Wednesday, November 11, 2015

ሰማያዊ ፓርቲ ህዳር 18 ህዝባዊ ስብሰባ ጠራ • መስተዳደሩ ለ5ኛ ጊዜ ማሳወቂያ ደብዳቤውን አልቀበልም ብሏል • ‹‹መልካም አስተዳደር የሚባለው ከወሬ ያለፈ እንዳልሆነ ያሳያል›› ኢ/ር ይልቃል ጌትነት -

ሰማያዊ ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከአባላቱና ደጋፊዎቹ ጋር ውይይት ለማድረግ ህዳር 18/2008 ዓ.ም በመብራት ኃይል አዳራሽ ህዝባዊ ሰብሰባ እንደሚያደርግ ሊቀመንበሩ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ይሁንና የማሳወቂያ ደብዳቤውን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት በአካል ለማድረስ ጥረት ቢደረግም በሰራተኞቹ ዘንድ ለአምስተኛ ጊዜ ‹‹ኃላፊዎቹ የሉም፡፡ እኛ አንቀበልም›› መባላቸውን ም/ሊቀመንበሩ አቶ ነገሰ ተፋረደኝ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ‹‹ጠዋት ስንሄድ፣ ከሰዓት ኑ፣ ከሰዓት ስንሄድ፣ ስብሰባ ላይ ናቸው ጠዋት ኑ እያሉ 5 ጊዜ አንቀበልም ብለውናል፡፡›› ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ‹‹ለአንድ መስሪያ ቤት ደብዳቤ ለማድረስ በመዝገብ ቤት አሊያም በፀኃፊ በኩል መቀበል በቂ ነው፡፡ ኃላፊውን የግድ መጠበቅ አያስፈልግም ነበር፡፡›› ያሉት ኢ/ር ይልቃል ‹‹ይህ አስተዳደራዊ በሆነ መንገድ ህገ መንግስታዊ መብትን የሚያግዱበት ስልት ነው›› ብለዋል፡፡ ሊቀመንበሩ አክለውም ‹‹ስለመልካም አስተዳደር በሚያወሩበት በአሁኑ ወቅት አስተዳደራዊ በሆነ መንገድ መብትን እያገዱ መቀጠላቸው መልካም አስተዳደር የሚባለው ከወሬ ያለፈ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው›› ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት ለ5ኛ ጊዜ የሰማያዊ ፓርቲን የስብሰባ ማሳወቂያ ደብዳቤ በአካል መቀበል ባለመፈለጉ ፓርቲው ደብዳቤውን በሪኮመንዴ ለመላክ መገደዱን ፓርቲው ለፅ/ቤቱ በላከው ደብዳቤ ላይ አመላክቷል፡፡ በዚህም መሰረት ዛሬ ህዳር 1/2008 ዓ.ም ፓርቲው ማሳወቂያውን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት በሪኮመንዴ መላኩን ሊቀመንበሩ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48184#sthash.cioSnkrv.dpuf

