Wednesday, April 27, 2016

የቀድሞ የጋምቤላ ፕ/ት 9 ዓመት ተፈረደባቸው (በእጅ ጽሁፋቸው የጻፉትና ምስጢር የያዘው የክስ መቃወሚያቸው እጃችን ገብቷል)

(ዘ-ሐበሻ) የኖርዌይ ዜግነት እንዳላቸው የሚነገርላቸውና ደቡብ ሱዳን ላይ ታፍነው ተወስደው የታሰሩት የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦኬሎ አኳይ “አገርን ለመገንጠል” በሚል በቀረበባቸው ክስ የ9 ዓመት እስራት ተፈረደባቸው:: ኦኬሎ ከፍርድ በፊት ለሚዲያ ይድረስልኝ በሚል የላኩትና ለፍርድ ቤቱም በእጅ ጽፉፋቸው አስገብተውት የነበረው የክስ መቃወሚያ ዘሐበሻ እጅ ደርሷል:: ይዘነዋል::
ከኦኬሎ ጋር በተባባሪነት የተቀሰሱት ዴቭድ ኡጁሉ 9 ዓመት; ኡቻን ኦፔይ 7 ዓመት; ኡማን ኝክየው 7ዓመት; .ኡጁሉ ቻም 7ዓመት; ኦታካ ኡዋር 7ዓመት እና ኡባንግ ኡመድ 7 ዓመት ተፈርዶባቸዋል::

Wednesday, April 13, 2016

በጅንካ የመከላከያ ሰራዊትና ልዩ ሃይል አባላት ከፍተኛ ቅኝት እያደረጉ ነው

 የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት በደቡብ ኦሞ በጅንካ ከተማና አካባቢዋ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከልዩ ሃይል አባላት ጋር በመሆን፣ በተለይ ከምሽቱ 2 ሰአት ጀምሮ በመኪኖች ላይ መትረጊስና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎችን ደግነው ቅኝት በማድግ ላይ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ የወጣቶች ነጻ እንቅስቃሴ የተገደበ ሲሆን፣ ነዋሪዎችም ጭንቀት ውስጥ ገብተዋል፡፡
ክትትሉ የተጀመረው በአካባቢው ከፍተኛ እውቅና ያላቸው የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት ም/ሊቀመንበርና የዞኑ ጽ/ቤት ቤት ኃላፊ አቶ ዓለማዬሁ መኮንን፣ አቶ አብረሃም ብዙነህ እና አቶ ስለሺ ጌታቸው መጋቢት 17፣ 2008 ዓም መታሰራቸውን ተከትሎና ፓርቲያቸው መሪዎቹና አባሎቹ ካልተፈቱ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚጠራ መግለጫ ማውጣቱን ተከትሎ ነው፡፡
እነ አቶ አለማየሁ መኮንንን በሽብር ወንጀል ለመክሰስ የተደረገው ሙከራ ፣ ለምስክር የተዘጋጁ ሰዎች በሃሰት አንመሰክርም በማለታቸው ላይሳካ እንደሚችል ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቶአል፡፡
ለምስክርነት በቅድሚያ የታጩት የታሳሪዎች መኖሪያ ሲፈተሸ የነበሩ ስድስት ሰዎች ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል አቶ መስፍን እርገጤ፣ አቶ ዓሊዬ ይታ፣ እና ወጣት ሃና ‹‹ከታሳሪዎች ቤት ክላሽንኮቭ ጠመንጃና ቦምብ በፍተሻ ሲገኝ አይተናል ›› ብላችሁ ከመሰከራችሁ ‹‹አዋሳ ወስደን ከመዝናናችሁ በተጨማሪ ለመቋቋሚያ የሚሆን ለእያንዳንዳቸው ብር 50 ሺህ፣ ይሰጣችኋል ››ቢባሉም የሃሰት ምስክርነቱን ኃሳብ ውድቅ ማድረጋቸውን ፣ ጉዳዩን በቅርብ ከሚከታተሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለማወቅ ተችሎአል፡፡
መስካሪዎች ‹‹ ከጂንካ ከተማ ህዝብ ጋር ከምንጋጭ ከነድህነታችን ከህዝብ ጋር መኖር እንፈልጋለን ›› ማለታቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ መስካሪዎቹ አዋሳ ለመሄድ ፈቃደኛ ያለመሆናቸውንና የዕለት ሥራቸውን ሰርተው ማደር እንደሚፈልጉ የገለጹ ሲሆን፣ ይህ ሳይሆን አዋሳ በግዳጅ ብንሄድ የተለየ እንደማንመሰክርና እየደረሰብን ያለውን ጫና ለህዝብ በአደባባይ ለማሳወቅ እንገደዳለን ማለታቸው ታውቆአል፡፡
በደቡብ ኦሞ መሬት ከወሰዱት ባለሃብቶች መካከል ከ98 በመቶ በላይ የሚሆነውን መሬት የወሰዱት የህወሃትና ከህወሃ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች መሆናቸውን የሚያመለክት ጥናት በወጣ ማግስት እነ አቶ አለማየሁ መታሰራቸውን ኢሳት መዘገቡ ይታወቃል፡፡
መረጃው ከወጣ በሁዋላ የአካባቢው ነዋሪዎች በስፋት እየተነጋገሩበት ሲሆን፣ የዞኑ መስዳደርም ሆነ ክልሉ በጉዳዩ ዙሪያ ለህዝቡ ጥያቄ መልስ አልሰጡም፡፡
ሚያዚያ ፬( አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :

Friday, April 8, 2016

ትግሉ ሰፊ የምሁራን ተሳትፎ ይሻል!

April 8, 2016
def-thumbኢትዮጵያ በበብዛትም ይሁን በጥራት በውጭው አለምም ይሁን በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ምሁራን ያፈራች ሀገር ነች። በጅጉ የሚያሳዝነው ግን በሀገሪቱና በሕዝቧ ችግር ላይ ሀሳብ ሲሰጡ ፣ ባደባባይ ሲከራከሩና ሲታገሉ የሚታዩት በጅጉ ጥቂቶች ናቸው። ርግጥ ነው ተከታታይ መንግስታት በምሁራን ላይ ያደረሱት ጥቃትና ማግለል ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት ብዙዎች መከራን ከህዝብ ጋር ከመጋፈጥ ይልቅ አጎንብሶ ማሳለፈን የመረጡበት ሁኔታ አለ። ቁጥራቸው ጥቂት ያልሆኑም ለግል ጥቅማቸው ቅድሚያ በመስጠት ከጨቋኝ ገዥዎች ጋር በመተባበር የሚሰሩ መኖራቸውም አይካደም። አብዛኛው ምሁራን በተለይም በብዙ የሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ጠለቅ ያለ እውቀት ያላቸው ጭምር ሀገሪቱን ከገባችበት ማጥ ለማውጣት በሚደረገው ትግል ውስጥ እየተሳተፉ አይደለም። ይህ ዛሬ ባለው ችግርም ይሁን በታሪክ ፊት አሳዛኝ ነው።
ሀገራችን ዛሬ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነች። የተማሩ ልጆቿ መላ እንዲመቱ በመጠየቅ ላይ ትገኛለች። ይልቁንም በሀገራችን ያለው ችግርና ሀገሪቱ እየሄደች ያለችበት መንገድና አቅጣጫ በተለይ ምሁራንን እንቅልፍ ሊነሰ ይገባል። ዕውነታው ከዚህም አልፎ የሀገሪቱን አሳዛኝና አደገኛ ሁኔታ ለመቀየር በሚደረገው ትግል ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ግድ ይላል። የመንግስት ግፍና ሰቆቃ በበዛበትና የሀገራችን ሕልውና አደጋ ላይ በወደቀበት በአሁኑ ሰዓት ምሁራን ላለመሳተፍ ምክንያት ማቅረብ የማይችሉበት ወቅት ላይ ደርሰናል። እንደማንኛውም ሀገር ምሁራን የኢትዮጵያ ምሁራን በሀገራችን ውስጥ ሰላምና ዲሞክራሲ እንዲሰፍንና ፍትሕ የሰፈነበት ስርዓት እንዲመሰረት ሊሸሹት የማይገባ ትልቅ ሚና አላቸው።
ዛሬ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ ዜጎች መንግስት በልማትና በልማት እያመካኘ የሚያካሂደውን ሰፊ ዝርፊያ እንዲሁም ወያኔ ሩብ ምዕተ አመት ሙሉ በብሄረሰብ እኩልነት ስም እየማለ የሚያደርሰውን ያንድ ብሄረሰብ ጉጅሌ የበላይነት ማስፋፋት እምርረው በመታገል ላይ ናቸው። መስዋዕትነቱን እየከፈሉ የሚታገሉትና የሚወድቁ የሚነሱት ወጣቶችና ምስኪን ገበሬዎች ናቸው። እነዚህ ወገኖቻችን ሕይወታቸውን ሳይቀር ሲገብሩ በየቀኑ እየሰማንና እያየን ነው። ይህንን የህዝብ ጥያቄና ትግል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ምሁር ተመልካች ሆኖ ሊቀመጥ አይገባም። ትግሉን ከመምራት ጀምሮ እስከ ተራ ታጋይነት ባሉት ረድፎች ሁሉ ምሁራን ቀጥተኛ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል። ሰለትግሉ እቅጣጫም ሆነ ስለሀገሪቱ መጻዔ ዕድል ሃሳብ ማመንጨትና ማሰራጨት ይኖርበታል። ሀገራችን የደለቡ ችግሮቿን ተቋቁማ ፍትሕ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈነባት ሀገር የሚያደርጋትን የምህንድስና ስራ አስቀድሞ ማሰብና ማመቻቸት ይኖርበታል። ርግጥ ነው ይህን መሰል ተሳትፎ የሚያደርጉ ምሁራን አሁንም አሉ። ቁጥራቸው ግን ሊሆን ከሚገባው ጋር ሲወዳደር በጅጉ አነስተኛ ነው።
