Tuesday, December 9, 2014

በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ የደረሰውን ጥቃት እናወግዛለን !!!

በአብዛኛው በወጣት ወንዶችና ሴቶች የተገነባው ሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነበት የዘጠኝ ፓርቲዎች ኅበረት፣ “ነፃነት ለፍትሃዊ ምርጫ” የተሰኘ የአንድ ወር መርሀ ግብር አውጥቶ፤ ችግሮችን ተጋፍጦ አብዛኛውን ተግባራዊ አድርጓል። የመርሀ ግብሩ አቢይ አካል የነበረውና በህዳር 27 እና 28 ሊከናወን ታድቆ የነበረው የ24 ሰዓት የአደባባይ ተቃውሞ ግን በአገዛዙ የኃይል እርምጃ ምክንያት በታቀደው መንገድ ሊከናውን አልቻለም። የህወሓት ቅልብ የሆኑት ሲቪል የለበሱ ሰላዮችና የፌደራል ፓሊስ በተቃውሞው ተሳታፊዎች ላይ ኢሰብዓዊ የሆነ ጥቃት ፈጽመዋል።
ከጅምሩ፣ የፓርቲዎቹ ኅበረት የተቃውሞ ማሳወቂያ ደብዳቤውን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለማስገባት የገጠመው ችግር የህወሓት አገዛዝ የመንግሥትን መዋቅር ለፓርቲ ሥራ፤ የመንግሥት ተቀጣሪዎችን ደግሞ እንደ ህወሓት አገልጋዮች የሚጠቀምባቸው መሆኑ አንዱ ማሳያ ሆኗል። ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርጉ ማሳወቅ የፈለጉት ፓርቲዎች ህወሓት የዘረጋውን አፋኝ ሥርዓት የሚታገሉ በመሆናቸው ብቻ ደብዳቤዓቸውን የሚቀበል እንኳን አጥተው ተጉላልተዋል። ለሰልፉ ቅስቀሳ ማድረግም በራሱ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ ወጣቶች ተንገላተዋል፣ ተደብድበዋል፣ ታስረዋል። ያም ሆኖ ውጣ ውረዶች ታልፈው ቅዳሜ ህዳር 27 ቀን 2007 ዓ. ም. ደረሰ።
የኅበረቱ አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና ጥሪውን የሰማ ሕዝብ ወደ መስቀል አደባባይ ማምራት ሲጀምር ሲቪል የለበሱ የአገዛዙ ታጣቂዎች እና ፌደራል ፓሊሶች ከሰንደቅ ዓላማዎችና መፈክሮች ባለፈ አንዳች ነገር ያልያዙትን እድሜያቸው ከሃያዎች ያልዘለሉ ውድ የኢትዮጵያ ልጆችን ደብድበዋል፤ ብዙዎቹም አፍነው በአሰቃቂ ሁኔታ እያንገላቱ ወደ እስር ቤቶች ወስደዋል። ወጣቶች ተወልደው ባደጉበት አገር፤ ስሜታቸውን በነፃነት ለመግለጽ በመድፈራቸው ብቻ በጭካኔ ተረግጠዋል፤ ተፈንክተዋል፤ እጅና እግሮቻቸው ተሰብሯል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ይህ የህወሓትን ፋሺስታዊ እርምጃ አጥብቆ ይቃወማል። ግንቦት 7፣ ህወሓት ከስልጣን እስካልተወገደ ድረስ እንዲህ ዓይነቱን ፋሺስታዊ ተግባር መፈፀሙን የማይተው እኩይ ኃይል እንደሆነ ያውቃል፤ በዚህም ምክንያት የትግላችን ግብ ህወሓትን ማስወገድና በምትኩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁንታ ያገኘ መንግሥት መመሥረት መሆን ይኖርበታል ብሎ ያምናል፤ ለዚህም ይታገላል።
ግንቦት 7፣ ህዳር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. “መብቶቻችንን በህወሓት ዘረኛ አምባገነኖች አናስነጥቅም” በማለት አደባባይ የወጡ ወጣቶችን ጽናት ያደንቃል። ህወሓት የሚለውን ሳይሆን የይስሙላ ህጉ የፈቀደላቸውን ለማድረግ በመድፈራቸው በህወሓት የህግ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ የሚደረገውን ትግል አንድ እርምጃ ወደፊት አራምደውታል።
እያንዳንዱ የፓለቲካ ድርጅት ከዚህ ኩነት የሚወስዳቸው ተጨማሪ ትምህርቶች ቢኖሩም የሚከተሉትን ነጥቦች ብዙዎችን ያስማማሉ ብለን እናምናለን።
1. ህወሓት በምንም ዓይነት ቢሆን የያዘውን ስልጣን ለሕዝብ ፈቃድ ማስገዛት አይፈልግም፤
2. ህወሓት አገራችን ወደ ትርምስ እየገፋት እንደሆነ ግልጽ እየሆነ መጥቷል፤
3. ስልጣኑን የሚያሳጣው ከመሰለው እና አቅሙ እስካለው ድረስ ዘግናኝ እርምጃዎችን ከመውሰድ አይመለስም፤
ከህወሓት አገዛዝ መገላገል የሚቻለው ተገዶ ሲወገድ ብቻ ነው። ህወሓት እንዲወገድ ደግሞ የመጨቆኛ አቅሙ መዳከም ይኖርበታል። ህወሓትን የማስወገጃ አማራጭ መንገዶች ብዙ ሲሆኑ ተቀናጅተው ቢሠሩ የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ ብለን እናምናለን፤ “ሁለገብ ትግል” የምንለው የትግል ስልት ጭብጥ ይህ ነው። “እምቢ ለነፃነቴ” ብሎ የተነሳ ሕዝብ ህወሓትን ምን ያህል እንደሚያስደነግጥ በተደጋጋሚ ታይቷል። ህዳር 27ን መንደርደሪያ አድርገን በመውሰድ ከዚህ በተሻለ ለተደራጀ ሕዝባዊ እምቢተኝነትና አመጽ ራሳችን እናዘጋጅ።
በዚህ አጋጣሚ ግንቦት 7፣ ለመከላከያ ሠራዊት እና ፓሊስ አባላት ተደጋጋሚ ጥሪዎችን ማድረግ ይሻል። የመከላከያ ሠራዊት እና ፓሊስ አባላት እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ በህወሓት ዘረኛና አምባገነን አገዛዝ የተበደላችሁ መሆኑን እናውቃለን። የህወሓት ሹማምንት ከሆኑ አዛዦቻችሁ መላቀቅና ራሳችሁን ነፃ የማውጣት ኃላፊነት የወደቀው በእናንተው በራሳችሁ ላይ ነው። ሠራዊቱ ራሱን በራሱ ነፃ ማውጣት ይኖርበታል። የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ህወሓት መወገዱ የማይቀር በመሆኑ ሠራዊቱ ራሱን ነፃ አውጥቶ ከሕዝብ ጋር ካልወገደ እጣ ፈንታው የተሸነፈ ሠራዊት መሆን ነው። ከዚህ በላይ የሠራዊቱ አባል እየደበደበ ያለው የራሱን ልጅ፣ ወንድሙን ወይም እህቱን እንደሆነ ይወቅ። ይህ ወሳኝ ጊዜ ነው እያንዳንዱ የሠራዊቱ አባል በግል ኃላፊነት ያለበት መሆኑ ሊሰማው ይገባል።
በሁሉም ዓይነት የትግል ዘርፎች የኢትዮጵያ ወጣቶች በስፋት እየተቀላቀሉ መሆኑ ተስፋ ሰጪ ነው። ጊዜው የለውጥ ነው። የተለያዩ ስትራቴጂዎች ተደጋግፈው እንዲሄዱ መደረግ ያለበት ወቅት ላይ ነን። በህዳር 27 ቀን በህወሓት ቅልብ ሰላዮችና የፌደራል ፓሊሶች አማካይነት የደረሰው ጉዳትና የፈሰሰው ደም ለፍትህና ለነፃነት የተከፈለ ዋጋ ነው። ህመማችሁ ህመማችን፤ ትግላችሁ ትግላችን ነው። የተለያዩ መንገዶች ወደ ነፃነት አደባባይ እያመሩ ነው።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

Monday, December 8, 2014

የህወሃት ምርጫ የህዝብ መከራ!

ህወሃቶች እኛ ከሌለን ይህችን አገር እንበትናታለን፤ ይህችን አገር የምንሰብር እኛ የምንጠግን እኛ እያሉ እንደሚያሟርቱ ሰምተናል። እኛ የቀረፅነው ፖሊስ ከሚቀየር ሞታችንን እንመርጣለን እያሉ ማቅራራታቸውም ከህዝብ የተሰወረ ነገር አይደለም። የህወሃት ፖሊሲ የሚቀየረው በመቃብርችን ላይ ነው የሚል የማይናወፅ አቋማቸው መቼም ቢሆን በሠለጠነ መንገድ በውይይትና በድርድር እንደማይቀየር ደጋግመው አሳይተውናል። ህወሃቶችን በሠለጠነ መንገድ ተደራድሮ እና ሰጥቶ በመቀበል መርህ ለለውጥ አዘጋጃለሁ ማለት ከእባብ የእርግብ እንቁላል እንደመመኘት ያህል ነው። ከእባብ የእርግብን ዘር የሚጠብቅ ማን ነው?
እንግዲህ ህወሃቶች ይህን የመሰለ የከረረ አቋም ይዘው ምርጫ ለምን ያደርጋሉ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል። ይሄ ህወሃቶች ለኢትዮጵያና ለህዝቧ ራዕይ የሌላቸው ከመሆን የሚመነጭ ነው። ድርጅቱ ራዕይ አልባ የሆነው ደግሞ በህወሃት ውስጥ የተሰባሰቡ ግለሰቦች ራዕይ አልባ በመሆናቸው ነው። ህወሃቶች የሚኖሩለትም ሆነ የሚሞቱለት ቁም ነገር ከመብልና መጠጥ የዘለለ አይደለም። ህወሃቶች ራዕይ ቢኖራቸው ኑሮ በታሪክ የሚያስወቅሳቸውንና የህዝቡን ፍቅር የሚያሳጣቸውን እኩይ ተግባራት ባልፈፀሙ ነበር። ራዕይ የሌላቸው በመሆኑ ለሚፈፅሙት ወንጀል ሁሉ ገደብ እንዳይኖራቸው ሆኑ። ራዕይ ያለው ሰውም ሆነ ድርጅት እኔ ብቻ አይልም። ራዕይ የሰነቀ ድርጅትም ሆነ ሰው ከራሱ ክበብ አልፎ ሌላው እንደምን ሁኖ በሠላም እና በደስታ እንደሚኖር ያስባል እንጂ ዕለት ዕለት ደም በማፍሰስ አይኖርም።
ህወሃት በምርጫ ስልጣኑን እንደማይለቅ ለራሱ የማለ ድርጅት ነው። እዚህ መሃላ ላይ ያደረሰው ደግሞ እስከ ዛሬ የፈፀማቸው ወንጀሎቹ ናቸው።የጨበጠውን ስልጣን በምርጫ ቢለቅ ነገ የሚከተለውን ጠንቅቆ ያውቃል። ትላንት ያፈሰሱት የንፁሃን ደም ከኢትዮጵያ ምድር ላይ እየጮኸ ነው። ዘርፈው የገነቡት ህንፃ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ቆመው ሌብነታቸውን እየመሰከሩባቸው ነው። በልማት ሥም ከኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ተዘርፎ የተደራጀው የንግድ ተቋም በኢትዮጵያ ህዝብ ወዝና ደም ታጥኖ እንዳማረበት አለ። ህወሃት የኢትዮጵያ የህዝብ ጠላት ሆኖ ራሱን ያቆመ ቡድን በመሆኑ በሰላማዊ እና በሰለጠን መንገድ የያዘውን ሥልጣን ለህዝብ አይለቅም።
እንግዲህ ምን ይሻላል ?
ህወሃቶች ኑና እንወዳደር ብለዋል። እነዚህ ቡድኖች ኑና እንወዳደር ሲሉ እነርሱ የብረት ቦክስ ጨብጠው፤ ሌሎቹ ደግሞ ሌጣቸውን ሁነው ያለ በቂ ታዛቢ እንዲፎካከሯቸው ወስነው ነው። እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ሁነንም ቢሆን የምንወዳደረው ለነፃነት መሆን ይኖርበታል። ከነፃነት በመለስ ያለው ማንኛውም ዓይነት የምርጫ ውጤት በአገራችን እየተካሄደ ያለውን ዝሪፊያ፤ ዘረኝነት፤ እሥራት እና ግድያ ያስቆማል የሚል ዕምነት በማንም ዘንድ ያለ አይመስለንም። በምርጫ ውድድር የምናተርፈው የህግ የበላይነት፤ እኩልነት እና ነፃነት ካልሆነ ተጎጂው ሰፊው ህዝብ ይሆናል።
