Saturday, February 28, 2015

በአዋሳ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ የሟቾች ቁጥር ከ20 በላይ ነው ሲሉ የቃጠለው ሰለባ የሆኑ ሰዎች ገለጹ

-በደቡብ ክልል ዋና ከተማ በአዋሳ የካቲት 14 ቀን 2007 ዓም በደረሰው ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ የሟቾች ቁጥር በመንግስት እንደተገለጸው አንድ ሳይሆን ከ20 በላይ መሆኑን ተገጂዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
ከፍተኛ ንብረት ከወደመባቸውና እሳቱ ሲነሳ በስፍራው ከነበሩት መካከል አንዱ ለኢሳት ሲናገር፣ እርሱ የ6 ሰዎችን የተቃጠለ አስከሬን ማየቱን፣ በስፍራው የሚገኙ ጓደኞቹ ደግሞ በአጠቃላይ እስካሁን 27 አስከሬን ተፈልጎ መቀበሩን ተናገሩዋል።
አንድ ህጻነት እና አንዲት እናት ከ3 ልጆቿ ጋር ሞታ መመልከቱን፣ በማግስቱ ደግሞ ተጨማሪ ሁለት ሰዎች ሞተው ማየቱን የሚናገረው ግለሰቡ፣ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች አካባቢውን ከነዋሪው በመከለል ማታ ማታ የተቃጠለ አስከሬን እየፈለጉ በመቅበር ላይ ናቸው ብሎአል። እናቶች አሁንም ድረስ ልጆቻቸውን እየጠየቁ ቢሆንም፣ በከንቲባው በኩል የሚሰጠው ምላሽ አሳዛኝ መሆኑን ግለሰቡ ገልጿል። ነዋሪዎቹ በመንግስት በኩል በቂ እርዳታ እንዳልተደረገላቸው በምሬት ተናግረዋል።
መንግስት የእሳቱን መነሻ እስካሁን ይፋ አላደረገም። ነዋሪዎች እንደሚሉት ግን መስተዳድሩ ቦታውን ለመሸጥ እሳቱን ሆን ብሎ አስነስቶታል። በጉዳዩ ዙሪያ የአዋሳን ከንቲባ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።
የካቲት ፳(ሃያ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና

Monday, February 23, 2015

የ2007ቱን ሀገራዊ ምርጫ ሂደት እና ከምርጫዉ ዉጭ ያሉ አዋጭ አማራጮችን በተመለከተ የአርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ የአቋም መግለጫ

አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሰላማዊ፣ ተዓማኒና ፍትሀዊ በሆነ ምርጫ የማይፈልጋቸውን መሪዎች መሻር፤ የሚፈልጋቸውን ደግሞ መሾም የሚያስችሉትን መሠረቶች ለመጣል የሚታገል ንቅናቄ ነው። እንደሚታወቀው የሕዝብ እውነተኛ ፍላጎት የሚገለጽበት እውነተኛ ምርጫ እንዲኖር ገለልተኛና ቀልጣፋ የፍትህ ሥርዓት፣ የጦርና የፓሊስ ሠራዊት ሊኖሩ ይገባል። ነፃ የሚዲያ ተቋማትና በነፃነት የሚንቀሳቀሱ የሲቪክ ማኅበራት መኖርም መታለፍ የሌለባቸው አቢይ ጉዳዮች ናቸው። አማራጭ ፓሊሲዎችን ማቅረብ የሚችሉ በነፃነት የሚንቀሳቀሱ የፓለቲካ ፓርቲዎች ከሌሉም አማራጮች የሉምና ምርጫ ትርጉም የለውም። ይህ ሁሉ ቢሟላ እንኳን ምርጫውን የሚያስፈጽመው አካል ገለልተኛ፣ ሀቀኛና ተዓማኒ ካልሆነ የሚደረገው ምርጫ የመራጩን ሕዝብ ፍላጎት የሚያንፀባርቅ ሊሆን አይችልም።
g 7ከላይ የተዘረዘሩትን የምርጫ እሴቶች ሙሉ በሙሉ ባይሆንም እንኳን የተወሰኑትን በመጠኑም ቢሆን ያካተተ ምርጫ እንዲኖር መጣርና በሂደት የምርጫውን አፈፃፀም ማሻሻል ይቻል ይሆናል በሚል እምነት የዲሞክራሲ ኃይሎች በህወሓት የሴራ ምርጫዎች ሲሳተፉ ቆይተዋል። ሆኖም በህወሓትና በእውነተኛ ምርጫ መካከል  ያለው ተቃርኖ እያደር እየሰፋ ሲሄድ እንጂ ሲጠብ አልታየም።  በህወሓት ሙሉ ቁጥጥር ስር በሚካሄድ ምርጫ ኢትዮጵያን የሚጠቅም ለውጥ ሊመጣ ይችላል የሚለው እምነት ለአርበኞች ግንቦት 7 ፈጽሞ የተሟጠጠው ከምርጫ 97 ማግስት ጀምሮ  ነው። በግንቦት 7 ቀን 1997 ዓም የኢትዮጵያ ሕዝብ በታላቅ የለውጥ ተስፋ የሰጠው ድምጽ በህወሓት የተዘረፈው ከላይ የተዘረዘሩት ተቋማት ያልነበሩ በመሆናቸው፤ ስለዚህም ከምርጫ በፊት ተቋማቱን መገንባት፤ ተቋማቱን ለመገንባት ደግሞ ህወሓትን ከስልጣን ማስወገድ ይገባል ብሎ በማመኑ ነው አርበኞች ግንቦት 7 በሁለገብ የትግል ስልት በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው።
ያም ሆኖ ግን በምርጫ ላይ ያላቸው ተስፋ ፈጽሞ ያልተሟጠጠ ፓርቲዎችን በማክበርና ሥራቸውንም አስቸጋሪ ላለማድረግ ሲባል ከምርጫ 97 ወዲህ የነበሩ ብሄራዊም ሆነ ክልላዊ ምርጫዎችን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከምርጫ ዉጭ ያሉ ሌሎች አማራጮችን ብቻ እንዲመለከት አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ አድርጎ አያውቅም ነበር። አሁን ግን የአገራችን ኢትዮጵያ የፓለቲካ ሁኔታዎች  ይህንን የቆየ አቋም በሚያስቀይር መንገድ፤ የአገራችንን የወደፊት ዕድል ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ ያካባቢውን ሰላም በሚጎዳ መልኩ ተቀይሯል። የሰሞኑ የወያኔ እርምጃዎች ትንሽ ተስፋ ያደርግ የነበረውን የዴሞክራሲ ወገንተኛ ተስፋም እምሽክ አድርጎ በልቶታል:: እየተቃረበ ያለው ዓይነት የፌዝ ምርጫ ወያኔ እንደ እንጄራ የራበውን የተቀባይነት እጦት ለአጭር ጊዜ ያስታግስለት ይሆናል እንጂ የሀገሪቱን እያደር እየተወሳሰበ የመጣ ችግር ለጊዜውም እንኳን የሚያስታግስ አይሆንም፤ ይልቁንም ጊዜው በገፋ ቁጥር ችግሩ መቋጠሪያ የጠፋው እየሆነ ይሄዳል::
የሁኔታውን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የአርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ አመራር የወቅቱን የአገራችን የፓለቲካ ሁኔታ በጥንቃቄ መርምሮ የሚከተሉት ግንዛቤዎች ላይ ደርሷል።
  1. ህወሓት ብዙዎች እትዮጵያዊያን የተሰውላቸውን አንድነት ፓርቲንና መኢአድን በመበተን የድርጅቶቹን ስምና ንብረት ለአገልጋዮቹ መስጠቱ፤ ከዚህ በፊት ሲያደርግ እንደነበረው የመራጭን ድምጽ መስረቅ ሳይበቃው የምርጫ ተወዳዳሪንም መዝረፍ መጀመሩን አመላካች ነው። ይህ ተግባር ህወሓት የምርጫ ውጤትን ብቻ ሳይሆን ተወዳዳሪዎችንም እሱ ራሱ ለመምረጥ መወሰኑን ያሳያል፤ ከዚህ በተጨማሪ የሴራ ምርጫውን ከጅምሩ ጀምሮ አስቀድሞ እስከተወሰነለት መዳረሻው ድረስ ለምንም ዓይነት ያልተጠበቀ አጋጣሚ (በምርጫው ወቅት የሚደረጉትን ክርክር ተብዬዎች ጨምሮ) እድል ላለመስጠት ወስኖ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በግልጽ ያሳያል፤
  2. ይህ እኩይ ውሳኔ በምርጫ ቦርድ ፊርማና አንደበት ቢነገርም ምንጩ የህወሓት ፓሊት ቢሮ  መሆኑን የሚከተሉት ተግባራት ይጠቁማሉ፤
2.1.         በምርጫ ቦርድ በኩል እንዲገለጽ የተወሰነው እርምጃ ለማስመሰል ያክልም ቢሆን የህጋዊነት ሽፋን እንዲኖረው አለመደረጉ ውሳኔው ፍጹም እብሪተኛ በሆነ አካል መወሰኑን ያመለክታል። እንዲህ                   ዓይነቱ እብሪተኛ አካል ደግሞ የህወሓት ፓሊት ቢሮ ነው። ውሳኔውን ለማስፈፀም የነበረው ጥድፊያም ይህንኑ ያጠናክራል።
2.2.        ለማስመሰያ ያክል እንኳን ምንም አይነት የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳይኖር ፓሊስ የአንድነትና የመኢአድ ቢሮዎችን መውረሩ፤ ህወሓት አንድነትንና መኢአድን አጥፍቶ የድርጅቶቹን ስሞችና ንብረቶች                   ለሚፈልጋቸው ሰዎች ሰጥቶ በአስቸኳይ ለምርጫ ድራማው በፊት መስመር ሊያሰልፋቸው መወሰኑን አመላካች ነው። እንዲህ ዓይነት ከባድ ውሳኔ የሚሰጠው ደግሞ የህወሓት ፓሊት ቢሮ ብቻ                    ነው።
