Thursday, February 18, 2016

ቻርል ዳርዊንና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ


Darwin-and-land-to-the-tiller
ቻርል ዳርዊንና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ
ቢላል አበጋዝ
ዋሽግቶን ዲ ሲ፣ሐሙስ ፣ ፌብሩወሪ 18 ቀን 2016
የታላቁ ሳይቲስት የቻርል ዳርዊን 207ተኛው ልደቱ በዚህ ወር ተከብሯል። እሱ ካልው አንዱ ነገር
“ከዝርያዎች መካከል ጠንካራው አይደለም ኗሪነቱ ቀጣይነት ያለው(እማይመክነው:እማይጠፋው)። እጅግ ብልሁም አይደለም። ለለውጥ ዝግጁ የሆነው እንጂ”
ቻርልስ ዳርዊን 1809
መግቢያ
ቻርል ዳርዊን የሳይንስ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካም ሰውም የነበረ ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ መረጃ ተሰብስቦ ቀርቦለት ምን ታስባለህ ቢባል በኦሮሞ ክፍለ አገር እየሆነ ያለው ዓመጽ የኢትዮጵያ ህዝቦችሁሉ የሚያደርጉት አገር አቀፍ ዴሞክራሲያዊ ትግል አካል ነው። ይህ እንዴት ይህ ተሰወራችሁ? ብሎን ይታዘበን ነበር እላለሁ። የሰውን ልጅ አስተሳሰብ፤ሳይንስን እንዳለ ቀየረው የሚባለውን መላምቱን ለመቅረጽ ዳርዊን የፈጀበት ጊዜ እኛ ወያኔን ስናስታምም የፈጀነውን ዘመን ያንሳል።
ለውጥ ሲመጣ እያየነው ለውጡን ወያኔ ሲያውገረግረው እኛ ግን አስተሳሰባችንንና መንገዳችንን መቀየር ካቃተን ለውጡን ወያኔ እንዲጠቀምበት አደረግን ማለት ነው።በዚህ እራሳችንንም አገራችን ኢትዮጵያንም እንበድላለን ማለት ነው። አዲስ ሁኔታ ሲከሰት ወዲያው ሁኔታውን አገናዝበን አስተሳሰባችንንም ቀይረን ዛሬ የሚጠይቀውን አቅጣጫ መቀየርን፤ማረምን፤ዝግጅትን ማድረግ እስካልቻልን ወያኔን መርታት ዳገት መሆኑ ግልጥ ነው።ጥንካሬም ብልሃትም እያለን እንዴት ወያኔ ሰነበተን? ካልጠየቅን ወያኔ አፍዝ አደንግዝ እንዳስደገመብን ያለ ነው። በኦሮሞ ክፍለ አገር እየሆነ ያለው ዓመጽ ልድገመው የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ የሚያደርጉት አገር አቀፍ ዴሞክራሲያዊ ትግል አካል ነው።
ትንታኔ
በዚህ ጽሁፍ የቻርል ዳርዊንን የአራዊትና እጽዋትን ዝርያ አመጣጥና ዝምድና ገላጭ መላምቱን የማቅረብ ዓላማ የለኝም።ከላይ የጠቀስኩት የዳርዊን አባባል የሚለግሰንን ብልሃት ለዲሞክራሲያዊ ትግላችንም ምን ይዘይድበታል ለማለት ብቻ ነው።