ምሁርነት ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ መቀዳጀት ብቻ እንዳልሆነ የታወቀ ነገር ነው። ምሁርነት ምሉዕ የሚሆነው መላውን የተፈጥሮ ከባቢ ከህዝብ ማህበራዊ ሕይወት ጋር አጣምሮ የሚያስብ አዕምሮን በዕውነት ላይ ለተመሰረተ ሀሳብና ዕውቀት ክብር መስጠትን ለተግባራዊነቱ መሟገትን የጨመረ ሲሆን ነው ። በመሆኑም ሁሌ እንደሚባለው ምሁርነት የጋን መብራትነት አይደለም። ምሁርነት በጨለማ ውስጥ ችቦ ሆኖ ብርሃን መፈንጠቅን ይመለከታል። ምስዋዕትነትንም ይጠይቃል።
ያለንበት ወቅት ለኢትዮጵያ ምሁራን ከፍተኛ ፈተናም ዕድልም ይዞ ቀርቧል። ይህ ልሽሽህ ቢሉት የማይሸሽ ፈተና ከመሆኑ ባልተናነሰ በታሪካችን እንድ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የጎላ አሻራን ለማኖርም ትልቅ የታሪክ ዕድል ነው። ይህ ፈተና ከፍተኛ ያርበኝነት ስሜትንና ሀላፊነት መውሰድን ይጠይቃል። አገር በተወሳሰበ ችግር ምክንያት ወደ አረንቋ እየገባች ምንም ሳይሰሩ መቀመጥ ወይም ዝም ብሎ ከመመልከት የበለጠ ለምሁር ሂሊና የሚከብድ ነገር ሊኖር አይችልም:: በጣም ላስተዋለ ሰው እንዲህ አይነት ዝምታ ሐጢያትም ነው። በእንዲህ አይነት ፈታኝ ወቅት የኢትዮጵያ ምሁራን ሀገሪቱን ወደተሻለ አቅጣጫ እንድትሔድ ላለመታጋል ምንም ምክንያት ማቅረብ አይችሉም። ሀሳብ የሚሰራጭባቸው የሀሳብ ክርክር የሚካሔድባቸው መድረኮች ፣ አደባባዮች ፣ የመገናኛ መሳሪያ አይነቶች የፖለቲካና የሲቪክ ማህበሮች ባገር ውስጥም በውጭም ያሉት መሳተፊያ ናቸው።
ድርጅታችን አርበኞች ግንቦት 7 ምሁራን በሰፊውና እንደየፍላጎቶቻቸውና ችሎታቸው ሊሳተፉ የሚችሉባቸው በርካታ የትግል መስኮች አሉት። የሀገሪቱን ውስብስብ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ የጥናት ውጤቶች ፣ ሀሳቦች ፣ ምክሮችም ሆነ ቀጥተኛ የምሁራን ተሳትፎ ለማስተናገድ አመቺ ሁኔታ ያለበት ድርጅት ነን። ወደፊትም የምሁራን ተሳትፎ እንዲጎለብት ሁኔታዎችን ይበልጥ ለማመቻቸት እንሰራለን። ዽርጅታችን የሀገራችን ችግር የሚወገደውና ዲሞክራሲና የዜጎች እኩልነት የሚረጋገጠው በበሰለና ከተራ ዜጋ እስከ ብስል ምሁራን በሚያከሂዱት ክርክርና የበሰለ ሃሳብ ላይ ተመስርቶ መሆኑን ያምናል። አሁን ያለው የሀገራችን ምሁራን ተሳትፎ ደረጃ ሁላችንም ከምንጠብቀው በታች በጅጉ ያነሰ መሆኑ ሁላችንንም ከማሳዘን አልፎ የሚያስቆጭና የሚያንገበግብ ሆኖአል:: አገርና ህዝብ ድረሱልኝ እያለ በሚጣራበት በዚህ የታሪክ አጋጣሚ አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ የተለያዩ ምክንያቶችን እየደረደሩ ማለፍ ይቻል ይሆናል። ይዋል ይደር እንጂ ለነጻነቱ ቀናዕ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የደረሰበትን አፈናና ጭቆና እምቢኝ ብሎ ነጻነቱን ሲቀዳጅ ግን ከታሪክ ፍርድና ከህዝብ ትዝብት ማምለጥ አይቻለም።
አርበኞች ግንቦት 7 በአገር ውስጥም ሆነ በተለያየ ምክንያት በአለም ተበትኖ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ምሁር ለወገን ደራሽነቱንና አለኝታነቱን አሁኑኑ ይወጣ ዘንድ ወገናዊ ጥሪውን ያቀርባል::
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

