Tuesday, February 18, 2014

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተጠለፈበትን ምክንያት ለማወቅ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንደቀጠሉ ነው

አየር መንገዱ ከአዲስ አበባ ወደ ሮም ጣሊያን በማምራት ላይ በነበረበት ጊዜ  ረዳት አብራሪው የጉዞውን አቅጣጫ በመቀየር ጄኔቭ አውሮፓላን ማረፊያ በማሳረፍ እጁን ለፖሊስ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ መንግስት የኮሚኒኬሽን ባለስልጣን የሆኑት ሬድዋን ሁሴን አየር መንገዱ የተጠለፈው ሱዳን በቆመበት ጊዜ በተሳፈሩ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች ነው በማለት መጀመሪያ ላይ ለረዩተርስ መግለጫ ቢሰጡም፣ የስዊዘርላንድ ፖሊስ ግን ፈጥኖ ጠላፊው የአየር መንገዱ ረዳት አብራሪ መሆኑንና የደህንነት ስጋት እንዳለበት በመግለጽ እጁን በሰላም መስጠቱን አስታውቀዋል።
በአለም የጠለፋ ታሪክ ያልተመደ ክስተት ነው የተባለው ይህ የአውሮፕላን ጠለፋ፣ የፖለቲካ ይዘት ያለው ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል።
ማንነቱ ያልታወቀው ረዳት ፓይለት በ30 ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ ጄኔቭ አውሮፕላን ማረፊያ እንደደረሰ በመስኮት በኩል በመውጣት እጁን በሰላም ለፖሊስ ሰጥቷል። ፖሊስ እንዳስታወቀውም ጠላፊው ምንም አይነት የጦር መሳሪያ አልያዘም።
በአውሮፕላኑ ውስጥ በነበሩ ተሳፋሪዎች ላይ ምንም አይነት ጉዳትም አልደረሰም።
ጄኔቭ የሚገኘው የኢሳት ወኪል እንደዘገበው ምንም እንኳ ጄኔቫ አየር ማረፊያ ከሰአታት በሁዋላ ተራግገቶ ስራውን ለማከናወን የቻለ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር እስከ ቀኑ 9 ሰአት ድረስ ተሳፋሪዎች ወደ ሮም አልተመለሱም፣ አውሮፕላኑም ባለበት ቆሞ ይታይ ነበር። ከቀኑ 9 ሰአት ከሰላሳ አካባቢ አውሮፕላኑ ለጥገና ወይም ተሰፋራዎችን ወደ ሮም ለመመለስ ሲንቀሳቀስ መታየቱን ወኪላችን ገልጾ፣ ጠላፊውን ለማግኘት የተደረገው ሙከራ በፖሊስ ጥብቅ ቁጥጥር የተነሳ ሊሳካ አልቻለም።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች በተለያዩ ጊዜያት በአስተዳደሩ እንደሚማሩ ይታወቃል። አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሀን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በማንሳት ጠለፋውን ከፖለቲካ ጋር በማያያዝ ለማየት እየሞከሩ ነው።
ረዳት ፓይለቱ አላማው ጥገኝነት መጠየቅ ቢሆን ኖሮ አውሮፕላኑን ሮም ላይ ካሳረፈ በሁዋላ ጄኔቭ ገብቶ በሰላም እጁን መስጠት ይችል እንደነበር ጁኔቭ የሚገኙ አንዳንድ አስተያየት ሰጪ ይናገራሉ።  ረዳት ፓይለቱ ይህ እድል እያለው እና አውሮፕላን መጥለፍ ወንጀል መሆኑን እያወቀ እንዲህ አይነት እርምጃ ለመውሰድ የተነሳሳው አንድ ከባድ ምክንያት ቢኖረው ነው በማለት እኝሁ አስተያየት ሰጪ ገልጸዋል።
በስዊዝ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጠበቆች ረዳት ፓይለቱን ለማግኘትና ጠበቃ ቐጥረው ለመከራከር ፍላጎት እንዳላቸው ለኢሳት ገልጸዋል።
ስቱዲዮ ከመግባታችን በፊት በአውሮፕላኑ ወስጥ ተሳፍራ የነበረች አንዲት ወጣት አግኝተናል። ወጣቱዋ እንደምትለው አውሮፐላኑ የተጠለፈው ከሮም ወደ ሚላን በሚመበርበት ጊዜ ነው። ሮም ማረፉንና መንገደኞችን ማሳፈሩን ወጣቷ ተናግራለች። አቶ ሬድዋን በበኩላቸው አውሮፐላኑ ሮም ሳያርፍ ወደ ጄኔቭ መሄዱን ተናግረዋል። ወጣቱዋ አብራሪው ረጅም ና ጠይም መሆኑንሮም ላይ ሻንጣውን ማውረዱንና ፊቱ ላይ አለመረጋጋት ይታይበት እንደነበር ገልጻለች።
ኢሳት ዜና