Tuesday, November 10, 2015

በሰሜን ጎንደር ዞን በርካታ የልዩ ሃየል አባላትና ሰላማዊ ዜጎች ተገደሉ

ኢሳት ዜና :-ከቅማንት ብሄረሰብ ጥያቄ ጋር በተያያዘ በአርሶ አደሩና በክልሉ ልዩ ሃይል መካከል ከማውራ 15 ኪሜ ርቃ በምትገኘዋ ሮቢት አካባቢ እንዲሁም በላይ አርማጭሆ ዋና ከተማ ትክል ድንጋይ ከፍተኛ ውጥረት ነግሶአል። እስከትናንት ድረስ በአርሰዶ አደሩና በልዩ ሃይል መካከል በተደረገ የተኩስ ለውጥጥ ከ100 በላይ የልዩ ሃይል አባላት ሲገደሉ፣ ከ36 ያላነሱ ንጹሃን ዜጎች ደግሞ በልዩ ሃይል አባላት ተገድለዋል። ዛሬ በበርካታ መኪኖች የተጫኑ የመከላከያ ሰራዊት አባላትና የልዩ ሃይል አባላት ከባድ መሳሪያዎችን ሳይቀር ወደ ትክል ድንጋይ በማስገባቱ ህዝቡ ቤቶቹን ዘግቶ ከመቀመጡም በላይ፣ ትምህርት ቤቶች የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የንግድ ድርጅቶች በሙሉ ተዘግተዋል። የልዩ ሃይል አባላት የተገደሉባቸውን ባልደረቦቻቸውንሊበቀሉ ነው በሚል የቻለው ወደ ጫካ መውጣቱንም ያካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ተናግረዋል። በርካታ የተገዱ የልዩ ሃይል አባላት በአዘዞ የመከላከያ ካምፕ እና በጎንደር ሪፈራል ሆስፒታል መወሰዳቸውን የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። የልዩ ሃይል አባላት እህትማማች ሴቶችን በጩቤ ገድለው መገኘታቸውን የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ አስነዋሪ በሆነ መልኩ ባለትዳር ሴቶችን ሳይቀር መድፈራቸው የህዝቡን ቁጣ አባብሶታል በማለት ነዋሪዎች ተናግረዋል። ጥያቄውን ከሚያስተባብሩ ወገኖች መካከል አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ሰው ለኢሳት እንደተናገሩት በህዝቡ በኩል ከልዩ ሃይል አባላት መካከል 102 ከህዝቡ ደግሞ 33 ሰዎች ተገድለዋል ይላሉ።

Monday, November 9, 2015

በጎንደር ጭልጋና ትክል ድንጋይ መካከል በሚገኝ ማውራ የተባለ ቦታ በገበሬዎችና በህወሓት ልዩ ኃይል ጦር መካከል ውጊያ ተካሄደ - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48081#sthash.FOzLOtJp.dpuf

በጎንደር ጭልጋና ትክል ድንጋይ መካከል በሚገኝ ማውራ የተባለ ቦታ ላይ በአካባቢው ገበሬዎችና በህወሓት ልዩ ኃይል ጦር መካከል ከፍተኛ ግጭት ተቀስቅሶ ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ፍልሚያው የተጀመረው ትናንት ረፋድ ላይ ሲሆን አሁንም ተባብሶ እንደቀጠለ ነው፡፡ አካባቢው ትንሽ እንኳን ፋታ በሌለው ተከታታይ የጦር መሳሪያ ፍንዳታ ድምፅ እየተናጠ ይገኛል፡፡
እስካሁን ድረስ በደረሰን መረጃ መሰረት በትንሹ 5 የልዩ ኃይሉ ጦር አባላት ተገድለዋል ከ9 በላይ ደግሞ ቆስለዋል፡፡ ነገር ግን በማውራ ገበሬዎች በኩል የደረሰ ጉዳት ይኑር አይኑር ምንም የታወቀ ነገር የለም፡፡
የጎንደር-ጭልጋ ማውራ ገበሬዎችንና የህወሓትን ልዩ ኃይል ለመዋጋት ያበቃቸው ምክንያት ምን እንደሆነ በውል ተለይቶ አልታወቀም፤ ነገር ግን በጭልጋና አካባቢው ቀደም ሲል የተነሳው የብሄር ጥያቄ ሳይሆን እንዳልቀረ ምንጮቻችን ያላቸውን ግምት አስቀምጠዋል፡፡
በተጨማሪም በጭልጋና አካባቢው የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከግጭቱ አንድ ሳምንት ቀደም ብለው መዘጋታቸውና ሙሉ በሙሉ ማስተማር ማቆማቸው ተገልጿል፡፡
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48081#sthash.FOzLOtJp.dpuf