ለኮ/ል አታክልቲ ገ/ሚካዔል ልጅ ማሳከሚያ ከብረታ ብረት ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን 3 ሚሊዮን ወጪ ተደረገ

የብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ለአንድ ባለስልጣን ልጅ ማሳከሚያ ሶስት ሚሊዮን ብር የህዝብ ገንዘብ ወጪ ማድረጉን ለኢሳት የደረሰው ሰነድ ያስረዳል። ኮሮፖሬሽኑ የወጣውን ገንዘብ በስሩ ያሉ ድርጅቶች በመዋጮ እንዲሸፍኑት መመሪያ ተላልፏል።
በብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የሰው ሃይል አስተዳደርና ዕቅድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በኮ/ል ፅጌ አለማየሁ ስምና ፊርማ ህዳር 8 ፥ 2005 የተጻፈው ደብዳቤ ለኮ/ል አታክልቲ ገ/ሚካዔል ልጅ ማሳከሚያ የወጣው ወጪ በስሩ ያሉ ድርጅቶች በመዋጮ እንዲሸፍኑት ያዛል። ህክምናው በታይላንድ ባንኮክ መከናወኑንም ያስረዳል።
ጉዳዩ የኮ/ል አታክልቲ ልጅ ተማሪ ዮናስ አታክልቲ ታይላንድ ሄዶ የታከመበትን የህክምና ወጪ ይመለከታል በሚል ርዕስ የወጣው ደብዳቤ የሚከተለውን መልዕክት ይዟል። 
የብረታብንረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የህወሃት ታጋዮች በነበሩት መኮንኖች የሚመራ ሲሆን፣ ዋና ዳይሬክተሩም አንጋፋ የህወሃት ታጋይ የነበሩት ብ/ጄኔራል ክንፈ ዳኘው መሆናቸው ይታወቃል።
ኮርፖሬሽኑ ከመንገዶች ባለስልጣን ለዕድሳት ብሎ የወሰደውን 88 ማሽነሪ ለትግራይ ክልል አሳልፎ መስጠቱ በአለም ባንክ ኦዲተሮች መጋለጡ በቅርቡ በሰነድ አስደግፈን መዘገባችን ይታወሳል። የማሽነሪዎች ዋጋም ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።
