Friday, March 27, 2015

“ጦር ሠራዊቱ ሕዝባዊ እምቢተኛነት ሲያይል የወያኔን መቃብር ይቆፍራል” – አርበኞች ግንቦት 7

የአርበኞች ግንቦት 7 ወቅታዊ መጽሐፍ
ጉዞአችን ወደ ነፃነት ነው!! መዳረሻችንም የነፃነት አደባባይ ብቻ ነው!!
አለማችን አንባገነን ስታስተናግድ ወያኔ የመጀመሪያው አይደለም። ዘረኛንም እንዲሁ …….. እኛም ስለነፃነት ብለን ለትግል ሰንነሳ የመጀመሪያዎቹ አይደለንም …… አለማችን እንደየዘመኑና እንደ የወቅቱ አንባገነኖች ያለ የሌለ የመሳሪያና ወታደራዊ ሀይላቸውን በመጠቀም ህዝብን በፍርሀት አሸማቀውና ረግጠው ለመግዛት ሲውተረተሩ በተደጋጋሚ ታይተዋል። በዚያው ልክ ህዝባዊ ሀይልና መመከት ተስኗቸው ሲንኮታኮቱ በተደጋጋሚ የታየ ወደፊትም አናባገነኖች እስከተከሰቱ ድረስ በህዝባዊ ሀይል ተጠራርገው መቀመቅ ሲወርዱ መታየቱ አይቀሬ ነው ። ህዝብ የወደደውን አስተዳዳሪ እንጂ ረግጦ ሊገዛው የሚፈልገውና አንባገነን ተቀብሎ አያውቅም ፤ዛሬም አልተቀበለም ፤ ነገም አይቀበልም ። ይህን በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ በተደጋጋሚና በጉልህ የሚታይ ግዙፍ እውነት መቼም ተቀብለውና ከታሪክ ተምረው ስለማያውቁ አሳፋሪው ውድቀታቸው በተደጋጋሚ ሲታይ አለ።
ginbot 7
ሀገራችን የአለማችን አካል እንደመሆኗ አንባገነኖች ተፈራርቀውባታል። አንባገነኖችም በህዝባዊ ሀይል ተጠራርገውባ ታል። ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ ትልቅ ወታደራዊ ሀይል የነበረው የትናንቱ ደርግ እንደ እንቧይ ካብ ሲናድ ተመልክተናል። አንባገነኖችመናገር እንጂ መስማት የማ ችሉ፤ ማየት እንጂ ማስተዋል የተሳናቸው በመሆናቸው እነሆ ዛሬም የወያኔ ዘረኛው ቡድን ህዝባ ላነሳው የነፃነትና የፍትህ ጥያቄ ያለ የሌለውን ወታደራዊ ሀይል በጠራራ ጸሀይ በማሰለፍ መቼውንም ያልተቻለ ውን ህዝብን በሀይል አሸማቆ ለመግዛት መከራውን ሲያይ ይስተዋላል። ለዚህም ነው ….. ከሌላው የሀገራችን ክልሎች ከፍ ባለ ሁኔታ የህዝባዊ እንቢተኝነት እየታየ ባለበት ጎንደርና አካባቢው በሰራዊት ማጥለቅለቅ የተያያዘው።
ለሚነሱ ህዝባዊ ተቃውሞዎችና ህዝባዊ የመብት ጥያቄዎች የሚሰጡት ምላሾች እስር፤ አፈናና ግድያ ከሆነ ህዝባዊ እንቢተኝነትን ማስከተሉ አይቀሬ ነው። በእስር ፤በአፈናና በግድያ እንዲሁም በሰራዊት ሀይል ህዝብን በማሸማቀቅ በስልጣን መቆየት የሚቻል ቢሆን ደርግም ከቤተ-መንግስት ባልወጣ፤ ወያኔም ዛሬ ከቤተ-መንግስቱ ባልተንፈልለሰ ነበር። ይህ ደግሞ ሊያስተምር በተገባ ነበር።
እስከ ዛሬ የትኛውም አንባገነን ስርአት በሚተማመንበት የወታደራዊ ሀይል አማካይነት የመንኮታኮቻቸውን ሰአት በአንድ ሰኮንድ ማዘግየት የቻለ እንደሌለ ሁሉ ወያኔም ያለ የሌለውን ወታደራዊ ሀይል ሲያርመሰምስ ውሎ ቢያድር ውድ ቀቱን በአንድ ሰኮንድ ማዘግየት እንደማይችል በተለይ እንቢ ለነፃነቴ፤ እንቢ ለሀገሬ… ብለን ለትግል የተነሳን ሀይሎች በመረ ዳት፤ ይበልጡኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተቀጣጠለ ያለውን ህዝባዊ እንቢተኝነት ይበልጥ እያሰፋን የጀመርነውን የነፃነት ጉዞ ከነፃነታችን አደባባይ ለማድረስ ሌት ተቀን የመስራት ሀላፊነታችናና መወጣት ይገባናል።
በጎንደር የሚታየውን የአልገዛም ባይነት ትንቅንቅ በሌሎች ክልሎችም በማቀጣጠል፤ በደብረወርቅ የታየውን የመምህራን የስራ ማቆም አድማ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በማስፋት፤ እንደ ድምፃችን ይሰማ ሁሉ ተቃውሞን ወደ እንቢተኝነት በማሸጋ ገር …… ወዘተ የነፃነታችንን ቀን ለማቅረብ መከፈል የሚገባውን መክፈል ይገባናል።
በደርግ ል የተነሳው እንቢተኝነት እያየለ ሲመጣ ያሰለፈው ሰራዊት ወያኔን አጅቦ የደርግን ቀብር እንደቆፈረለት ሁሉ ዛሬም በወያኔ ላይ እየተቀጣጠለ የሚገኘው ህዝባዊ እንቢተኝነት እየጠነከረ በመጣ ቁጥር የደረደረው ሰራዊት የወያኔን ቀብር ቆፋሪ ከመሆኑ እንደማኢመለስ ከቅርብ ጊዜ ታሪካችን በመማር ነፃነታችንን ለማስከበር የጀመርነውን የእንቢተኝነት ትግል በ መ ላው የሀገራችን ክፍሎች በማስፋትና በማቀጣጠል አይቀሬውን የወ ኔ ቀብር ለማቅረብ በአንድነት የነፃነት ጉዞውን እንቀ ላቀል። የጀመርነው የነፃነት ጉዞ መቆሚያው የነፃነታችን አደባባይ መሆኑን በተግባር ከምናሳይበት ወቅት ላይ እንገኛለንና በአንድነት እንነሳ!!!!!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!!