ህወሃት የብረት ቦክስ ጨብጦ እኛ ደግሞ ሌጣችንን ሁነን መወዳደር ፍትሃዊ አይደለም በማለት ድምፃቸውን እያሰሙ ያሉት ወገኖችም የህዝብን መሠረታዊ ፍላጎት ለሟሟላት አስፈላጊ የሆነው ነፃነት ዋነኛው ግባቸው መሆን ስለሚኖርበት ይመስለናል። ወደ ውድድር ከመግባታችን በፊት ህወሃት የብረት ቦክሱን ያውልቅ፤ የመወዳደሪያ መድረኩም እኩል ይሁን ማለታቸው የሚሰማ ቢኖር ፍትሃዊ ጥያቄ ነው።የህወሃትን የብረት ቦክስ ለማስወለቅ መሥዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውም ለነፃነት የሚከፈል ዋጋ ይሆናል። ከህወሃት ጭካኔና ድንቁርና ስንነሳ በዚህ መንገድ የሚሄዱት የሚከፍሉት መሥዋዕትነት ከባድ እንደሚሆን እንጠብቃለን። ግን ደግሞ ነፃነት ያለ መሥዋዕትነት እንደማይገኝ ሌላው ቀርቶ ነፃነትን የማያውቁት ህወሃቶች ያውቃሉ። በማንኛውም መልኩ ከህወሃቶች ጋር አገት ለአንገት ተናንቀው በአገር ቤት ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ያሉት ድርጅቶች ልበ ሙሉነታቸውን እጅግ አድርገን እናደንቃለን። እምቢ ለነፃነቴ፤ እምቢ ለክብሬ፤ እምቢ ለህወሃቶች ቀይ መስመር ማለት ይሄ እንጂ ሌላ አይደለም። እንግዲህ ዘረኞቹና ዘራፊዎቹ ቡድኖች ሊያደርሱ የሚችሉትን ጉዳት መቀነስ የሚቻልበትን መንገድ ማሰብ ተገቢ ይሆናል። ህዝቡ በልዩ ልዩ ሰንሰለት የታሠረ በመሆኑም በሚፈለገው መጠን ወጥቶ የትግሉ አካል ካልሆነም ተስፋ መቁረጥ አይገባም።በተጀመረው ላይ ይበልጥ እያጠናከሩና እየጨመሩ እየተካሄደ ያለውን ትግል መቀጠል ምርጫ የሌለው ሥራ ነው።
ግንቦት ሰባት የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አገር ቤት ሁነው ከጭካኔ በቀር ሌላ ዕውቀት ከሌላቸው ህወሃቶች ጋር በትግል ላይ ያሉ ድርጅቶችን ያደንቃል። ያመስግንማል። በርቱ ከማለት በቀር የምንለው ሌላ የለንም።
እኛ የጀመርነውን ሁለ ግብ ትግል እያጠናከርነው ነው። የአገራችንን ውርደት፤ የወገኖቻችንን ጉስቁልና እያየን ዝም ብንል እርግማን ይሁንብን ያሉ ወጣቶች የአያቶቻቸውን ጋሻና ጦር አንስተዋል። እናቶችም ልጆቻቸውን መርቀው ፋኖ ተሠማራ ብለዋል። ሌሎች ደግሞ የኋላ ደጀን ሁነው ሳያቅማሙ ቁመዋል። ብዙ ባለሙያዎች ለአገራቸው የሚከፈልውን መሥዋዕትነት ለመክፈል ተዘጋጀተዋል።
እንግዲህ የጀመርነውን ትግል የሚያስቆመን ምድራዊ ኃይል የለም። የህወሃት የመረጃ መረብ ይበጣጠሳል። የጦር ኃይሉ ከጥቂት ዘረኞችና ሌቦች ይልቅ ወገኑን እንደሚመርጥ በየቀኑ የሚደርሱን መረጃዎች ያሳዩናል። የከተማው ህዝብ ህወሃቶችን አክ እንትፍ ካላቸው ብዙ ዘመን ሁኖታል። የገጠሩም ህዝብ የህወሃት ዋሻ የመሆኑ ነገር አብቅቷል። ይሄ ሁሉ የእኛ አቅማችን ነው። ይሄን አቅም አደራጅተንና ሥራ አሲይዘን አገራችንን ነፃ የምናወጣበት ግዜ ሩቅ አይደለም።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !



    ከኢቲቪ ዋና ሥራአስኪያጅነት በአቅም ማነስ ተሰናብተው ለማካካሻ ወደ ኢትዮጽያ ብሮድካስት ባለስልጣን የተመደቡት አቶ ዘርዓይ አስገዶም በብሮድካስት ባለስልጣን የህትመት ድርጅቶች የሚገቡት አስገዳደጅ ውል በማዘጋጀት በግዴታ በማስፈረም ላይ መሆናቸው ተሰማ፡፡

    -ባለስልጣኑ አሳታሚዎች ዓመታዊ የንግድ ፈቃዳቸውን ለማሳደስ ወደንግድ ሚኒስቴር ሲሄዱ በየዓመቱ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ እንዲያቀርቡ የሚገደዱ ሲሆን የሙያ ብቃቱን ለማግኘት ባለፉት ወራት ወደብሮድካስት ባለሰልጣን የሄዱ አሳታሚዎች ያልጠበቁትን ግዴታ እነዲገቡ የሚቃወሙ ከሆነ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሠርተፊኬት እንደማይሰጣቸው በተነገራቸው መሠረት አብዛኛዎቹ ተገደው ፈርመዋል፡፡
    በንግድ ምዝገባ ፈቃድ መስጫ መደብ ቁጥር 89 ሺ 510 የጋዜጣና መጽሔት አሳታሚ የምዝገባ ምስክር ወረቀት የሚሰጣቸው ሰዎች ከሚፈርሙዋቸው ግዴታዎች መካከል ” የተሟላ የሥራ ሪከርድ እና ሰነዶች አደራጅቼ እይዛለሁ፣ ለምርመራ ሲፈለግም ለባለሰልጣኑም ሆነ ለሚመለከታቸው ሕጋዊ አካል የማቀርብ መሆኔን አረገጋግጣለሁ”  የሚል ይገኝበታል፡፡ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት አዋጁ ቁጥር 590/2000 አክብሬ አስራለሁ የሚልም ተከታይ አስገዳጅ ውል ውስጥ ሰፍሮአል፡፡
    አሳታሚዎች በተለይ “ሰነድ አሳያለሁ፣ ሪከርድ እይዛለሁ” የሚለው አስገዳጅ አንቀጽ ከባለስልጣኑ ሥልጣን ውጪ የሆነና የፕሬስ ነጻነትን የሚጻረር መሆኑን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ አሳታሚዎቹ በሥራ ላይ ያለ አዋጅ አክብሮ መሥራት የሁሉም ዜጋ ግዴታ መሆኑ እየታወቀ እንደገና በውል አከብራለሁ የሚል አስገዳጅ ፊርማ ለምን እንደተቀመጠ ግራ እንደገባቸው፣ ምናልባት አሳታሚዎች ተሸማቀው በጋዜጣና መጽሔት ይዘቶቻቸውን ምንም ዓይነት የተቃውሞ ጽሑፍ እንዳያስተናግዱ የተደረገ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡
    በዚሁ አስገዳጅ ውል አንቀጽ 9 ላይ «ከባለለስልጣኑ የምዝገባ የምስክር ወረቀት ስወስድ የመረጥኩትን ይዘት ከባለለስልጣኑ ዕውቅና ውጪ ለውጥ ባደርግ እና የብቃት ማረጋገጫ መስፈርቱን መሰረት የህትመት ሥራዬን ባላከናውን የተሰጠኝ የምዝገባ የምስክር ወረቀት ሊሰረዝብኝ እንደሚገባ ተስማምቼ ይህን የውል ግዴታ መግባቴን በፊርማዬ አረጋግጣለሁ» የሚልም ሰፍሯል፡፡ ይህ አንቀጽ ምናልባትም እነ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የመሳሰሉ ጋዜጠኞች አንዱ ሕትመት ሲዘጋባቸው በሌላ ህትመት ብቅ የማለታቸው ልምድ ሌሎችም እንዳይከተሉት  ለመዝጋት ሆን ተብሎ የተቀመጠ ሊሆን እንደሚችል ጉዳዩን የተከታተሉ ወገኖች ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
    የመንግስትን ኢፍትሃዊ አሰራሮችን በድፍረት በመዘገብ የሚታወቁት ጋዜጦች ከመንግስት በሚደርስባቸው ጫና እንዲዘጉ መደረጉ ይታወቃል። በርካታ ጋዜጠኞች በእስር ላይ ሲገኙ ብዙዎቹ ደግሞ ወደ ጎረቤት አገሮች ተሰደዋል።
     ኢሳት ዜና