ለባለስልጣን ልጆች ማሳከሚያ በመስጠት የህዝብና የሃገር ሃብት በመመዝበር ላይ መሆኑ የብዙዎች ስጋት ሆኗል። በኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሃገረ-ስብከት ስራ አስኪያጅ ሊቀማዕምራን የማነ ዘመንፈስቅዱስ ለልጃቸው ማሳከሚያ በሚል ለአዲስ አበባ አብያተክርስቲያናት ባቀረቡት ጥሪ ከአንድ ደብር ከአንጦጦ ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ብቻ 500ሺ ብር እንዲወጣ መወሰኑ ባስነሳው ውዝግብ ጉዳዩ መጋለጡ ይታወሳል።
ፓትሪያርኩ በወሰዱት እርምጃ የማነ ዘመንፈስቅዱስ ከሃላፊነት የተነሱ ቢሆንም፣ የተዋጣውን ገንዘብ በተመለከተ ስለተደረሰው ውሳኔ የታወቀ ነገር የለም።
ኢሳት (መጋቢት 29 ፥ 2008)

በአምቦ ወህኒ ቤት አንድ ወጣት በደረሰበት አሰቃቂ በድብደባ ተገደለ

አምቦ ወህኒ ቤት ውስጥ የታሰረ አንድ ወጣት በድብደባ መገደሉን ወላጅ እናቱ ለኢሳት ገለጹ። ላለፉት 10 አመታት በወህኒ ቤት ውስጥ የቆየው ወጣት ጌጡ በቀለ ቶሎሳ፣ ህይወቱ ያለፈው ከአምቦ ወህኒ ቤት ቃጠሎ ጋር በተያያዘ እጅ አለበት በሚል በደረሰበት ድብደባ መሆኑም ተመልክቷል።
በፖለቲካ ሳቢያ ከ10 አመት በፊት ወህኒ ቤት መግባቱ የተገለጸው ወጣት ጌቱ በቀለ፣ እዚያው እያለ በመጣበት ተጨማሪ ክስ ወህኒ ቤት ውስጥ እንዲቆይ መደረጉን ከወላጅ እናቱ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል። የመጣበትም ተጨማሪ ክስ በአካባቢው ከተገደለ የኦህዴድ ካድሬ ጋር በተያያዘ ሲሆን፣ ገዳዩ አንተነህ በሚል ተወንጅሎ መቆየቱንም መረዳት ተችሏል። Ambo
ወላጅ እናቱ በቅርቡ ወህኒ ቤት ሄደው ሲጎበኙ ጤነኛ የነበረው ጌቱ በቀለ ቶሎሳ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ህይወቱ ማለፉን አስረድተዋል። ሆስፒታል መግባቱን ገልጾ በላከላቸው መልዕክት ሊጎበኙት ሲሄዱ አስከሬኑ መላኩ እንደተነገራቸው አስረድተዋል።
አስከሬኑን ለማግኘት የደረሰባቸውን መጉላላትም ያስታወሱት የሟች ወጣት ጌቱ በቀለ ቶሎሳ እናት፣ አስከሬኑ ሲደርሳቸው ከፍተኛ ድብደባ ያደረሱበት መሆኑን ገልጸዋል።
ሟች ወጣት በአካሉ ላይ በደረሰበት ድብደባ ከፊል ሰውነቱ በፋሻ መጠቅለሉንም ለኢሳት አስረድተዋል።
ኢሳት ( መጋቢት 29 ፥ 2008)

