Friday, January 31, 2014

ወያኔን ያሸበረው የግንቦት 7 መንገድ ምንድነው?

የትግራይን ሕዝብ ከብሄር ጭቆና ነጻ አወጣለሁ በሚል ጠባብ ዓላማ ተደራጅቶና ታጥቆ ለበትረ ሥልጣን የበቃው ህወሃት ወይም ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሥልጣን ከተቆጣጠረ 23 አመት ሊሞላው እነሆ ጥቂት ወራቶች ብቻ ቀርተውታል።
ለጋራ ቤታችን ለሆነቺው አገራችን ኢትዮጵያና በአስተዳደር በደል ለከፋ ድህነት ለተዳረገው መላው ሕዝቦቿ የሚሆን አንዳችም ራዕይ ሳይኖረው ለመንግሥትነት ሥልጣን የበቃው ይህ ቡድን ላለፉት 23 ዓመታት ከግል ኑሮአቸው አሻግረው የአገርንና የወገንን ጥቅም ማየት የማይችሉ ወይም የማይፈልጉትን በዙሪያው አሰባስቦ እያካሄደ ካለው ዘርፈ ብዙ የሃብት ምዝበራ ወንጀል በተጨማሪ እየፈጸመ ያለው የመብት ጥሰትና አፈና ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።
ሰሞኑን እያፈተለኩ በመውጣት ላይ ከሚገኙ ምስጥራዊ የድምጽ መረጃዎች ለማረጋገጥ እንደተቻለው ደግሞ ለጥቂቶች የሃብትና የብልጽግና ምንጭ የሆነው ሥልጣን ከእጃቸው እንዳይወጣ በአንድ በኩል በምርጫ ስም እንዴት አድርገው ሕዝቡን ቀፍድደው የምርጫው ተሳታፊ ማድረግ እንደሚችሉ ሲዶልቱና በሌላ በኩል ደግሞ በቁጥጥራቸው ሥር የሌሉትንና ለሥልጣናቸው ያሰጉናል ያሉዋቸውን የደሃዉን ልጅ በማጋፈጥ እንዴት በጦርነት እንደሚጨፈልቁዋቸው ሲመክሩ ተሰምተዋል።
ከወያኔው ቁንጮ አንዱ የሆነው በረከት ስሞን በየደረጃው ላሉት የአገዛዙ ሹሞችና ካድሬዎች ባደረገው ገለፃ መሬትን የመንግሥት ባደረገው ኮሚኒስታዊ አዋጅ ምክንያት የመንግሥት ጭሰኛ ለመሆን የተፈረደበትን ሰፊውን አርሶ አደር “ተኛ ስንለው ይተኛል፤ ቁም ስንለው ይቆማል ፤ እንደፈለግን ብንበድለው እንኳ አያማርረንም ” እያለ ሲዘባበትበት ተደምጦአል ። በአንድ ለአምስት ኮሚንስታዊ አደረጃጀት ተጠርንፎ የወያኔ የንግድ ድርጅቶች ብቻ የሚያቀርቡትን ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ያለውዴታው እንዲራገፍበትና ከአቅሙ በላይ ዕዳ እንዲቀፈቅፍ የተፈረደበት የኢትዮጵያ አርሶ አደር በዚህ አይነት ንቀት ደረጃ የሚዘባበትበትን መሪ ከወያኔው በረከት ስሞን በፊት ገጥሞት አያውቅም ። ለወደፊትም ሊያይ አይፈልግም ። ወያኔን ሥልጣን ላይ ለማምጣት የሰሜኑ ክፍለአገራችን አርሶ አደር የተጫወተው ሚና ተዘንግቶ በበረከት ስሞን እንዲህ መዋረዱ እጅግ ያሳዝናል። ለነገሩ ከፍተኛ የህይወት መስዋዕትነት ከፍሎ ለድል ያበቃው የትግራይ ሕዝብ ቁም ስቅሉን እያየ አይደል?
ሌላው አስገራሚ ክስተት በአገር ደህንነት ሥራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች ባደረጉት ዝግ ስብሰባ ታማኝነታችን ለአገራችን ነው ወይስ የሥርዓቱን አገዛዝ ዕድሜ ለማራዘም? ብለው ላነሱት ጥያቄ የጠቅላይ ሚንስትር ተብዬው የህግ አማካሪ ጌታቸው ረዳ የሰጠው መልስ ነው። ደህንነት ብቻ ሳይሆን የመከላኪያ ሠራዊትና ፖሊስ ጭማር ታማኝነታቸውና ግዴታቸው ሥርዓቱን ሥልጣን ላይ ማቆየት መሆን አለበት ሲል ጌታቸው እንቅቹን ነግሮአቸዋል ። በምላሹ “ላለፉት 23 አመታት እያደረግነው ያለው ይሄው ሆኖ ሳለ አሁን ምን ብታስቡ ነው ጥያቄ ያነሳችሁ?” የሚል ይመስላል ። ይባስ ብሎም ሥርአቱን ለመጠበቅ ያልቻለና በግንቦት 7 መንገድ የሚጓዝ ደህንነት ሠራተኛ የተስፋየ ገብረስላሴን ያህል የደህንነት እውቀት ቢኖረውም ሆነ እስራኤል አገር የዓመታት ስልጠና ያገኘ ቢሆን ዋጋ የለውም ብሏቸዋል።
ለመሆኑ ወያኔዎች እንደመርገም የቆጠሩትና ተከታዮቻቸውን የሚያስፈራሩበት የግንቦት 7 መንገድ ምንድ ነው።?
ግንቦት 7 የፍትህና፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አገራችን ኢትዮጵያ የእያንዳንዱ ዜጋ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት የተከበረባት፤ የኢኮኖሚ ብልፅግናና ማኅበራዊ ፍትህ የሰፈነባት ፤ የዜጎች ሕይወት፣ ደህንነትና ጥቅም የተከበረባት እና የሕዝቧ አንድነትና ትስስር የጠነከረባት ሃገር ሆና ማየትን ብቸኛ ራዕይ አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ድርጅት ነው። ይህንን ራዕይ እውን ለማድረግ ደግሞ እስከ ዛሬ በጠመንጃ ኃይልና በጉልበተኖች ጡንቻ ከአንዱ ወደሌላው የሚፈራረቀው የመንግሥት ና የፖለቲካ ሥልጣን በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሂደት የሚያዝበትን ፤ የሃገሪቱ ዜጎች ምርጫ በተግባር የሚገለፅበት፤ ማኅበራዊና የፖለቲካ ችግሮች በዲሞክራሲያዊ መንገድ የሚፈቱበት እና ዲሞክራሲያዊ ባህል የሚበለፅግበት ብሄራዊ የፖለቲካዊ ሥርዓት መገንባት አማራጭ የሌለው ነው ብሎ ያምናል።
ይህ ደግሞ ያለምክንያት አይደለም። ወያኔ የዓለም አቀፍ ድጋፍ ለማግኘት ሲል ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ በሩን ከፈት አድርጎ በነበረበት ምርጫ 97 ወቅት ከተገኘው ልምድና ከተመዘገበው ውጤት ሕዝባችን በአምባገነኖችና በከፋፋዮች ለመገዛት አለመፈለጉን በግልጽ አስመስክሮአል።
ንቅናቄያችን ግንቦት 7 ሕዝባችን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በነቂስ ወጥቶ መሪዎቹን የመረጠበትንና ድሉን የተነጠቀመበትን ታሪካዊ የግንቦት 7 1997ን ቀን ምን ጊዜም አይረሳም። መጠሪያ ስሙንም በዚያ ታሪካዊ ቀን የሰየመው ሕዝብ የተነጠቀውን ድል በማስመለስ ፍትህ የሰፈነባት፤ የበለጸገችና የተከበረች አገር ባለቤት እንሆን ዘንድ ነው። ሁላችንም አትራፊ እንጂ ተጎጂ ለማንሆንበት ለዚህ ቅን አለማና ራዕይ ደንቃራ ሆኖ የተገኘው ወያኔና ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ከወያኔ ጋር የተጣበቁ አንዳንድ ባዕዳን አገሮች ናቸው።
ወያኔ የግንቦት 7 መንገድ የሚለው ለዚህ ክቡር ዓላማ ሲባል እንቅፋት የሆነውን ሥርዓቱን በሁለ- ገብ ትግል አስገድዶ ለሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር አካል ማድረግ ካልተቻለ ደግሞ በተባበረ ትግል አስወግዶ በምትኩ በሕዝብ ለሕዝብ ከሕዝብ የሚመጣ ሰላማዊ የመንግሥት ሥርዓት መመሥረትን ነው። ይህንን የተቀደስ አላማ ለማክሸፍና የተጀመረውን ትግል ለመጨፍለቅ ሲባልም ወደ ሥልጣን ለመምጣት በጦርነት ማግዶ ካስጨረሳቸው የደሃ ልጆች በእጥፍ የሚበልጡትን መልምሎ በጸረ ሽምቅ ውጊያ ከማሰልጠን ጎን ለጎን ለግንባታ ቢውል ስንት ፋይዳ ሊያስገኝ ይችል የነበረ በርካታ ገንዘብ በማፍሰስ ተቃዋሚ ድርጅቶችን ድምጽ ለማፈንና ለመሰለል እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ለአገራችን ሉአላዊነት ጠቀሜታው እስከዛሬ ምንም ባልታወቀ ጦርነት ወደ መቶ ሺ የሚጠጉትን ያስጨፈጨፈ፤ የተልዕኮ ጦርነት ለማካሄድ በመንግሥት አልባዋ ጎረቤት ሱማሌ እስከዛሬ ቁጥራቸው ያልተገለጸ ወገን ያስፈጀ ፤ ለሥራ ፍለጋ ውትድርና የገቡትን ወጣቶች ለይቶ በሰላም አስከባሪ ስም በድንበር ዘለል ጦርነቶች እየማገደ ገንዘብ የሚቀበል፤ ስለአገርና ስለወገን ምን ሊገደው ይችላል?
ትናንት ትግል ላይ በነበሩበት ወቅት የቀደምቶቹ መንግስታት ልጆቻቸውን ለትምህረት ወደ ፈረንጅ አገር እየላኩ የደሃውን ልጅ በጦርነት ይማግዳሉ በማለት በጅምላ ሲከስ የኖረ ዛሬ በተራቸው ልጆቻቸውን ብቻ ሳይሆን ዘርማንዘሮቻቸውን ታይቶ በማይታወቅ ብዛት ወደ ፈረንጅ አገር ለትምህርት እየላኩ ለነጻነታችንና ለክብራችን የምንታገለውን እርስ በርስ ለማጨራረስ ሲዶልቱ ዝም ብሎ መመልከት ከየትኛውም ቅን ዜጋ የሚጠበቅ አይሆንም።
ስለሆነም የበላይ አዛዦቻቸው በሚሰርቁት የሕዝብ ገንዘብ ፎቅ ላይ ፎቅ እየገነቡ ሃብት በሚያካብቱት አገር ሠራዊቱን እረፍት ለመንሳት ሆን ተብለው በሚቀሰቂሱት ግጭቶች ከአንዱ ማዕዘን ወደ ሌላው ማዕዘን ያለ ዕረፍት እየተንከራተተ ያለው የመከላኪያ ሠራዊት ፤ የፖሊስና የደህንነት ኃይል ለአገዛዙ አልታዘዝም በማለት ተገዶ ሥልጣን ለሕዝብ እንዲያስረክብ የማድረግ ወገናዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ግንቦት 7 የፍትህ የነትጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ጥሪውን ያቀርባል።
የግንቦት 7 መንገድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት የተጠማውን ፍትህ እኩልነትና ነጻነት በአገራችን ለማስፈን አሁን ሥልጣን ላይ ያለው የጎጠኞችና የዘራፊዎች ስብስብ በማስገደድ ወይም በማስወገድ ሰላማዊ ህጋዊና ዲሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር እንዲኖር ማድረግ ነው። ይህንን ደግሞ የሚፈሩት በሥልጣን ቱርፋትና በሃብት ዘረፋ የሰከሩ ብቻ ናቸው።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ

Wednesday, January 29, 2014

የኢትዮጵያ መንግስት የግንቦት7 መሪዎችን ኮምፒዩተሮች በዘመናዊ የስለላ መሳሪያዎች ሲሰልል እንደተደረሰበት አንድ አለማቀፍ ተቋም አጋለጠ

-የህዝቦችን ደህንነት ከመንግስታት ጥቃት ለመከላከል የተቋቋመው ፕራይቬሲ ኢንተርናሽናል የተባለው  ተቋም ለእንግሊዝ መንግስት የገቢዎቸና ጉምሩክ መስሪያ ቤት በጻፈው ደብዳቤ “ጋማ ኢንተርናሽናል የተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ በአለም ላይ የሰብአዊ መብቶችን በመጣስ ለሚታወቁ አገሮች ኮምፒይተሮችን፣ የሞባይልና የስካይፕ የስልክ ግንኙነቶችን እንዲሁም የኢሜል ልውውጦችን በርቀት ሆኖ ለመከታተል የሚያስችለውን ፊን ፊሸር ወይም ፊን ስፓይ በሚል ስም የሚጠራውን የመሰለያ መሳሪያ ከአውሮፓ ህብረት ውጭ ላሉ አገሮች በመሸጥ ዜጎች እንዲሰለሉና ደህንነታቸው አደጋ ላይ እንዲወድቅ በማድረጉ  ምርመራ እንዲጀመር” ሲል ጠይቋል።
የግንቦት7 ከፍተኛ አመራር በሆኑት በ ዶ/ር ታደሰ ብሩ የግል ኮምፒዩተር ላይ የመሰለያ ቫይረሱ መገኘቱን በቶሮንቶ ዩኒቨርስቲ የሙንክ ስኩል ግሎባል አፌርስ የምርምር ተቋም የሆነው ሲትዝን ላብ ማረጋገጡን ፕራይቬሲ ኢንተርናሽናል በደብዳቤው ገልጿል።
የመሰለያ መሳሪያው የሰብአዊ መብቶችን በሚጥሱ 36 አገራት ላይ መሸጡን የገለጸው ፕራይቬሲ ኢንተርናሽናል፣ በተለይም በቬትናም፣ ማሌዚያና ኢትዮጵያ የፖለቲካ ተቀናቃኞችን ለመሰለያነት እየዋለ ነው ብሎአል።
በኢትዮጵያ የግንቦት7 ከፍተኛ አመራር የሆኑት ዶ/ር ታደሰ ብሩ ኮምፒተራቸው ሲሰለል መቆየቱን የገለጸው ፕራይቬሲ ኢንተርናሽናል፣ በአንድ የብሃሬን የሰብአዊ መብት ተማጓች ኮምፒዩተር ላይም ተመሳሳይ የስለላ ሶፍት ዌር መገኘቱን ገልጿል።
ዶ/ር ታደሰ ብሩ ለፕራይቪሴ ኢንተርናሽናል ጠበቃ የምስክርነት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተናግረዋል። ፕራይቪሲ ኢንተርናሽናል የስለላ ቫይረሱን የሸጠውን ጋማ ኢንተርናሽናልን የተባለውን ድርጅት ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ማቀዱን ዶ/ር ታደሰ ገልጸዋል፡ ኢሳት ዜና

የአረና ትግራይ መሪዎች ለቅስቀሳ በሄዱበት አዲግራት ተደበደቡ

-ነባሩ የቀድሞው የህወሀት ታይ እና አሁን የአረና ከፍተኛ አመራር አቶ አስገደ ገብረስላሴ፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች በመጻፍ የሚታወቀው ና የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህር አብረሃ ደስታ እንዲሁም የፓርቲው የአመራር አባል አቶ አምዶም ገ/ስላሴ እሁድ እለት ከአዲግራት ህዝብ ጋር ለመነጋገር ወደ ስፍራው ቢያቀኑም በከተማው የደህንነት ፣ የፖሊስና የቀበሌ ሹሞች የሚመሩ ወጣቶች ድብደባ በመፈጸማቸው ስብሰባውን ማከሄድ ሳይችሉ ቀርተዋል።
መምህር አብርሃ ለኢሳት እንደገለጸው ድብደባው ሆን ተብሎ በመንግስት ሃይሎች የተቀናበረ ነው። ለድብደባው ምክንያት የሆነውም በከተማዋ ውስጥ ቅስቀሳ ማድረግ አይቻልም በሚል ነው
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰማያዊ ፓርቲ  በጎንደር ከተማ ለሚያደርገው ሰልፍ በማስተባበር ላይ የሚገኙት የፓርቲው የአደረጃጀት ኃላፊ ኢንጅነር ጌታነህ ባልቻ፤እንዲሁም በሰሜን ጎንደር ዞን የፓርቲው የዞን ሰብሰቢ የሆኑት አቶ አግባው ሰጠኝን በፖሊስ መያዛቸውን ፓርቲው አስታውቋል። ኢሳት ዜና 