በወጣትነት ዘመኑ ቻርል ዳርዊን ለአምስት ዓመታት በመርከብ ዓለምን ዞሮ የጽዋትና የእንስሳትን መረጃና ናሙናም ሰብስቦ ለሃያ ዓመታት ከተመራመረ በኋላ ዝርያዎች በቀጣይነት ዘራቸው የማይጠፋው [survival] ተፈጥሮ ራሱ በደነገገው መሰረት የገጠማቸውን ነባራዊ ለውጥ ለመቀበል የተመቻቹትን ብቻ የሚመርጥ ስርዓት ስላለ መሆኑን በገናናው መላምቱ ሲያስረዳ፤ ለውጥ ለመቀበል ያቃታቸው፤መራባትም ያልሆነላቸው ዘራቸው መክሰሙንም በመላመቱ አካቶታል።
ህወሃት መሩ መንግስት ልክ እንደወታደራዊ ደርግ አዋጅ፤ህገ መንግስት፤ብሄር ገለመሌ እያለ ቀስ ብሎ ስልጣን ላይ ጉብ ሲል፤ፊቱ ለሚደቀኑ የነበሩ ተለዋጭ ሁኔታዎች መልስ እያዘጃጀ እራሱንም ለለውጥ እያመቻቸ ነበር። ዛሬም ይህንኑ ያደርጋል። እስታሁንም ለውጥ ሲመጣ ቢደናገጥም ተንገዳግዶ ይቆማል።ለለውጥ ዝግጁ መሆንና፤ፊታችን የሚከሰተውን ለውጥ ማየት እየተሳነን ህወሃትን አቸናፊ እናደርገዋለን። ይህንን ቀጥዬ ላስረዳ።
ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ወያኔ ገና ከተማ ሳይገባ ማን ብርቱ ተቃውሞ እንደሚያደርግበት በመረዳት የኅይልም የፕሮፓጋንዳውንም በትር አማራው ብሄር ላይ ያሳርፍ ነበር።ህወሃት ጋር የተደለሉ ኦሮሞዎች ሎሎችም እየተባበሩ።ከአማራውም ከሌሎች ብሄሮችም ተጨምረው አድር ባዮችን በጥቅም አሰልፎ ሲያበቃ የራሱን በፖለቲካ ስልጣን መደርጀትን የዝምድና ሀረግ በማድረግ ሰንብቶበታል። ይህ ዛሬም ያለ ዝምድና ነው።ይህን ዝምድና ስር ነቀል ለውጥ ብቻ የሚሽረው ነውና ህወሃት እስታለ ደግሞ ይቀጥላል።ህወሃትን ዲሞክራሲያዊው ትግል በድል ሲሽረው ወያኔ ጋር አብሮ ታሪክና ትዝብት ይሆናል። ባጭሩ ወያኔ ዝግጅት አድርጎ ሲገባ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሀይሎች አልተዘጋጁም ነበር።ይሄው ሃያ አምስት ዓመታ እየተቆጠሩ ነው።
እንዳአሁኑ የወጣት ተማሪዎች እንቅስቃሴ የኦሮሞ ብሄረሰብ በብዛት በሚኖርባቸው የኢትዮጵያ ክፍላተ አገር እንደሚካሄደው በሌሎቹም ቦታዎች እየተነሱ ተራ በተራ መመታታቸውን አይተናል።ህወሃት አገር አቀፍ እንዳይባልበት እጅግ ሲጥር የመጣውን ለው የሁላችን የጋራ ነው ለማለት ተስኖን በመደናገር ራሱ ህወሃት ያለው ደግመን [ትቀብለን] አመጹን “የኦሮሞ”፤ “የአማራ” እናደርገዋለን።ባጭሩ ቻርልስ ዳርዊን እንደሚለው ሀይል ቢኖረንም ለውጡን ለመጠቀም ራሱን ያመቻቸው ህወሃት ሆኖ እናገኘዋለን።
