የኢትዮጵያን ሕዝብ ከጎጠኛውና ከአሸባሪው የወያኔ አምባገነናዊ ስርዓት ለማላቀቅ የትጥቅ ትግሉን አማራጪ አድርጎ ለሀገርና ለወገኑ መስዋዕትነት ለመክፈል ቆርጦ የተነሳው የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር /ኢሕአግ/ ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ ከሚታገሉ ድርጅቶች ጋር ውህደት በመፍጠር የፀረ- ወያኔ ትንቅንቁንና ፍልሚያውን አጠናክሮ በመቀጠል በተሰለፈባቸው አውደ-ውጊያዎች በጠላት ላይ ወታደራዊ የበላይነትን በመቀዳጀት የሀገርና የወገን መከታነቱን እያስመሰከረ ይገኛል።
በዚህም መሰረት የጋራ ጠላትን በጋራ ለመደምሰስና የኢትዮጵያን ሕዝብ የመብቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ ውህደት በመፍጠር በመጋቢት 12 ቀን 2006 ዓ.ም በሰሜን ጎንደር ጠገዴ ወረዳ ልዩ ስሙ ግጨው በተባለ ቦታ ከወያኔው የሚሊሺያ ታጣቂ ሀይል ጋር ባደረጉት ውጊያ ከፍተኛ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ድል ማስመዝገባቸዉን የድርጅቱ አመራሮች አስታውቀዋል።
በዚህ ውጊያ የሚሊሺያ ሰራዊት አመራር የነበሩት፦
1ኛ. አየልኝ ጫቅሌ 2ኛ. ደጀን ተጫኔ 3ኛ. ተስፉ አያናው የተባሉትን የሚሊሺያ ሰራዊት አመራሮች በመማረክ ስለድርጅቱ አላማና ፕሮግራም በማስተማር ወደ መኖሪያ ቀያቸው እንዲመለሱ ተደርጓል ።
በዚሁ እለትም በተደረገው ውጊያ በቅርቡ የወያኔውን አምባገነን ሥርዓት እድሜ ለማሳጠር ድርጅቶች በአንድነት መስራት አለባቸው በሚል ግንባር የፈጠሩት የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ ባደረጉት ወታደራዊ የማጥቃት እርምጃ 17 የወያኔ የሚሊሺያ አባላትን ገድለው 14 በማቁሰል እንዲሁም የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ከነመሰል ጥይቶቻቸው ጋር በተጨማሪም 2 ሽጉጦችን በመማረክ በጠላት ላይ ወታደራዊ የበላይነትን በመቀዳጀት አንፀባራቂ ድል ማስመዝገባቸውን የሁለቱ ድርጅቶች አመራሮች አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞ ግንባርና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ የፈጠሩት ወታደራዊ ግንባር አብሮ መስዋዕትነት ከመክፈል ባሻገር አምባገነኑን የወያኔ ገዥ ቡድን እድሜ ለማሳጠር ውሕደት ፈጥረው የትግሉን ሂደት ለማፋጠን ከመቸዉም ጊዜ በበለጠ መልኩ ጠንክረው እንደሚሰሩ የድርጅቶቹ አመራሮች ገልፀዋል።
|
Tuesday, March 25, 2014
የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰራዊትና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ ሰራዊት ወታደራዊ ጥቃት ፈፀሙ።
Friday, March 14, 2014
በምእራብ አርማጮ የሽፍታ ቤተሰቦች ናችሁ በሚል ብዙ ነዋሪዎች ታስረው በመሰቃየት ላይ ናቸው
-በኢትዮ-ሱዳን ድነበር አካባቢ ነዋሪ የሆኑ የምእራብ አርማጭሆ ነዋሪዎች እና በሽፍታ ቤተሰብነት የተጠረጠሩ ከ20 ያላነሱ ቤተሰቦች ታስረው እንደሚሰቃዩ ከአካባቢው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