Wednesday, March 25, 2015

ድምፃችን ይሰማ 2ኛውን የሰላማዊ ተቃውሞ ይፋ አደረገ * “ሳንቲም በመሰብሰብ በራስ ላይ እቀባን በማድረግ ለመንግስት ተቃውሞን መግለጽ”

2ኛው አነስተኛ የትብብር መንፈግ ተቃውሞ መርሃ ግብር
ሳንቲም በመሰብሰብና በማጠራቀም ራስ ላይ የመቆጠብ እቀባ በማድረግ ለመንግስት የተቃውሞ መልእክት ማስተላለፍ
ረቡዕ መጋቢት 16/2007
በሰላማዊ ህዝባዊ ትግል ውስጥ ትብብር የመንፈግ እና የቦይኮት ተቃውሞ ከመንግስት ኃይሎች ጋር ሳይፋጠጡ እና አካላዊ ግጭት ውስጥ ሳይገቡ ትብብርን በመንፈግና የቦይኮት እንቅስቃሴዎችን በማድረግ በደል እያደረሰ ለሚገኘው አካል የተቃውሞ መልእክት የማተላለፍ ስልት ነው፡፡ የትብብር መንፈግ ተቃውሞዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓይነቶች ያሏቸው ሲሆን በአገሪቱ ውስጥ የሚገባንን የዜግነት መብት እስክናገኝ ድረስ ለመታገል ቆርጠን በገባንበት ታላቅ ህዝባዊ ትግል ውስጥ ካሁን ቀደም እምብዛም ሳይሞከር ቆይቷል፡፡
yisema
ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተቃውሟችን ወደቦይኮት እና ትብብር የመንፈግ ስልቶች እንደሚሸጋገር፣ ይህም አደባባይ ተኮር በሆኑ ተቃውሞዎች የገዛ ህዝቡ ላይ ጥይት ለመተኮስ የማያመነታው መንግስት ጡጫ እንዳያሳርፍብን ለመከላከል እንደሚያስችል መገለጹ ይታወሳል፡፡ እስካሁንም በጥቂት አጋጣሚዎች በቀኑ ክፍለ ጊዜ ስልክን በማጥፋት እና በአስገዳጅ ሁኔታዎች ውስጥ ካልሆነ ባለመጠቀም ውስንና አነስተኛ የቦይኮት ተቃውሞን በኢትዮ ቴሌኮም ተቋም ላይ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ አሁን ደግሞ ትንሽ ከፍ ያሉ የትብብር መንፈግ ስልቶችን ቀስ በቀስ ወደመላመዱ እና ወደመተግበሩ፣ ቀስ በቀስም ወደማሳደጉ መግባት ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ ባለፈው ጁሙዓ እየገባንበት ያለውን የትግል ስልት ስኬታማ እንዲያደርግልን እና መሪዎቻችንንም ከእስር ነጃ እንዲልልን በአገሪቱ በሚገኙ መስጂዶች ተሰባስበን ዱዓ ማድረጋችን ይታወሳል፡፡ በመሆኑም ከፊታችን ጁሙዓ መጋቢት 18/2007 ጀምሮ ሳንቲም በመሰብሰብና በማጠራቀም ራስ ላይ የመቆጠብ እቀባ በማድረግ ለመንግስት የተቃውሞ መልእክት ወደማስተላለፍ እንቅስቃሴ የምንገባ ይሆናል፡፡
መንግስት በገዛ ህዝቦቹ ላይ በሃይማኖታችን ምክንያት እያደረሰብን የሚገኘው ከፍተኛ በደል የሚሳለጠው ከእኛው በሚሰበሰብ ግብር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ህዝቡን እየደበደቡ እና እየገደሉ ያሉት የመንግስት ኃይሎች ደሞዛቸው የሚከፈለውም ከህዝቡ ኪስ በሚወጣ ገንዘብ ነው፡፡ በመሆኑም እንደዜጋ ገንዘባችንን በራሳችን ላይ ኢንቨስት ያለማድረግ የዜግነት መብታችንን በመጠቀም የሳንቲም ዝውውሩ ላይ እጥረት ስንፈጥር በእርግጥም ከእኛ ኪስ የሚገኘው ገንዘብ ላይ እኛም እንደህዝብ የተወሰነ ስልጣን እንዳለን ለመንግስት ግልጽ እናደርጋለን። ጥያቄዎቻችንን ባለመመለሱም የተቃውሞ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡
እንደሚታወቀው መንግስት አንዲትን ሳንቲም ከዓለምአቀፍ የገንዘብ አምራች ተቋማት ሲያሰራ ከዋጋዋ በላይ አውጥቶባት ነው፡፡ ለሳንቲም ማሰሪያ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑም ሳንቲም ዝውውሩ ላይ ችግር ሲፈጠር ከፍተኛ ጫና ይደርስበታል፡፡ ምናልባት መንግስት ክፍተቱን ተጨማሪ ሳንቲም በማተም ለመሙላት ቢሞክር እንኳን የሰበሰብነውን ሳንቲም መልሰን ወደ ገበያው በማስገባት የዋጋ ዝቅጠት መፍጠር የምንችልበት አጋጣሚ የሚኖር መሆኑም ከግንዛቤ የሚገባ ነው፡፡ በዚህ የተቃውሞ ዘዴ ልናሳካው የምንሻው ጊዜያዊ ዓላማ ለሶስት ዓመታት ‹‹የፍትህ ያለህ!›› ስንል ቆይተን ከተጨማሪ በደል ውጭ መልስ ላልሰጠን መንግስት እንደህዝብነታችን አቅም እንዳለን እና ተጽእኖ ማሳደርም እንደምንችል ማሳየት ነው – ያለህዝብ ይሁንታ የመንግስት ህልውና ቢዘግኑት የማይዘገን ጉም መሆኑን ማስመስከር!!
ሳንቲም ሰብስቦ የመቆጠቡ ተቃውሞ አተገባበር
1/ የምንሰበስበው እና ቆጥበን የምናስቀምጠው እጃችን ላይ የገባውን ሳንቲም በሙሉ አይደለም! ይልቁንም ለኑሯችን አስገዳጅ የሆነውን ያክል ብቻ በመጠቀም ቀሪውን ማስቀመጥን ዓላማ ያደረገ ነው፡፡ በመሆኑም እጃችን ላይ ከሚገቡት ሳንቲሞች የግድ አስፈላጊ የሆነውን ያክል ብቻ በመጠቀም ቀሪውን በማስቀመጥ ብቻ እንወሰናለን፡፡
2/ ሳንቲም ቆጥቦ የመሰብሰብ ተቃውሞው የሚካሄደው በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች እና ከተሞች ነው፡፡
3/ ሳንቲም ቆጥቦ የመሰብሰብ ተቃውሞው የሚጀምረው የፊታችን አርብ መጋቢት 18/2007 ጀምሮ ሲሆን በዚሁ ገጻችን ማብቃቱ እስኪገለጽ ድረስም ላልተወሰነ ጊዜ ይቀጥላል፤ በአላህ ፈቃድ!
አዎን! እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በሃይማኖታችን ምክንያት በመንግስት ከፍተኛ በደል እየደረሰብን ያለን ሰላማዊ ዜጎች ብንሆንም መንግስት ከበደሉ ሊቆጠብ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ለዓመታት ሰላማዊ ትግል ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ሰላማዊነታችንን ለመግለጽ ነጭ ጨርቅ እያውለበለብን በአደባባይ በተገኘን ቁጥር መንግስት አስፈራርቶናል፤ ዘልፎናል፤ ደብድቦናል፤ ዘርፎናል፤ አስሮናል፤ ገድሎናል፡፡ እኛ ነጭ ሶፍት ይዘን ሰላማዊነታችንን በአደባባይ ስንዘምር መንግስት ደግሞ ዝናሩን ታጥቆ በጥይት እሩምታ ተቀብሎናል፡፡ የማይጠፋ ጠባሳ የጣለ ጥቁር ሽብር ፈጽሞብናል፤ ፈርመን የላክናቸውን ወኪሎቻችንን በግፍ እስር እና በከፍተኛ ቶርቸር አሰቃይቶብናል፡፡ እስካሁንም ነጻነታቸውን ነፍጎ የምርጫ ቅስቀሳ መጠቀሚያ እያደረጋቸው ነው። እንግዲህ አሁን ላይ መንግስት ጥይት ሊተኩስበት በማይችለው ሜዳ ሰላማዊ ተቃውሟችንን ከመቀጠል ውጭ ሌላ ምርጫ ያለን አይመስልም፡፡ ዛሬ ይፋ ያደረግነው የትብብር መንፈግ ተቃውሞ ዋነኛ ዓላማም መንግስት ጥይት የሚተኩስበት ዒላማ የማያገኝበትን የትግል ድባብ በመፍጠር መብታችንን የማጎናጸፍ ግዴታውን እንዲወጣ የተቃውሞ መልእክት ማስተላለፍ ነው፡፡ ወደፊትም አንድ ብርና ከዛም በላይ ያሉ የብር ኖቶችንም ከመሰብሰብ ጀምሮ ሌሎች በአተገባበራቸውም ሆነ በእንድምታቸው ጠንክረው እያደጉ የሚሄዱ የትብብር መንፈግ እና የቦይኮት ስልቶችን ቀስ በቀስ በመለማመድ ሰላማዊ ትግላችንን እስከድል ደጃፎች እንቀጥላለን፡፡ ከአላህ ፈቃድ ጋር ይሳካልናል፤ ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለምና!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!
ze-habesha.com