Wednesday, April 6, 2016

በስሉልታ ፌደራል ፖሊስ ከወጣቶች ጋር ተፋጧል – የአላሙዲ መኪኖች ተሰባበሩ * ፖሊስ እየተኮሰ ነው

Share0  0  0 
 Share0

Zehabesha News
 ከአዲስ አበባው ቤተመንግስት 28.4 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሱሉልታ ከተማ የአካባቢው ወጣቶች ከፌደራል ፖሊሶች ጋር በፋጠጣቸው ተሰማ:: ከአካባቢው የሚመጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የሱሉልታ ወጣቶች የኢትዮጵያን ሕዝብ እየገደለ ያለውን የሕወሓት መንግስት በገንዘብ ይደግፋሉ ያላቸውን የሼህ መሀመድ አላሙዲ 3 መኪኖችን በድንጋይ ሰባብሯል::
በሱሉልታ ከተማ የሚገኘ አንድ የኤሌክትሪክ ትራንፎርሜሽን መፈንዳቱን ተከትሎ አካባቢው በፌደራል ፖሊሶች በመከበቡ የተነሳ ሕዝቡ ፖሊሶቹን አትወክሉንም; ከአካባቢያችን ዞር በሉ በሚል ተቃውሞውን ማሰማቱን ተከትሎ ፖሊሶች በወጣቶች ላይ ዱላ ሰንዝረዋል:: አንዳንድ ወታቶችም አጸፋውን በፖሊሶች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን የሚገልጹት የዘ-ሐበሻ የዜና ምንጮች ፖሊሶች በተኩስ የወጣቱን ተቃውሞ ለመበተን ሞክረዋል ብለዋል::
ይህ ተቃውሞ እየተደረገ ባለበት ወቅት በአካባቢው ይንቀሳቀሱ የነበሩ የሼህ መሀመድ አላሙዲ ንብረት የሆኑ መኪኖች በድንጋይ ሲደበደቡ የሦስቱም መኪኖች መስታወቶች መርገፋቸው ተሰምቷል::
በሌላ በኩልም በሰበታ የሁለተኛና የፕሪፓራቶሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ ወታደሮች እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች አስታውቀዋል:
:(ዘ-ሐበሻ)

በጋምቤላ የእርሻ መሬት የወሰዱ 93 ባለሃብቶች መሬታቸውን እንዲመልሱ ተደረገ

በጋምቤላ ክልል የወረዳ አስተዳደሮች በህገወጥ መንገድ የእርሻ መሬት ተሰጥቷችኋል የተባሉ 93 ባለሃብቶች መሬታቸውን እንደመልሱ ተደረገ።
በህጋዊ መንገድ የእርሻ መሬቱን እደተረከቡ የሚገልጹት ባለሃብቶች በበኩላቸው መሬቱን ከክልሉ ባለስልጣናት በህጋዊ መንገድ ከተረከቡ በኋላ የፌዴራል ባለስልጣናት ርክክቡ ህገወጥ ነው ማለታቸው ተገቢ አለመሆኑን አስታውቀዋል።
በጋምቤላና ሌሎች ክልሎች ለውጭና ለሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ሲሰጥ የቆየው ሰፋፊ የእርሻ መሬት በመንግስት ላይ ኪሳራን አስከትሏል መባሉን ተከትሎ የመሬት መስጠቱ ሂደት እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወሳል።
መንግስት ደርሶበታል የተባለን ኪሳራ እንዲያጣራ የተቋቋመ አካልም በክልሉ ባለሃብቶች ያለግባብ ተሰጥቷል የተባለ 200ሺ ሄክታር መሬት እንዲመለስ ማድረጉን የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ማክሰኞ ገልጿል።
ይኸው ሰፋፊ የእርሻ መሬትም በ93 ባለሃብቶች ተይዞ የነበረ እንደሆነ የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዳንዔል ዘነበ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
መሬቱን በህጋዊ መንገድ ከክልሉ እንደተረከቡ የሚገልጹት ባለሃብቶች በበኩላቸው በፌዴራልና የክልል መንግስታት በኩል የመናበብ ችግር በመኖሩ ሳቢያ በስራቸው ላይ ኪሳራ መድረሱን እንዳስታወቁ ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
የመሬት አስተዳደር ኤጀንሲ በበኩሉ በጎግና ዲማ ወረዳዎች ለ93ቱ ባለሃብቶች የተሰጠው መሬት ለኢኮኖሚ ዞን የተያዘ እንደነበርና ባለስልጣናት በህገወጥ መንገድ ርክክብ መፈጸማቸውን አመልክቷል።
በክልሉ ለበርካታ ባለሃብቶች ተሰጥቷል በተባለ ተደራራቢ የመሬት ርክክብ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ቢያበድርም ገንዘቡ የገባበት አለመታወቁን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በመንግስታዊ ባንኩ ላይ ደርሷል የተባለን ኪሳራ ተከትሎም ባንኩ ለሰፋፊ የእርሻ መሬቶች የሚሰጠውን ብድር ያቋረጠ ሲሆን፣ የፌዴራል መንግስትም የመሬት ቅርምት ነው የተባለውን መሬት ለባለሃብቶች የመስጠት ስራ እንዲቀር ወስኗል።
ከመንግስት ብድርን የተረከቡ በርካታ ባለሃብቶችም ከወሰዱት ብድር ጋር ከሃገር መኮብለላቸውን የልማት ባንኩ ሃላፊዎች በቅርቡ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ኢሳት (መጋቢት 27 ፥ 2008)