Tuesday, January 28, 2014

ከወራት በፊት ሁለት የተቃዎሚ ፓርቲ አመራሮች የተሳተፉበት የ አሜሪካ ኮንግረንስ
ውጤት እያስመዘገበ ነው።

Monday, January 27, 2014

ዛሬ የሚያስፈሯሯችሁን እስከ ዘላለሙ የማትሰሙበት ግዜ ይመጣልና አትፍሩ

ህወሃት የሚያራምደው የዘረኝነት ፖለቲካና፤ የተዘፈቀበት የሙስና አዘቀት ሊወጣ ከማይችልበት አዙሪት ውስት ከተውታል።ከእንግዲህ ወዲህ ለህወሃቶች የቀራቸው አንድ አማራጭ ብቻ ነው። ሁሉንም ዜጎች በዘረኝነት ሰንሰለት አስሮ ቀጥቅጦ እና አፍኖ መግዛት ቀጣዩ ቅዥታቸው ነው።
የዚህ አፍኖ የመግዛት ቅዥታቸው መገለጫም ዜጎች ህወሃት ስለሚፈፅመው ወንጀል ምንም ዓይነት መረጃ እንዳያገኙ ማድረግ አንዱ ነው።ህወሃት የሚፈፅመው ወንጀል ከህዝብ ዓይንና ጆሮ ተሠውሮ እንዲረሳ ይመኛል። ይሄን ምኞቱን እውን ለማድረግም ሌሎች ነፃ ሚዲያዎችን አሸባሪ ማለት ወይም ደግሞ ሌላ የተሰወረ አጀንዳ ያላቸው እያለ ማላዘንን ሥራየ ብሎ ተያይዘውታል። ከሰሞኑ አዲስ አበባ ውስጥ የሚታተሙ ስምንት የግል ህትመቶችን አሸባሪዎች በማለት ክስ መስርተዋል። አስቀድመው ፈርደው ከጨረሱ በኋላ ክስ መመሥረት የህወሃቶች የተለመደ የፍትህ ሥርዓት ነው። በአገሪቷ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ግዜ ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ ሁኖ የተቋቋመውን ኢሳትንም አሸባሪ እያሉ ሰሚ አልባ ጩኸት እየጮኹ ነው። የኢሳት ቴሌቭዥንና ሬዲዮንን የሚሰማም በአሸባሪነት ይከሰሳል እያሉ በየዜጎች ደጅ እየተንከላወሱ ለማስፈራራት እየሞከሩ ነው።
እኛ ግን እንዲህ እንላለን !!! አትፍሩ ! አትፍሩ ! አትፍሩ ! ኢሳትን ሰምታችኋል ብሎ የሚያስፈራሯችሁን ለዘላለሙ የማትሰሟቸው ግዜ እየመጣ ነው። የነፃነት ጎህ ቀዶ ሁላችን የፈለግነውን ሰምተን፤ ያልፈለግነውንም የምንተውበት ዘመን እሩቅ አይደለም። ግንቦት ሰባት የፍትህ የነፃነት እና የእኩልነት ንቅናቄም የተቋቋመው ዜጎች ያለማንም ጣልቃ ገብነት የወደዱትን ወስደው፤ የጠሉትን መተው የሚችሉበትን መንገድ ለማመቻቸት ነው። ዘረኞቹ በደምና አጥንት ታውረው ጭካኔን ከጀግንነት ቀላቅለው እኛ ብቻ ወንድ ባሉበት መንደር ሌላ ጀግና ኢትዮጵያዊ ወንድ ገስግሶ የሚመጣበት ዕለት እየደረሰ ነውና እንዳትፈሩ እንመክራችኋለን። ህወሃቶች ዜጎችን ከሰው በታች አድርገው ለመግዛት እንዲመኙ ያደረጋቸው እብሪት የሚተነፍስበት ዘመን እሩቅ አይሆንምና አሁንም አትፍሩ።
ህወሃቶች ከእነርሱ ቁጥጥር ውጪ ያሉ ነፃ ሚዲያዎችን እንደማይታገሱ የታወቀ ነው። ለምን ቢሉ የወንጀላቸው ብዛት፤ የክፋታቸው ጥልቀት ሳይነገር ተሠውሮ እንዲቀር ስለሚመኙ ነው። ይህን ምኞታቸውን እውን ለማድረግም ራሳቸው የሠረቱን ህግ ውልቅልቁን አውጥተው ያፈራርሱታል። ዜጎች መረጃ የማግኘት መብት አላቸው ተብሎ እነርሱ “ህገ-መንግስታችን” እያሉ በሚጠሩት ላይ በማያሻማ ሁኔታ የተቀመጠ ቢሆንም እነርሱ ግን ለራሳቸው ህግ መታመንን አልመረጡም። እንዲያውም እነርሱ ሞተንለታል የሚሉትን ህግ አፈር አስገብተው ራሳቸው ህግ ሆነው ተፈጥረዋል። እነርሱ ህግ ሁነው በመፈጠራቸውም በየዜጎች ደጅ እየተንከላወሱ ኢሳትን ብትሰሙ ወዮላችሁ እያሉ ያስፈራራሉ። ዜጎች ግን የሞኝ ዘፈናቸውን መልሰው መልሰው ለሚያላዝኑ ኢሕአዴጋዊያን ዛቻ የሚንበረከኩ አይሆኑም። አገራቸውን በተመለከተ ማንኛውንም መረጃ ለመስማት ያላቸውን ነፃነትም ለምናምንቴዎች አሳልፈው የሚሰጡ አይሆኑም።
ጎሬቤታችን ኬኒያ ከአስር በላይ የግል ቴሌቭዥን ጣቢያዎች አሏት።በርካታ በአጭር ሞገድና በኤፊኤም ሞገዶች የሚተላለፉ ሬዲዮኖችም አሏት። የኬኒያ መንግስት ለዜጎቹ ክብርና ፍቅር ስላለው የተቻለውን ያክል ነፃ ሚዲያ እንዲኖር ይጥራል። ለህዝቡ ክብርና ፍቅር የሌለው ህወሃት ግን በወረቀት ላይ በፃፈው ህግ ዜጎች መረጃ የማግኘት መብታቸው ያልተገደበ ነው ቢልም በተግባር ግን የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት ያፍናል። ነፃ ሚዲያ እንዳይፈጠር ለማድረግ፤ የተፈጠሩትንም ለማጥፋት ግዜውንና የአገሪቷን ሃብት በከንቱ ያባክናል። ህወሃት ከድሃ ጉሮሮ እየነጠቀ ኢሳትን ለማፈን በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር አባክኗል። የአገሪቷ የህግ ተቋማትም ሌቦችንና ነፍሰ ገዳዮችን መከታተል ትተው በነፃነት እንፃፍ ብለው የተነሱ ጋዜጠኞችን በማሳደድ የአገሪቷን የሥራ ሠዓትና ሃብት በከንቱ ያባክናሉ። ህወሃቶች ይሄው ናቸው። አገር፤ ወገን፤ ህዝብ የሚባል ነገር በሂሊናቸው ያልተፈጠረ፤ እነርሱ ብቻቸውን ሌላውን ተጭነው መኖር የሚፈልጉ፤ የጨካኞችና የእብሪተኞች ስብስብ መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም።
የተከበራችሁ ያገራችን ዜጎች !
