Monday, May 23, 2016

ዛሬ በመርካቶ አሜሪካን ጊቢ አካባቢ የበርካታ ድሆች ቤት እየፈረሰ ነው


(ዘ-ሐበሻ) ካለምንም በቂ ካሳና ካለምንም የሕዝብ ይሁንታ በመርካቶ አካባቢ በተለምዶው አሜሪካን ጊቢ አካባቢ በርካታ የድሆች መኖሪያ ቤቶች  እና የንግድ ቤቶች በልማት ሰበብ ዛሬ እንደፈረሱ ከስፍራው የደረሱን መረጃዎች አመለከቱ::
እነዚህ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ለረዥም ዓመታት የኖሩት ወገኖች የሚኖሩበት ቤት ለሃብታሞች በሚሊዮኖች ብር ስር ዓቱ እየቸበቸበው ሲሆን ለነዋሪዎቹ በቂ የሆነ ካሳ አለመከፈሉ ብዙዎችን እያስቆጣ ነው::
ዛሬ ከፈረሱት መኖሪያ ቤቶች በተቸማሪ የተለያዩ የንግድ ድርጅቶችም እንደፈረሱ ያስታወቁት ምንጮች ሕዝቡ መሬቱ ለሃብታሞች ሲሰጥበት በቁጭት እየተምከነከነ መሆኑን አስረድተዋል::

Monday, May 9, 2016

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያልተወራረደና የተበላሸ ብድሩ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል።

ሚያዚያ ፩(ግንቦት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በየአመቱ በሚያወጣቸው የሂሳብ አያያዝ መግለጫዎቹ ከፍተኛ ትርፍ እንዳገኘ ሲናገር የቆዬው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2006 እና 2007 ዓም ባሉት 2 ዓመታት ብቻ 11 ቢሊዮን 273 ሚሊዮን ብር ያላወራረደው ገንዘብ ሲኖር፣ 1 ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ብር ደግሞ የተበለሻ ብድር እንዳለው ሰነዶች አመለከቱ።
በአውሮፓውያን አቆጣጠር እስከ ሰኔ 30፣ 2014 ድረስ የተለያዩ የድርጅቱ ቅርንጫፍ ባንኮች 3 ቢሊዮን 590 ሚሊዮን ከ30 ሳንቲም ፣ በ2013 ደግሞ 6 ቢሊዮን 956 ሚሊዮን ከ20 ሳንቲም ያላወራረዱት ገንዘብ መኖሩን ከንግድ ባንኩ ሰራተኞች የተገኘው የሂሳብ መዝገብ ያሳያል።
ብድር ወስደው መክፈል ያልቻሉት ድርጅቶችና ብድራቸው በተበላሸ ብድር መዝገብ ከሰፈሩት መካከል፣ ሳይጀን ዲማ ቴክስታይል ፋብሪካ 437 ሚሊዮን ብር፣ ሙሉነህ ካካ ላኪ ድርጅት 94.2 ሚሊዮን ብር፣ አኪር ግንባታ 87.1 ሚሊዮን ብር፣ ካራቱሬ እርሻ ደርጅት 55.3 ሚሊዮን ብር፣ ባዘን እርሻ እና ኢንዱስትሪ ልማት የግል ማህበር 42.1 ሚሊዮን ብር፣ የጌታ ትሬዲንግ 39.3 ሚሊዮን ብር፣ ማሜ ብረታብረት ፋብሪካ 39.2 ሚሊዮን ብር፣ የገነት ላኪና 62 ሚሊዮን ብር፣ ሸበሌ ትራነስፖርት 17.2 ሚሊዮን ብር፣ ፍጹም ዘአብ አስገዶም 14.2 ሚሊዮን ብር ቤድፋም ኢንተርናሽናል 21 ሚሊዮን ብር ይገኙበታል።
ባንኩ በ2013/14 በጀት አመት 17.2 ቢሊዮን ብር እንዳተረፈ ቢገልጽም፣ የባንኩ ሰራተኞች እንደሚሉት ግን የተበላሸው ብድርና ያልተወረራደው ገንዘብ ግምት ውስጥ ሲገባ ባንኩ ያተረፈው ከ5 ቢሊዮን ብር አይበልጥም።