በኦሮሞ ክፍለ አገር ዛሬ ተቀጣጥሎ እየነደደ ያለው ዓመጽ እንዴት ተከሰተ?የህዝባዊ ብሶቱ መነሻ ምንድን ነው?በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍላተ አገራት ከተነሱት ዓመጾች በምን ይመሳሰላል?እንዴት ሊራመድ ይችላል?ወያኔን ለማንበርከክ ምን ቀጥሎ ምን ይደረግ እንደማለት ህወሃት ለመጣው ለውጥ የሰጠውን ስያሜ ውጠን “የኦሮሞ ክልል” የዚያ ክልል የሚል ታርጋ እንለጥፍበታለን።ለህወሃትም የሌለውን ብላተኛነት አክለንለት ከናካቴው አመጹን ወያኔ በውስጥ እጅ ሆን ብሎ በራሱ ሰዎች እንዳስነሳው የምናስብም አለን። የተንኮል ቅንብር (Conspiracy Theory) ድረስ የምንሄድና ወጣቱ በደሙ የከፈለበትን መና ለማድረግና ህወሃትም ለመርታት አስቸጋራ መስሎ እንዲታይ ያለማስተዋል እንናገራለን።ህወሃት ጠንካራ አይደለም።ብልሃትም የለውም።የለት ተለትዋን ለማድረግ ግን ጮሌ ነው። እስታሁን በራሱ ላይ ህዝባዊ አመጽ ሆን ብሎ የሚዶልት አምባገነን ታይቶ የሚታወቅ አይመስለኝም።ህወሃት ግን የተፈጠረውን ሁኔታ ሊጠቀምበት የማያደርገው የለም ማለት ይቻላል።በግልጹ ለመናገር አማራው ኦሮሞውን፤ኦሮሞው አማራውን እንዲጠላውና እንዲጠራጠረው በመሆኑ የህወሃት ፍላጎት እደተመኘው የምንሆንለት እራሳችኑ ነን።ተመቸነው ልበል ወጣቶች እንደሚሉት ?ለውጥን ፈርተን መለወጥ አቅቶን እንዴት ወያኔን ለማሰናበት እንችላለን?
ነገ የአማራው ህዝብ በብዛት በሚኖርበት ክፍለ አገር አመጽ ቢቀጣጠል።የጋምቤላውና የአፋሩ እንደቀድሞው ቦግ ሲል የህወሃት መሩን መንግስት መግለጫ ተቀብለን የምናስተጋባ ከሆነ ብልሃትም ጉልበትም የኛ ቢሆንም ወያኔ የለመደውን ግዜያዊ ድል አግኝቶ ቀጠለ ማለት ነውና፤ ሲሆን ለውጥ ሳይመጣ ቀድመን እናስላ ካልሆነ ለውጡ፤አመጽ ሲከሰት ሌላ ስም ሳይሆን አገር አቀፍ ዴሞክራሲያዊ ትግል መሆኑን ኢትዮጵያ አገሬ የምንል ይህን ስያሜ እንጂ የወያኔን አናስተጋባ።ሌላ ምሳሌ ”ኢትዮጵያ ትፈራርሳለች” ሲል የወያኔ ተረት ተረት “ወያኔ ስንት ቦታ ተሰንጥቆ ይፈርሳል ?” ብለን ይህን ሂደት ለማፋጠን ምን ይደረግ እንበል።ዛሬ ኢትዮጵያ ለለውጥ ዝግጁ ናት የምሁራንዋ ዝግመት እንጂ !” ይህን እናስብበት::
የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚያደርጉት አገር አቀፍ ዴሞክራሲያዊ ትግል ያቸንፋል!
የፖለቲካ መሪዎች አሁኑኑ ይፈቱ!
የሃይማኖት መሪዎች አሁኑኑ ይፈቱ!
የታሰሩ ጋዜጠኞች አሁኑኑ ይፈቱ!
ለወጣቶች ግድያ ህወሃት እንጂ ማንም ተጠያቂ አይደለም !