Monday, November 2, 2015

የአዲስ አበባና አካባቢዋ ወተት ከፍተኛ መርዛማ ህፃናትን የሚያቀጭጭ እና የሚያሳጥር ኬሚካል አለው ተባለ -

ነገሩ፣ ለዘመናት ከምናውቀው እውቀት የተለየ በመሆኑ ግራ ማጋባቱ አይቀርም፡፡ እስካሁን ለሕፃናት ዕድገትና ጥንካሬ ጥሩ ነው በማለት ሕፃናትን ስንመግብ የኖርነው ወተት፤ በተቃራኒው ለሕፃናት ዕድገት ጥሩ አይደለም፤ ያቀጭጫቸዋል ቢባሉ ምን ይላሉ? የሚገርም ነው!ሰሞኑን በሂልተን ሆቴል ሲካሄድ በቆየው 4ኛ የአፍሪካ የምግብና የኑትሪሽን ፎረም ላይ አንድ ተመራማሪ፤ በመርዛማ ኬሚካሎች (አልፋ ቶክሲን) ላይ ያደረጉትን የምርምር ውጤት ሲያቀርቡ፤ እግረ መንገዳቸውን የአዲስ አበባና አካባቢዋ ወተት ከመጠን በላይ መርዛማ ኬሚካል (አልፋ ቶክሲን) እንዳለው ገልፀዋል፡፡ ተመራማሪው ዶ/ር አሻግረ ዘውዱ፤ ዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት (ILRI) ባወጣው ሪፖርት፤ በ2016 በአዲስ አበባና አካባቢዋ ባደረገው ጥናት፣ ከተሰበሰቡት 140 ናሙና ከ90 በመቶ በላይ ዓለምአቀፍ ሕግ ከሚፈቅደው በላይ መርዛማ ኬሚካል (አፍላቶክሲን M1) እንዳለው ማስታወቁን ተናግረዋል፡፡ አልፋ ቶክሲን በሻጋታ ምክንያት የሚፈጠር መርዛማ ኬሚካል ነው ያሉት ተመራማሪው፤ መርዛማ ኬሚካሉ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ቢጐዳም በሕፃናት ላይ የበለጠ ጉዳት ያደርሳል፣ መቀጨጭና መጫጫት ያስከትላል፡፡ በዕድሜያቸው ልክ ቁመታቸው አያድግም፡፡ በኢትዮጵያ 40 በመቶ ሕፃናት ቀጫጫ ናቸው፡፡ መርዛማ ኬሚካሉ ከማጫጨት በተጨማሪ ረዥም ዕድሜ ሲቆይ የጉበት ካንሰር ያስከትላል ብለዋል፡፡ አልፋ ቶክሲኖች የተለያዩ ናቸው፡፡ እህል ላይ የሚገኙትና በይበልጥ የሚታወቁት 4 ናቸው፡፡ እነሱም B1 B2 G1 G2 ይባላሉ ያሉት ዶ/ር አሻግሬ፤ እህሉ ላይ የሚገኘውን B1 አልፋ ቶክሲን የበላ ከብት በሰውነቱ ውስጥ በሚካሄደው ሜታቦሊዝም፣ B1 መርዛማ ኬሚካል ወደ M1 ይቀየራል፡፡ ኤች አይ ቪ ከእናት ወደ ልጅ እንደምታስተላልፍ እናት ለልጇ ጡት ስታጠባ መርዛማውን ኬሚካል ወደ ሕፃኑ ታስተላልፋለች፡፡ ከብትም እንደዚሁ፡፡ ሕፃኑ በአልፋ ቶክሲን የሚጠቃው፣ ጡት መጥባት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡ ወተት ለሕፃናት ዕድገት ጥንካሬና ውፍረት ጥሩ ነው ስለሚባል ወተት እየጠጡ ያድጋሉ፤ ለአልፋ ቶክሲን እየተጋለጡ ናቸው ያሉት ተመራማሪው፤ “በወሎ ድርቅ ጊዜ የእርጐ ፈንገስ የሚባል ነገር ተፈጥሮ ነበር፡፡ የሚበላ ነገር ሲጠፋ ፈንገስ የተቀላቀለበት ምግብ በልተው፤ ጋንግሪን ተፈጥሮባቸው እግራቸው የተቆረጠ ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡” ብለዋል፡፡ ዓለምአቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ያወጣውን መረጃ በተመለከተ፤ መንግስት ከኢትዮጵያ ፐብሊክ ኢንስቲትዩት፣ የደረጃዎች ምዘናና ተስማሚነት፣ የምግብ ሳይንስና ኑትሪሽን ማዕከል እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ ባለሙያዎች ጥናት እንዲያደርጉበት ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡ ውጤቱ ልክ እንደተባለው ከሆነ ምን እናድርግ? በማለት ምክክር ይደረጋል ያሉት ዶ/ር አሻግሬ፤ ልክ ካልሆነ ደግሞ ኅብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ ይደረጋል ብለዋል::   ምንጭ አዲስ አድማስ ጋዜጣ (ዛሬ በአዲስ አበባ ታትሞ የወጣ) - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/47909#sthash.9lxCGAJc.dpuf