    Friday, December 5, 2014

    የሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ በፖሊስ ተከብቦ አደረ

    ምንነቱ የማይታወቅ ወረቀት ሲበተን አድሯል

    የሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት በፖሊስ ተከብቦ ማደሩንና አባላት ከውጭ እንዳይገቡ መደረጋቸውን ለአዳር ሰልፉ ቅስቀሳ ዝግጅት ቢሮ ያደሩ የፓርቲው አመራሮችና አባላት ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ አመራሮችና አባላቱ እራት በልተው ወደ ፓርቲው ጽ/ቤት ሲመለሱ ቢሮው በፖሊስ ተከብቦ እንዳገኙትና ወደ ውስጥ እንዳይገቡ እንደተከለከሉ በቦታው የነበሩት የፓርቲው አመራሮችና አባላት ገልጸዋል፡፡ 

    አመራሮችና አባላቱ ፖሊስ ከ200 ሜትር ርቀት ውጭ ወደ ፖለቲካ ፓርቲ ጽ/ቤት መጠጋት እንደማይችል ቢከራከሩም ፖሊሶቹ ‹‹መመሪያ ተሰጥቶናል፤ አንሄድም!›› ማለታቸው ገልጸዋል፡፡ አመራሮቹና አባላቱ ከፖሊስ ጋር ሲከራከሩ የአካባቢው ህዝብ በመውጣቱ ፖሊሶቹ ፓርቲው ጽ/ቤት እንደራቁ ታውቋል፡፡

    በሌላ በኩል ከውጭ ወደ ቢሮ ከሚመጡበት ወቅት የፓርቲው ቢሮ አካባቢ ምንነቱ ያልታወቀ ወረቀት ተበትኖ እንዳገኙና እነሱ ሲደርሱ ፖሊሶቹ እንዳነሱት የፓርቲው የምክር ቤት አባል ወጣት እየሩስ ተስፋው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጻለች፡፡

    Thursday, December 4, 2014

    ፀረ-ኢትዮጵያዊውና ዘረኛው ወያኔ በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ስም አይነግድም!

    ኮለምበስ፣ ኦሃዮ – ፀረ-ኢትዮጵያዊውና ዘረኛው ወያኔ በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ስም አይነግድም!

    December 3, 2014
    መርሐ አንድነት የኢትዮጵያውያን ሲቪክ ማህበር በኮለምበስ፣ ኦሃዮ

    Click here for PDF

    የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ቅጥረኛ የሆነው ፀረ-ኢትዮጵያዊውና ቅኝ-ገዥው ወያኔ ባሕር ማዶ ተሻግሮ በሃገረ አሜሪካ ኮለምበስ ኦሃዮ “በስሜን አሜሪካ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች Tigray People Front, TPLFየባሕል ክብረ በዓል” በሚል ስም እሑድ ኅዳር 28 ቀን 2007 ዓ/ም ( Sunday, December 7, 2014 ) ከቀኑ 1:00pm ጀምሮ በሃያት ረጀንሲ ሆቴል (Hyatt Regency Hotel @ 350 North High Street, Columbus, OH 43215) ለማክበር በዝግጅት ላይ ይገኛል። ለዚህ በዓል መሰናዶ፤ ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የወያኔ ኢምባሲ የበላይ መሪ በመሆን፤ በአካባቢያችን ያሉትን የለየላቸው ከሃዲዎችና የባንዳ ልጆችና የልጅ ልጆች በአስተባባሪነት በማሰለፍ ነው።
    ለአለፉት 23 ዓመታት ሃገራችንን ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር በማዋል የፖለቲካውን ኃይል፣ የኢኮኖሚውን ዘርፍ፣ የማህበራዊ አውታሩን፤ የወታደራዊ ተቋሙንና የደኅንነቱን መረብ በሙሉ የተቆጣጠረው ፀረ-ኢትዮጵያዊውና ዘረኛው ወያኔ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የባሕል ክብረ በዓል ለማክበር የኅሊና ብቃት አለው ወይ?
    1. ማን ሆነና ነው ብሔር ብሔረሰቦችን እርስ በእርሳቸው ለያይቶና ከፋፍሎ የሚያስጨራርሰው?
    2. ማን ሆነና ነው ብሔር ብሔረሰቦችን በሃይማኖት ከፋፍሎ የሚያወዛግበውና የሚያዋጋው?
    3. ማን ሆነና ነው ወገናችን አማራውን፣ ኦሮሞውን፣ ሱማሊውን፣ አኝዋኩን፣ አፋሩን ወዘተ… እየጨፈጨፈ የምድር ሲዖል እያሳየ የዘር ማጽዳት ዘመቻ የሚያካሂደው?
    4. ማን ሆነና ነው በቅርብ ጊዜ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩትን አማራዎች ሃብትና ንብረታቸውን እያዘረፈ፣ ቤታቸውን እያቃጠለና እየገደለ ከሃገራችን ውጡ እያለ ከጉራፈርዳ፣ ከቤኒሻንጉል-ጉሙዝ፣ ከጋምቤላ ወዘተ.. ያፈናቀለውና ያባረረው?
    5. ማን ሆነና ነው ለቀንደኛ ደንበር-ዘለል ተስፋፊና ዘራፊ ሃገሮችና ኩባኒያዎች ለም ድንግል መሬቶቻችንን በመሸጥ በመቶ ሺህዎች የሚገመቱትን የደቡብ ኢትዮጵያና የጋምቤላ ብሔር ብሔረሰቦችን ከቀያቸው በማፈናቀል ሃገራችንን ለከፍተኛ አደጋ ያጋለጠው?
    6. ማን ሆነና ነው ከፍተኛ የተፈጥሮ ሃብት ክምችት ያለውን የሃገራችንን ዳር-ድንበር ለም መሬት ለሱዳን የሽጠው?
    7. ማን ሆነና ነው የብሔር ብሔረሰቦችን የጋራ ማህበራዊና ባሕላዊ እሴቶቻቸውንና አብሮነታቸውን የሸረሸረውና ለማጥፋት ተንኮልንና ሴራ የሚሸርበው?
    8. ማን ሆነና ነው ርካሽና አስነዋሪ የባእድ ባሕሎች በብሔር ብሔረሰቦቻችን ላይ እንዲስፋፋ ያደረገው?
    9. ማን ሆነና ነው በሺህዎች የሚቆጠሩትን ወገኖቻችንን በብሔር ማንነታቸው እየወነጀለ ወደ ወህኒ የሚወረውረው?
    10. ማን ሆነና ነው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ቁጥር አንድ አጀንዳውን አንግቦ ከደደቢት፣ ትግራይ የተነሳው?
    ይህን ሁሉ ግድያ፣ ግፍ፣ መከራ፣ በደልና ሰቆቃ በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ላይ የሚፈጽመው ፀረ-ኢትዮጵያዊውና ዘረኛው ወያኔ አይደለምን? አዎ ነው። ስለዚህ፣ እኛ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ልጆችም በነፍስ ገዳያችን ድግስ አንገኝም። በታላቅ ቆራጥነት በነፍስ ገዳያችን ላይ ሕዝባዊ ትግሉን እናጧጥፋለን እንጅ።
    ስለዚህ፣ በኮለምበስ ከተማና በአካባቢው ከተሞች፤ እንዲሁም በአጎራባች ስቴቶች የምትገኙ ሃገር-ወዳድ ኢትዮጵያውያን፤ ዘረኛውና ጎጠኛው ወያኔ እሑድ ኅዳር 28 ቀን 2007 ዓ/ም ( Sunday, December 7, 2014 ) ከቀኑ 1:00pm ጀምሮ ኮለምበስ ኦሃዮ በሚገኘው ሃያት ረጀንሲ ሆቴል ( Hyatt Regency Hotel @ 350 North High Street, Columbus, OH 43215) በጠራው ስብሰባ ላይ እንዳትገኙ፤ ወራሪውንና ፋሽስቱን ወያኔ ሲፋለሙ በታላቅ ጀግንነት በተሰውት የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የሱማሊ፣ የአኝዋክ፣ የአፋር ወዘተ… የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ልጆች ስም ሃገራዊ ጥርያችንን እናስተላልፋለን። ሆኖም ግን፣ ይህን ሕዝባዊ ጥሪ ባለመቀበል በዚህ የወያኔ ስብሰባ የምትገቡ፤ የተሰውትን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ልጆች አጥንት ረግጣችሁ እንደገባችሁ እወቁት። እኛም እንደ እናንተ ያለውን ሆድ-አደር ባንዳ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በይፋ የምናጋልጥ መሆኑን ከወዲሁ በጥብቅ እናሳስባለን።
    የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት በትግላችን ይመሠረታል!
    ፀረ-ኢትዮጵያዊውና ቅኝ-ገዥው ወያኔ በሕዝባዊ ክንዳችን ይደመሰሳል!
    ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
    መርሐ አንድነት የኢትዮጵያውያን