የሽፍቶቹ ቤተሰቦች ለእስር የሚዳረጉት ሽፍቶችን አሳምነው እጃቸውን ለመንግስት እንዲሰጡ ወይም ገድለው እንዲያቀርቡ ለማድረግ ነው። ይሁን እንጅ አብዛኞቹ ሽፍቶች እጃቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በቤተሰቦቻቸው ላይ የሚደርሰው እንግልት እየጨመረ ነው። በእስር ላይ ከሚገኙት የሽፍታ ቤተሰቦች መካከል መልካሙ አዛናው፣ መልካሙ መንግስቱ፣ ብርሃኔ ደምለው፣ ወ/ሮ አረቄ መላሽ፣ ዳኙ ካሴ፣ ደስታ ካሳ፣ ገብሬ አዳነ፣ ሁናቸው እና ሌሎች ከ20 በላይ ቤተሰቦች በእስር ላይ ይገኛሉ። በእስር ላይ ከሚገኙት በተጨማሪ ሌሎች ደግሞ አፈናውን በመስጋት ጫካ ለማደር ተገደዋል።
ጭንቋና በሚባል ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ አረቄ መላሽ ሙቀት የተባለው ልጃቸው በቅርቡ በዚህ ስርአት ውስጥ መኖር አልችልም በሚል መሸፈቱን ተከትሎ፣ ቀሪ ልጆቻቸውን በትነው መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሎአል። ግለሰቡዋ የሸፈተው ልጃቸው እጁን እስካልሰጠ ድረስ በእስር እንደሚማቅቁ በፖሊስ ተነግሮአቸዋል።
ከ5 አመታት በፊት የሸፈተውና እስካሁን የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር ሊያውሉት ያልቻሉት የአበራ ጎባው ቤተሰቦች በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሎአል። አበራ ጎባው ስርአቱን በመቃወም ከሸፈተበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ወጣቶች እየተቀላቀሉት መምጣቱን የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ።
ጉዳዩን በማስመልከት በሰሜን አርማጭሆ የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆነውን ወጣት አባይ ዘውዱን አነጋግረነው ነበር። አባይ እንደሚለው ፓርቲያቸው የሽፍታ ቤተሰቦች ተብለው የሚያዙ ሰዎች መኖራቸውን ማረጋገጡንና ብዙ ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑንና መንግስት ለምን በጸጥታ ሃይሎች ሊይዙዋቸው እንዳልቻሉ ገልጿል
ለሽፍትነት ያበቃቸውን ምክንያትም በስርአቱ በመማረር መሆኑን ወጣት አባይ ይናገራል በሌላ በኩል ደግሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ የምእራብ አርማጭሆ ወጣቶች ” ለሱዳንና ለውጭ ኩባንያዎች መሬት እየተሰጠ እኛ ግን የምናርሰው መሬት አጥተናልና መሬት ይሰጠን” የሚል ጥያቄ አንስተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ከወጣቶች አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ለመረዳት ተችሎአል። ወጣቶቹ ጥያቄቸውን ከወረዳ እስከ ዞን ላሉ ባለስልጣናት ቢያመለክቱም ምላሽ አላገኙም። በዛሬው እለትም ለክልል ባለስልጣናት አቤት ለማለት ከ50 በላይ ተወካዮች ወደ ባህርዳር አቅንተዋል።
ለሱዳን በተሰጠው መሬት አካባቢ በሱዳኖችና በኢትዮጵያውያን መካከል ግጭት እየተከሰተ መሆኑንም የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ። በቅርቡ አብዱ የሚባል የሱዳን ባለሀብት በኢትዮጵያውያን መገደሉን ተከትሎ ሱዳኖች በወሰዱት እርምጃ ሚካኤል የተባለ የአብረሃ ጅራ ነዋሪ መገደሉን የከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ኢትዮጵያና ሱዳን ድንበሮቻቸውን በጋራ ወታደሮች ለመጠበቅ በቅርቡ አዲስ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል።ኢሳት ዜና
Tuesday, March 11, 2014
አንድነት ፓርቲ ሁለተኛውን ዙር የሚሊኖች ድምፅ ለነፃነት ህዝባዊ ንቅናቄ ይፋ አደረገ
አንድነትለዲሞክራሰና ለፍትህ ፓርቲ ዛሬ ይፋ ያደረገው የህዝባዊ ንቅናቄ መርሃግብር በተከታታይ ሊካሂዳቸው ካቀዳቸው ህዝባዊ ንቅናቄዎች መካከል አንዱ በየሆነውን የሚሊዮኖች ድምፅ ለመሬት ባቤትነት(Millions of voices for land
ownership) የሚል ስያሜ የሰጠውን የህዝባዊ ንቅናቄ ነው፡፡ መረሃ ግብር በዛሬው እለት ይፋ የተደረገው ቀበና መድኃኔዓለም ቤ/ክ ፊተ ለፊት በሚገኘው የፓርቲው ጽ/ቤት ነው፡፡ ህዝባዊ ንቅናቄው ይፋ በተደረገበት መግለጫ ላይ አንድነት የመሬትን ጉዳይ በአጀንዳነት በመምረጥ ህዝባዊ ንቅናቄ ለማድረግ የመረጠባቸው ምክንያቶች በዝርዝር ቀርበዋል፡፡

በአዲስ አበባ በሚደረግ ትዕይንተ ህዝብ እንደሚጀመር የሚጠበቀው “የሚሊዮኖች ድምፅ ለመሬት ባቤትነት” ህዝባዊ ንቅናቅ 14 ከተሞች ላይ ሰላማዊ ሰል እንደሚደረግና ሶስት ከተሞችም በተጓዳኝ ለህዝባዊ ንቅናቄው መመረጣቸው ታውቋል፡፡ ንቅናቄው የሚካሄድባቸው ከተሞች አዲስ አበባ ፣ደሴ ፣ሐዋሳ ፣አዳማ/ናዝሬት ፣መቀሌ ፣ደብረታቦር ፣ ደብረ ማርቆስ ፣ድሬ ደዋ፣ ጅንካ፣ ቁጫ፣ አሶሳ፣ነቀምት፣ለገጣፎ፣አዲስ አበባ ሲሆኑ ተጓዳኝ ከተሞቹ ወልዲያ፣ ጋምቤላ፣ ም/አርማጨሆ(አብርሃ ጅራ) እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አንድነት ፓርቲ ባለፈው ዓመት(2005ዓ.ም) ለሶስት ወራት “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” በሚል መሪ ቃል ስክታማ ህዝባዊ ንቅናቄ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
በፍኖተ ነጻነት
Sunday, March 9, 2014
ወያኔ በግንቦት 7 ስም ሠላማዊ ዜጎችን ማሰቃየቱን ባስቸኳይ ማቆም አለበት
ባለፉት አራትና አምስት አመታት በግልጽ እንዳየነዉ የኢትዮጵያ ህዝብ እኩልነቱን፤ መብቱንና ነጻነቱን ለማስከበር የሚያደርገዉ ትግል ጫና በፈጠረበት ቁጥር ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ የራሱን ህገመንግስት የሚደፈጥጡ ህጎች አርቅቆ አያጸደቀ ሠላማዊ ዜጎችን አስሯል፤ ገድሏል ከአገር እንዲሰደዱም አድርጓል። ለምሳሌ በ2003 ዓም የኢትዮጵያ ፓርላማ ከቤተመንግሰት የተላለፈለትን ትዕዛዝ አክብሮ ለኢትዮጵያ ህዝብ መብትና ነፃነት መከበር የሚታገለዉን የግንቦት 7 ንቅናቄ ሽብርተኛ አድርጎ ፈርጇል። ይህ ፈር የለቀቀ ፍረጃ ደግሞ ወያኔ የሱን ዘረኛ ስርዐት የሚቃወሙ ግለሰቦችን፤ ሀሳባቸዉን በነፃነት የሚገልጹ ዜጎችን፤ ጋዜጠኞችን፤ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችንና ከወያኔ ጋር አናብርም ያሉ ወጣት ኢትዮጵያዉያንን “ግንቦት ሰባቶች” ናችሁ እያለ በጅምላ እያሰረ እንዲያሰቃይ ህጋዊ ሽፋን ሰጥቶታል። ለምሳሌ ከፍትህና ከነጻነት ጥማት ዉጭ ከግንቦት 7 ንቅናቄ ጋር ምንም አይነት ግኑኝነት የሌለዉን የፖለቲካ ፓርቲ መሪዉን አንዱአለም አራጌን፤ ታዋቂዉን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋንና መምህርት ርኢዮት አለሙን የግንቦት 7 አባላት ናቸዉ የሚል ሰንካላና መሠረተ ቢስ ክስ መስርቶ ለረጂም ዘመን እስራት ዳርጓቸዋል።
ወያኔ እንደ ዛሬዉ ከተማ ዉስጥ ሆኖ ሥልጣን ሳይቆጣጠር ገና ጫካ ዉስጥ እያለ ጥርሱን ከነከሰባቸዉና ከተቻለ አጠፋቸዋለሁ ካለዚያም አሽመደምዳቸዋለሁ ብሎ አስራ ሰባት አመት ሙሉ ከተዘጋጀላቸዉ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ የአማራ ብሄረሰብ ነዉ። በለስ ቀንቶት ሥልጣን ከጨበጠ ማግስት ጀምሮም በወሎና በጎንደር በኩል ከትግራይ ጋር የሚያዋሰኑ ሰፊ የሆነ ለም መሬቱን ጠቅልሎ በመውሰድ ዘረኛ ሥርዓቱን ዕድሜ ሊያራዝሙልኛል ይችላሉ ብሎ የሚተማመንባቸውን የቀድሞ የትግል አጋሮቹንና ካድሬዎቹን አስፍሮበታል:: ይህ በደልና ግፍ አልበቃ ብሎትም ቀደምቶቹ የኢትዮጵያ ገዥዎች ለፈጸሙት ግፍና የአስተዳደር በደሎች ሁሉ አማራዉን በጅምላ ተጠያቂ የሚያደርግ ፕሮፖጋንዳ እነሆ እስከዛሬ በመርጨት ለዘመናት በሠላም ከኖረው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር በጠላትነት እንዲተያይ አድርጎታል:: በወያኔ አጋፋሪነት በበደኖ ፡በአርሲ በአረካና ሌሎች አካባቢዎች አማራው ላይ በግፍ የተፈጸመው ጭፍጨፋና ከ2004 እስከ 2005 ዓም አማራዉን ከጉራፈርዳና ከቤንሻንጉል ለማፈናቀል የተወሰደው እርምጃ የዚህ የወያኔ የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ውጤት መሆኑን የምስት የለም::
ሟቹ መለስ ዜናዊና በህይወት የሚገኙ ቀንደኛ የወያኔ መሪዎች የተጠናወታቸው የአማራ ጥላቻ በጸረ ፋሽስት ዘመቻ ወቅት ባንዳ ከነበሩ አባቶቻቸዉና አያቶቻቸዉ የተወረሰ ፋሽስት ጣሊያን ለደረሰባት ሽንፈት በዘርና በሃይማኖት ተከፋፍለን እርስ በርሳችን እንድንጠፋፋ ተክላብን የሄደቺው ተንኮል አካል ነው ::
የዚህ የጥፋት አጀንዳ አስፈጻሚ የሆነው ወያኔ የጀመረውን አገር የማፍረስና ህዝብ የመከፋፈል አጀንዳ ለማሳካት በየክልሉ የተኮለኮሉ ምስሌኔዎች እንወክለዋለን በሚሉት ህዝብና ክልል ላይ እየፈጸሙት ያለው በደልና ሰቆቃ አዲስ ምዕራፍ በያዘበት በአሁኑ ወቅት እራሳቸዏን ለባርነት አዋርደው ህዝባቸውን በማዋረድ ላይ የሚገኙት የብአዴኑ አለምነህ መኮንንን የመሳሰሉ ሆድ አደሮች ውርደት በቃን ዘረኝነት በቃን ብለው በተነሱ ዜጎች ላይ እየወሰዱ ያለው ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ እጅግ አሳሳቢ ሆኖአል::
ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና ሞክራሲ ንቅናቄ ከሰሞኑ በደረሰው መረጃ ወያኔ ከአማራው ቀምቶ በትግራይ ክልል ባስገባቸው ወረዳዎች ላይ የሚኖሩ ንጽሃን ዜጎች ለምን በወያኔ የግፍ አገዛዝ ትማረራላችሁ እየተባሉ በወያኔ ታማኝ ሚሊሻዎች