Tuesday, April 5, 2016

የዋዜማ ጠብታ- በኢትዮዽያ የሚንቀሳቀስ ኩባንያ በፓናማ (የሙስና ቅሌት ስነድ) ውስጥ ተጋልጧል

ከሁለት ቀናት በፊት በአለም አቀፍ ደረጃ ይፋ የተደረገውና ፓናማ ፔፐርስ (Panama Papers) በሚል የተሰየመው የሙስናና የገንዘብ ማሸሽ ቅሌት የተጋለጠበት ግዙፍ መረጃ የአለም የመገናኛ ብዙሀንን ስራ    አብዝቶባቸዋል።የእነማን ስም ተነሳ? የትኞቹ ኩባንያዎችስ አሉበት? የሚለውን ለማጣራት ጋዜጠኞች በር ዘግተው ስነዱን እየመረመሩ ነው።
በርካታ የላቲን አሜሪካ የእስያና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በቅሌት መዝገቡ በስፋት ተዳሰዋል። አፍሪቃም ከቅሌቱ አላመለጠችም። ባለሀብቶችና የፖለቲካ ሹማምንት በድብቅ በቤተሰቦቻቸው አልያም በቅርብ ወዳጆቻቸው ስም ከሀገር አሽሽተው የደበቁትን ገንዘብ የደበቀላቸው በፓናማ የሚገኝ ሞሳክ ፎንሲካ (Mossack Fonseca) የተባለ የህግ አማካሪ ነው። ይህ ተቋም ገንዘቡን የህግ ክፍተት ወዳለባቸው ትናንሽ ሀገሮች በማሸሽ የማማከር አገልግሎት ይሰጣል።የስዊስን ባንክ የመሳሰሉትን ደግሞ ለመሸጋገሪያነት ይጠቀምባቸዋል።
ባለሀብቶች ታክስ ለመሸሽና በስርቆት ያገኙትን ሀብት ወደዚህ ተቋም በመውሰድ ይሸሽጋሉ።የሩሲያው ቭላድሚር ፑትቲን ስማቸው እየተብጠለጠለ ነው። በስማቸው ሁለት ቢሊያን ዶላር በወዳጆቻቸው ስም ደግሞ የትየለሌ የሆነ ገንዘብ መዘረፉን ስነዶች ያመለክታሉ። የደቡብ አፍሪቃው ጃኮብ ዙማና የቀድሞ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሀፊ ኮፊ አናን በወጣት ልጆቻቸው ስም የተቀመጠ ገንዘብ ተግኝቷል።
ይህ አይነቱ የገንዘብ ማሸሽ በተለየ ታክስ ላለመክፈል የሚደረግ ሲሆን በዘረፋ የተገኘንም ገንዘብ ለመሸሸግ ይመረጣል። ታዋቂ ስፖርተኞችና የፊልምና ሙዚቃ ኢንደስትሪው ባለፀጎች እዚህም እዚያም የራሳቸውም ሆነ የቤተሰቦቻቸው ስም መነሳቱ አልቀረም።
የእንግሊዙ ጠ/ሚ/ር ዴቪድ ካሚሮን አባት ስም ከዝርዝሩ መገኘቱ ፖለቲካዊ አተካሮ እንዳይቀሰቅስ ስጋት አለ። በሌሎች ሀገሮችም ቢሆን የፖለቲካ ቅሌቱ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ያነሳሳ ይሆን ወይ የሚለውን ሁሉም በጉጉት እየጠበቀው ነው። ከመረጃው ገና የቀረ ስላለ የብዙዎች ስም በመጪው ሰነድ ውስጥ ይኖር ይሆናል።