2.3.        ወደ ፈቃድ መንጠቅ ከመደረሱ በፊትም በሰማያዊ ፓርቲ፣ በአንድነትና በመኢአድ አባላት የደረሰው አረመኔያዊ ድብደባ፤ ንቁ የፓለቲካ ተሳትፎ የሚያደርጉ ዜጎች ላይ የሚደርሰው እስር፣ መሰወርና                 እና ባልታወቁ ሰዎች ተገድሎ መገኘት መብዛት እነዚህን አገራዊ ፓርቲዎች የመበተን የፓለቲካ ውሳኔ መሰጠቱን አመላካቾች ናቸው።
  1. ለጊዜው የፈቃድ ነጠቃና የንብረት ዘረፋ የተፈፀመው በአንድነትና በመኢአድ ላይ ቢሆንም በሰማያዊ ፓርቲ ላይ በየእለቱ እየጠነከረ የመጣው የአፈና እርምጃም በተመሳሳይ ፓርቲውን ወደማገድ አለዚያም ፈጽሞ መንቀሳቀስ ወደማይችልበት ደረጃ ሊያደርሰው ይችላል የሚል እምነት አሳድሯል። ሌሎች ፓርቲዎችም ከዚህ ህወሓት ካሰመረው የውሸት ጫወታ መስመር የመውጣት ዝንባሌ ቢያሳዩ ተመሳሳይ እርምጃ አይቀርላቸውም።
  2. የህወሓት የወቅቱ የጥፋት ዒላማ ያነጣጠረው አንፃራዊ በሆነ መንገድ የተሻለ መዋቅርና ማኅበራዊ መሠረት ባላቸው እና በአገራዊ አጀንዳዎቻቸው በሚታወቁ ፓርቲዎች ላይ መሆኑ፤ የወቅቱ የጥፋት ዘመቻ የኢትዮጵያ አንድነትን የማዳከምና ከፋፍሎ የመግዛት የህወሓት ትልቁ አጀንዳ አካል መሆኑን ያሳያል።
  3. እራሱን በዘር ያደራጀዉና ኢትዮጰያ ዉስጥ ያለዉ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አደረጃጀት ከዚሁ እሱ ከተደራጀበት የዘር አደረጃጀት ዉጭ እንዲሆን በፍጹም የማይፈቅደዉ የወያኔ አገዛዝ፤ መጣፊያው ሲያጥረውና ወደ ማይቀረው ውድቀቱ ሲያመራ፤ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው አህያ አገራችን ኢትዮጵያን በቀላሉ ወደማትወጣዉ የዘዉግ ግጭት ዉስጥ አስገብቶ ዘመናት ያስቆጠረዉ አንድነቷ እንዲፈረስ በትጋት እየሠራ መሆኑን ያሳያል።
  4. ከመለስ ዜናዊ ሞት ወዲህ ህወሓት ከሁሉን ጠቅላይ (totalitarian) አገዛዝ ወደ ፋሽስታዊ ቡድንነት ያሽቆለቆለ መሆኑን አርበኞች ግንቦት 7 ተገንዝቧል። ህወሓት ዘረኛ፣ ጠቅላይና ፈላጭ ቆራጭ ጨቌኝ በመሆኑ ፋሽስት ብለነዋል።  ሆኖም በታሪክ የሚታወቁ ፋሺስታዊ አገዛዞች ከፍተኛ ብሄራዊ ስሜት የነበራቸው ሲሆን የህወሓት ፋሽስታዊ አገዛዝ ግን ብሔራው ስሜት አልባ መሆኑ ልዩ እና የበለጠ አደገኛ ያደርገዋል። ይህ ፋሽስታዊ ቡድን የህወሓት መሪዎችንና ጥቂት ሌሎች አጫፋሪዎቻቸውን የያዘ ለጊዜው አስተባባሪ መሪ የሌለው ሆኖም ግን የጦር ሠራዊትን፣ የስለላ መዋቅሩንና ፓሊስን ተቆጣጥሮ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያን እየገዛ ያለው ይህ አስኳል የለሽ ፋሽስታዊ ቡድን መሆኑ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን አርበኞች ግንቦት 7 ተገንዝቧል። ይህ ፋሽስታዊ ቡድን ተደላድሎ መሪ እንዲፈጥር ከተፈቀደለት አገራችንን የከፋ መከራ ውስጥ ሊከታት እንደሚችል ግንዛቤ ተወስዷል።