Thursday, October 29, 2015

መምህር ግርማ ዋስትና ተከለከሉ * የማታለል ክስ የቀረበባቸው መምህሩ “ሴራ ነው – ከሳሹን አይቼው አላውቅም” አሉ - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/47805#sthash.G6117g2V.dpuf

ትናንት ዘ-ሐበሻ በሰበር ዜና መምህር ግርማ ወንድሙ መታሰራቸውን መዘገቧ አይዘነጋም:: ፖሊስ ዛሬ መምህር ግርማን ፍርድ ቤት አቁሞ ጠርጥሮ ያሰረበትን ምክንያት አስረድቷል:: የፌደራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የወንጀል ችሎት በመምህር ግርማ ላይ ፖሊስ የፈጸመውን ክስ ከሰማ በኋላ ፖሊስ አቶ ግርማ ቢፈቱብኝ መረጃና ሰነዶችን ሊያሸሹ ይችላሉና 14 ቀን ይፈቀድልኝ ሲል ጠይቋል:: የመምህር ግርማ ጠበቃ የተጠረጠሩበት ክስ ዋስትና የሚያስከለክል አይደለም ሲል ሲል በዋስ እንዲለቀቁ ጠይቆ ነበር:: ሆኖም ፍርድ ቤቱ ፖሊስ አብዛኛውን ምርመራ በማጠናቀቁ የጠየቀውን 14 የምርመራ ቀን ሰርዞ በ7 ቀን ውስጥ አሉኝ የሚላቸውን ማስረጃዎች አሰባስቦ እንዲጨርስ ፈቅዶ ውጤቱን ለመስማትም ጥቅምት 25 2008 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል። መምህር ግርማ ወደ ማረፊያ ቤት ሄደዋል:: በመምህር ግርማ ወንድሙ ላይ የቀረበው ክስ የሚከተለው ነው:- (ከመንግስት ሚዲያዎች እንደወረደ የተገኘ ነው) የወንጀሉ ዝርዝር ፖሊስ መምህር ግርማ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ምክንያት የሆነው ወንጀል የተፈፀመው መስከረም 2006 ዓ.ም ነው ብሏል። በየካ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ወሰን ግሮሰሪ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩት አቶ በላይነህ ከበደ በመምህር ግርማ የማታለል ወንጀል የተፈጸመባቸው ግለሰብ ናቸው። እንደ ፖሊስ የምርመራ መዝገብ እኚህ ግለሰብ ከትዳር አጋራቸው ጋር 400 ካሬ ሜትር ላይ ባረፈ መኖሪያ ቤታቸው ይኖሩ ነበር። እንደ ምርመራ መዝገቡ መምህር ግርማ የግል ተበዳይን እምነት በመጠቀም የምትኖርበትን መኖሪያ ቤት እስከ ጥር 30 2006 ሽጠህ ካልወጣህ አስከሬንህ ይወጣል ይሏቸዋል። የፖሊስ የምርመራ መዝገብ እንደሚለው ልጅ ያልወለዱት ባልና ሚስት ከመሞት መሰንበት በማለት ይህንን ቤት በጣም በዝቅተኛ ዋጋ በ800 ሺህ ብር ይሸጡታል። ቤቱ በዚህ ዋጋ እንዲሸጥ መምህር ግርማ በራሳቸው ሰዎች አማካኝነት ብዙ ያልተገባ ስራ ሰርተዋል ነው የሚለው የምርመራ መዝገቡ። ከዚያም መምህር ግርማ በዚህ ብቻ ሳይመለሱ የግል ተበዳዩን ቦሌ አካባቢ በራዕይ ያየሁት ቦታ አለ እዚያ ነው ገዝተህ የምትኖረው ይሏቸውና ሌላ የማታለያ ዘዴ ቀየሱ ይላል ምርመራው። ቤቱ የተሸጠበትን 800 ሺህ ብር አምጣና እንዲበረክትልህ ልፀልይበት ብለው በመውሰድ በዚያው ውለው አደሩ፤ የግል ተበዳዩም በእርሳቸው ላይ ያላቸው እምነት ባለመጥፋቱ በትዕግስት ስልክ ቢደውሉላቸውም ስልካቸው ዝግ ሆነባቸው፤ ይባስ ብሎ ከሀገር ወጡ ተባለ የሚለውም ተጠቅሷል። የግል ተበዳይ ሁኔታው ማታለል መሆኑን ስለተረዱ 2007 መጋቢት ወር ገደማ ለፖሊስ ያመለከቱ ሲሆን፥ እርሳቸው ከሄዱበት እስኪመለሱ ፖሊስ የግል ተበዳዩን እና የምስክሮችን ቃል ተቀብሎ ቆይቶ ተጠርጣሪው መምህር ግርማ ወንድሙን ትናንት በቁጥጥር ስር አውሏቸው ነው ዛሬ ፍርድ ቤት ያቀረባቸው። ተጠርጣሪው መምህር ግርማ እኔ የተባለውን ሰው ቀይ ይሁን ጥቁር አይቼው አላውቅም፤ ሆን ተብሎ ከጀርባ የተጠነሰሰብኝ ሴራ አለ በማለት ለችሎቱ አስረድተዋል። - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/47805#sthash.G6117g2V.dpuf