      ሲቪክ ማህበር በኮለምበስ፣ ኦሃዮ

      Monday, December 1, 2014

      ከ40 በላይ የአንድነት አባላትና አመራሮች በቃሊቲ እስር ቤት ታገቱ

      Nov 29, 2014 (በኤልያስ ገብሩ)
      የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሃን ጨምሮ ከአርባ በላይ የሚሆኑ የፓርቲው አባላት ቃሊቲ እስር ቤት ውስጥ ታገቱ፡፡
      አንድነት ፓርቲ የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች በሚል መሪ ቃል ከህዳር 14 ጀምሮ እያካሄደያለው የማህበራዊ ሚዲያ ንቅናቄ አካል የሆነውን የህሊና እስረኞችን የመጎብኘት መርሀ-ግብር ለመሳተፍ ወደ ቃሊቲ እስር ቤት ያቀኑት የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሃ እና የፓርቲው የአዲስ አበባ ሰብሳቢ አቶነገሰ ተፋረደኝን ጨምሮ 40 የአንድነት ፓርቲ አባላት ለግዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ሰበብ በእስር ቤቱ ግዜያዊ ማቆያ እንዲገቡ መደረጋቸውን የፍኖተ ነፃነት ምንጮች ከስፍራው ዘግበዋል፡፡
      አንድነት የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች በሚል መሪቃል በዚህ ሳምንት እያካሄደ ያለው ንቅናቄ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን ትኩረት ማግኘቱ ገዢውን ቡድን ማስቆጣቱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
      ዘግይቶ የደረሰን ዜና እንዳመለክተው ከሆነ ደግሞ; የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ነገሰ ተፈረደኝ፣ ንዋይ ገበየሁ፣ ዳንኤል ሙላትና አቶ ብርሐኑና ትግስት ክራውን ሆቴል አካባቢ አሁንም ታስረው እንደሚገኙ ምንጮች ገለጹ፡፡
      ስማቸው ከላይ የተጠቀሱት ግለሰቦች የታሰሩ የህሊና እስረኞችን ለመጠየቅ ወደቃሊቲ አምርተው ከነበሩት ሰዎች መካከል ይገኛሉ፡፡

      ተማሪዎች፣ መምህራን እና የተቋማት ፕሬዚዳንቶች ለአመጽ ተነሱ!