ከላይ በአጭሩ ከተራ ቁጥ 1 እስከ 6 የተዘረዘሩትን በማገናዘብ በግንቦት 2007 ሊደረግ የታቀደውን አምስተኛው ዙር ሀገር አቀፍ የሴራ ምርጫን በተመለከተ የአርበኞች ግንቦት 7 አመራር ውሳኔዎችን አስተላልፎ ከዚህ የሚከተሉት ጥሪዎችን ለኢትዮጵያ ሕዝብ አቅርቧል።
  1. በምርጫ 2007 መሳተፍ ለዲሞክራሲያዊ ለውጥ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ይልቅ ፋሽስታዊውን ቡድን የሚያጠናክርና የኢትዮጵያን ሕዝብ የወደፊት ዕድል የሚገድል በመሆኑ፣ ለፍትህ፣ ለነፃነት፤ ለዲሞክራሲና ለአገር አንድነት ግድ ያላቸው ወገኖች ሁሉ ከአሁኑ ከዚህ የይስሙላ ምርጫ ዉጭ ዓይኖቻቸውንና ሙሉ ጉልበታቸዉን በሌሎች የኢትዮጵያን ሕዝብ ነፃነት በሚያፋጥኑ አማራጮች ላይ እንዲያሳርፉ ጥሪ ያደርጋል። አርበኞች ግንቦት 7 የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ ዓይን ያወጣ የሴራ ምርጫ ይልቅ መብቱን፤ ነፃነቱንና እኩልነቱን በሚያፋጥኑለት በሕዝባዊ እምቢተኝነትና በሕዝባዊ አመፅ የትግል አመራጮች ላይ እንዲሳትፍ ለመላው ያገሪቱ ሕዝብ ጥሪ ያስተላልፋል።  ህወሓት ማኅበረሰባችንን ለመከፋፈልና ለማባላት የሚያደርገውን እኩይ ሴራ በጋራ እንድናከሽፈው ወገናዊ ጥሪ ያስተላልፋል፤ “አንከፋፈልም፤ ተከፋፍለንም አንጠቃም“ እንበል ይላል::
  2. ህወሓትን ማስወገድ የሚቻለው በሕዝባዊ እምቢተኝነትና በሕዝባዊ አመጽ በመሆኑ፤  ከሁለቱ አንዱንም አለመያዝ ሌላ ሰው ታግሎ ነፃነቴን ያቀዳጀኝ እንደማለት የሚቆጠር በመሆኑ፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በአፋጣኝ ከእነዚህ ሁለት የትግል ዘርፎች ዉስጥ የተሻለ አስተዋጽኦ አበረክታለሁ በሚለው የትግል ዘርፍ ውስጥ ተሳትፎ  እንዲያደርግ ጥሪ ያቀርባል።
  3. አርበኞች ግንቦት 7፣ በሁለቱም የትግል ዘርፎች ድርጅታዊ መዋቅሩን እያሰፋና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመተባበር በሕዝባዊ እምቢተኝነትና በሕዝባዊ አመጽ ህወሓትን ከስልጣን ለማስወገድ አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን በስፋት እንዲቀላቀሉት፤ በኅብረት እንድንቆም እና የህወሓትን ውድቀትና የኢትዮጵያን ትንሳኤ እንድናፋጥን ጥሪ ያደርጋል::
  4. ያለንን አቅም በሙሉ ህወሓትን በማስወገድ ላይ ካዋልነው አንድ ጠንክር ያለ ሕዝባዊ አመጽ አገዛዙን ሊያፍረክርክው የሚችል በመሆኑ፤ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ከምርጫ ጋር ለተያያዙ ሥራዎች ሊውል ታስቦ የነበረው የሰው ኃይል፣ ጊዜ፣ ገንዘብና እውቀት ለሕዝባዊ አብዮት መቀስቀሻነት እንዲውል ጥሪ ያደርጋል።
  5. በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንም በ2007 ምርጫ ላይ ጊዜና ንብረት ከማባከን ይልቅ በአንድ ልብ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሕዝባዊ አብዮት መቀስቀስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ ያደርጋል።   ከሁሉም ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች የተውጣጣ አካል የዚህን ጥሪ ተፈፃሚነት እንዲከታተል ቢደረግ ይበልጥ ውጤታማ ይሆናል ብሎ ያምናል።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ


    ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

    Monday, February 9, 2015

    ቀኑ ሲቃረብ መውጫው ይጠባል!


    ቀኑ ሲቃረብ መውጫው ይጠባል!

    ቀኑ ሲቃረብ መውጫው ይጠባል!

    ኢትዮጵያ ሀገራችን በታሪኳ ከአስከፊ የፈተና አረንቋ ውስጥ ተገፍታ የገባችበት ዘመን ቢኖር ይህ የምንገኝበት ዘመነ ወያኔ ብቻ ነው፡፡ ዜጎችዋ ከፋሽስት ኢጣልያ በከፋ ሁኔታ ይህ ቀረሽ የማይባል የመከራ መአት የወረደባቸውና እየወረ ደባ ቸው የሚገኝበት ዘመን ቢኖር ይህ የምንገኝበት ዘመን ወያኔ ብቻ ነው፡፡ እስር ቤቶች ሞልተው ተጨማሪ እስር ቤቶች መገ ንባት ከልማት ተቆጥሮ የሚፎከርበት ዘመን ቢኖር ይኸው ዘመነ ወያኔ ብቻ ነው፡፡ የሀገሪቱ ብሄራዊ ባንክ ንብረት የሆ ነው ወርቅ በባሌስትራ ለውጦ እስከ መዝረፍ የደረሰ በጠራራ ፀሀይ የህ ዝብና የሀገር ሀብት ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ በጥቂቶች የሚዘረፍበት ዘመን ቢኖር የምንገኝበት ዘመነ ወያኔ ብቻ ነው፡፡ የጅምላ እስር፤ የጅምላ ግድያ፤ የጅምላ ስደትና መፈናቀል፤ ይበልጡንም በታሪካችን ታይቶ በማያውቅ መልኩ ለሞት፤ ለእስር፤ ለመፈናቀልና ለስደ ት ምክንያቱ የተገኘንበት ዘውግ የሆነበት ዘረኛ ዘመን ቢኖር ይኸው ዘመነ ወያኔ ብቻ ነው፡፡
    g7-logo
    ባጠቃላይ ላለፉት 23 አመታት ወያኔ ማድረግ የሚችለውን አስከፊ ነገር ሁሉ በሀገርና በህዝብ ላይ ሲፈፅም ቆይቷል፡፡ ዛሬ ከ23 አመ ታት በዃላ ሀገራችንና ህዝባችን ያልተዘፈቁበት የችግር ማጥ፤ ያልደረሰ የሀብትና የሰብአዊ ውድመት፤ ያልተፈፀመ የግፍና የሰቆቃ አይነት የለም፡፡ ወያኔ ይህን ሁሉ ሲፈፅም መሳሪያ አድርጎ ከተጠቀመባቸው ተቋማት ውስጥ ዋነኛዎቹ የመከላከያ፤ ፍርድ ቤትና የፖሊስና የደህንነት መሆናቸው ጥያቄ የለውም፡፡ የእነዚህ ተቋማት አባላት ከወያኔ ጥቃት ሰለባ ከመሆን ባይተርፉም የዚህን ወንጀለኛና ዘረኛ ቡድን እድሜ በአንድ ቀን በመጨመሩ ስራ ላይ ከፍተኛውን ድርሻ እንደያዙ ዛሬም መገኘታቸው አሌ የማይባል እውነት ነው፡፡ይህ ሲባል ግን በሀገርና በህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ክህደት፤ ግፍና ሰቆቃ የሚያማቸው፤ መከራው መረራቸው፤ ብሶቱ ብሶታቸው የሆኑ አባላት የሉም ማለት እንዳልሆነ፤ ይልቁንም አብዛኛዎቹ የዚህ ስሌት ተካፋይ ስለመሆናቸው የሚጠራጠር የለም፡፡
    ነገር ግን ከህዝብ አብራክ በወጡና ልጆቹን ሳይመግብ በከፈለው ታክስ በተደራጀ የመከላከያ፤ የፖሊስና የደህንነት ተቋማት ውስጥ የምትገኙ አብዛኛውና የግፉ ቀማሽ የሆናችሁ አባላት ዛሬ የምትገኙበት ሁኔታ እንደ አለፉት 23 አመታት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፤ ከዛሬ ነገ የተሻለን ነገር ተስፋ በማድረግ፤ በግርግሩ ፍርፋሪ ሊወድቅልኝ ይችላል ከሚል ራስ ወዳድነት…… ወዘተ በመሳሰሉ በርካታ ምክንያቶች ለፍትህ፤ ለነፃነትና ለዲሞክራሲ ብሎም ለኢትዮጵያችን ቀጣይ ህልውና በሚደረጉ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በመቆም