Wednesday, October 28, 2015

አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ ከውጭ ሚ/ር ደኤታነት ተነሱ

(ዘ-ሐበሻ) የሟቹ አምባገን የኢትዮጵያ መሪ የቅርብ ሰው የነበረውና በውጭ ሃገር በተለይም በአሜሪካ እና በብራሰልስ በቆየባቸው ጊዜያቶች የአምባሳደርነት ስም ይዞ የገዢውን ፓርቲ አምባገነን መሪዎችን ገንዘብ በማሸሽ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ቆይቷል እየተባለ በሰፊው የሚተቸው ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ደኤታነት ስልጣኑ ድንገት ተነሳ::   አንዳንድ የቅርብ ምንጮች ብርሃነ ስልጣኑን የለቀቀቀው በፈቃዱ ነው ይበሉ እንጂ ጉዳዩ በአዲስ አበባውና በመቀሌው የሕወሓት ቡድን ክፍፍል ጋር የተያያዘ ነው እየተባለ ነው:: በ2013 ዓ.ም ከደደቢት በረሃ ጀምሮ ለዓመታት ሕወሓት ውስጥ በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ያገለገሉት አምባሳደር ስዩም መስፍን፣ አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ ፣ አቶ አርከበ ዕቁባይና አቶ ዘርዓይ አስገዶም ባቀረቡት ጥያቄና ፓርቲው እየተገበረ ባለው የመተካካት ሂደት በሚል ሽፋን መሰረት ሥልጣናቸውን እንዲለቁ የተደረጉ ሲሆን አቶ መለስ ከሞቱ በኋላ እነዚሁ ባለስልጣናት ወደ ሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ለመግባት ጥረት አድርገው ነበር:: በተለይም ከአቶ አርከበ እቁባይ ጋር በጋብቻ ዝምድና እንዳላቸው የሚነገርላቸው አቶ ብርሃነ ገብረክርስቶስ አቶ አርከበን የሕወሓትና የኢትዮጵያ ጠ/ሚ/ር ለማድረግ ከሚሰራው ቡድን ጀርባ ሆነው ብዙ ሲንቀሳቀሱ ቆይተው በመቀሌው ቡድን በባለፈው የሕወሓት ጉባኤ ላይ መሸነፋቸው ይታወሳል:: አቶ ብርሃነ ከዚህ ቀደም በሕጋዊ ባለቤቱ ላይ ሲወሰልት በመያዙ የቀድሞ ሚስቱ ከዛሬ 12 ና 13 ዓመታት ገደማ በፊት ብርሃነን በዝሙት ጉዳይ ክስ መስርታበት በመረታቱ በርሱ ስም በኒውዮርክ ከተቀመጠው የሕወሃት ባለስልጣናት ገንዘብ ውስጥ ካሳ እንዲሆናት 5 ሚሊዮን ብር እንደተፈረደላት በተለያዩ ሚዲያዎች መዘገቡ አይዘነጋም:: በአቶ ብርሃነ ገብረክርስቶስ ቦታ ሌላ ሚ/ር ደኤታ መሾሙም ተሰምቷል:: ባለስልጣኑ ወደ ሌላ ቦታ ይዘዋወሩ/ አይዘዋወሩ ያገኘነው መረጃ የለም:: - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/47789#sthash.jB36S8wc.dpuf