Friday, February 14, 2014

ተዋርዶ መገዛት ይብቃን!

የወያኔ ሹማምንትና አደርባይ ሎሌዎቻቸው አንገቱን አስደፍተው የሚገዙትንና የሚዘርፉትን ህዝብ ይበልጥ ስብእናውን አዋርደው ሊገዙት ለምን እንደሚፈልጉ የማይገባን ጥቂቶች አይደለንም። እነዚህን ግፈኞች ቀረብ ብሎ ላያቸው ግን ይህ ድርጊታቸው እንቆቅልሽ አይደለም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህዝብ አይሰማንም ብለው በር ዘግተው ከሚያካሂዷቸው ጉባኤዎች እያፈተለኩ የሚወጡ የቪዲዮና የድምጽ መረጃዎች የነዚህን ግፈኞች ስነ ህሊና ግልጽ አድርገው ያሳያሉ።
ከወራት በፊት የሶማሊያ ክልል ፕሬዝዳንት የሀገር ሽማግሌ ሰብስቦ የወያኔ አላማ ከእሱ ጎሳ ጋር ተባብሮ ሌላውን ብሄረሰብ የበታች አድርጎ መግዛት መሆኑን ሲናገር የሚያሳይ ቪዲዮ ተመልክተን ነበር። የክልሉን ህዝብ የሚጨፈጭፈው ለዚህ ሲባል መሆኑን ለማሳመን ነበር በሩን ዘግቶ የተናገረው።
ሰሞኑን ደግሞ አንድ የአማራ ክልል የወያኔ ሹምና ሎሌ አንደ እንደሶማሌ ሹም ካድሬዎቹን ሰብስቦ በአማራው ህዝብ ላይ ተሳለቀ፤ ለ እግራቸው ጫማ የላቸውም በሚላቸው የአማራው ተወላጅ ላይ ለሰሚ በሚሰቀጥጥ ቋንቋ ያወርደው የነበረ ስድብ የሚነግረን ተጨማሪ ነገር ተመሳሳይ የወያኔን ምንነትን ነው።
እነዚህ ግፈኞች በህዝብ ላይ የሚሰሩትን አዋርዶ የመግዛት ግፍና ዝርፊያ አሳምረው ያውቃሉ። ከዚበላይ ደግሞ የዚህ ሁሉ ንቀትና ጥላቻ ሰለባ የሆነው ህዝብ እንደሚጠላቸውና ቀን እንደሚጠብቅላቸው ያውቃሉ። ስለዚህም ህዝቡን ይፈሩታል። ከፍርሃታቸው የሚያስታግስላቸው ህዝቡን ይበልጥ ቅስሙን ለመስበር ከቻሉ ስለሚመስላቸው በተዘጋ ቤት ውስጥ እየተሳለቁ ያስጨበጭባሉ።
የወያኔ ሹማምንት የህዝብ ብሶትና እሮሮ ማየሉን ሲሰሙ መልሰው ህዝቡን የሚሰድቡትና የሚያጠቁት፣ እንዲሁም ግንቦት 7 ሲጠነክርባቸውና የመውደቂያ ቀናቸው ሲያስቡ አሸባሪ ብለው የሚሸበሩትም ለዚህ ነው።
ህዝቡ ቅስሙ ከተሰበረ ሰላም ያገኙ ይመስላቸዋል። ወያኔዎችና የሲቪል ሰርቪስ ሎሌዎቻቸው በር ዘግተው በተሰበሰቡ ቁጥር ይህንን ፍራቻቸውን የሚያስታምሙት ህዝቡን ቅስሙን መስበራቸውን ለማረጋገጥ በሚያካሄዱት ወይይት ነው። ለዚህ ነው ህዝባችን እርስ በርሱ የሚባላበትን፤ እርስ በርሱ ጎሪጥ የሚተያይበትን መንገድ ሲቀይሱ የሚውሉት በዚህ ምክንያት ነው።
ወያኔዎች በየክልሉ እንደ አለምነው መኮነን አይነት ከጭንቅላታቸው፣ከህሊናቸው ይልቅ አፋቸው የሚቀድም ጥራዝ ነጠቅ ሎሌዎችን የሚያሰማሩትም የህዝብን ቅስም የሰበሩ አየመስላችዉ ነው::
 ወያኔና ሎሌዎቹ ህዝብየሚያታልሉበት ካርድ ከእንግዲህ አልቋል። አዋርደውናል፣ ገድለውናል፣ አስረውናል፣ አስርበውናል፣ ለስደት ዳርገዉናል፣ አለያይተውናል። ከዚህ በላይ ምን ሊያደርጉን ይችላሉ? ስለዚህ ቀኑ መሽቶባቸዋል እናበፍጥነት  ሊወገዱ ይገባል
በዚህ ወሳኝወቅት ሁሉምየኢትዮጵያእንደ አንድ ህዝብ በአንድ ላይ በመነሳት የወያኔ ጉጅሌና አጎብጓቢ ሎሌዎቻቸው ያዘጋጁልንን ወጥመድ መስበርና ክብራችንን ማስመለስ ይኖርብናል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተዘጋው የወያኔ በር እየተዋረደ፣ እየተገረፈ ነውና።
ግንቦት 7 እንደሁልግዜው ዘላቂ መፍትሄ የሆነው ዴሞክራሲያዊ አንድነታችን እንዲጎለብት፣ ማንነታችን ክብራችን እንጂ መሳለቂያ እንዳይሆን በተባበረ ሃይላችን የክብራችን ባለቤት እንድንሆን ጥሪውን ያቀርባል።
በተባበረ ሃይላችን ክብረ-ስብእናችንን እናስመልስ! ተዋርዶ መኖር ይብቃን! በቃ!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