ብሎም የጥቂት ዘረ ኛች ስልጣንና ምቾት እድሜ ለማራዘም የተጓዛችሁበት መንገድ ብዙም ማስኬድ ከማያስችልበት፤ ይልቁንም ዛሬ ከሁለት መንታ መንገድ የ ደረሳችሁበትና ቆም ብሎም ማየትና ማገናዘብን ከሚጠይቅ ወቅት ላይ ትገኛላችሁ፡፡ አንዱ በዘረኝነት በትር እየተወቀጡ የወያኔ ሎሌ ሆኖ መቀጠል፤ ሌላው ከህዝብ አብራክ የተገኛችሁ ናችሁና ከህዝብ ወገን ተቀላቅሎ ሀገርን፤ ወገንንና ራስን ነፃ ለማውጣት መነሳት..
    ለመከላከያ ሰራዊት፦ ላለፉት 23 አመታት ከጠመንጃ ተሸካሚነት ላለፈ ለማይፈልጉህ፤ ለአንተነትህ መለኪያው እውቀትህ፤ ችሎታ ህና አገልግሎትህ ሳይሆን የተገኘህበት ዘውግ መስፈሪያህ ለሆነበት ዘረኛ ስርአት፤ መቀየሪያ መለያ ልብስ ተነፍጎህ ቀዳዳ እየጣፍክ የልጆችህን የረሀብ ልቅሶ እያዳመጥክ በአንተ ትከሻ በዘረፉት ሀብት የገነቧቸውን ህንፃዎች ጠባቂ ላደረጉህ፤ ፍትህ ነፃነት ሲል በተራበ አንጀታቸውና በደ ከመ ድምፃቸው በጠየቁ ወገኖችህ ላይ ይህ ቀረ የማይባል ግፍ ሲያ ስፈፅምህ ለቆየው የወያኔ ዘረኛ ቡድን ዛሬም ተገቢውን ምላሽ የመስጠት እድሉ አለህ፡፡አልረፈደምና ተጠቀምበት!!!
    የፖሊስ ሰራዊት አባላት፤- ፍትህ ላሉ ጥይትን፤ ነፃነት ላሉ የጭካኔ በትርን፤ ሀገሬን ላሉ ከጨለማ ዘብጥያ መወርወርን.. ዋነኛ ተግባርህ በሆነበት በዚህ ዘረኛና በወንጀል የተጨማለቀ ስርአት ውስጥ የቆየህበት ያለፉት 23 አመታት ለአንተም፤ ለቤተሰብህም፤ ለተገኘህበት ህብረ ተሰብ ሆነ ለሀገርህ የፈየደው አንዳች ነገር ያለመኖሩን ይበልጡኑ ከእሳት ወደ እረመጥ ከሆነው የወያኔ ጉዞ ራስህን አውጥተህ ከህዝባዊው ወገን የምትቀላቀልበት የመጨረሻው ሰአት መሆኑን ተገንዝበህ ምርጫህን ከወገንህ አድርግ፡፡ ለአንተም አልረፈደም!!
    የደህንነት አባላት፦ ለሀገር ደህንነት ለህዝብ ሰላም ሲባል በህዝብ ሀብት በተደራጀ ተቋም ተጠቅመህ በሀገርህ ላይ ክህደትን፤ በወገ ንህ ላይ ግፍና ሰቆቃን ስትፈፅም መቆየትህ ከወንጀሎች ሁል የከፋ ወንጀል መሆኑን ተገንዝበህ ለፍትህ ለነ ፃነትና ለዲሞክራሲ ሲሉ በተነሱ ወገኖችህ ላይ ስትሰነዝር የቆየኸውን በትር በፍትህ በነፃነትና በዲሞክራሲ ላይ በቆሙት ዘ ረኛ አዛዦችህ ላይ የማሻው ጊዜ አሁን ነው፡፡ ስለ ዚህም ከህዝባዊው ወገን ተቀላቅለህ ህዝባዊ ወገንተኝነትህን የምታሳይበት ብሎም የበደልከውን የምትክስበት ጊዜውም እድሉ አለህና ተጠ ቀምበት፡፡ላንተም አልረፈደም!!
    በመጨረሻም ልጇን የምትጠላ እናት፤ ወገኑን የሚገፋ ህዝብ፤ ዜጎቹን የማይቀበል ሀገር የለምና ይህን በአስከፊነቱ ወደር የማይገኝለት የወያኔ ዘረኛ ስርአት ደግፎ ማቆየት ከማይቻልበት ይበልጡንም እንደ ትሪፖሊና ኢያሪኮ የግፈኞች ግንብ በህዝባዊ ሀይል ከሚገረሰስበት ከ መጨረሻዋ ደቂቃ ከመደረሱ በፊት ከእናታችሁ እቅፍ ከወገናችሁ መሀል ግቡ!! ተቀላቀሉ!! ቀኑ ሲቃረብ መውጫው ይጠባልና ጊዜ ሳታጠ ፉ ፈር ቀዳጅ ወንድሞቻችሁን መከተል ብልህነት ነው እንላለን!!!
    የኢያሪኮም የጋዳፊም ግንብ ተንዷል፤ የወያኔም ይናዳል!!!
    ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