አገራችሁን በተመለከተ መረጃ ማግኘት የዜግነት መብታችሁ መሆኑን እንዳትረሱ። ይሄም እነርሱ “ህገ-መንግስት” ብለው በሚጠሩት ላይም በግልፅ ተቀምጧል። ይሄን በህግ ደንግጎ ሲያበቃ ኢሳትንና ሌሎችን ነፃ ሚዲያዎችን መስማት አትችሉም ሲል የማውቅላችሁ እኔ ነኝና የምትሰሙትንና የምታዩትን የምመርጥላችሁ እኔ ነኝ እያለ መሆኑን አስታወሱ። ይሄ ማለት አዋቂው እኔ እንጂ እናንተማ ክፉን ከደጉ ለመለየት ገና አልደረሳችሁም ማለት መሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል።መንግስት ነኝ ብሎ በአገሪቷ ጫንቃ ላይ የተቀመጠው ህወሃት-ኢሕአዴግ ህዝቡን የማያከብር ብቻ ሳይሆን ለህዝብ ያለው ንቀትም ወሰን የሌለው ሁኗል። ይሄ ዘረኛና ዘራፊ ቡድን ክብራችንን አዋርዶና አንገታችንን አስደፍቶ ሊገዛን አይገባውም። ፍርሃት ይብቃ። ህወሃት እየፈጠረ ያለው ፍራቻን መሸሸ አይገባም፤ ይሄን ፍርሃት መጋፈጥ የጀግና ተግባር ነውና ለክብራችሁና ለነፃነታችሁ ስትሉ ፍርሃቱን ተጋፈጡት እንጂ አትሽሹት።
በዚያ በጨካኞች መንደር ሁናችሁ በሠላማዊ ትግል ብቻ ለውጥ እናመጣለን ብላችሁ የተደራጃችሁ የፖለቲካ ድርጅቶችም መረጃ የማግኘት፤ መረጃ የመሰብሰብ እና የማሰራጨት መብታችሁ ነው ብለን ልንነግራችሁ አንዳዳም። በነፃ ሚዲያ መናገርም ሆነ ለማንኛውም ሚዲያ መረጃ የመስጠት ማንም የሚሰጣችሁ መብት እንዳልሆነ ታውቃላችሁ። እኛ እንደምንገምተው ኢሳትም ሆነ ሌሎች ነፃ ሚዲያዎች የእናንተም ሃብት ናቸው። ህወሃት-ኢሕአዴግ አትስሙ ወይም ደግሞ አትናገሩ ሲላችሁ ያንን የእብሪተኛ ትዕዛዝ አለመቀበላችሁን ለነፃ ሚዲያዎች መረጃ በመስጠትና ሃሳባችሁን በነፃው ሚዲያ በመግለፅ እምቢተኝነታችሁን በማሳየት ለምትመሩት ህዝብ አርአያ እንድትሆኑ ብናሳስባችሁ ደፈሩን እንደማትሉ ተስፋ እናደርጋለን። ከዚህ አንፃር ሰማያዊ ፓሪትና አንድነት ያወጡትን መግለጫ በአድናቆት የምንመለከተው መሆኑን ለማስታወቅ እንወደላን።
ለህወሃት-ኢሕአዴጎች !
ራሳችሁን ከአሸባሪ ምግባርና መዝገብ ማስፋቅ ሳትችሉ የነፃነት ፍላጎት ያላቸውን ሁሉ አሸባሪ እያላችሁ ማላዘናችሁን የምታቆሙበት ግዜ እየመጣላችሁ ነው። እናንተ ከላይ ሁናችሁ ህዝቡ ከሥር ሁኖ እናንተን ተሸክሞ ለዘላለም እንደማይኖር አበክረን ልናሳውቃችሁ እንወዳለን።በየሰው ደጅ ካድሬዎቻችሁን ልካችሁ ኢሳትን አትስሙ እያላችሁ የማስፈራራት እብሪታችሁ ረገብ የሚልበት ግዜ እየመጣላችሁ ነው። ዛሬ ህዝባችንን የእኛን ብቻ ስሙ፤ የእነርሱን አትስሙ ማለታችሁ ለህዝባችን ያላችሁን ንቀት የሚያመላክት ነው።ህዝባችንን እንደናቃችሁና እንዳዋረዳችሁ አትቀጥሉም። የነፃነትን ፍላጎት አፍናችሁ አታቆሙትም። የፍትህ ጥማታችንን በአፈሙዝ ልትገቱት አትችሉም። የእኩልነትን ጥያቄ በውሸትና በዛቻ አታዳፍኑትም። እውነት እውነት እንላችኋለን ወንጀላችሁ ሳይነገር፤ በስውር የዘረፋችሁት በአደባባይ ሳይገለጥ አይቀርም። እኛም ቀንና ማታ ለዚያ ግብ ሳናገራግር እየሰራን ነው። በአገራችን የነፃነት ጎህ ሳይቀድ ለሽፋሽፎቶቻችን እንቅልፍ፤ ለስጋችንም ዕርፍት አይሆንም። የዘረኞችና የዘራፊዎች ጀንበር ሳትጠልቅ፤ የእኩልነት ናፋቂዎች ጎህ ሳትቀድ አናርፍም። ያነገታችሁት መሣሪያ የሸንበቆ ምርኩዝ እስከ ሚሆን የጀመርነውን ትግል ዕለት ዕለት እያጎለበትነው እንቀጥላለን።
ህወሃት-ኢሕአዴጎች ሆይ ስሙ! ይሄን ህዝብ ከሚችለዉ በላይ ገፍታችኋታል። ህዝቡም ሊሸከማችሁ ከሚገባ በላይ ተሸክሟችኋል።እንዲህ ህዝባችንን መፈናፈኛ አሳጥታችሁ እና እስከ ልጅ ልጆቻችሁ ረግጣችሁ ለመግዛት ያለማችሁት ህልም በህልምነቱ ብቻ እንደሚቀር ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አይግባችሁ። ትግላችን ጥሩ መሠረት ይዟል። ከዚህ በኋላ ወደ ኋላ የሚመልሰን ምድራዊ ኃይል የለም።እውነት እውነት እንላችኋለን ለዘላለም ኢትዮጵያዊያንን አዋርዳችሁ የመግዛት ህልማችሁ ቅዥት መሆኑን ደግመን ልንነግራችሁ እንወዳለን።
በህወሃት-ኢሕአዴግ ውስጥ ሁናችሁ የነፃነት፤ የፍትህ እና የእኩልነት ጥያቄያችንን የምትጋሩን ወገኖቻችን እሰክ አሁን የምታደርጉት የውስጥ ትግል ፍሬ እያፈራ ነው። ፍሬውን በራሪ ወፍ እንዳይለቅመው የተለመደው ጥንቃቄ እንዳይለያችሁ ይሁን። አሁን ህዝቡ መረጃ እንዳያገኝና፤ መረጃ እንዳይሰጥ የሚሞከረው ሙከራ ህገ-መንግስት ተብየውን የሚጥስ መሆኑን ታውቃላችሁ። ይሄን ካድሬው ሁሉ እንዲገነዘበው የውስጥ ትግሉ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ራሱ ያወጣውን ህገ መንግስት አፈራርሶ ከትቢያ የሚቀላቅል ቡድን በምን ሞራል ብቃት ነው ሌላውን ህገ-መንግስቱን ሊንዱ ነበር እያለ የሚከሰው ? በኢትዮጵያዊያን ላይ የተጫነው ህገ-መንግስት በህወቶች ሲፈርስ ትክክል ፤በሌላው በተግባር እንዲውል ሲጠየቅ ደግሞ ስህተት ሁኖ በአሸባሪነት የሚያስከሥሥ መሆኑን ግንዛቤ መጨበጥ ይጠቅማል።
በመጨረሻም በህወሃት-ኢሕአዴግ የጭቆና ቀንበር ሥር ለምትንገላቱ ወገኖቻችን ሆይ ! አትፍሩ። ይህን የሚያስፈራራችሁን አካል እስከ መጨረሻው የማትሰሙበት ዘመን እየመጣ ነው። አሁን ፍርሃታችሁን ግደሉት።የምትሰሙትንና የምታዩትን እኔ ነኝ የምመርጥላችሁ ከሚል እብረተኛ እጅ ራሳችሁን ለማላቀቅ የግንቦት ሰባት ንቅናቄ እያደረገ ያለውን የነፃነት፤ የፍትህና የእኩልነት ትግል ተቀላቀሉ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