እስር እንግልትና ድብደባ እየተፈጸመባቸው መሆኑን አረጋግጦአል:: በዚህ በአዲስ መልክ በተጀመረዉ የወያኔ የጥቃት ዘመቻ መሳሪያ ያነገቡ የህወሃት ሚሊሻዎች ከክልላቸዉ ዉጭ ወደ ተለያዩ የአማራ ከተማዎችና ወረዳዎች ሰርገዉ እየገቡ የእነሱን ቋንቋ የማይናገረዉን ሁሉ የግንቦት 7 ተላላኪዎች ናችሁ በሚል እያሰሩ በመደብደብ ላይ ናቸዉ።
ይህ በመሆኑ ዛሬ አትዮጵያን ከሱዳንና ትግራይን ከጎንደር ጋር በሚያዋስኑ የአማራ ክልል ዉስጥ የሚገኙ ገበሬዎች እጃቸዉ እርፍ ከሚጨብጥበት ግዜ በወያኔ ሰንሰለት የሚታሽበት ግዜ ይበልጣል፤ የመንግስት ሰራተኛዉና የከተማ ነዋሪዉም ቢሆን አብዛኛዉን ግዜ የሚያጠፋዉ ከወያኔ ካድሬዎች ጋር ግምገማ በመቀመጥ ሲሆን ተማሪዉና ወጣቱ ህብረተሰብ ደግሞ “መጡ አልመጡም” እያለ ሌሊቱን የሚያሳልፈዉ በየጫካዉ እየተሸሸገ ነዉ።
የዚህ አይነት አስከፊ ግፍና መከራ በአፋር ፡ በጋምቤላ በኦጋዴንና በኦሮሚያ በሚኖሩ ዜጎቻችን ላይ ሲፈጸም ቆይቶአል:: ? ወያኔ እራሱ አርቅቆ ባጸደቀውና በሐምሌ ወር 1987 ዓም በስራ ላይ የዋለዉ የወያኔ ህገ መንግስት ኢትዮጵያ በዘጠኝ የፌዴራል ክልሎች መከፈሏንና እያንዳንዱ ክልል እራሱን በእራሱ የማስተዳደር መብቱ የተረጋገጠ እንደሆነ ይደነግጋል። በዚህ ህገ መንግስት መሠረት እያንዳንዱ ክልል የራሱ ቋንቋ፤ የአስተዳደር ማዕከልና እንዲሁም የክልሉን ሠላምና ጸጥታ የሚያስከብር የፖሊስ ኃይል ይኖረዋል ይላል። ታድያ ለምንድነዉ እያንዳንዱ ክልል የራሱ ፖሊስ ኃይል አያለዉ ከትግርኛ ቋንቋ ዉጭ ሌላ ቋንቋ የማይናገሩ የህወሃት ታማኝ ሚሊሻዎች አማራ ክልል ዉስጥ እየገቡ አማራዉን የሚያሰቃዩት?
መልሱ ቀላል ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ህዝባዊ አምቢተኝነቱ እያየለ በመጣና የነጻነት ኃይሎች ጡንቻ በፈረጠመ ቁጥር ወያኔ አንገቷ ላይ ቀጭል እንደታሰረባት በቅሎ ይደነብራል። የደነበረ ደግሞ መራገጡ አይቀርምና መሳሪያ ያነገቡ ኃይሎችን እንቅስቃሴ እገታለሁ በሚል ከንቱ ጥረት ደንባራዉ ወያኔ የፈሪ በትሩን በድንበር አካባቢ በሚኖሩ የአማራ ክልል አርሶ አደሮች፤ ወጣቶችና ሠራተኞች ላይ ማሳረፍ ጀምሯል።
ወያኔ እንደ ግንቦት ሰባት የኮነነዉና የህዝብና የአገር ጠላት አድርጎ የሳለዉ ድርጅት የለም፤ የወያኔ የዜና ማሰራጫዎችም ይህንን የአገዛዙን አቋም በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ ህዝብ አሰምተዋል።የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ማን ለመብቱና ለነጻነቱ እንደቆመና ማን መብቱና ነጻነቱ ላይ እንደቆመበት ለይቶ የሚያዉቅ ህዝብ ነዉ። ስለዚህም ግንቦት ሰባት ወያኔዎች አላፊዉንና አግዳሚዉን “ግንቦት ሰባት” ነህ እያሉ ከሚያሰቃዩ፤ ህዝብንና ግንቦት ሰባትን ያስተሳሰረዉ ነጻነት፤ ፍትህና ዲሞክራሲ ነዉና የኢትዮጵያን ህዝብ ጥያቄ ቢመልሱ ለእነሱም፤ ለእኛም ለአገርም ይበጃል የሚል የጸና እምነት አለዉ። ወያኔ በኢህአዴግ ስም ያሰጠጋቸዉን ምሰለኔዎች ጨምሮ ከራሱ ዉጭ ሌላ ማንንም አያምንም፤ ስለዚህም ነዉ የአገሪቱን የመከላከያ፤ የደህንነትና የፖሊስ ተቋሞች በራሱ ሰዎች ቁጥጥር ስር ያደረገዉ። ዛሬ በግልጽ እንደምንመለከተዉ ወያኔ በጉልበት ለያዘዉ ስልጣን ያሰገኛል ብሎ በሚጠረጥረዉ ቦታ ሁሉ የራሱን ልዩ ሚሊሺያ እየለላከ የኢትዮጵያን ህዝብ መኖሪያ ቤቱ ድረስ አየሄደ እያጠቃ ነዉ። ግንቦት ሰባት ወያኔና የፈጠረዉ ዘረኛ ስርዐቱ የቆሙት በፍጹም ማንሰራራት የማይችሉበትት የመጨረሻ መቀበሪያ ጉድጓዳቸዉ ጫፍ ላይ ነዉ የሚል ጽኑ እምነት አለዉ። ሆኖም ጉድጓድ ጫፍ ላይ የቆመ ጠላት በራሱ ተወርዉሮ ጉድጓዱ ዉስጥ አይገባምና ይህንን የተዳከመ ጠላት እተፈራገጠ ጉዳት ከማብዛቱ በፊት ለመደምሰስ ክንዳችንን አጠናክረን በህብረት እንደ አንድ ሰዉ እንነሳ ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
Wednesday, March 5, 2014
ወያኔን ካላጠፋነዉ ዘረኝነቱና ዉርደቱ ይቀጥላል
ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች በራሳቸዉ እጅ የጻፉት ማኒፌስቶ በግልጽ እንደሚያሳየን እነዚህ ዘረኞች ጫካ ገብተዉ የትጥቅ ትግል እንዲጀምሩ ያነሳሳቸዉ በአማራ ህዝብ ላይ ያላቸዉ ጥላቻና መሰረተ ቢስ ቂም በቀል ነዉ። ይህ ጥላቻቸዉ ደግሞ አማራዉን በመግደልና ግዛቱን ሲያሻቸዉ ከራሳቸዉ ክልል ጋር በመቀላቀል አለዚያም ለጎረቤት አገሮች በመሸለም ብቻ ሊቆም ወይም ሊገታ አልቻለም። እነሆ የአማራው ህዝብ የወያኔ ዘረኞች ዋነኛ ዒላማ ሆኖ የአገዛዙን የግፍ ፅዋ ያለማቋረጥ መጋት ከጀመረ ድፍን 23 አመታት ተቆጠሩ። ፋሽስቱ ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ ብሔራዊ ስሜት በማምከን ፣ የዘመናት ተገዥነቱን ለማረጋገጥ በቅድሚያ የአማራን ሕዝብ ማንነት ማጥፋት ፣ የአማራን ሕዝብ ስነ ልቦናዊ ጥንካሬ መስለብ እና አንገቱን ማስደፋት አስፈላጊ መሆኑን በጽናት ያምናል። ይህ በመሆኑም ፣ በአማራ ህዝብ ላይ በወያኔ የሚፈፀመው ግፍ እና በደል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ስር እየሰደደና እየከፋ በግልፅም በስውርም በተቀነባበረ መንገድ ቀጥሏል።
ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ ብሔራዊ ስሜት በማዳከም፣ ለዘመናት ሥልጣን ላይ ለመቆየት ያገለግለኛል ብሎ ዘመቻ ከከፈተባቸው ብሄረሰቦች አንዱና ዋንኛው የሆነው የአማራ ህዝብ በራሱ ማንነት እንዲያፍርና ብሄራዊ ኩራቱ እንዲሟሽሽ ላለፉት 23 አመታት በግብር ከፋዩ ህዝባችን ገንዘብ በሚተዳደሩ የመንግሥት መገናኛዎች ሳይቀር ከፍተኛ የስነ ልቦና ዘመቻ ተካሂዶበታል። በአማራ ሥም አማራውን የወያኔ አገር የማፍረስ አጀንዳ አስፈጻሚ ለማድረግ የተሾሙበት ተላላኪዎች በህወሃት አለቆቻቸው የተሰጣቸውን ተልዕኮ ለመፈጸም በተለያዩ አጋጣሚዎች አማራውን የሚያዋርድና የሚዘልፍ አስተያየት በአደባባይ ሲሰጡ ሰምተናል አይተናል። ይህ ተግባራቸው ለአማራ ህዝብ ቅንጣት ታህል ክብርና ፍቅር ያልነበረው ዘረኛው አለቃቸው መለስ ዜናዊ ከዚህች አለም በሞት ከተሰናበተ ቦኋላም ተጠናክሮ ቀጥሎአል።