Tuesday, February 11, 2014

በአዲስ አበባ በሌሊት የሚጻፉ የተቃውሞ ጽሁፎች ቁጥር እየጨመረ ነው

ከታህሳስ ወር 2006 ዓም ጀምሮ በመዲናዋ ሌሊት የሚጻፉ የተቃውሞ ጽሁፎችን ማየት የተለመደ እየሆነ መምጣቱን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ትናንት ሌሊት በአስኮ መስመር ጀኔራል ዊንጌት ከሚገኘው አደባባይ ጀምሮ አወሊያ፣ካኦጄጄ፣ አስኮ የሚወስደውን ዋና መንገዱን በመሃል በሚከፍለው እስከ 2.5 ሜትር ቁመት ባለው ግድግዳ ላይ የሙስሊሙን የመብት ጥያቄና የትግል ቀጣይነት የሚያንፀባርቁ ጽሁፎች በተለያዩ ቀለማት ተጽፈው ዛሬ ህዝብ ሲያነባቸው ታይቷል።
በአዲስ አበባ ጦር ሀይሎች፣ ወይራ ሠፈር ፣ አዉጉሥታ፣ቤቴል እና ሌሎችም አከባቢዎች ተመሳሳይ መልእክቶችን ያዘሉ ጽሁፎች ተለጥፈው ማደራቸውን ለማወቅ ተችሎአል፡፡
የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ጽሁፎችን በተመሳሳይ ቀለም ለማጥፋት ሙከራ እንደሚያደርጉ አልሆን ሲልም ስሚንቶ በመለጠፍ ለማጥፋት እንደሚሞክሩ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