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

Thursday, February 4, 2016

የሀገር አድን ጥሪ ለወጣቱ!(ከአርበኞች ግንቦት7 ወጣቶች መምርያ )

ማክሰኞ ፣2 ፌብሩወሪ 2016
12042873_868355303254893_5731700769108826326_nወጣቶች በሃገራችን ላይ የተጫነብን የወያኔ የመርገምት አገዛዝ ያጎሳቆለን፤ በኑሮ የተበደልንና በሰላም ለመኖር ያልታደልን ፍጡሮች ብንሆንም ህዝባችን ነጻነቱን ሲቀማ፣ መብቱ ሲደፈር፣ ክብሩ ሲዋረድ ከዳር ቁመን የምንመለከትበት አንዳች ምክንያት ሊኖረን አይገባም። ወቅቱ ለነፃነታችንና ለመብታችን ባላንጣ የሆነውን አምባገነን የወያኔን ስርዓት ፊት ለፊት ተጋፍጠን፣ በትግላችን ደቁስን ማንነታችንን የምናስመስክርበት ወቅት እንጂ በፍርሃትና በዝምታ ተውጠን ወደኋላ የምንልበት ስዓት አይደለም። ደግሞም እኛ ወጣቶች ለመብት እና ነፃነታችን ተፈጥሮ የለገሰችንን እምቅ ኃይልና ጉልበት ተጠቅመን በቁርጠኝነት ተነስተን ካልታገልን የሥርዓቱን አምባገነናዊ የጭቆና አገዛዝ በፍርሃትና በዝምታ እንደተቀበልን ተደርጎ መወስዱ የማይቀር ነው።
ከምንግዜውም በላይ እኛ ወጣቶችን ዛሬ ሁለት አበይት ጉዳዮች በጉልህ ያሳስቡናል፤ ሊያሳስቡንም ይገባል። እነዚህም ሃገራችን ያለችበት አሳሳቢ ሁኔታና የኛ የተተኪው ትውልድ የወደፊት ተስፋ ምን ሊሆን ይችላል? የሚሉት ናችው። በቀደመው ጊዜ በሃገራችን የተፈራረቁት አምባገነን ገዥዎች ለወጣቱ ተስፋና የተሻለ ነገር ከመስጠት ይልቅ በጠላትነት ፈርጀው በሽብር እየገደሉና ጥቃት እየፈጸሙበት ሲያሳድዱት ኖረዋል። የወጣቱ ሰቆቃ አሁን በወያኔ ዘመን ደግሞ እጅግ በጣም በከፋ ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሏል።
የወያኔ መሪዎች ለኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ማዕከላዊን፡ ቃሊቲን፤ ሽዋሮቢትን፣ ዝዋይን እና የመሳስሉ የሰቆቃ እስር ቤቶችን ሲያሰፉ እንጂ የሥልጠናና የምርምር ተቋም ሲያድሱና ሲገነቡ ለማየት አልታደልንም። የሚገነቡ የትምህርት ተቋማትም ለሥርዓቱ የእድሜ ማራዘሚያ እንጂ የእውቀት ማስጨበጫ ተቋም እንዳልሆኑ ተግባራቸውንና ውጤታቸውን መመልከት ይቻላል። በአደባባይ ያለፍትህ የሚገደለው ወጣት ባንክ ሲዘርፍ ተገኘ፣ ወንጀል ሲሰራ ተያዘ የሚሉ የሀሰት ምክንያቶች እየተለጠፉበት ያለኃጢአቱ የሀሰት ስም በመቀባት ዳግም ይገሉታል።
የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ከሚፈራበት የትምህርት ተቋም ድረስ በመግባት የአማራ ህንጻ፣ የኦሮሞ ህንጻ፣ የትግሬ ህንጻ…ወዘተ እያሉ የትምህርት ሥርዓቱን ከጠባቡ የፓለቲካ ግባቸው ጋር በማያያዝ በነገ ተስፋችን ላይ ዘምተው የልዩነት ግድግዳ ባሳፋሪ መልክ እየገነቡ ቀጥለዋል። አላማው ደግሞ በጎስኝነት በሽታ ተውጠን ከእህቶቻችንና ከወንድሞቻችን ጋር እየተባላንና እየተገዳደልን የምንኖርበት ሲኦል ለመፍጠር መሆኑ አያጠያይቅም። በዚህም ሳቢያ ብሔራዊ ሰሜታችን እየደበዘዘ ሄዷል። ብሔራዊ ሰሜት ከሌለን ደግሞ አገር አለን ማለት ጨርሶ የሚታስብ እንደማይሆን ግልጽ ነው።