የህወሃት መሪዎች አማራው ላይ ያላቸው ጥላቻ ወደሥልጣን ከመጡ ቦኋላ የተፈጠረ ሳይሆን ገና በጫካ ትግል ላይ በነበሩበት ወቅት በጻፉት የድርጅታቸው የፖለቲካ መረሃግብር በግልጽ እንደተቀመጠው ለትግል ያነሳሳቸውም አማራ ብለው የሚጠሩት ብሄረሰብ እንወክለዋለን በሚሉት ብሄረሰብ ላይ አድርሰዋል በሚሉት የፈጠራ በደልና ቂም እንደሆነ አረጋግጠዋል። ላለፉት 23 አመታት አማራው ከሚኖርበት የራሱ ክልሉ ሳይቀር እንዲፈናቀል ተደርጎ እየደረሰበት ያለው በደል የዚህ የቆየ የወያኔ ቂም በቀል ውጤት መሆኑ ግልጽ ነው።
ሰሞኑን አለምነው መኮነን የተባለ ሆድ አደር የባንዳነት ተግባሩን በመፈጸም በአለቆቹ ፊት ግርማ ሞገስ ለማግኘት እመራዋለሁ የሚለውን የአማራ ህዝብ እጅግ በወረደና ጸያፍ በሆነ ቃላት ያን ያህል ሲዘባበትበት መደመጡ አማራውን ብቻ ሳይሆን መላውን የአገራችንን ህዝብ አስቆጥቶአል።
በእርግጥ አለምነው መኮንን አማራን በማዋረድ የመጀማሪያው የወያኔ ተላላኪ አይደለም። የህወሃቶቹን ቁንጮዎች ስድብና ዘለፋ ወደ ጎን ትተን በወያኔ የዘር ፖለቲካ አማራውን እወክለዋለው የሚለው ብአዴን ከፍተኛ አመራር እነ እነታምራት ላይኔ ተፈራ ዋልዋና በረከት ስሞን በተለያየ ወቅት ንቀትና ስድባቸውን አሰምተውናል። አለምነህ መኮንን እንደዚያ በወረደ ቃላት አማራውን ሲያዋርድ በስብሰባው አዳራሽ የነበሩ ህወሃት የፈጠራቸው የብአዴን ልጆች በሳቅ ካካታ ሲያጅቡት እንደነበረ እድሜ ለኢትዮጵያ ሳታላይት ቴለቪዥን ከአዳራሹ ሾልኮ ለህዝብ ጀሮ የደረሰው የኦዲዮ ድምጽ አጋልጦአል።
ሁላችንም፤ እንደምንገነዘበው ወያኔ የገዛ ብሄረሰባቸውን ረግጠው በመግዛት የጥፋት አላማውን እንዲያስፈጽሙለት በራሱ አምሳል ከፈጠራቸው ድርጅቶች አንዱ የሆነው ብአዴን በታሪኩ አንድም ለህዝቡ የቆመ መሪ አፍርቶ አያውቅም። ለራሳቸውና ከአብራኩ ለተገኙት ህዝብ ምንም አይነት ክብር የሌላቸው የብአዴን መሪዎች ጣሊያን አገራችንን በወረረችበት ወቅት ለሆዳቸው ሲሉ ከባዕድ ጋር ተሻርከው ህዝባቸውን ካስጨፈጨፉት ባንዳዎች የከፋ ተግባር በህዝባቸው ላይ እየፈጸሙ ነው።
ወያኔ ለም የሆነውን የአማራ ግዛት እንዳለ የኔ ነው ወደሚለው የትግራይ ከልል ሲወስድ፤ በአማር ክልል ወስጥ በቀሩት ለም ቦታዎች የህወሃት ታማኝ ካድሬዎችን ከያሉበት እያጓጉዘ ሲያሰፍር፤ የአገሬውን አርሶ አደር እያፈናቀለ ለራሱ ታማኞች ለም መሬት እየሸነሸነ ለሰፋፊ እርሻ አገልግሎት ሲያድል አማራውን እወክለዋለው የሚለው ብአዴን አንድም የተቃውሞ ድምጽ አሰምቶ አያውቅም። የብአዴን መሪዎች የወያኔን ተልዕኮ ከማስፈጸም አልፈው በሟቹ አለቃቸው በመለስ ዜናዊ ሥም እየማሉ በአገራችን ኢትዮጵያና በሚያስተዳድሩት የአማራ ህዝብና ክልል የሚፈጽሙት በደል ብዙ ነው። ልክ እንደ ብአዴን የዘረኛውን ወያኔ የጥፋት ፖሊሲ ለማስፈጸም ከሚተጉት አንዳንዶቹ አማራውን ከክልላቸው ለማጽዳት በቤኒሻንጉል፤ በቤንች ማጅና ጉራፈርዳ ወረዳ እርምጃ ሲወስዱና ንብረታቸውን ቀምተው ባዶ እጃቸውን ሲያባርሩዋቸው ብአዴን ቁጭ ብሎ ተመልካች ነበር። ከአማራ ክልል ጋር የሚዋሰነው ዳር ድንበራችን ላይ በተነሳው የባለቤትነት ጥያቄም ላይ የወሰደው አቋም በህዝብና በታሪክ ፊት ውሎ አድሮ የሚያስጠይቀው ነው።