    Friday, February 6, 2015

    በአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰት ዙሪያ መከረ

    በአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰት ዙሪያ መከረ

    Feb 05, 2015
    EU Union


      ጥር ፳፰(ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ህብረቱ ጥር 27፣2007 ዓም በብራሰልስ ቤልጂየም የአውሮፓ ህብረት ጽ/ቤት ውስጥ ለ3 ሰአታት ባደረገው የኢትዮጵያ የሰአብአዊ መብት ግምገማ በኦጋዴን ክልል እና በተቀሩት የኢትዮጵያ ግዛቶች በዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ሰቆቃ የአውሮፓ ህብረትና አባል መንግስታት በዝምታ መመልከታቸውን ማብቃት አለበት የሚል ውሳኔ አስተላልፈዋል።
      ስብሰባውን ያዘጋጁት የህብረቱ የሶሻሊስትና የዲሞክራቲክ ፓርቲዎች ጥምር ህብረት ፣ ውክልና አልባ ህዝቦች ተቆርቋሪ ድርጅት ጋር በመተባበር ነው።
      በስብሰባው ላይ የኦጋዴን ክልል ፕ/ት አማካሪ የነበረና በክልሉ የሚፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በመረጃ በማጋለጥ ላይ የሚገኘው ወጣት አብዱላሂ ሃሰን፣ ተቀማጭነቱ በጄኔቫ የሆነ የአፍሪካ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ባልደረባ፣ አቶ አብዱላሂ ሙሃመድ፣ የኦጋዴን ሴቶች ተወካይ ፣ ጋዜጠኛና የክሬት ትረስ ዳይሬክተር ግርሃም ፌብልስ፣ እንዲሁም በኦሮሞ ሴቶች ላይ የሚደረሰውን ሰቆቃ በማስመልከት ጥናት ያካሄዱት፣ ዶ/ርባሮ ቀኖ በቪዲዮ የተደገፈ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
      Abdullahi
      እንግሊዛዊው ግራሃም ፌብልስ በኢትዮጵያ 2 አመታት ቆይታቸው የታዘቡትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተለይም በኦጋዴን ክልል በሴቶች ላይ ተፈጽሟል ያሉትን አስገድዶ መድፈር ወንጀል የታዳሚውን ስሜት በነካ መልኩ አቅርበዋል። በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በዜጎች ላይ ሽብርን እያኬደ ነው ያሉት ሚ/ር ፌብልስ የዚህ ሶቆቃ ፈጻሚዎች፣ ከአውሮፓ ህበረትና መንግስታት በእያመቱ ከፍተኛ የገንዘብ እርዳታ የሚያገኙ መሆናቸው እጅግ የሚያሳዝነው ነው ብለዋል።
      በጉባኤው ላይ የኦጋዴን ነጻነት ግንባር ተወካይ ዶ/ር ባዳል አህመድ እና አርበኞች ግንቦት7 ተወካይ አቶ አበበ ቦጋለ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸመ ነው የሚሉትን የሰብአዊና የፖለቲካ መብቶች እረገጣና አስከፊ ሰቆቃ በእየተራ አቅርበዋል።
      Abebe Bogale
      የአውሮፓ ህብረትን ወክለው በስብሰባው ላይ የተገኙት ወ/ሮ አና ጎሜዝና የእንግሊዝ የፓርላማ ተወካይ ወ/ሮ ጁሊ ዋርድ በየተራ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ መንግስት ከ60 በመቶ በላይ በጀቱን ከአውሮፓ ህበረት እየተቀበለ ዜጎች ላይ እየፈጸማቸው ያለው አስከፊ ሰቆቃዎችን አውሮፓ ካሁን በሁዋላ በዝምታ ማየት የለባትም ካሉ በሁዋላ፣ ኢትዮጵያኖች በአገራቸው እየተፈጸመ ያለውን አፈናና ጭቆና የውች ማህበረሰብ ያስቆምልናል ብለው ከመጠባበቅ ለራሳቸው ነጻነት ልዩነቶቻቸውን በማቻቻልና መለስተኛ ፕሮግራም በማዘጋጀት ህብረት ፈጥረው በአንድነት መታገልና ለለውጥ መነሳት አለባቸው ብለዋል።
      የአውሮፓ ህብረት በዘንድሮው ምርጫ ላይ ታዛቢዎችን እንዳይልክ የወሰነው የኢህአዴግ መንግስት በየ5 አመቱ የሚያደርገውን የተሳሳተ ምርጫ በማጀብ ህጋዊነት ለማሰጠት እንደከዚህ በፊቱ ለመተባበር ፈቃደኛ አለመሆኑን ለመግለጽ ሆኖ ሳለ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ግን ህበረቱ በገጠመው የበጀት ችግር ምክንያት ታዛቢ አልክም ብሎአል ብሎ የጀመረው ቅስቀሳ መሰረተ ቢስና የተለመደ ህዝብን የማዘናጊያ ወሬ እንደሆነ ገልጸዋል። የአመቱን 60 በመቶ የሚሸፍን በጀት የሚሰጠው ህብረቱ፣ ኢትዮጵያን የመሰለ ስትራቴጂክ አገር፣ ህብረቱ የገንዘብ እጥረት ገጥሞታል ብሎ ማሰብ ራስን እንደማታለል ይቆጠራል ብለዋል።
      ህብረቱ ምርጫው ከመደረጉ ከሚቀጥለው ወር በፊት የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችንና ሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን በስፋት የሚያሳትፍ ትልቅ ጉባኤ በሚያዚያ ወር ላይ ለመጥራት በዝግጅት ላይ እንዳለ በዚህ ስብሰባ ላይ ተገልጿል።
      አንዳንድ የፓርላማ አባላት በዚህ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደግብጽ ህዝብ ሆ ብሎ በመነሳት ከመዒው ግንቦት ምርጫ በፊት አምባገነንነትን ከራሱ ትከሻ ላይ ለማውረድ መነሳት አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
      የኢትዮጵያ መንግስት በሚቀርብበት የሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ አቋሙን እንዲገልጽ ቢጋበዝም ፣ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ የሆነ ቤልጂየማዊ ዜጋ የሆነ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ሰራተኛ  የተገኘ ሲሆን ስራውም መረጃ መሰብሰብ እንጅ አስተያየት መስጠት አለመሆኑን ገልጾ፣ ምንም ንግግር ሳያደርግ ወጥቷል።