በአለማቀፍ የምርመራ ጋዜጠኞች ህብረት International Consortium of Investigative Journalists (ICIJ)  እና በመገናኛ ብዙሀን እጅ የገባው ይህ ሰነድ ማንነቱን ባልገለፀ አካል ተጠልፎ የተገኘ ነው። ይፋ የተደረገው መረጃ 11.5 ሚሊየን ስነድ የያዘ ነው።
በኢትዮዽያ በማዕድን ዘርፍ ለመሰማራት ከአምስት አመት በፊት ፈቃድ ያገኘው የእስራኤሉ ኤንግልኢንቨስት በዚሁ የቅሌት ሰነድ ላይ ስሙ ተጠቅሷል። ድርጅቱ በእስራኤልና በአዲስ አበባ ተቀማጭ የሆኑ ባለሀብቶቹን ዝርዝሯል። ከተዘረዘሩት ግለሰቦች መካከል አንዱ የስሙ የመጀመሪያ ፊደል “Y” ብቻ በሰነዱ ላይ ስፍሯል። ይህ ምናልባትም የግለሰቡን ማንነት የበለጠ እንድንጠይቅ የሚገፋፋ ሳይሆን አይቀርም። ግለሰቡ ኢትዮዽያዊ ላይሆን ይችላል፣ ስሙን መሸሸጉ ግን ሰለዚህ የማዕድን ኩባንያ እንድንመራመር የሚጋብዝ ነው። የእንግሊዘኛውን ዋና መረጃ ከታች ይመልከቱት

የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጣሪዎች ናቸው በሚል ከአዲስ አበባ በተባረሩ ፖሊሶች ምትክ አዲስ የቅጥር ምዝገባ እየተከናወነ ነው።

የአዲስአበባ ፖሊስ ኮምሽን ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት ከመጋቢት 20 እስከ የካቲት 10 ቀን 2008 አም 10ኛክፍል ያጠናቀቁ ተመዝጋቢዎች በአካባቢያቸው በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ እየቀረቡ እንዲያመለክቱ ጠይቆአል።
በስርአቱ ውስጥ ከሙስናና ብልሹ አስተዳደር ጋር በተያያዘ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሺ የሚቆጠሩ ፖሊሶችና አመራሮች እየተገመገሙ በመባረር ላይ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ክፍተቱን ለመሙላት አዲስ መቅጠር ማስፈለጉን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ተናግረዋል።
በመንግስት ወጪ በቅርቡ የፒኤች ዲ ዲግሪያቸውን የያዙት የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ ፣ ቀደም ሲል የፌዴራል ፖሊስ ኮምሽነር በነበሩበት ወቅት ከፍተኛ ሙስና በማካሄድ የሚታወቁ ሲሆን ፣ የእሳቸው ጉዳይ አስፈጻሚዎች አሁንም ባልተነኩበት ሁኔታ ተራ ወታደሩን በሌብነት አዋርዶ ማባረሩ በሰራዊቱ ውስጥ ከፍተኛ ቅሬታን ፈጥሮአል።
ኢሳት ዜና