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እንደሚገነዘበው ፋሽስቱ ወያኔ በአገራችንና በህዝባችን ላይ እየፈጸመው ያለው አንዱን ዘር ከሌላው ጋር የማጋጨትና በተናጠል ደግሞ እያንዳንዱን ለይቶ የማዋረድና የማጥፋት ተግባር አሁን የተጀመረ ክስተት አይደለም። የቆየና ወያኔ ህዝባችንን ከፋፍሎ ለመግዛት ከመነሻው ሲጠቀምበት የነበረ ስልት ነው። ስለዚህ ወያኔ በራሱና በተላላኪዎቹ አማካይነት ላለፉት 23 አመታት በህዝባችን ላይ እየፈጸመ ያለውና የፈጸመው ግፍ፤ ውርደትና መከራ እንዲያበቃ ሁላችንም እጅ ለ እጅ ተያይዘን መነሳት ይኖርብናል። በወያኔ ከፋፋይ አጀንዳ እርስ በርስ እየተናቆርን የጥቃት ሰለባ የመሆናችንን እንቆቅልሽ ለማስቀረት ከኛ በላይ ሃይል ያለው አይኖርም።
በተለይ ግንባር ቀደም የወያኔ ሰለባ የሆነው የአማራ ህዝብ ወጣት በጫንቃው ላይ ተፈናጠጠው የወያኔን የጥላቻና የበቀል እርምጃ የሚያስፈጽሙትን ከአብራኩ የተገኙ ባንዳዎች ላይ የጥቃት ክንዱን መሰንዘርና ለክብሩ መቆሙን ማሳየት ያለበት ጊዜው አሁን ነው።
በብአዴን ሥር የተሰባሰቡ የአማራ ተወላጆች፤ በመከላኪያ ሠራዊቱ፤ በፖሊስና በደህንነት፤ በወጣት ማህበር፤ በሠራተኛ ማህበርና በተለያየ ሙያ ማህበር ብአዴን ራሱ ያደራጃቸው ሁሉ ለክብራቸውና ለኢትዮጵያዊ ማንነታቸው ሲሉ ከትግሉ ጎን በመሰለፍ የወያኔን ዕድሜ ለማሳጠር ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የሚያካሂደውን ትግል እንዲቀላቀሉ ንቅናቄው ጥሪውን ያቀርባል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
Tuesday, March 4, 2014
12 ሺ ቶን ቡና በተጭበርበረ ሰነድ ወደ ውጭ አገር መላኩ ታወቀ
የስነምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን በቅርቡ በቡና አስተዳደር ላይ የሚታየውን ችግር አስመልክቶ ያወጣውን ሪፖርት ተከትሎ 12 ሺ ቶን ወይም 1 መቶ 20 ሺ ኩንታል ቡና በተጭበረበረ ሰነድ ወደ ውጭ ተልኮ መሸጡን አመልክቷል። ኮሚሽኑ ቡናው በማን በኩል ተሰርቆ እንደተላከ እያጣራ መሆኑን የዘገበው ሪፖርተር፣ የሽያጩ ገንዘብም ወደ አገር ውስጥ አለመግባቱን ገልጿል።
ዛሬ ባለው የአለም የቡና የመሸጫ ዋጋ 120 ሺ ኩንታል ቡና ከ16 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወይም ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያወጣል። ይህን ያክል ገንዘብ በአንድ ጊዜ በተጭበረበረ ሰነድ መዝረፍ የሚቻልባት አገር ሆናለች የሚለው ዘጋቢያችን፣ ድርጊቱ መንግስት አለ ወይ ያሰብላል ሲል ሃሳቡን አሰፍሯል።
አቶ መለስ በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት 10 ሺ ኩንታል ቡና መጥፋቱ ይታወቃል። ስለዚሁ ጉዳይ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ መለስ መንግስታቸው እያጣራ መሆኑን ተናግረው ነበር። ይሁን እንጅ የምርመራው ውጤት ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የታወቀ ነገር የለም።
ዘጋቢያችን እንደሚለው ጸረ ሙስና ኮሚሽን እየመረመርኩ ነው ቢልም፣ የምርመራው ውጤት ታፍኖ ሊቀር የሚችልበት እድሉ ሰፊ ነው። በጉዳዩ ዙሪያ የንግድ ሚኒስቴር ባለስልጣናትን ለማግኘት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም። ኢሳት ዜና
Subscribe to:
Posts (Atom)