩብ ምዕተ አመት ሙሉ በብሄረሰብ እኩልነት ስም እየማለ የሚያደርሰውን ያንድ ብሄረሰብ ጉጅሌ የበላይነት ማስፋፋት እምርረው በመታገል ላይ ናቸው። መስዋዕትነቱን እየከፈሉ የሚታገሉትና የሚወድቁ የሚነሱት ወጣቶችና ምስኪን ገበሬዎች ናቸው። እነዚህ ወገኖቻችን ሕይወታቸውን ሳይቀር ሲገብሩ በየቀኑ እየሰማንና እያየን ነው። ይህንን የህዝብ ጥያቄና ትግል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ምሁር ተመልካች ሆኖ ሊቀመጥ አይገባም። ትግሉን ከመምራት ጀምሮ እስከ ተራ ታጋይነት ባሉት ረድፎች ሁሉ ምሁራን ቀጥተኛ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል። ሰለትግሉ እቅጣጫም ሆነ ስለሀገሪቱ መጻዔ ዕድል ሃሳብ ማመንጨትና ማሰራጨት ይኖርበታል። ሀገራችን የደለቡ ችግሮቿን ተቋቁማ ፍትሕ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈነባት ሀገር የሚያደርጋትን የምህንድስና ስራ አስቀድሞ ማሰብና ማመቻቸት ይኖርበታል። ርግጥ ነው ይህን መሰል ተሳትፎ የሚያደርጉ ምሁራን አሁንም አሉ። ቁጥራቸው ግን ሊሆን ከሚገባው ጋር ሲወዳደር በጅጉ አነስተኛ ነው።
ምሁርነት ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ መቀዳጀት ብቻ እንዳልሆነ የታወቀ ነገር ነው። ምሁርነት ምሉዕ የሚሆነው መላውን የተፈጥሮ ከባቢ ከህዝብ ማህበራዊ ሕይወት ጋር አጣምሮ የሚያስብ አዕምሮን በዕውነት ላይ ለተመሰረተ ሀሳብና ዕውቀት ክብር መስጠትን ለተግባራዊነቱ መሟገትን የጨመረ ሲሆን ነው ። በመሆኑም ሁሌ እንደሚባለው ምሁርነት የጋን መብራትነት አይደለም። ምሁርነት በጨለማ ውስጥ ችቦ ሆኖ ብርሃን መፈንጠቅን ይመለከታል። ምስዋዕትነትንም ይጠይቃል።
ያለንበት ወቅት ለኢትዮጵያ ምሁራን ከፍተኛ ፈተናም ዕድልም ይዞ ቀርቧል። ይህ ልሽሽህ ቢሉት የማይሸሽ ፈተና ከመሆኑ ባልተናነሰ በታሪካችን እንድ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የጎላ አሻራን ለማኖርም ትልቅ የታሪክ ዕድል ነው። ይህ ፈተና ከፍተኛ ያርበኝነት ስሜትንና ሀላፊነት መውሰድን ይጠይቃል። አገር በተወሳሰበ ችግር ምክንያት ወደ አረንቋ እየገባች ምንም ሳይሰሩ መቀመጥ ወይም ዝም ብሎ ከመመልከት የበለጠ ለምሁር ሂሊና የሚከብድ ነገር ሊኖር አይችልም:: በጣም ላስተዋለ ሰው እንዲህ አይነት ዝምታ ሐጢያትም ነው። በእንዲህ አይነት ፈታኝ ወቅት የኢትዮጵያ ምሁራን ሀገሪቱን ወደተሻለ አቅጣጫ እንድትሔድ ላለመታጋል ምንም ምክንያት ማቅረብ አይችሉም። ሀሳብ የሚሰራጭባቸው የሀሳብ ክርክር የሚካሔድባቸው መድረኮች ፣ አደባባዮች ፣ የመገናኛ መሳሪያ አይነቶች የፖለቲካና የሲቪክ ማህበሮች ባገር ውስጥም በውጭም ያሉት መሳተፊያ ናቸው።
ድርጅታችን አርበኞች ግንቦት 7 ምሁራን በሰፊውና እንደየፍላጎቶቻቸውና ችሎታቸው ሊሳተፉ የሚችሉባቸው በርካታ የትግል መስኮች አሉት። የሀገሪቱን ውስብስብ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ የጥናት ውጤቶች ፣ ሀሳቦች ፣ ምክሮችም ሆነ ቀጥተኛ የምሁራን ተሳትፎ ለማስተናገድ አመቺ ሁኔታ ያለበት ድርጅት ነን። ወደፊትም የምሁራን ተሳትፎ እንዲጎለብት ሁኔታዎችን ይበልጥ ለማመቻቸት እንሰራለን። ዽርጅታችን የሀገራችን ችግር የሚወገደውና ዲሞክራሲና የዜጎች እኩልነት የሚረጋገጠው በበሰለና ከተራ ዜጋ እስከ ብስል ምሁራን በሚያከሂዱት ክርክርና የበሰለ ሃሳብ ላይ ተመስርቶ መሆኑን ያምናል። አሁን ያለው የሀገራችን ምሁራን ተሳትፎ ደረጃ ሁላችንም ከምንጠብቀው