Monday, March 23, 2015

የመከላከያ ሰራዊት አባላት በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ታዘዙ

-የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ሰሞኑን በሰሜን ጎንደር አካባቢ የታየውን የጸጥታ መደፍረስ ተከትሎ የአገሪቱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ካለፈው ሃሙስ ቀን ጀምሮ በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ታዛዋል።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት የአየር ሃይል አባላት ካለፈው ሃሙስ ጀምሮ ከግቢ እንዳይወጡ ሲታዘዙ የተወሰኑት ደግሞ ከደብረዘይት እና ድሬዳዋ አየር ሃይል  ወደ መቀሌ አምርተዋል። ብዛት ያለው የእግረኛ ሰራዊትም ወደ ኤርትራና ሱዳን ድንበሮች አቅንቷል።
ወታደራዊ ልምምዶችና አዳዳስ ምልመላዎችም እየተካሄዱ መሆኑንም ምንጮች ገልጸዋል።
ማንነታቸው በውል ያልታወቀ የተቃዋሚ ሃይሎች ጎንደር ከተማ ውስጥ የሚሊሺያ አዛዥ የሆነውን ኮማንደር ተፈራን ገድለው  ካመለጡ በሁዋላ፣ እነሱን ለመያዝ መጋቢት 12 አርማጭ ልዩ ቦታው እንኮይ ተራራ ላይ በተደረገ ጦርነት ፣ ከተቃዋሚዎች በኩል ሻምበል ይርዳውና
አዲሱ የተባሉ  ሲገደሉ፣ ከመንግስት ታጣቂዎች በኩል ደግሞ  የልዩ ሃይል አባል የሆነው  እባበይ እንዲሁም አንድ ስሙ በውል ያልታወቀና ሁለት የሚሊሺያ አባላት ተገድለዋል። ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ጀምሮ እስከ ምሽት በቀጠለው የተኩስ ልውውጥ፣ አንድ ተማሪ በመንግስት
ሃይሎች ተገድሏል። የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ምሽት ላይ አካባቢውን ጥለው መውጣታቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የመንግስትን አስተያየት ለማካተት የተደረገው ጥረት አልተሳካም።