      ዘረኛውና አምባገነኑ የህወሓት አገዛዝ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ከካድሬ ማሰልጠኛ ማዕከላትነት ለይቶ የማያይ ስለመሆኑ በተቋማቱ ውስጥ የሚደረጉ ተግባራት ማረጋገጫዎች ናቸው። ለዚህ ተግባሩ በሰነድ ደረጃ መቅረብ ከሚችሉት የቅርብ ጊዜ ማስረጃዎች ዋነኛው በህዳር 2007 ዓ.ም. በሥራ ላይ የዋለው “የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኢህአዴግ የምርጫ ድል ልማት ሰራዊት ግንባታ አደረጃጀት ማንዋል” የተሰኘው በትምህርት ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ለሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተላለፈው ሰነድ ነው። ይህ ሰነድ፣ የህወሓት አሳፋሪ የትምህርት ፓሊሲ ባፈጠጠ መልኩ የተገለፀበት፤ የኢፌዴሪ መንግሥት ተብሎ በሚጠራው የህወሓት አገዛዝ ተቋም እና በህወሓት/ኢህአዴግ ፓርቲ መካከል ለይምሰል እንኳን ልዩነት አለመኖሩ በግላጭ የሚታይበት ሰነድ በመሆኑ በዚህ ርዕሰ አንቀሳችን በስፋት ልንዳስሰው ወስነናል።
      ሰነዱ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ መርዙን መርጨት የሚጀምረው ገና በመግቢያው ስለማንዋሉ አስፈላጊነት ሲገልጽ ነው። ማንዋሉ “ከምንም በላይየብጥብጥና የሁከት መንስኤ የሆነውን ተማሪ በኢህአዴግ አመራር አባላት እየታገዙ ለመያዝ የሚያስችል ነው” በማለት ህወሓት ተማሪውን የሚመለከተው “ከምንም በላይ በብጥብጥ መንስኤነት” መሆኑ፤ ለዚህ መድሀኒቱ ደግሞ ተማሪውን በኢህአዴግ አመራር አባላት “መያዝ” መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ይገልፃል። ቀጥሎም “በምርጫው ሊፈጠር የሚችለውን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሁከትና ብጥብጥ ለማስቆም በማደራጀት መረጃ ለመጥለፍ አመችነቱ የላቀ እንደሚሆን ታምኖበታል” በማለት መረጃ መጥለፍ የዩኒቨርስቲዎችና የትምህርት ሚኒስቴር ሥራ እንደሆነ አድርጎ ያቀርባል።
      የማንዋሉን ዓላማዎች በሚገልፀው ክፍል ደግም “… የከፍተኛ ትምህርት የትምህርት የልማት ሰራዊት ግንባታን ወይም የፓለቲካ ሰራዊት ግንባታ በሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተደራጀና በተናቀጀ ሁኔታ በማቀጣጠልና በማስቀጠል … ምርጫ 2007 ውጤታማ ለማድረግ እና የኢህአዴግን አሸናፊነት ለማረጋገጥ ነው” በማለት ተቋማቱን የኢህአዴግ የምርጫ መሣሪያ መሆናቸውን፤ ግባቸውም የኢህአዴግ አሸናፊነትን ማረጋገጥ መሆኑ ይገልፃል።
      በገጽ 3 ላይ ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች “በኢህአዴግ ላይ ያላቸው አቋም የወረደ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በማንኛውም ተቃውሞ ድምፅ ከተጠሩ፤ ሰልፍ የሚያደምቁ፤ ተቃውሞን ከግብ ለማድረስ ሁነኛ መሳሪያ ናቸው። ተማሪዎች በየትኛውም ሐገር እንደታየው አደባባይን የመያዝ ህዝብን አስተባብረው ለተቃውሞ የማሳደም እድላቸው የሰፋ በመሆኑ ከዚህም ሲያልፍ፤ የኢህአዴግ ምከታን በመቃወም ለጠላት ጎራ ተሰልፈው የመታጠቅ እድላቸው ከፍተኛ ነው” ሲል “በወጣቱ እጠላለሁ” የሚለው የህወሓት/ኢህአዴግን ስጋት አፍረጥርጦ ያወጣል። ትንሽ ወረድ ብሎ ደግሞ “በተለይ በአሁኑ ሰዓት ፈተና ላይ የጣለን የምርጫ ጉዳይ እንደምናሸንፍ ቃል የተያዘለት ቢሆንም፤ ፈተናዎች የሚፈጠሩት በህዝብ እና በራሱ ታማኝ ባልሆኑ ሃይሎች ማለትም በመንግስት ክንፍ አይቀለበስም ብሎ ማሰብ አይቻልም። በዚህም ቀድሞ መዘጋጀት ያለበት እና ለሁከት እና ለብጥብጥ መሳሪያ ሊሆን የሚችለው የህዝብ ክንፍ የተማረው ሃይል ሊሆን ስለሚችል ሊታሰብበት ይገባል” ሲል በተማረው ወጣትና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሠራተኞች ላይ ያለው ጥርጣሬና ፍርሃት ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ይገልፃል።