በታች በጅጉ ያነሰ መሆኑ ሁላችንንም ከማሳዘን አልፎ የሚያስቆጭና የሚያንገበግብ ሆኖአል:: አገርና ህዝብ ድረሱልኝ እያለ በሚጣራበት በዚህ የታሪክ አጋጣሚ አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ የተለያዩ ምክንያቶችን እየደረደሩ ማለፍ ይቻል ይሆናል። ይዋል ይደር እንጂ ለነጻነቱ ቀናዕ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የደረሰበትን አፈናና ጭቆና እምቢኝ ብሎ ነጻነቱን ሲቀዳጅ ግን ከታሪክ ፍርድና ከህዝብ ትዝብት ማምለጥ አይቻለም።
አርበኞች ግንቦት 7 በአገር ውስጥም ሆነ በተለያየ ምክንያት በአለም ተበትኖ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ምሁር ለወገን ደራሽነቱንና አለኝታነቱን አሁኑኑ ይወጣ ዘንድ ወገናዊ ጥሪውን ያቀርባል::
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

ለኮ/ል አታክልቲ ገ/ሚካዔል ልጅ ማሳከሚያ ከብረታ ብረት ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን 3 ሚሊዮን ወጪ ተደረገ

የብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ለአንድ ባለስልጣን ልጅ ማሳከሚያ ሶስት ሚሊዮን ብር የህዝብ ገንዘብ ወጪ ማድረጉን ለኢሳት የደረሰው ሰነድ ያስረዳል። ኮሮፖሬሽኑ የወጣውን ገንዘብ በስሩ ያሉ ድርጅቶች በመዋጮ እንዲሸፍኑት መመሪያ ተላልፏል።
በብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የሰው ሃይል አስተዳደርና ዕቅድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በኮ/ል ፅጌ አለማየሁ ስምና ፊርማ ህዳር 8 ፥ 2005 የተጻፈው ደብዳቤ ለኮ/ል አታክልቲ ገ/ሚካዔል ልጅ ማሳከሚያ የወጣው ወጪ በስሩ ያሉ ድርጅቶች በመዋጮ እንዲሸፍኑት ያዛል። ህክምናው በታይላንድ ባንኮክ መከናወኑንም ያስረዳል።
ጉዳዩ የኮ/ል አታክልቲ ልጅ ተማሪ ዮናስ አታክልቲ ታይላንድ ሄዶ የታከመበትን የህክምና ወጪ ይመለከታል በሚል ርዕስ የወጣው ደብዳቤ የሚከተለውን መልዕክት ይዟል። 
የብረታብንረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የህወሃት ታጋዮች በነበሩት መኮንኖች የሚመራ ሲሆን፣ ዋና ዳይሬክተሩም አንጋፋ የህወሃት ታጋይ የነበሩት ብ/ጄኔራል ክንፈ ዳኘው መሆናቸው ይታወቃል።
ኮርፖሬሽኑ ከመንገዶች ባለስልጣን ለዕድሳት ብሎ የወሰደውን 88 ማሽነሪ ለትግራይ ክልል አሳልፎ መስጠቱ በአለም ባንክ ኦዲተሮች መጋለጡ በቅርቡ በሰነድ አስደግፈን መዘገባችን ይታወሳል። የማሽነሪዎች ዋጋም ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።
ለባለስልጣን ልጆች ማሳከሚያ በመስጠት የህዝብና የሃገር ሃብት በመመዝበር ላይ መሆኑ የብዙዎች ስጋት ሆኗል። በኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሃገረ-ስብከት ስራ አስኪያጅ ሊቀማዕምራን የማነ ዘመንፈስቅዱስ ለልጃቸው ማሳከሚያ በሚል ለአዲስ አበባ አብያተክርስቲያናት ባቀረቡት ጥሪ ከአንድ ደብር ከአንጦጦ ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ብቻ 500ሺ ብር እንዲወጣ መወሰኑ ባስነሳው ውዝግብ ጉዳዩ መጋለጡ ይታወሳል።
ፓትሪያርኩ በወሰዱት እርምጃ የማነ ዘመንፈስቅዱስ ከሃላፊነት የተነሱ ቢሆንም፣ የተዋጣውን ገንዘብ በተመለከተ ስለተደረሰው ውሳኔ የታወቀ ነገር የለም።
ኢሳት (መጋቢት 29 ፥ 2008)