Thursday, March 19, 2015

136 መምህራን የሥራ ማቆም አድማ መቱ • ‹‹ከአሁን በኋላ ለመምህራን ማህበርና ለአልማ አንከፍልም!››

(ነገረ ኢትዮጵያ) በምስራቅ ጎጃም ዞን የደብረወርቅ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 136 መምህራን ዛሬ መጋቢት 10/2007 ዓ.ም የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገለፁ፡፡ መምህራን ላይ እየተፈፀመ ያለውን የአስተዳደር በደል ተከትሎ 92 መምህራን ‹‹እኛ በደል እየደረሰብን ቢሆን መምህራን ማህበር ችግራችን እየፈታልን ባለመሆኑ ከአሁን በኋላ አባል እንዳልሆንን እንዲታወቅ፣ በየወሩ ከደመወዛችን እንዳይቆረጥብን›› በሚል ፊርማ አስገብተዋል፡፡ ከመምህራን ማህበር በተጨማሪ በየወሩ ከደመወዛቸው ለአልማ የሚቆረጠው ገንዘብም እንዲቆም መምህራኑ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
news
ባለፉት የመምህራን ስልጠናዎች የምስራቅ ጎጃም መምህራን ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራበት ማሳሰቢያ ተሰጥቶ እንደነበር የገለጹት መምህራኑ በተለይ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ የሆነው አቶ ዘላለም ጌታነህ የወረዳው መምህራን ማህበር ፀኃፊ ከሆኑ በኋላ ጫናዎች እንደበዙባቸው ገልጸዋል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና መምህራን ማህበር ፅ/ቤት የሚሰራው አቶ ዘላለም ዕጩ መሆኑ ከታወቀ በኋላ መምህራኑ አራት ጊዜ እንዲፈርሙ የተጠየቁ ሲሆን ይህም አቶ ዘላለም ለመምህራን ማህበሩ እያደረገ ባለው አስተዋጽኦና በፖለቲካ አቋሙ ምክንያት እየተፈፀመ ያለ በደል ነው ብለዋል፡፡
የመምህራኑን ፊርማ ተከትሎም መጋቢት 9/2007 ዓ.ም የወረዳው ምክር ቤት 18 ያህል መምህራንን ብቻ ጠርቶ ‹‹እንወያይ›› ባለበት ወቅት መምህራኑ ‹‹ካወያያችሁ ሁላችንም አወያዩን እንጅ እኛን ብቻ ነጥላችሁ ልታወያዩን አይገባም፡፡›› በማለታቸው ምክር ቤቱና መምህራኑ ሳይግባቡ ተለያይተዋል፡፡ መምህራኑ በትናንትናው ዕለት ስራ ገበታቸው ላይ እያሉ ተጠርተው ‹‹እንወያይ›› ቢባሉም በዝምታ ተቃውሟቸውን በመግለፃቸው የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ በለጠ ገሰሰ ‹‹አንወያይም ብላችሁ አምጻችኋል፡፡ ስለዚህ ነገ ስራ እንዳትገቡ፡፡ ስራ ገብታችሁ ትምህርት ቤቱ ውስጥ የሰው ነፍስ ቢጠፋ ተጠያቂዎቹ እናንተ ናችሁ፡፡›› በሚል እንደዛቱባቸው መምህራኑ ገልጸዋል፡፡ የወረዳው የትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅረአዲስ ሙሉሰው በበኩላቸው ‹‹ለአንድ ቀን ብቻ ሳይሆን ለአንድ ወርም መግባት የለባቸውም›› በሚል መምህራኑ ላይ ቅጣት እንዲወሰን መጠየቃቸው ተገልጾአል፡፡
መምህራኑም ለምክር ቤቱ ‹‹በቃል የነገራችሁንን ውሳኔ በጽሁፍ ስጡን›› የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም ውሳኔው በጸሁፍ ሊሰጣቸው እንዳልቻለና የወረዳውን ባለስልጣናት ውሳኔ የሰሙት 136 መምህራን ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ የስራ ማቆም አድማው ዛሬ ጠዋት ከተጀመረ በኋላ ተማሪዎች 3፡20 ላይ ክፍል ጥለው በመውጣት መምህራኑን መደገፋቸው ተገልጾአል፡፡
ደብረወርቅ የሰማያዊ ፓር ሊቀመንበር የኢ/ር ይልቃል ጌትነት የትውልድ ቦታ መሆኑን ተከትሎ የብአዴን ካድሬዎች በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ እንደሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

Wednesday, March 18, 2015

በሚስጢር የተያዘው የአባይ ግድብ ስምምነት ሊፈረም ነው

ግብጽ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ በሚስጢር ሲያደርጉት የቆዩት ድርድር ከተጠናቀቀ በሁዋላ፣ የሶስቱ አገር መሪዎች በተገኙበት በካርቱም እንደሚፈረም መረጃዎች አመልክተዋል።
የፊርማ ስነስርአቱ የፊታችን ሰኞ በካርቱም የሚካሄድ ሲሆን፣ ዝርዝር ይዘቱ ለህዝብ ይፋ እንዳይሆን ተደርጓል። የአባይ ግድብ  ከህዝብ በውዴታና በግዴታ በሚዋጣ ገንዘብ እየተገነባ መሆኑ እየታወቀ፣ ስምምነቱን ገንዘቡን ለሚያዋጣው ህዝብ ይፋ ለማድረግ ለምን እንዳልተፈለገ ግልጽ አይደለም።
ሱዳንና ግብጽ ስምምነቱ የግብጽን ፍላጎት ያረካ ነው በማለት አስተያየት በመስጠት ላይ ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ግን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አማካኝነት ” አዲስ ምእራፍ” የከፈተ ከማለት ውጭ ለኢትዮጵያ ስለሚያስገኘው ጥቅም ምንም ያለው ነገር የለም።
ኢሳት ዜና

Thursday, March 12, 2015

በህወሓት ላይ የሚቀርቡ ተቃውሞዎች ሁሉ ወደ እምቢተኝነት ይደጉ!