Monday, February 10, 2014

የሃይማኖት ተቋማትን በሚመለከተው አዋጅ ላይ የሚመክር ስብሰባ በአዋሳ ተጠራ

በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የተዘጋጀው  የእምነት አኩልነትና ተቻችሎ የመኖር የሃይማኖት እሴትን ሊያጎለብት ይችላል የተባለ ረቂቅ አዋጅ ላይ የሚመለከታቸውን ወገኖች ሃሳብ ለማሰባሰብ  ከነገ ጥር 30 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ቀናት በአዋሳ ከተማ እንደሚካሄድ ምንጮቻችን ጠቆሙ።
በዚሁ ስብሰባ ላይ በዋንኛነት የሚሳተፉት በአገሪቱ አሉ የሚባሉት 945 ያህል የእምነት ተቋማት መሆናቸውም ታውቆአል፡፡ መንግስት የሙስሊም ማህበረሰብ የመብት ጥያቄ ማንሳታቸውን ተከትሎ ለውይይት በተደጋጋሚ ሲያገኛቸው የነበሩትን የመፍትሄ አፈላላጊ ኮምቴ አባላት በአክራሪነትና በሽብርተኝነት ወንጅሎ እስር ቤት ከከተተ ወዲህ “መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፣አንዱ በሌላው ስራ ጣልቃ አይገባም” የሚለውን ሕገመንግስታዊ ድንጋጌ በመዘንጋት በሃይማኖት ጉዳይ እጁን ሙሉ በሙሉ ማስገባቱን ታዛቢዎች ይገልጻሉ፡፡
መንግስት ረቂቅ ህጉ  በሃይማኖት ስም  ይደረጋሉ የሚላቸውን የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት ይስችለኛል ብሎ ያምናል። የሃማኖት ተቁዋማቱ በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ከመጋበዝ ባለፈ የረቂቅ አዋጁ ኮፒ አስቀድሞ እንዲደርሳቸው እንዳልተደረገ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት የሕግ ሰውነትን በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕግ የተደነገገው በ1952 ዓ.ም በወጣው የፍትሐ ብሔር ሕግ ነው፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕጉ በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አቋቁሞ፣  ሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ሕጉን ተከትሎ በሚወጣ ልዩ ደንብ እንደሚመዘገቡ መደንገጉ ይታወቃል፡፡ በደርግ ዘመንም ሃይማኖትን የተመለከተ ድንጋጌ ወጥቶ አያውቅም።
ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ያወጣው ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 27 ላይ ማንኛውም ሰው የማሰብ፣የህሊናና የሃይማኖት ነጻነት እንዳለው በግልጽ ደነግጋል፡፡ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም መቀበል ፣ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣የመከተል፣የመተግበር፣የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን ያካትታል፡፡ከዚህ በተጨማሪም የሃማኖት ተከታዮች ሃማኖታቸውን ለማስፋፋትና ለማደራጀት የሚያስችላቸውን የሃማኖት ትምህርትና የአስተዳዳር ተቋማት ማቋቋም እንደሚችሉና ወላጆች ህጋዊ ሞግዚቶች በእምነታቸው መሰረት የሃይማኖታዊና የመልካም ስነምግባር ትምህርት በመስጠት ልጆቻቸው የማሳደግ መብት እንዳላቸው ደንግጓል።