የወያኔ የውሸት ዘገባዎች ሲጋለጡ

ኦክስፋም” በመልካም ሥራቸው ከታወቁ ትላልቅ ዓለም ዓቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አንዱ ነው። በቅርቡ አንድ መቶ ሀያ አምስት አገሮችን ያካተተ ከምግብ አቅርቦትና አጠቃቀም ጋር የተያያዘ ጥናት ውጤት ይፋ አድርጓል። ጥናቱ አራት ዝርዝርና አንድ አጠቃላይ አመላካቾች አሉት።
1. አመላካች አንድ: የምግብ እጥረት
ይህ አመላካች “በየአገሮቹ ምን ያህል ለበላተኛው የሚበቃ ምግብ አለ?” የሚለውን ይለካል። በጥናቱ ውጤት መሠረት በምግብ እጥረት እጅግ የተጎዱ የመጨረሻዎቹ አስር አገሮች የሚከተሉት ናቸው: – ቡሩንዲ፣ የመን፣ ቻድ፣ ኢትዮጵያ፣ ማዳጋስካር፣ ናይጄሪያ፣ ላኦስ፣ ባንግላዴሽ፣ መካከለኛዉ አፍሪካ ሪፑብሊክ እና ህንድ። ኢትዮጵያ አገራችን ከመጨረሻ አራተኛ ናት።
2. አመላካች ሁለት: ለምግብ የመክፈል አቅም (Affordability)
ይህ አመላካች “የአገሩ ሕዝብ በአገሩ ዋጋ ምግብ ገዝቶ ለመብላት ምን ያህል አቅሙ ይፈቅድለታል?” የሚለውን የሚመልስ ነው። አሁንም ከመጨረሻ እንጀምር። አንጎላ፣ ዚምባቡዌ፣ ቻድ፣ ጉያና፣ ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ፣ ኮንጎ፣ ኬንያ፣ ጋምቢያ እና ኢራን የየአገሩ ሕዝብ ምግብ መሸመት የሚቸገሩባቸው አገሮች ናቸው። አገራችን ኢትዮጵያ ከመጨረሻ አምስተኛ ናት።
3. አመላካች ሶስት: የምግብ ጥራት
ይህ የምግብ ይዘትንና የአያያዝ ንጽህናን የሚመለከት ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ማዳጋስካር፣ሞዛምቢክ፣ ቻድ፣ ቶጎ፣ ዛምቢያ፣ ማሊ፣ ናይጄሪያ፣ ባንግላዴሽ፣ ሌሶቶ ከመጨረሻው እስከ አስረኛ ደረጃ ይዘዋል። ኢትዮጵያ በምግብ ጥራት የመጨረሻዋ አገር ናት።
4. አመላካች አራት፡ የሰውነት ውፍረት እና የስኳር በሽታ
ይህ አመላካች ከልክ ያለፈ ውፍረት ዓለም ዓቀፍ የጤና ችግር እየሆነ በመምጣቱ የገባ አመልካች ነው። ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥሩ ውጤት ያመጣችሁ በዚህ አመላካች ብቻ ነው። ኢትዮጵያ አብዛኛው ሕዝቧ ቀጫጫ ነው፤ የስኳር በሽታም እንደሌላው አገር የተስፋፋባት አገር አይደለችም።
5. አማካይ ውጤት
የእነዚህ አራት አመላካቾች ድምር ውጤት አጠቃላይ ውጤትን ይሰጣል። በአጠቃላይ ውጤት: ቻድ፣ ኢትዮጵያ፣ አንጎላ፣ ማዳካስካር፣ የመን፣ ቡሩንዲ ናይጄሪያ፣ ሞዛምቢክ፣ ዚምባቡዌ፣ ሴራሊዮን ከመጨረሻ እስከ አስረኛ ወጥተዋል። ኢትዮጵያ ከመጨረሻ ሁለተኛ ነች።
ይህ ምንን ያመለክታል?
ወያኔ ባለፉት አስር ዓመታት በተከታታይ ከ11% በላይ ኢኮኖሚውን አሳድጌዋለሁ ሲለን ነበር። እድገቱ ያተኮረው ገጠር፤ ምንጩም ግብርና ነው ብሎን ነበር። ሐቁ ግን ከላይ የተመለከተው ነው።
እርግጥ ነው የወያኔ ሹማምንት በከተሞች ሕንፃዎችን ይገነባሉ፤ በገጠሮች በመቶዎች ሄክታር የሚለካ ለም መሬት ይዘው ፈጣን ገንዘብ በሚያስገኙ የአበባ፣ የጫትና የቃጫ ምርት ላይ ተሰማርተዋል። ከራሳቸውም አልፈው ሀብታም የውጭ አገራት ሸሪኮቻቸውን በአገራችን ለም መሬት ይበልጥ ያበለፅጓቸዋል። የእነሱ የግላቸው፣ የቤተሰቦቻቸው፣ የዘመዶቻቸው እና የሸሪኮቻቸው ኢኮኖሚ እየተመነደገ መሆኑን እናውቃለን። ይህን በገዛ ዓይኖቻችን የምናየው ሀቅ ነው።
ሆኖም ግን የእነሱ ኢኮኖሚ ማደግ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማደግ አለመሆኑ እናውቃለን። አገራችን ከጓረቤት አገሮች ጋር ስትነፃፀር ወደ ኋላ እየቀረች መሆኑ ያንገበግበናል። በቅርቡ አክስፋም በጥናት ያረጋገጠዉ የኢትዮጵያ ገበሬዎች በየቤታቸው ከወዳጆቻቸው ጋር በምስጢር የሚያወሩትን እውነት ነው።
ከሳምንት በፊት ደግሞ “ኢኮኖሚክ ኢንተለጀንስ ዩኒት” የተሰኘው ታዋቂ የምርምር ተቋም አንድ የጥናት ውጤት ይፋ አድርጎ ነበር። በዚህ የጥናት ውጤት መሠረት በዓለም በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ያሉ አስር አገሮች በቅደም ተከተል ሞንጎሊያ፣ ሴራሊዮን፣ ቱርክሜንስታን፣ ቡታን፣ ሊቢያ፣ ኢራቅ፣ ላኦስ፣ ቲሞር-ሊስቲ፣ ኤርትራ እና ዛምቢያ ናቸው። በዝርዝሩ ውስጥ ኢትዮጵያ አገራችን የለችበትም።
በዓለም አቀፍ መድረኮችም የወያኔ መረጃዎች ውሸትነት እየተጋለጡ መሆናቸው በጎ ምልክት ነው። የሚያሳዝነው ግን ይህንን ሀቅ የሚያዉቁ ምዕራባዉያን ለጋሽ አገሮች አሁንም ወያኔን እየረዱና እየደገፉ ሥቃያችን የሚያራዝሙብን መሆኑ ነው።
ለዚህም ነው ግንቦት 7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዘላቂ መፍትሔ ሊመጣ የሚችለው በአገራችን መሠረዊ የሆነ የአስተዳደር ለውጥ ሲኖር ነው ብሎ የሚያምነው። የወያኔ አገዛዝ በዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እስካልተተካ ድረስ የኢትዮጵያ አብዛኛው ሕዝብ መደህየቱ፤ ጥቂት ሀብታሞች ደግሞ በብዙሀኑ ድህነት መበልፀጋቸው አይቀርም። የወያኔ ውሸቶች ለኢትዮጵያ ድሀ ምግብና መጠለያ አይሆኑለትም። ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም ማምጣት የምንችለው ወያኔን አስወግደን በምትኩ ለሕዝብ ሁለተናዊ እድገት የሚጨነቅ መንግሥት መምረጥ ስንችል ብቻ ነው።
ስለሆነም ግንቦት 7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በውሸት እድገት እያደናቆረን፤ በተግባር ግን እያደኸየን ያለውን ዘራፊውን ወያኔን አስወግደን በሕዝብ ነፃ ምርጫ የተመረጠ መንግሥት እንዲኖረን ትግላችን እናጠንክር ይላል።


    ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

    Thursday, January 23, 2014

    Tuesday, January 21, 2014

    የደህንነት ሰራተኞች ሃላፊነታችን ለአገር ወይስ ለፖለቲካ ስርአቱ ነው የሚል ጥያቄ አነሱ

    ጥር ፱ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መንግስት በመረጃዎች አያያዝ ዝርክርክነት ፣ በሳይበር በሚደረጉ ስለላዎች እና ከውስጥ ባሉ የመንግስት አካላት እየሾለኩ በሚወጡ መረጃዎች ህልውናየ አደጋ ላይ ወድቋል በማለት ግመገማ ማድረጉን ተከትሎ  ”የደህንነት ሰራተኞች ሃላፊነታችን ለማን ነው?” የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውን  ከደህንነት መስሪያ ቤት ለኢሳት የደረሰው በድምጽ የተደገፈ መረጃ አመለከተ። በስብሰባው ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና የመንግስት ሹሞችም ተገኝተው ነበር።
    ጥያቄውን ያነሱት በፌደራል ስር የሚገኙ የደህንነት ስራተኞች እና ቀደም ብሎ በአቶ መለስ ዜናዊ ዘመን በትግራይ ውስጥ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ሽፋን የተቋቋመው ኤም አይ ቲ እየተባለ በሚጠራው ከመቀሌ ከተማ 9 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በተገነባው ተቋም ውስጥ ተመርቀው የወጡት የደህንነት ሰራተኞች ናቸው።
    የደህንነት ሰራተኞቹ “የእኛ ሃለፊነት የአገር ደህንነትን ማስጠበቅ ነው የፖለቲካ ስርአቱን ?” በሚል  ጥያቄ ያነሱ ሲሆን፣ አንድ  የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን  ” የፖለቲካ ስራ የማይሰራ ደህንነት የለም፣ የደህንነት ስራ ሲጀመር ስርአት የማቆየት ስራ ነው፤ ስርአቱን የምናቆይበት ደግሞ ፕሮፌሽናል ነው፣ በስርአቱ ላይ እምነት ማሳደር የሚጠይቅ ተግባር ነው፣ የግንቦት7ትን አስተሳሰብ የሚያቀነቅንና ስርአቱ በጉልበት መፍረስ አለበት ብሎ የሚያስብ ሰው፣ የተስፋየ ወልደ ስላሴ አይነት የደህንነት ብቃት አለው ቢባል፣ ሞሳድ 20 አመታት አሰልጥኖታል ቢባል ስርአቱን ከማፍረስ ውጭ ደህንነቱን ሊያስጠብቅ አይችልም” ፣ ስለዚህ የደህንነት ስራ ለሚሰሩ ወገኖች የፖለቲካ ወገንተኝነታቸው ወሳኝ ነው የሚል መልስ ሰጥተዋል ።
    “የደህንነት ተቋሙ ፣ ሰራዊቱና ሚዲያው በተቃዋሚዎች ዘንድ መቼውንም ቢሆን ገለልተኛ ተደርጎ አይቆጠርም” ያሉት እኝህ ከፍተኛ ባለስልጣን ፣ ገለልተኛ ማድረግ የሚባል አስተሳሰብ ያለው ካለ እንደዛ ሊሆን አይችልም፣ ሊሆን የሚችለው የተቃዋሚዎችን ሰዎች ደህንነት ውስጥ ማስገባት ነው ብለዋል። ” በተለይም በተቋም ደረጃ ፤በምህጻረ ቃል ኢንሳ እየተባለ የሚጠራው የመረጃ ደህንነት መስሪያ ቤት፤ የዜግነት እና ኤምግሬሺን ፤የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤በጀኔራል ሳሞራ የኑስ የሚመራው የመከላከያ ደህንነት ፤የአስተዳደር እና ፀጥታ ፤ የፌደራል ፖሊስ ፤ የፀረ ሽብር ግብረ ሃይል በእዝ ሰንሰለት በሚፈጠር ልዩነት እርስ በርስ እየተወዛገቡ ሲሆን፣ ተቋሞቹን በትክክል የሚመሩትን አካላት  ለመለየት አስቸጋሪ ሆኖ መገኘቱና እርስ በርስ በሚፈጥሩት  እሰጥ አገባ  አንዱ አንዱ የሚሰራውን የማጠፋፋት እርምጃ እየወሰዱ መሆኑ በግምገማው ላይ ተነስቷል፡፡
    የመንግስት ሚስጥሮች ለሶስተኛ ወገኖች ተላልፈው እየተሰጡ በመሆኑ ሚስጢሮችን  መደበቅ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ሲሉ አንዳንድ ባለስልጣኖች አስተያየቶችን ሰጥተዋል።
    ለተነሱት አስተያየቶች መልስ የሰጡት ባለስልጣኑ፣ ኢንሳ የተቋቋመውም ይህን ለመስራት መሆኑን  ገልጸው፣ “አገሮች ሙሉ በሙሉ ከሳይበር ስለላ ነጻ ባለመሆናቸው አቶ ሃይለማርያምም ነጻ ናቸው ብየ አላስብም” ብለዋል። “አሜሪካኖች የምንናገረውን ሁሉ ከፈለጉ ይሰሙታል” የሚሉት እኝሁ ባለስልጣን፣ “እኛም የአቅማችንን ያክል አሜሪካኖች የሚናገሩትን ለማዳመጥ እንሞክራለን” ብለዋል። የሳይበር ስለላ ለማካሄድ ጥሩ ጅምሮች ቢኖሩም፣ ያን ያክል የምንኩራራበት ግን አይደለም በማለት ኢነሳ ያለበትን ደረጃ አመላክተዋል
    ከኦሮሚያና ከደቡብ የመጡ የደህንነት ሹሞች ደግሞ “በመከላከያ የደህንነት ተቋሞች ውስጥ የአንድ ብሄር የበላይነት ጎልቶ ይታያል” በሚል ቅሬታ ያነሱ ሲሆን ፣ ባለስልጣኑም “የሰራዊት ማመጣጠን ስራ በረጅም ጊዜ የሚሰራ ስራ  ነው ” በማለት ለመመለስ ሞክረዋል።
    ” ትግሉን መርተው እዚህ ድረስ የመጡ ሰዎችና በመከላከያ ውስጥ ያለውን የመኮንኖች ቦታ የያዙት ከአንድ አካባቢ የመጡ መሆናቸው ግልጽ ነው የሚሉት ባለስልጣኑ፣ ያም ሆኖ ከትግራይ የመጡ በርካታ ጄኔራሎች ጡረታ እንዲወጡ ቢደረግም ሂደቱ ግን ረጅም ጊዜ የሚወሰድ ነው ሲሉ አክለዋል።
    “የብሄር ተዋጽኦ ብቻ የአንድን ሰራዊት ጠንካራና ደካማ ጎን መገለጫ ተደርጎ መወሰድ ካለበት አደጋ አለው ” ያሉት ባለስልጣኑ፣ የአንድ ብሄር የበላይነት አለ ተብሎ በአጭር ጊዜ ለማመጣጠን ብቻ በአንድ አዳር ሁሉንም ነገር መቀየር እንደማይቻል መንግስት ያምናል ሲሉ ተናግረዋል
    አቶ መለስ ዜናዊ በውጭ ሃይሎች ተገድለዋል ይባላልና በምን እንደሞቱ በትክክል ይነገረን በሚል ባለስልጣናት ላነሱት ጥያቄም የደህንነት ባለስልጣኑ፣ “አቶ መለስ በውጭ ሃይሎች ተገድለዋል የሚል ትክክለኛ ማስረጃ የለም በማለት መመለስ የጀመሩት ባለስልጣኑ፣ እርሳቸው የሞቱት በስራ ብዛት ተዳክመው እና ህክምናውን መቋቋም ባለመቻላቸው ነው ሲሉ ደምድመዋል።