      የ2007 ምርጫ በህወሓት ሹማምንት ላይ የፈጠረውን ጭንቀት በዚህ ሰነድ ላይ በገሀድ የሚታይ በመሆኑ እያንዳንዱ ዓረፍተ ነገር በጥንቃቄ ሊነበብና ሊተነተን የሚገባው ነው። ለምሳሌ በገጽ 6 ላይ ስለዩኒቨርስቲ ተማሪ ሲገልጽ “የአመፅ እና የብጥብጥ መነሻ ሊሆን የሚችል ሀይል መሆኑን በአክራሪዎች ሲጠለፍ፤ ከመንግስት ሃይማኖቱን እየመረጠ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ፤ በጅማ ዩኒቨርስቲ፤ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ እና በሌሎችም ትምህርቱን ትቶ ሲኮበልል ተመልክተናል” ይላል። ለተማሪዎች፣ ከመንግሥት እና ከሃይማኖት አንዱን እንዲመርጡ ተደርጎ ሃይማኖታቸውን የመረጡ መኖራቸውን እና ይህ ደግሞ አደገኛ ነገር መሆኑን ነው ይህ ዓረፍተ ነገር የሚነግረን። ለመሆኑ ይህ ምን የሚሉት ምርጫ ነው? በእንዴት ያለ ሥርዓት ነው ዜጎች ከመንግስትና ከሃይማኖት አንዱን ምረጡ የሚባለው? እንዲህ ዓይነት ምርጫ ቀርቦ ሃይማኖትን መምረጥ እንዲህ ክፉ ነገር የሆነው ለምንድነው? ይህ ጉዳይ ብቻውን ብዙ የሚያነጋገር ነገር አለው።
      በገጽ 8 ላይ ደግሞ “ከፍተኛ አመራሩ ተቋማዊ ለውጥ እንዲሁም የትምህርት ልማት ሰራዊት ግንባታ ቴክኒካዊ ሳይሆን ፓለቲካዊ ጉዳይ መሆኑን ተገንዝቦ ካለእርሱ ባለቤትነትና ቀጥተኛ ተሳትፎ ሰራዊት መገንባት እንደማይቻል በመገንዘብ የመሪነት ሚናውን ካለምንም ማወላዳት መወጣት ይጠበቅበታል” በማለት እየተሠራ ያለው የፓርቲ ወገንተኛ የሆነ ፓለቲካ መሆኑን ብቻ ሳይሆን የትምህርት ተቋማት መሪዎች ዋና ተልዕኮ ትምህርት ማስተማር ሳይሆን የወያኔ ፖለቲካን ማስፈጸም መሆኑን ምንም ሳይጎረብጠው ፍርጥርጡን ያወጣዋል። ትንሽ ወረድ ብሎም “የጋራ መግባባት የምንለካው በመጀመሪያ ለምርጫው የኢህአዴግ የድጋፍ የድል ሰራዊት ብዛት ነው” በማለት ከላይ ያለውን በማጠናከር ወገንተኛነቱም ለኢህአዴግ መሆኑ ያውጃል። በመጨረሻም “ … ሁሉም የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶች ውጤታቸው የሚሞላላቸው ለምርጫው በሚያዘጋጁት የድጋፍ ሃይል ይወሰናል” በማለት የአካዳሚ ነፃነት ብቻ ሳይሆን የከፍተኛ ትምህርት ሥርዓትን ለቀብር ያዘጋጃል።
      ይህ ነው የህወሓት የትምህርት ፓሊሲ! የዩኒቨስቲዎች ቁጥር ለማመን በሚቸግር መጠን ቢጨምር፤ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ቅበላ በብዙ መቶኛዎች ቢያድግ ጥቅሙ ምኑ ላይ ነው። በእንዲህ ዓይነቱ ፓሊሲ ከተገነባ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም ይገኛል የምንለው ፋይዳ ምንድነው?
      ህወሓት በገሀድ በጠላትነት የፈረጃቸው የአገራችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ መምህራንና ሠራተኞች ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ በአጽንኦት እንዲመለከቱ ግንቦት 7፣ የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ያሳስባል። ትውልድንም የትምህርት ሥርዓቱንም የማዳን ግንባር ቀደም ኃላፊነት በተማሪዎችና በመምህራን የወደቀ ሸክም ነው ብሎ ግንቦት 7 ያምናል። መላው የትምህርት ሥርዓት ለአንድ ፓርቲ የምርጫ ውድድር መሣሪያነት ሲውል ማየት እና የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶች የሥራ አፈፃፀም የሚወሰነው ለገዢው ፓርቲ ባስገኙት ድምጽ ብዛት ነው መባሉ፤ እነሱም ይኸንን ተቀብለው መሥራት መቀጠላቸውን የመሰለ አሳፋሪ ነገር በአካዳሚያ ውስጥ የለም። የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን ይህን ውርደት መቀበል የለባቸውም። ሰነዱ ህወሓት ከፍተኛ ትምህርትን የሚመለከትበት ዕይታ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነውና ለምርጫ ወቅት ብቻ የተዘጋጀ የአጭር ጊዜ መመሪያ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ይህ ሰነድ ህወሓት፣ ተማሪዎችንና መምህራንን እንደጠላት፤ ተቋማቱን ደግሞ ጠላትን እንደመቆጣጠሪያ መሣሪያ እንደሚመለከት፤ ይህ ዕይታው ደግሞ ቋሚ መሆኑ በግልጽ ያሳያል። በህወሓት ዕይታ ከተገነቡ ተቋማት ምን ዓይነት ትምህርት ይገኛል?
      የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የትምህርት ኃላፊዎችና ፕሬዚዳንቶች ሆይ! ለገዛ ራሳችሁ ክብር፣ ለአካዳሚ ነፃነት፣ ለትውልድ ስትሉ በዚህ መመሪያ ላይ አምጹ! “እንቢ፣ አሻፈረን፣ በዚህ መመሪያ አንገዛም” በሉ! የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናችሁ ይቆማል።
      ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!


        ginbot7.org