Friday, February 7, 2014

በለገጣፎ ለገዳዲ አስደንጋጭ የመሬት ዝርፊያ እየተካሄደ ነው

ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው የኦሮምያ ልዩ  ዞን እየተባለ በሚጠራው  የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ የሚገኘው የአርሶአደሩ መሬት በከተማዋ ውስጥ ባልኖሩና ማንነታቸው በማይታወቅ ሰዎች ስም መያዙን ለኢሳት የደረሰው ሰነድ አመልክቷል።
ከ4 ሺ በላይ ሰዎችን ስም ዝርዝር በያዘው በዚህ ሰነድ ማንነታቸው የማይታወቁ ሰዎች የአባታቸውን ስም ብቻ በመቀያየር ከ  140 እስከ 500 ካሬ ሜትር  ቦታዎችን ይዘዋል። አለማየሁ ፣ አልማዝ፣ አለምጸሃይ፣ አሰፋ፣ አበራ  ፣ አብርሃም ፣ አበበ የሚሉ ስሞች ከ15 እስከ 30 የሚጠጉ የቦታ ካርታዎችን በስማቸው አሰርተው ይዘዋል። ግለሰቦቹ  ቦታውን ያገኙት ከ2000 እስከ 2001 ዓም ባለው የአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ነው።
የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በአንድ ወቅት 15 ሺ በላይ ሰዎች በህገወጥ መንገድ የቦታ ካርታዎችን መያዛቸውን የሚገልጽ መግለጫ ማውጣቱ ይታወቃል። ለኢሳት በደረሰው ሰነድ ላይ ለማየት እንደሚቻለው አብዛኞቹ ሰዎች ቦታዎችን የሚወስዱት ጂ+2 እየተባለ የሚጠራውን ቤት ለመስራት ነው።
በከተማው የሚታየውን የቦታ ዘረፋ በተመለከተ የከተማው ነዋሪ ህዝብ በተደጋጋሚ የተቃውሞ ሰልፍ አድርጓል። የኦሮሚያ ክልል ችግሩን ለመፍታት ቃል ቢገባም የከተማዋ አመራሮች ወርደው በሌሎች እንዲተኩ ከማድረግና የተተኩትም ሰዎች ተመሳሳይ ድርጊት ከመፈጸም ው   የተለወጠ ነገር አለመኖሩን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
በለገጣፎ ለገዳዲ በኮምኒኬሽን ሰራተኛነት ሲያገለግል የነበረው የገዢው ፓርቲ አባል  ወጣት መኮንን ተስፋየ በከተማዋ ውስጥ የሚፈጸመውን ዝርፊያ ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመሆን በማጋለጥ በኩል ከፍተኛ ሚና ሲጫወት ከቆየ በሁዋላ፣ በመጨረሻም ህይወቱን ለማትረፍ ሲል በቅርቡ ከአገር ተሰዷል። ወጣት መኮንን እንደሚለው እብዛኞቹ የከተማዋ ቦታዎች በባለስልጣናት የተቸበቸቡ ናቸው።
በሙስና የተከሰሱት የቀድሞው የገቢዎችና ጉምሩክ ምክትል ሃላፊ አቶ ገብረውሃድ ወልደ ጊዮርጊስ በዚሁ በለገጣፎ ለገዳዲ የቦታ ካርታ በብዛት ይዘው ከተገኙት መካከል ናቸው።
የአዲስ አበባ መስተዳድር እነዚህን ከተሞች ከአዲስ አበባ ጋር ለመቀላቀል ቢያቅድም፣ የኦሮምያ ክልል ፈቃደኛ ባለመሆኑ እስካሁን አልተሰካም። የኦሮምያ ክልል ከእንግዲህ ለአዲስ አበባ የምንሰጠው መሬት የለም በሚል አቋሙ በመጽናቱ የፌደራሉ መንግስት የቤቶች ልማት እቅድን ለመተግበር እየተሳነው መጥቷል። ከወጣት መኮንን ተስፋየ ጋር ያደረግነውን ቃለምልልስ በቅርቡ ይቀርባል።