    Monday, January 20, 2014

    የአማራ ክልል የድርጅት ጉዳይ ሃላፊዎች ከአሸባሪዎች ጋር ግንኙነት ይኖራቸል ብለው የሚጠረጥሩትን ሁሉ እንዲይዙ ታዘዙ

    -ባለፈው ወር በአማራ ክልል ርዕሰ ከተማ ባህርዳር የተካሄደውን የብአዴን እና የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ ላይ የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የዞን እና የወረዳ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊዎች ኢህአዴግ አሸባሪ እያለ ከሚጠራቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር  በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ግንኙነት ይኖራቸዋል ተብሎ በሚጠረጠሩት ወጣቶች ላይ  የቁጥጥር ዘመቻ እንዲካሄዱ ትእዛዝ ተላልፎላቸዋል።
    ጥር 8፣ 2006 ዓም በሁሉም የአማራ ክልል ወረዳዎች በተደረገው የብአዴን ስብሰባ ላይ ወጣቶች መረጃ በማስተላለፍ እና ለአሸባሪዎች መሳሪያ የሚሆኑ ሰዎችን በመመልመል ላይ በመሆናቸው  የግንኙነት ሰንሰለቱን ለመበጠስ አባላቱና አመራሩ ጠንክረው መስራት እንደሚገባቸው ተገልጾላቸዋል። እያንዳንዱ አባል በአሸባሪዎች ፕሮፓጋንዳ ሳይዘነጋ ጠንክሮ እንዲሰራም ትእዛዝ ተላልፎለታል።
    “ከየትኛውም የሀገሪቱ ክልል ወጣቶች ባላይ የአማራ ክልል ወጣቶች ከአሸባሪዎች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው መረጃ አለኝ” ያለው ኢህአዴግ በክልሉ እነዚህን ወጣቶች የመቆጣጠርና የመከታተል ዘመቻ በዘርፈ ብዙ ስልቶች ታጅቦ መካሄድ እንዳለበት አሳስቧል።
    “በመሰረተ ቢስ አሉባልታዎች ከኢህአዴግ የኮበለሉና ወስጣቸው የሸፈተ የብአዴን አባላትም ሀቁን ተገንዝበው ከኢህአዴግ ጋር እንዲቀጥሉና ሀገሪቱን ወደ ላቀ እድገት እንዲያሸጋግሩ የድርጅት ጉዳይ ሀላፊዎች በስብሰባው ላይ ተናግረዋል፡፡
    የመወያያ አጀንዳዎች ትምህርትና የመኖሪያ ቤት ሊዝ ጉዳይ ቢሆኑም የስብሰባው ውሎ ግን ከአጀንዳዎች ውጭ አሸባሪዎች በሚሏቸው አካላት ላይ ነበር ያሉት ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ የድርጅት አባላት፣  መንግስት በመኖሪያ ቤት ሊዝ ያቀረበው ጉዳይ ግን ከፍተኛ ተቀዋውሞ አስነስቷል ብለዋል፡፡ ህጉ የማንንም ኢትዮጵያዊ ምጣኔ ሀብታዊ አቅም ያላገናዘበ፣በአሰራር ውጣ ውረድ የተበተበና በዘፈቀደ እንዲወጣ የተደረገ ይመስላል ያሉት አባላቱ በተለይ የመንግስት ሠራተኞችን ከጨዋታ ውጭ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
    አዲሱ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከብአዴን እየኮበለለ የሚጠፋውንና ለአሸባሪዎች መጠቀሚያ እየዋለ ነው ያሉትን ሃይል እንቅስቃሴ ለመግታት እርምጃ መውሰድ መጀመራቸውንም የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
    በአማራ ክልል የሚገኙ ወጣቶችና የብአዴን አባላት ” ብአዴን የህወሀት በቅሎ መሆኑ ያብቃ” በማለት ጥያቄዎችን እያነሱ ነው።
    በክልሉ ውስጥ የተንሰራፋው ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር እጦትና አፈና መባባስ አባላቱን ለተስፋ መቁረጥ መዳረጉንም ወጣቶች ይናገራሉ።

    Wednesday, January 15, 2014

    የኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ ደብዳቤ ላከ

    ጥር ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኮሚሽኑ በደብዳቤው የኢህአዴግ መንግስት ሰፊ የሆነውን የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የመንግስትታቱ ዋና ጸሀፊ እንዲያዩት ጠይቋል።
    ገዢው ፓርቲ በሱዳን ውስጥ ተቃዋሚዎች የመደራጃ ቦታ እንዳያገኙ በሚል ከሱዳን ጋር ተቀባይነት የሌለው የድንበር ውል እያደረገ መሆኑንም ኮሚሽኑ ገልጿል።
    የአፍሪካ ቀንድ በዚህ መሬት የተነሳ ለሌላ ግጭት ሊዳረግ እንደሚችል ኮሚሽኑ አስጠንቅቋል።

    ኢህአዴግ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መመሪያን መተውን አስታወቀ

    ጥር ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ አማካሪ የሆኑት አቶ በረከት ስምዖን በቅርቡ ከሚኒስትሮች እና ከኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይትና ግምገማ ላይ ” ህዝቡን ለመምራት የሚነደፉ ንድፈ ሀሳቦች ( ቲዮሪዎች) በየጊዜው ካልተሻሻሉ የሚዝጉ በመሆናቸው አብዮታዊ ዲሞክራሲ በልማታዊ ዲሞክራሲ እንዲተካ ተደርጓል ብለዋል። የኢህአዴግ መንግስት ይበልጥ የሚገለጸው በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ሳይሆን በልማታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ነው በማለት አቶ በረከት ገለጽዋል
    አቶ በረከት አብዮታዊ ዲሞክራሲ በልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ከመተካቱ በፊት ፣ ግንባሩ ለ3 ተከፍሎ እንደነበር ገልጸዋል። አንደኛው የአመራር ወገን “ችግራችን የውስጥ ነው እና በቅድሚያ የውስጥ ችግራችንን እንፈትሽ የሚል” አቋም ሲይዝ ፣ ሌላው ወገን ደግሞ ዋናው ችግራችን ሻዕቢያ በመሆኑ በቅድሚያ ሻዕቢያን እንውጋ የሚል አቋም ይዞ እንደነበር፣ እና ሻእቢያን ከወጋን በሁዋላ ወደ ውስጥ ችግራችን እንመልከት የሚለው ሶስተኛው አማራጭ አሸንፎ መውጣቱን ገልጸዋል
    በ1997 ዓም ዋናው የአመጽ ሀይል የነበረው ስራ ያጣውና ተስፋ የቆረጠው ወጣት ነው በማለት የገለጹት አቶ በረከት ለወጣቱ ስራ ካልተፈጠረለት በመንግስት እና በአገር ላይ እንደሚያምጽ ገልጸዋል። መንግስት የምርጫ 97ትን አመጽ ያስነሱት ተቃዋሚዎች ናቸው ብሎ ሲከስ መቆየቱ ይታወቃል።
    ኢህአዴግ ከባላሀብቱ ነጻ የሆነ መንግስት ለመመስረት መነሳቱን የገለጹት አቶ በረከት፣ ስልጣን ላይ የሚያመጣን አርሶአደሩና በከተማ ያለው ጭቁኑ ህዝብ ነው እንጅ ባለሀብቱ  አይደለም ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በባለሀብቱ ገንዘብ የሚተዳደር አይደለም ያሉት አቶ በረከት፣ ገንዘብ ከፈለገ ከባላሀብቱ በግብር መልክ መውሰድ እንደሚችል ተናግረዋል። ይህ መንግስት ለህልውናው የራሱ የገቢ ምንጭ እንዳሉት የጠቀሱት አቶ በረከት፣ አየር መንገድን ባንኮችን እና መብራት ሀይልን በምሳሌነት አንስተዋል። የመንግስትን አስተዳደር ያለምንም ችግር ለማስኬድ የባለሀብቱም የውጭ ድጋፍም እንደማያስፈልግ አቶ በረከት አክለዋል።
    አቶ በረከት፣  ኢህአዴግ ምርጫውን ያለባለሀብቶች ድጋፍ ማሸነፍ እንደሚችል እየገለጹ ባለበት ጊዜ በድንገት የመንግስት ተቋሞችን በመግለጽ በቂ ገንዘብ አለን ማለታቸው ተሰብሳቢዎችን ማስገረሙን ስብሰባውን የተከታተሉት አንድ ከፍተኛ የኢህአዴግ  አመራር ገልጸዋል። አመራሩ እንዳሉት ኢህአዴግ ለምርጫ ማስኬጃ ከመንግስት ገንዘብ እንደሚወሰድ የ  አቶ በረከት ንግግር በቂ ማሳያ ነው ።
    መንግስት የራሱ ገንዘብ ከሌለው እንደምእራብ የአፍሪካ አገራት ይሆናል ያሉት አቶ በረከት፣ የኮትዲቩዋር ሚኒስትሮች ደሞዛቸውን የሚወስዱት ኮትዲቯር ከሚገኘው የፈረንሳይ ኢምባሲ ነው ይላሉ። በኬንያም ሁኔታው ተመሳሳይ መሆኑን አቶ በረከት አክለዋል
    ኢህአዴግ በ2002 በተደረገው ምርጫ ከግል ባለሀብቶች ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡ ይታወቃል።
    በባቡር ግንባታ፣ በመንገድ ቁፋሮና በትራንሰፖርትና እጥረት የተነሳ በአዲስ አበባ መኖር ያስጠላል ያሉት አቶ በረከት ያም ቢሆን ግን ህዝቡ ልማት ነው በሚል እንደሚቀበለው ገልጸዋል ።