pg7-logoየኢትዮጵያ ሕዝብ በአለፉት 23 ዓመታት በህወሓት ዘረኛ አገዛዝ የደረሰበት ስቃይ እንዲቀንስ፤ ገዢዎቹ ከጫንቃው እንዲወዱ፤ ህወሓትን አውርዶ የሚፈልጋቸው መሪዎችን በነፃነት እንዲመርጥ ሲጠይቅና አቤቱታ ሲያሰማ ቆይቷል። በ1997 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕዝብ ምኞት የሚሳካ መስሎ የታየ የነበረ ቢሆንም በአገዛዙ አረመኔዓዊ እርምጃ ተሰናክሏል። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ “ድምፃችን ይሰማ” የሚሉ አቤታዎች ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መምጣት ጀምሯል – “ድምፃችን ይሰማ ሙስሊሞች”፣ “ድምፃችን ይሰማ ኦርቶዶክሶች”፣ “ድምፃችን ይሰማ መምህራን”፣ “ድምፃችን ይሰማ ተማሪዎች”፣ … ወዘተ። በተለይ ሙስሊም ወገኖቻችን በተደራጀ መንገድ “ድምፃችን ይሰማ” እያሉ ሲወተውቱ ሦስት ተከታታይ ዓመታት አልፈዋል። ወገኖቻችን “ድምፃችን ይሰማ” በማለታቸው ተደብድበዋል፣ ታስረዋል፣ ተገድለዋል።
አቤቱታ የሚሰማ ጆሮ የሌለው አገዛዝ ሲገጥም ምን ይደረጋል? ለአቤቱታ አቅራቢው ያለው ምርጫ ከሁለት አንድ ነው። ወይ አቤቱታን እርግፍ አድርጎ ጥሎ በደልን ተቀብሎ “እህህ !” እያሉ መኖር፤ አሊያም “በቃኝ፣ እንቢ አልገዛም” ማለት፤ ሦስተኛ ምርጫ የለም።
አቤቱታ ሰሚ ሲያጣ እና ሕዝብ መሮት “እንቢኝ፣ አልገዛም” ሲል ነው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ተቀሰቀሰ የሚባለው። ሕዝባዊ እምቢተኝነት ብዙ መልኮችና ቅርጾች ቢኖሩትም ዋነኛዎቹ መገለጫዎች ሁለት ናቸው። አገዛዙ ሕዝብ እንዲያደርግ የሚፈልገውን አለማድረግ እና/ወይም አገዛዙ ሕዝብ እንዲያደርግ የማይፈልገውን ማድረግ።
ለምሳሌ፣ አገዛዙ ሹማምንቱ እንዲከበሩ፣ ሕዝብ እንዲታዘዝላቸው ይፈልጋል፤ እንቢ ያለ ሕዝብ ግን የአገዛዙን ሹማምንት ይንቃል፣ በየደረሱት ያዋርዳቸዋል፣ “አልታዘዛችሁም” ይላቸዋል። ማንኛውም መንግስት የዳኝነት ሥርዓቱ እንዲከበርለት ይፈልጋል፤ በደል የመረረው ሕዝብ ግን የአምባገነኖች ችሎት ውሳኔ አይቀበልም፤ ዳኞችንም ዳኝነትንም አያከብርም። ሕዝብ የመንግሥትን ግብር በወቅቱ እንዲከፍል የማንኛውም መንግሥት ፍላጎት ነው። በመንግሥት ያመረረ ሕዝብ ግን ግብር አይከፍልም፤ መክፈል ግድ ከሆነበትም አዘግይቶ፣ አስለፍቶ ነው። የመረረው ሕዝብ ምሬቱን መፃፍ በሌለበት ቦታ ይጽፋል። በደል የበዛበት ሕዝብ “ዝም በል” ሲሉት ይናገራል፤ “ተናገር” ሲሉት ዝም ይላል።
አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝባዊ እምቢተኝተኝነት እርምጃዎች ጅምሮች እየታዩ ነው። በአማራ ክልል፣ ሕዝብ በሹማምንት ላይ የራሱን እርምጃ መውሰድ ጀምሯል። ሕዝብ ራሱ የፓሊስንም የፍርድ ቤትንም ሥራ ተክቶ እየሠራ ነው። ይህ መበረታታት ያለበት ትልቅ እርምጃ ነው። እንደዚሁም ሁሉ በተለይ ወጣቶች ብሶቶቻቸውን በብር ኖቶች ላይ ጽፈው ገበያው እንዲያዘዋውራቸው እያደረጉ ነው። ይህም “የወረቀት ገንዘብን ለተሠራበት ዓላማ ብቻ ተጠቀሙ” የሚለውን ህግ በመጣስ ለቅስቀሳ ሥራ መጠቀም በመሆኑ የሕዝባዊ እምቢተኝነት አካል ነው። በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ በርካታ የወረቀት ገንዘቦች በምሬት መግለጫነት ይውላሉ ተብሎ ይገመታል።
በተጓዳኝ በርካታ አማራጭ ስልቶች ሥራ ላይ መዋል ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ፣ ተቀማጭ ገንዘብን ከህወሓት ባንኮች ማውጣት በቀላሉ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ስልት ነው። በውጋጋን ባንክ ተጀምሮ ወደ አንበሳ ኢንተርናሽናል ከዚያም ወደ ንግድ ባንክ ማሸጋገር ይቻላል።
በወገኖቻችን ላይ የግፍ ፍርድ የሚያስፈርዱ አቃቢያነ ህግ እና የግፍ ብይኖችን የሚሰጡ ዳኞች በቸልታ ሊታለፉ አይገባም። በእስር ቤቶችም በወገኖቻችን ላይ ሰቆቃ እየፈፀሙ ያሉ ጨካኞች ከሰላማዊ ሕዝብ ጋር ተደባልቀው ሰላማዊ ሕይወት እንዲመሩ ሊፈቀድላቸው አይገባም። እነዚህ ሁሉ ሊወገዙ፣ ሊገለሉ፣ በየደረሱበት ሊዋረዱ ይገባል።
በአገዛዙ መንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችን በሥራቸው ላይ መለገም ተቀባይነት ያለው በጎ ተግባር እንደሆነ ሰፊ ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባል። ከአምባገነን ሥርዓት ጋር መተባበር እኩይ ተግባር ሲሆን አምባገነን ሥርዓትን ከውስጥ መቦርቦር ደግሞ የሚበረታታ ሰናይ ሥራ ነው።
ለወያኔ አገዛዝ ግብር መክፈል የምናቆምበት ሰዓትም ተቃርቧል። በራሳችን ገንዘብ ገዳዮቻችን እንዲሰለጥኑብን መፍቀድ የለብንም። ስለሆነም “ግብር አንከፍልም”፤ “መዋጮዎቻችሁ አይመለከቱንም” የምንልበት ቀን ቀርቧል።
በፋይዳ የለሽ ምርጫ የሀገር ሀብት ሲመዘበር ማየት አንሻም። በአግባቡ ለማይቆጠር ድምፃችን አንድም ደቂቃ የምናባክንበት ምክንያት የለምና ሁላችንም የምርጫ ካርዶቻችንን ቀዳደን ቁርጭራጮቹን በየመንገዱ ልንበትናቸው ይገባል።
እነዚህን እነዚህን የመሳሰሉ ናቸው የሕዝባዊ እምቢተኝነት የመጀመሪያ ደረጃዎች። እነዚህን እያደረግን በምስጢር መደራጀታችንን እንቀጥል። ከጥቂት በኋላ አምባገነኑን ሥርዓት የሚያንበረክክ ኃይል እንፈጥራለን። ጥቃት ቢደርስ የሚመክት ኃይል የተደራጀ በመሆኑም ሕዝባዊ እምቢተኝነትና ሕዝባዊ አመጽ ተቀናጅተው እንዲሄዱ ይደረጋል።
አርበኞች ግንቦት 7:የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ሕዝባዊ እምቢተኝነትንና ሕዝባዊ አመጽን አቀናጅቶ ለመምራት የተዘጋጀ፤ ለዚህ የሚያበቃው ድርጅታዊ አቅም እየገነባ ያለ ድርጅት ነው። አርበኞች ግንቦት 7 “እንሰባሰብ በወያኔ ላይ የምናቀርባቸው ተቃውሞዎች በሙሉ ወደ እምቢተኝነት ከፍ እናድርጋቸው” ይላል።


    ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

    Wednesday, March 11, 2015

    የወያኔ ጥላቻ ፍሬ (ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)