Thursday, February 6, 2014

ትግሉ የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅበት ወሳኝ ምእራፍ ላይ ደርሷል

ራሱን የብሄረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ብሎ የሚጠራው ድርጅት በከፍተኛ የፖለቲካ ኪሳራ ውስጥ ገብቷል። የህወሀትን ዙፋን ከመጠበቅ ባለፈ ምንም ሚና የሌላቸው የብአዴን  አመራሮች ያለፉትን ሶስት  ወራት በተለያዩ መንገዶች የድርጅቱን አባሎች ሲገመግሙ ከርመዋል። በግምገማዎች ላይ በግልጽ እንደታየው ብአዴን በክልሉ ከሚገኙ ወጣቶች አባሎቹ ጋር ሆድና ጀርባ ሆኗል፤ ወጣቶቹ በግልጽ “ዙፋን ጠባቂነቱ ይብቃ፣ ለውጥ እንፈልጋለን፣ ብአዴን ለ22 ዓመታት ተፈትኖ የወደቀ ድርጅት ነው” የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል። ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች እየተጫወቱ ያለው ሚና በሌሎች የኢህአዴግ ድርጅቶች ውስጥ ላሉ ወጣት አባላት ጥሩ ትምህርት የሚሰጥ ነው።  ሰሞኑን በገሀድ በግምገማዎች ላይ ሲነገር እንደነበረው ብአዴን እወክለዋለሁ ከሚለው የአማራ ህዝብ ሙሉ በሙሉ ተነጥሎ በአየር ላይ የተነሳፈፈ ድርጅት እንዲሆን ወጣቶቹ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
ይህን እውነታ ዘግይተው የተረዱት የብአዴን ዙፋን ጠባቂ አመራሮች የሚይዙትን የሚጨብጡትን በማጣት የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ላይ ይገኛሉ። ታማኝ የሚሉዋቸውን ካድሬዎች በየወረዳዎች እና በየቀበሌዎች  በመላክ በግንቦት7 አባልነት ወይም ደጋፊነት የሚጠረጠሩትን ወይም የግንቦት7 አባሎች ናቸው ተብሎ ከሚገመቱ ሰዎች ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ግንኙነት አላቸው ተብሎ የሚጠረጠሩትን ሰዎች በመያዝና በማሰቃየት ሌላው ወጣት ተቃውሞውን እንዳይቀላቀል ለማድረግ እቅድ ነድፈው ለመንቀሳቀስ አስበዋል። እንዲሁም አንድ ለአምስት የተባለውን የመጠርነፊያ ስልት በመስሪያ ቤቶች፣ በቤተሰብ፣ በትምህርት ቤቶችና በተለያዩ ተቋማት ላይ በስፋት በማውረድ፣ የህዝቡን የእለት ተለት እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር አልመዋል።  የግንቦት7ን ህዝባዊ ሀይል ለመቀላቀል ቆርጦ የተነሳውን ወጣት እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የአካባቢ ፖሊሶችንና የድንበር ጠባቂዎች ሚሊሺያዎችን በማጠናከር እና በማብዛት ለመቆጣጠር ውሳኔ አሳልፈዋል። በድርጅቱ ውስጥ የግንቦት7 ደጋፊዎች ናቸው ተብሎ የሚጠረጠሩትን ወይም ለድርጅቱ ታማኝ አይደሉም የሚባሉትን ሁሉ በመመንጠር ብአዴንን እንደገና በእግሩ ለማቆም ውሳኔ አሳልፈዋል።
በጭካኔያቸው፣ በጎጠኝነታቸው፣ በንቅዘታቸው እና በሎሌነታቸው የሚታወቁትን ታማኝ ካድሬዎች ወደ ፊት በማምጣት ለድርጅቱ እስትንፋስ ለመስጠት ደፋ ቀና እያሉ ነው። ሰሞኑን የተደረገው ሹም ሽርም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው። ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም እንደሚባለው የሰዎች መለዋወጥ የብአዴንን ህልውና ከመክሰም አያድነውም።
ለመሆኑ ብአዴን የህወሀትን ዙፋን ከመጠበቅ በስተቀር ባለፉት 22 አመታት እወክለዋለሁ ለሚለው ህዝብ ምን ሰራ? ሰፊው የአገራችን መሬት ለሱዳን ተላልፎ ሲሰጥ የስምምነት ፊርማውን ከማስቀመጥ፣ ህዝቡ ከቦታ ቦታ ሲፈናቀል፣ ለአመታት  በኤድስና በወባ  እንደቅጠል ሲረግፍ ፣ ወጣቱ ስራ አጥቶ በአደገኛ እጾች ደንዝዞና ተስፋ ቆርጦ የወጣትነት እድሜውን በከንቱ ሲያሳልፍ ብአዴን የት ነበር? አንድ የብአዴን ከፍተኛ አመራር በገሀድ እንዳመኑት  ድርጅቱ ከህዝቡ ጋር ሳይተዋወቅ 22 አመታት አልፈዋል።
ግንቦት7 መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ከዘረኛውና ዘራፊው የህወሀት ጎጠኛ አገዛዝ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመገላገል እና በምትኩ የሁሉም የምትሆን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የጀመረውን ትግል ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠናክሮ ቀጥሏል። በዚህ ወሳኝ የትግል ምእራፍ ወቅት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ ነው። በተለይም በኢህአዴግ ድርጅቶች ውስጥ ታቅፈው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ እውነተኛ የስርአት ለውጥ እንዲመጣ የሚፈልጉ ሀይሎች የብአዴን ወጣት አባላት ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ልምድ በመቅሰም በውስጥ የሚያደርጉትን ትግል አጠንክረው እንዲገፉበት ንቅናቄያችን ጥሪውን ያቀርባል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!