    Tuesday, January 14, 2014

    የአባይ ግድብ በተያዘለት እቅድ መሰረት ያለምንም ችግር እየተከናወነ ነው ሲሉ ሚኒስትሩ ተናገሩ

    ጥር ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሚኒስትር አለማየሁ ተገኑ ይህን የተናገሩት አንድ የግብጽ ጋዜጣ የአገሪቱን ከፍተኛ ባለስልጣን በመጥቀስ የዘገበውን ዜና ተከትሎ ነው። ጋዜጣው ፣ ኢትዮጵያ ለፖለቲካ ፍጆታ ለማዋል በማሰብ ግድቡ 30 በመቶ እንደተጠናቀቀ እያስወራች መሆኑዋንና ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት እንዳጋጠማት” መዘገቡ ይታወቃል።
    የአባይ ግድብ ግንባታ የገንዘብም ሆነ የቴክኒክ ችግር አላጋጠመውም ያሉት ሚኒስትሩ፣ በተያዘለት የጊዜ ገደብም እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል። ይሁን እንጅ ይህ የተያዘለት የጊዜ ገደብ መቼ እንደሆነ አልገለጹም።
    በግብጽ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ መካከል ሲደረግ የነበረው የሶስትዮሽ ውይይት መቋረጡን ተከትሎ፣ የግብጽ ወታደሮችና ፖለቲከኞች በቀጣይ ስለሚወስዱት እርምጃ እየመከሩ ነው።

    ኢህአዴግ ከምርጫ 2007 በሁዋላ ረብሻ ሊነሳ ይችላል አለ

    ጥር ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኢትዮጵያን ላለፉት 23 ዓመታት የገዛው ኢህአዴግ መጪውን ምርጫ ተከትሎ በአዲስ አበባና በዋና ዋና የአገሪቱ ከተሞች ረብሻዎች ሊነሱ እንደሚችሉ ፓርቲው ድምዳሜ ላይ መድረሱን አስታውቋል።
    የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት በኢትዮጵያ መንግስት አሸባሪ ተብለው የተፈረጁት በተለይ ግንቦት7 እና ኦነግ ምርጫውን ተከትሎ በምርጫ 97 የታየውን አይነት የህዝብ አመጽ ለማስነሳት እየሰሩ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሰው ኢህአዴግ፣ ከአሁኑ ጀምሮ በአንድ ለአምስት አደረጃጀትና የከተሞችን ነዋሪዎች ስለ አሸባሪዎች አላማ እና ግብ በማስረዳት ህዝቡ በአመጹ ተሳታፊ እንዳይሆን እንደሚያስተምር አስታውቋል።
    አሸባሪ የተባሉ ድርጅቶች በመልካም አስተዳደር፣ በሙስና እና በኢኮኖሚ ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችን ተጠቅመው ህዝቡ በመንግስት ላይ እንዲነሳ ሊያደርጉ ይችላሉ አለው ኢህአዴግ፣ ለዚህ አላማ እንዲረዳቸው ደግሞ ኢሳትንና ቪኦኤን የመሳሰሉ የመገናኛ ብዙሀንን በአገር ውስጥ ደግሞ አንዳንድ ጽንፈኛ አስተሳሰብ ያላቸውን መጽሄቶች ሊጠቀሙ ይችላሉ ብሎአል። በአገር ውስጥ በሰላማዊ ትግል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ፣ ለአመጽ ጥሪው ህጋዊ ሽፋን ለማሰጠት ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ ።
    በተለይ የአዲስ አበባ ህዝብ የአሸባሪዎች ኢላማ እንዳይሆን ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ኢህአዴግ ገልጿል።
    በሚቀጥለው አንድ አመት ውስጥ በአዲስ አበባ እና በክልል ዋና ዋና ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች እና የመንግስት ሰራተኞች በሽብረተኝነት ዙሪያ ተከታታይ ትምህርት የሚሰጣቸው ሲሆን፣ ግንባሩም ከእዚህ ስልጠና የአካባቢ የሰላም ጠባቂዎችን እንደሚመለምል ፣ በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ገዢውን ፓርቲ አይደግፉም የሚባሉትን የመለየት ስራም እንደሚሰራ ታውቋል።
    ኢህአዴግ ምርጫውን ተከትሎ ሊነሳ የሚችል ማንኛውም ተቃውሞ ሽብርተኝነት ነው ሲል ድምዳሜ ላይ ደርሷል። በምርጫ ሂደቱ ላይ ፍትሀዊ ያልሆኑ አሰራሮች እንዲሁም የድምጽ ማጭበርበሮች እንኳን ቢከሰት ተቃዋሚዎች የተቃውሞ ሰልፍ እንዲያደርጉ አይፈቀድላቸውም።

    Thursday, January 9, 2014

    የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት ወታደራዊ ጥቃት ፈፀመ፡፡

    PDFPrintE-mail
    Written by Administrator   
    Tuesday, 07 January 2014 17:36
    በሀገራችን ላይ የተንሠራፋውን አምባገነናዊ ሥርዓት ገርስሶ ለመጣል የመጨረሻ አማራጭ የሆነውን የትጥቅ ትግል በማካሄድ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት በጠላት ላይ የሚወስዳቸውን ወታደራዊ የማጥቃት እርምጃዎች አጠናክሮ በመቀጠል በታህሳስ 23 ቀን 2006 ዓ/ም በሰሜን ጎንደር በላይ አርማጭሆ ወረዳ ልዩ ስሙ ገራርዋ ባምብላ ወንዝ በተባለው ቦታ መሽጎ የአካባቢውን ህብረተሰብ ሲያሰቃይና ሲያንገላታ ከነበረው የወያኔ 24ኛ ቴዎድሮስ ክ/ጦር እና ከፀረ-ሽምቅ ታጣቂ ኃይሎች ጋር ባደረገው ውጊያ 24 የጠላት ወታደሮችን ገድሎ 11 በማቁሰል የግንባሩ ሠራዊት አንፀባራቂ ድል አስመዝግቧል፡፡ በዚሁ ዕለትም በተደረገው እልህ አስጨራሸ ውጊያ የወያኔ 24ኛ ቴዎድሮስ ክ/ጦር ከኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት የሚደርስበትን የተኩስ ናዳ መቋቋም ተስኖት ሙትና ቁስለኛውን እያዝረከረከ እግሬ አውጪኝ በማለት መፈርጠጡን ታውቋል::
    ይህ በእንዲሀ እንዳለ የአካባቢው ነዋሪዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት በጠላት ላይ ባስመዘገበው ከፍተኛ ወታደራዊ ድል መደሰታቸውና ወደፊትም ሀገራዊና ሕዝባዊ አላማን አንግቦ የህብረተሰቡን እምባ በማበስ ግንባር ቀደም በመሆን ለሀገርና ለወገን ደራሽነቱን እያስመሰከረ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊትን በመደገፍ የቆመለትን አላማ ከግብ ለማድረስ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀው ግንባሩ በተከታታይ ጊዜያቶች የሚወስዳቸው ወታደራዊ ጥቃቶችና የሚያስመዘግባቸው አንፀባራዊ ድሎች የወገንን አንጀት በማራስ በአንፃሩ ደግሞ የጠላትን አንገት በማስደፋቱ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡
    በመጨረሻም የአካባቢው ህብረተሰብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት የጀግና አቀባበል ያደረጉለት ሲሆን ወታደራዊ የማጥቃት እርምጃው ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ከግንባሩ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ ሀገራዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ቆርጠው መነሳታቸውን አስታውቀዋል፡፡
     የኢትዮዽያ ህዝብ አርበኞች ግንባር