በነገራችን ላይ ዛሬም ድረስ ወያኔዎች ለእድገትና ለልማት መዘጋጀታችውን እየደሰኮሩ ህዝብን በማታለል የስልጣን ዘመናቸውን ለማርዘም መውተርተራቸውን አላቆሙም። በየጊዜው ኢትዮጵያ ተመነደገች፤ ልማቱ ተፋጥኗል እያሉ በሃሰት ህዝብን ለማወናበድ ይሞክራሉ።እውነታው ግን በእጅጉ ተቃራኒ መሆኑን የህዝቡን የኑሮ ሁኔታን በመመልከት መረዳት ይቻላል። ዛሬ የፋሽስቱ ወያኔ አገዛዝ በፈጠረው የተወሳሰበ ችግር በሀገሪቱ የወጣት ሥራ ፈትና ተጧሪ ሞልቶና ተትረፍርፎ በሚታይበት፤ ሥራ የማግኘት እድል በፓለቲካ ታማኝነት ብቻ በሆነባት ሃገርና ወያኔ የፓለቲካ ሥልጣኑንና ወታደራዊ ኃይሉን ተጠቅሞ የሀገሪቷን ሀብት እያጋበስ በሚዘርፍበት ሁኔታ ላይ ቆመን ልማትና እድገት ማለት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ተራ ማጭበርበሪያና ዲስኩር ካልሆኑ በስተቀር ፈጽሞ ትርጉም የሚሰጥ አይደለም።
ለነገሩ ወያኔ ከመጀመሪያው ጀምሮ ያዘጋጀልን ቃሊቲ፤ ማዕከላዊ፤ ሁርሶን፤ ሽዋሮቢትንና የመሳሰሉትን የማሰቃያ ማጎሪያዎች መሆኑን የተረዳን ስለሆነ በዚህ የምንደናገር አይደለም። ለዚህም ነው በአሁኑ ወቅት እኛ ወጣቶች ተሰባስበንና ተደራጅተን ከመታገል ውጪ ሌላ ምርጫ የለንም ብለን በድፍረት የምንናገረው።
አምባገነንነት ስርዓት ካልተገታ የአገር ሰላም ሆነ የህዝብ ህልውና እና አንድነት ዋስትና አያገኝም። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሥልጣን የጨበጡት ወንበዴ ግለሰቦች የኢትዮጵያ ህዝብን ሀብት እየተቀራመቱ ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉ፣ ህዝቡን የሚገሉ፤ የሚረግጡና የሚበድሉ በተለይ ደግሞ ለባእድ ጥቅም የተገዙ ናቸው። እነዚህ ግለስቦች ብሔራዊ ስሜታችውን አሽቀንጥረው የጣሉ፤ የራሳችውን ባህል፤ ወግ፤ ታሪክና ሕዝብ አምርረው የሚጠሉ ከራሳቸውና ሥልጣን ላይ ካስቀመጧቸው መንግሥታት ጥቅም ውጪ ሌላ ምንም የማይታያቸው ናችው።
ታዲያ የሃገራችን ህልውና ከመቼውም በላይ ለከፋ አደጋ ተጋልጦ ባለበት በአሁኑ ወቅት በተለይ የእኛ የወጣቶች ግዴታና ድርሻ ምን መሆን አለበት ብለን ራሳችንን መጠየቅና ብሎም መልስ ለመስጠት መዘጋጀት ሀገራዊ ግዴታንና ኃላፊነትን ለመወጣት የመጀመሪያው እርምጃ መሆን ይኖርበታል።
ጭቆናንና በደልን በመታገል ረገድ ደግሞ የቀደምት የታላላቅ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አኩሪ ገድል ለዛሬው ትግላችን ትልቅ የትምህርት ማእከል ሆኖ ያገለግለናል። ሀገራችን ከኋላቀር ሥርዓትና ከብልሹ አገዛዝ ተላቅቃ፤ ድህነትን አሸንቀጥራ ጥላ በልማት ጎዳና እንድትራመድ፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን እንዲሆን፤ ማህበራዊ ፍትህ እንዲስፍን ባጠቃላይም ተጨባጭና ዘላቂ ለውጥ በሃገራችን እንዲመጣ ጽኑ እምነት ሰንቀው ለሕዝባዊ ትግሉ ሕይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ሲታገሉ የነበሩ ጀግና ወጣቶች እንዳሉ ታሪክ ያስገነዝበናል።