    ወያኔ ለትግራይ ሕዝብ ሀብትንና ብልጽግናን አመጣ ብለው የሚያምኑ ሰዎች ብዙ ናቸው፤ ወያኔ የሥልጣን ወንበሩ ላይ በመውጣቱ ትግሬዎች ሁሉ አልፎላቸዋል ተብሎ ይታመናል፤ በተለይ በአውሮፓና በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዚህ ላይ የጠነከረ እምነት አላቸው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ውጭ ብዙ ውይይትም ይሁን ንትርክ ይደረጋል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ግን የተፈራ ርእስ ነው፤ ውስጥ-ውስጡን እንጂ አደባባይ አይወጣም፤ ይህንን ጉዳይ በኢትዮጵያ ውስጥ አደባባይ ለማውጣት ጊዜው የደረሰ ይመስለኛል፤ አረጋዊ በርሄ፣ ገብረ መድኅን አርአያ፣ አስገደ ገብረ ሥላሴ፣ አብርሃ ደስታ (አሥር ቢሞሉልኝ ደስ ይለኝ ነበር!) እየደጋገሙ ቢያነሡትም ሌሎች በቁም-ነገር የተቀበሉት አይመስልም፤ ሕዝቡ ግን በራሱ መንገድ እየተናገረና ምስክርነቱን እየሰጠ ነው፤ በመቀሌ የተሠራውን የመኳንንት መንደር ሕዝቡ አፓርቴይድ ብሎ ሲሰይመው፣ በአዲስ አበባ የተሠራውን መንደር መቀሌ ብሎ ሲሰይመው እየመሰከረ ነው፤‹‹የለሁበትም!›› እያለ ነው።Prof. Mesfin Woldemariam : is an Ethiopian Human Rights activist and philosopher
    የትግራይ ሕዝብ መደህየቱ አልበቃ ብሎት ሲለምንም እየተሳቀቀ ነው፤ የሚለምነው ትግሬ ለብዙ ሰዎች ትግሬና ወያኔ አንድ መስሎ እንደሚታየው ያውቃል፤ አብዛኛው ሰው በወያኔ ላይ ያለውን ስሜት ያውቃል፤ ስለዚህም ሲለምን ሰዎች በወያኔ ላይ ያላቸውን ስሜት ስለሚያራግፉበት እየተሸማቀቀ ነው፤ አንድ የትግራይ ቄስ ከአርሲ ነኝ አሉኝና ለምን እውነቱን አይናገሩም ስላቸው እውነቱን ስናገር የማገኘው ስድብ ብቻ ነው አሉኝ፤ እኒህ ሰው ምን በወጣቸው የወያኔን ኃጢአት ተሸካሚ ይሆናሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በትግሬነቱ የተጠቀመ አለ፤ እኔ የማውቀው የደርግ ወታደር የነበረ ትግሬ ቆስሎ ከውትድርና ወጣና በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የጥበቃ ሥራ ላይ ነበር፤ በጣም ይቸግረው ነበር፤ ሚስቱ ሕመምተኛ ነበረች፤ የቤት ኪራይ መክፈል ይቸገር ነበር፤ ዛሬ ግን የሚለብሰው ልብስ ሌላ ነው፤ ከኑሮውም ተርፎ ለሲጃራና ለጫት እያወጣ ነው፤ ወይም ሌሎች እያወጡለት ነው፤ ትግሬነታቸው ብቻ እንዲህ የደላቸው በጣም፣ በጣም ጥቂቶች ናቸው፤ ስለዚህም በወያኔ አገዛዝ ትግሬ ሁሉ ተጠቅሞአል ማለት ከጉልሁ እውነት ጋር የሚጋጭ ስሕተት ነው፤ አብርሃ ሰዎች ትግሬ ሁሉ ተጠቃሚ ሆኗል ሲሉ ‹‹ያመኛል›› ማለቱ ይገባኛል።
    ወያኔ ትግሬ በመሆኑ ብቻ ትግሬ ሁሉ ዕዳ አለበት ማለት እንደወያኔ ማሰብ ነው፤ ወንጀል በዘር አይተላለፍም፤ እያንዳንዱ ሰው ለሠራው ሥራ ሁሉ ኃላፊነትን ይወስዳል፤ ጊዜው ሲደርስ ውጤቱንም ለመቀበል ይገደዳል፤ ይህ የሚሆነው ሰው ሁሉ በመንፈሳዊ ኃይል በጎ መንፈስ አድሮበት፣ አእምሮው በትምህርት ተገርቶ በትክክል ማሰብ ሲችል ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን በአለበት ሁኔታ በጎ መንፈስ የራቀው ይመስላል፤ አእምሮም ጭራሹኑ በእኩይ መንፈስና በጥላቻ እየዛገ ነው፤ ስለዚህ ያስፈራል፤ በደቡብ ሱዳን ሁለት መቶ ሰዎች በዘር ተለይተው ታረዱ ሲባል ያስፈራል፤ በናይጂርያ፣ በኮንጎ የሚካሄደውን የዘርና የሃይማኖት እልቂት ስንሰማ ያስፈራል፤ በ1997 ዓ.