Wednesday, February 5, 2014

በደቡብ እና ምስራቅ ኢትዮጵያ አሰቃቂ ረሀብ መከሰቱ ተዘገበ

አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሀን የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን በመጥቀስ እንደዘገቡት በደቡብ እና ምስራቅ ኢትዮጵያ አስከፊ ረሀብ መከሰቱን ተከትሎ የህዝቡ ህልውና አደጋ ውስጥ ወድቋል። የሲኤን ቢሲ ዘጋቢ እንደገለጸው ችግሩን ለመቅረፍ እስከ 100 ሚሊዮን የእንግሊዝ ፓውንድ ያስፈልጋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የያዘው የምግብ ክምችት ማለቁንም በዘገባው ተገልጿል። እንደ ሲኤን ቢሲ ዘገባ በአፍሪካ ወደ 14 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚፈልግ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋው ኢትዮጵያዊ ነው።
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው ሰሞኑን በፓርላማ ተገኝተው ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አፋጣኝ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸው የነበረ ቢሆንም ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግን አፋጣኝ ምግብ የሚፈልጉ ሰዎችን ቁጥር ወደ 10 ሚሊዮን አድርሶታል. esat news

Tuesday, February 4, 2014

በርካታ የአዲስ አበባ ቤት ተመዝጋቢዎች ገንዘባቸውን ከባንክ እያወጡ ነው

ጥር ፳፮ (ሃያ ስድት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከውስጥ አዋቂ ምንጮች ለማዎቅ እንደተቻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚታየውን የመኖሪያ ቤቶች ችግር በዘላቂነት ለማቃለል በሚል ከዚህ በፊት ከነበረው የ 20/80 የጋራ መኖሪያ ቤት ልማት ፕሮግራም በተጨማሪ በአማራጭ የ 10/90 አነስተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እና ለመለስተኛና መካከለኛ ገቢ ላላቸው በ40/60 የቁጠባ ቤት ፕሮግራም መቅረጹን ተከትሎ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ተመዝግቦ ነበር።
ይሁን እንጅ በአሁኑ ወቅት እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው የተለያዩ የቤት ልማት ፕሮግራም ተሳታፊ ዜጎች ከፕሮግራሙ እየወጡ መሆኑ ታውቋል። ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ከ30 ሺ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ገንዘባቸውን ከባንክ አውጥተዋል።
ባንክ ቤቶች ከዚህ በፊት ለምዝገባ ስራ ሲጨናነቁ ከነበረው ባልተናነሰ በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ የስራ ጫና ውስጥ እንዳሉና ለዚህ አገልግሎት ብቻ አንድ መስኮት ለመልቀቅ እንደተገደዱ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የ20 /80፣ የ10/90 እና የ40/60 ቤቶችን ለመገንባት ከገንዘብ እጥረት በተጨማሪ የቦታ እጥረት ማጋጠሙን ኢሳት የውስጥ መረጃዎችን በማሰባሰብ መዘገቡ ይታወሳል። በተለይም የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞችን በአዲስ አበባ ታላቁ ካርታ ውስጥ ለማስገባት ፈቃደኛ ሆኖ ባለመገኘቱ የፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት አደጋ ውስጥ ወድቋል።
መንግስት ወደ 10 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ከባንክ በመበደር ቤቶችን ለመስራት ቢያስብም፣ ንግድ ባንክ በርካታ የብድር አገልግሎቶችን በመሰረዝ ለማግኘት የቻለው 6 ቢሊዮን ብር ነው። መንግስት በተለይ 40 በ60ን ተግባራዊ ለማድረግ ያወጣው እቅድ ቅጅው ለኢሳት ደርሶአል። በዚህ እስካሁን ይፋ ባልተደረገው እቅድ የቤቶች ዋጋ ቀድሞ ከተያዘለት በእጥፍ ጨምሮ በግል ከሚሰሩ ቤቶችም ጋር ሲነጻጸር እጅግ ውድ ሆኖ ተግኝቷል።