ዛሬም ጭምር ግንባራችውን ሳያጥፉ መስዋእትነትን በመክፈል እያስመስከሩ ያሉ መኖራቸውን ስንመለከት ጀግና የሚያፈራው ጀግናን ነውና እኛም ወጣቶች አንገታችንን ቀና አድርገን ዛሬም እንደ ትናንቱ ለሃገራችንና ለህዝባችን ነፃነት መታገል ብሔራዊ ግዳጃችን ብቻም ሳይሆን ታላቅ ክብርም ጭምር መሆኑን ተገንዝበን ለሞት ሽረቱ ትግል በቁርጠኝነት መነሳት ይኖርብናል። ከፊታችን ለሚጠብቀንና ሃገራችን እያሰማች ላለው የሀገር አድን ጥሪ መልስ ለመስጠት እኛ የኢትዮጵያ ወጣቶች ከሃገር ቤት እስከ ውጪው አለም ድረስ የተቀናጀና የተቀነባበረ ንቅናቄ በመፍጠር ምላሽ ልንሰጥ ይገባል።
በኅብረትና በጽናት ከታገልን ደግሞ የወያኔን የሰቆቃ አገዛዝ አሰወግደን የሕዝባችንን ሮሮ የማናስቆምበት እና ተጨባጭ ለውጥ በሀገራችን ለማምጣት የማያስችለን አንዳች ምድራዊ ሃይል እንደማይኖር በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል። ዛሬ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንዳለ ብልጭ ብልጭ እንደሚል ኮኮብ ብንመስልም በርግጠኝነት ነገ ከፀሐይ ደምቀን ከአሽዋ በርከትን የምንታይበት ጊዜ ይመጣል፤ እየመጣም ነው።
በመጨረሻም የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ወጣቱን ትውልድ መብቱንና የዜግነት ክብሩን ለመጎናጸፍ እንዲችል ብሎም የሀገር እና የወገን ነፃነትን ለማምጣት ወያኔን ታግሎ ማሸነፍና ከስልጣኑ ማውረድ ግድ ነው ብሎ በጽኑ ያምናል። በአገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም ተበታትኖ የሚገኘውን ወጣት በአገሩ ተከብሮ እንዲኖር የተለየና የተቀደሰ አማራጭ አለው። ይኸውም እየተደራጁ መታገል፣ እየታገሉ መደራጀት ነው ብሎ ንቅናቄያችን ያምናል።
የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ የነደፈውን ጊዜ የማይሽረውን ሁለገብ የመታገያ ስልትና አላማን ከግብ ለማድረስ ትግልን በጽናት መቀጠል የሚለው መርሁ ሲሆን ተደራጅቶ በጽናት መታገልን በተግባር ለማዋል ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወጣት ንቅናቄውን እንዲቀላቀል ጥሪ ያደርጋል። ተደራጅቶ ሊያጠፋን የተነሳን ጠላት በተደራጀ ሃይል ማንበርከክና ከስር መሰረቱ ማስወገድ ይቻላልና። ስለዚህ የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ በአረመኔው የወያኔ አገዛዝ ላይ የሚካሄደውን ትግል አጠናክሮ በመቀጠል በአገር ውስጥ ወጣቱን በህቡዕ ከማደራጀት ጀምሮ በውጭው ዓለም በየአህጉሩ በተዋቀሩ የንቅናቄው መዋቅሮች አማካኝነት ወጣቱን አደራጅቶ በማንቀሳቀስ አስፈሪ የሆነ የነፃነት ማዕበል ፈጥሯል። አሁንም የንቅናቄውን ዓላማ የሚደግፉና በነፃነት ትግሉ ለመሳተፍ የቆረጡ ወጣቶች እንዲቀላቀሉ የአርበኞች ግንቦት7 ወጣቶች መምርያ በድጋሚ ሃገራዊ ጥሪ ያቀርባል!
ፈሪዎችንና ባንዳዎችን ወደ ጎን በመተው እውነተኛ ታጋዮችን ይዘን ትግላችንን እንቀጥላለን!!!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!