ም. መለስ ዜናዊና አዲሱ ለገሰ እንዳስታወሱን የሩዋንዳ የጎሣ እልቂት በብዙ ሰዎች አእምሮ ውስጥ አለ፤ የቅርብ ተኳሽ የሆነው የአግዓዚ ጦርም አድፍጦ መጠበቅ ያስፈራል፤ ሌላውም ይህንን አውቆ አድፍጦ መጠበቁ ያስፈራል፤ ሰማይ ጠቀስ የሠሩት፣ የሥልጣን ኃላፊነትን ችላ ብለው በሥልጣን የሚነግዱና የሚከብሩት፣ የማይኖሩበትን ሕንጻ የሚክቡት፣ ከሕዝብ ጋር ያላቸው የአይጥና የድመት ኑሮ ያስፈራል፤ አቶ አስገደ ወያኔ መደንገጡን ይነግረናል፤ መደንገጥ የማይቆጣጠሩት ፍርሃት ነውና አደጋ ያመጣል፤ አደጋው አደጋን ይጠራል፤ ይህም ያስፈራል።
    በትግራይ ዙሪያ ያለው ምንድን ነው? የትግራይ ሕዝብ በየትኛው አቅጣጫ ነው አንደልቡ እየተዘዋወረ ለመሥራትና ለመኖር የሚችለው? ወያኔ የትግራይን ሕዝብ ከሰሜን ከወገኑ ከኤርትራ ሕዝብ ጋር ደም አቃብቶታል፤ በደቡብ-ምሥራቅ ከወሎ መሬት ቆርሶ የወሎን ሕዝብ ቂም አስቋጥሯል፤ በደቡብ-ምዕራብ ከጎንደር መሬት ቆርሶ የጎንደርን ሕዝብ ቂም አስቋጥሯል፤ የራስን ወገኖች አስቀይሞ ሱዳንን በመሬት ለመደለል የሚደረገው ጥረት ሁሉ ፋይዳ የለውም፤ ሱዳን ለራሱም ያልበጀ አገር መሆኑ እየታየ ነው፤ ወደፊት ደግሞ ይበልጥ ይታያል፤ በትግራይ ውስጥ ደግሞ ወያኔ የፈጠረው አፓርቴይድ የወያኔን የኑሮ ደረጃ ወደሰማይ ሲያስጠጋው፣ የቀረውን ወደአንጦርጦስ የደሀነት ገደል ውስጥ ከቶታል፤ በዚህም ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ ከነልጆቻቸው እየተዘዋወሩ የሚለምኑ ሞልተዋል፤ ይህ ልመናም ለወያኔ ለመገበር ነው፤ ብዙዎቹ እንደሚናገሩት የሚለምኑት የማዳበሪያ ዕዳቸውን ለወያኔ ለመክፈል ነው።
    ወያኔ ከሀያ ዓመታት በላይ አፍንጫ እየያዘ ያስከፈለውን የሚመልስበት ጊዜ እየተቃረበ ነው፤ ጥያቄው ወያኔ እንዲመልስ የሚገደደው እንዴት ነው? የሚል ነው፤ጥላቻ ወደንዴት፣ ንዴት ወደቁጣ ተለውጦ ሲገነፍል ምጽዓት ደረሰ ማለት ነው፤ ሁሉም ሰው ራቁቱን ይሆናል፤ አንደአውሬ ከጥፍሩና ከጥርሱ በቀር ሌላ መሣሪያ አይኖረውም፤ ሰው ሁሉ በክፋት ወደአውሬነት ይለወጣል፤ ጠመንጃና ቦምብ አያገለግሉም፤ ሕንጻው ምሽግ አይሆንም፤ መኪናው፣ ባቡሩ፣ ታንኩ ከቆመበት አይነቃነቅም፤ የትም አያደርስም፤ ጭፍራ ሁሉ በየራሱ ፍዳ ታንቆ እንኳን ለሌላ ሊተርፍ ለራሱም የማይበቃ ይሆናል፤ ለነገሩ ጌታና ሎሌም የለም፤ ሁሉም በአውሬ እኩልነት የተፋጠጠ ነው፤ ርኅራኄ ተሟጦ፣ መግል ያዘለ ልብ ፈርጦ፣ ውይይትና ክርክር አብቅቶ፣ ጥርሱን ያገጠጠና ጥፍሩን የሳለ መንጋ በደም የሚራጭበት ሁኔታ ነው።
    ሌላ አገር እንዲህ አልሆነም፤ እዚያ አገር እንዲህ አልሆነም፤ የሚባል ነገር የለም፤ እኛ ዘንድ ሌላ ነው፤ የኢትዮጵያ ደሀዎች እንባ የእግዚአብሔርን ሰማይ አጨቀየው!
    ክፋት እንደ እሳት ይቃጠላል፤ ኵርንችቱንና እሾሁን ይበላል፤ ጭፍቅየሆነውንም ዱር ያቃጥላል፤ ጢሱም ተትጐልጕሎ እንደ ዓምድ ይወጣል፤በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ቁጣም ድር ተቃጥላለች፤ ሕዝቡም እሳትእንደሚበላው እንጨት ሆኖአል፤ ሰውም ለወንድሙ አይራራም፤ ሰው በቀኙ በኩልይነቅላል፤ ይራብማል፤ በግራም በኩል ይበላል፤ አይጠግብምም፤ እያንዳንዱምየ ክንዱን ሥጋ ይበላል፤ ምናሴ ኤፍሬምን፣ ኤፍሬምም ምናሴን ይበላል፤ …ኢሳይያስ 9/18-21
    ትንቢተ ኢሳይያስ ለሩዋንዳውያን ብቻ አይደለም፤ ጥላቻና ክፋት በተዘራበት ቦታ ሁሉ ውጤቱ ጥፋት ነው፤ ምናሴ ኤፍሬምን በልቶ አይቀርም፤ ኤፍሬምም ምናሴን ይበላዋል።

    Wednesday, March 4, 2015

    ምርጫ ለኢትዮጵያ ወታደርና ፓሊስ: – ለህወሓት ባርነት ወይስ ለኢትዮጵያ ነፃነት

    የኢትዮጵያ ሕዝብ ለውትድርና ከፍተኛ ክብር አለው። ውትድርና ከሙያና ሥራ በላይ የነፃነትና የክብር መገለጫ፤ ሀገርን ከባዕድ ወረራ መከላከያ ጋሻ ነው ብሎ ያምናል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ህግና ሥርዓት አክባሪ በመሆኑ ለፓሊስም ከፍተኛ አክብሮት አለው። የፓሊስ ሥራ ወንጀልን መከላከልና ወንጀለኞችን ወደ ፍርድ ማቅረብ መሆኑ በኢትዮጵያ ባህል የተከበረ ቦታና እውቅና አለው።
    በህወሓት የአገዛዝ ዘመን ግን ይህ እየተቀየረ ነው። የህወሓት አዛዦች እየመሩት ያለው የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ሀገርን ከባዕድ ጠላት ከመከላከል ጋር ምንም ዝምድና በሌላቸው ሁለት አበይት ተግባራት ላይ ተጠምዷል። በህወሓት አዛዦች የሚመራው ሠራዊት ዋነኛ ተግባር ለሰብዓዊ መብቶቻቸው መከበር እና ለፍትህ መስፈን የሚታገሉ ዜጎችን ማጥቃት ሆኗል። የጦሩ ሁለተኛው አቢይ ተግባር ደግሞ ለአዛዦች የግል ጥቅም ማካበቻ ገቢዎችን በሚያስገኙ ሥራ ላይ መሠማራት ነው።
    የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ኢትዮጵያዊያንን ማጥቂያ ሠራዊት መሆኑ ሲቪሉን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የሠራዊቱንም አባላትን ጭምር ለህሊና ወቀሳ የዳረገ ጉዳይ ነው። ሆኖም ግን ይህ በህሊና ወቀሳ ብቻ ሊታለፍ የማይችል ወንጀል ነው። ሠራዊቱ በህወሓት እየታዘዘ የሚዘምተው በገዛ ራሱ ልጆች፣ እህቶች፣ ወንድሞችና ወላጆች፤ በገዛ ራሱ ጥቅሞች እና በገዛ ራሱ ላይ መሆኑ መገንዘብ ይኖርበታል። በገዛ ራሱ ጥቅሞች ላይ የሚዘምት አንድም ህሊና የሌለው አሊያም ነፃነት የተነፈገው ሰው ብቻ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሠራዊቱ እየተራበና እየታረዘ አለቆቹ የታላላቅ ህንፃዎች ባለቤቶች፣ ባለፋብሪካዎች፣ የባንክና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ባለአክሲኖች የሚሆኑበት ሥርዓት ከዳር ሆኖ የሚመለከት መሆኑ የሚገርም ነው። ሠራዊቱ ቤተሰቦቹን መመገብ አቅቶት እያለ የአዛዦቹ ልጆች ለሽርሽር ዓለምን ይዞራሉ። እንዴት ነው ሠራዊቱ እየደኸየና እየሞተ አዛዦቹ እየከበሩ የሚሄዱት? ይህ አዋራጅ ሁኔታ እንዲያበቃ መታገል የሠራዊቱ ግንባር ቀደም ኃላፊነት ነው። ሠራዊቱ ወይ ባርነትን አሜን ብሎ መቀበል አለበት አለበዚያም እሱም እንደነሱ ሰው መሆኑን ማሳየት መቻል አለበት። በኢትዮጵያ ውስጥ የህወሓት አገዛዝ ወድቆ የሕዝብ ይሁንታ ያገኘ መንግሥት መመሥረቱ በከፍተኛ ሁኔታ ከሚጠቅማቸው የኅብረተብ ክፍሎች ግንባር ቀደሙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ናቸው። በዚህም ምክንያት የሠራዊቱ አባላት ለሥርዓቱ መውደቅ በግልጽም በስውርም መታገል የዜግነት ብቻ ሳይሆን አዕምሮ ያለው ሰው ሆነው በመፈጠራቸው የተቀበሉት ግዴታ ነው።
    ፓሊስን በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ህወሓት የኢትዮጵያን ሕዝብ አፍኖ ለመግዛት የቻለው በዋኛነት የፓሊስን ኃይል ለአፈናው ተግባር የሚጠቀም በመሆኑ ነው። የተቃውሞ ድምጾች በተሰሙ ቁጥር የኢትዮጵያ ፓሊስ በወገኖቹ ላይ የሚያወርደው ዱላ የሚዘገንን ሆኗል። ሰላማዊ ሰልፈኞችን በጥይት መግደልና ማቁሰል፤ አረጋዊያንን፣ ሴቶችንና ሕፃናትን መግደል፣ ማቁሰል፣ መደብደብ በዚህ ተግባር የተሠማሩ ፓሊሶችን በቡድንም በግልም በህግ የሚያስጠይቅ ከባድ ወንጀል ነው። በህወሃት እየተመራ ያለው የኢትዮጵያ ፓሊስ ተግባራት ተበዳዮችን ብቻ ሳይሆን ራሱ ፓሊስንም ጭምር አንገት የሚያስደፋ ተግባር ነው። ለመሆኑ አንድ ተራ የኢትዮጵያ ፓሊስ ባልደረባ ከህወሓት አገዛዝ ምን ተጠቀመ? መልሱ “ምንም” የሚል ነው። ይልቁንስ በህወሓት የአገዛዝ ዘመን ፓሊስ የተናቀና የተዋረደ ሥራ ሆነ። በህወሓት አገዛዝ ፓሊስ እንደሰለጠነ አዳኝ ውሻ “ያዝ” ሲሉት የሚነክስ፣ የሚያደማ፣ የሚቦጭቅ ሆኗል። ይህ ለፓሊስ፣ ወንጀልም ውርደትም ነው። በህወሓት አገዛዝ መገርሰስ እና በምትኩ የህግ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት መስፈን ፓሊስ ከሁሉ በላይ ተጠቃሚ ነው፤ ሰብዓዊ ክብሩን ያረጋግጥለታልና።
    ዛሬ በኢትዮጵያችን ውስጥ የታዘዙትን የሚፈጽሙ የጦርና የፓሊስ ሠራዊት አባላት ስላሉ ነው የህወሓት ሹማምንት ልባቸው ያበጠው። ለማስረጃ ያህል ሰሞኑን የህወሓቱ ሹም አባይ ፀሐዬ የአዲስ አበባ ዙሪያ ገበሬዎች በግዴታ መነሳታቸው የሚቃወሙትን ዜጎችን ሁሉ ”ልክ እናስገባቸዋለን” ብሎ በሸንጎ የዛተው የታዘዘውን የሚፈጽም የጦርና የፓሊስ ሠራዊት መኖሩን ተማምኖ ነው። እስከ መቼ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊትና ፓሊስ ሕዝብን ማስፈራሪያ መሣሪያ ይሆናል?
    አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ የኢትዮጵያ የመከላከያና የፓሊስ ሠራዊት አባላት ለራሳቸው እና ለወገናቸው የሚበጀው ሥርዓት የቱ እንደሆነ ያውቃሉ ብሎ ያምናል። በዚህም ምክንያት ስብዕናቸውን እያዋረደ እና እያደኸያቸው ያለውን የህወሓት አገዛዝን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመሆን ይፋለሙታል ብሎ ያምናል። ይህ ውሳኔ ግን ሠራዊቱ በጅምላ ሳይሆን እያንዳንዱ የሠራዊቱ አባል በግሉ የሚወስደው ውሳኔ እንደሆነ አርበኞች ግንቦት 7 ይገነዘባል።
    በዚህም መሠረት ተደጋጋሚ ጥሪ እየተደረገለት፤ ጥሪውንም እየሰማ ከህወሓት ጋር ወግኖ ሕዝብን መውጋት የቀጠለ የሠራዊቱ አባል ላደረሰው ጥፋት በግል መጠየቁ የማይቀር መሆኑ ሊገነዘብ ይገባል። በእያንዳንዳንዱ የጦርና ፓሊስ ሠራዊት ባልደረባ ፊት የቀረበው ምርጫ “ለህወሓት ባርነት ታድራለህ ወይስ ራስህንና ሀገርን ነፃ ታወጣለህ” የሚል ነው።
    ራስህንና ሀገርህን ነፃ ለማውጣት የመረጥክ የሠራዊቱና የፓሊስ ባልደረባ አሁኑኑ ሕዝባዊ ትግሉን ተቀላቀል። እስከዛሬ የበደልከውን ሕዝብ ለመካስ ምቹ ሁኔታ አለህ። በግልጽ የነፃነት ኃይሎችን እንድትቀላቀል፤ አሊያም አለህበት ሆነህ በውስጥ አርበኝነት እንድትደራጅና ተግባራዊ ሥራ እንድትጀምር መንገዱ ተመቻችቶልሃል።
    ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!