Tuesday, October 6, 2015

የኃይለማርያም ካቤኔ አባላት ታወቁ * ሬድዋን ወደ ወጣቶች እና ስፖርት ሚ/ር ተገፉ * ሶፍያን አህመድ ተሰናበቱ * ሕወሓት አሁንም የአንበሳውን ድርሻ ይዟል

(ዘ-ሐበሻ) የሕዝብ ተወካዮች የሌሉበት የኢህ አዴግ ፓርላማ ዛሬ ተሰብስቦ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ያቀረቡትን የካቢኔ አባላት አጸደቀ:: በዚህ ካቢኔ ውስጥ አሁንም ሕወሓት ዋና ዋና የስልጣን ቦታዎችን ይዟል:: የውጭ ጉዳይ ሚኒስተርነቱ; ኢኮኖሚው በሕወሓት ስር እንዲቆይ ሲደረግ አሁን ደግሞ በተጨማሪም አቶ ሬድዋን ሁሴን ይመሩት የነበረውን የመንግስት ኮሙዩንኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሀላፊ ሚኒስትር ቦታም ወስዷል:: በዚህም ቦታ ላይ የሕወሓቶ አቶ ጌታቸው ረዳ ተሹመዋል:: ለረዥም ጊዜ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ሁነው ሲሰሩ የቆዩት አቶ ሶፍያን አህመድ በአቶ አብዱላዚዝ መሀመድ ተተክተዋል::
Hailemariam
የሕወሓቱን የካዛንቺሱን መንግስት የሚላላኩት የካቤኔ አባላቱ ዝርዝር እንደሚከተለው ቀርቧል::
አቶ ደመቀ መኮንን – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ
ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል – በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ እና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር
ወይዘሮ አስቴር ማሞ – በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ እና የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስትር
አቶ ሲራጅ ፈጌሳ – የመከላከያ ሚኒስትር
ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም – የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
አቶ ካሳ ተክለብርሃን – የፌደራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር አካባቢ ልማት ሚኒስትር
አቶ ጌታቸው አምባዬ – የፍትህ ሚኒስትር
አቶ አብዱላዚዝ መሀመድ – የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር
አቶ ተፈራ ደርበው – የእርሻ እና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሚኒስትር
አቶ ስለሺ ጌታሁን – የእንሰሳትና የዓሳ ሀብት ልማት ሚኒስትር
አቶ አህመድ አብተው – የኢንዱስትሪ ሚኒስትር
አቶ ያዕቆብ ያላ – የንግድ ሚኒስትር
አቶ አብይ አህመድ – የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር
አቶ ወርቅነህ ገበየሁ – የትራንስፖርት ሚኒስትር
አቶ ሙኩሪያ ሀይሌ – የከተማ ልማት እና ቤቶች ሚኒስትር
ዶክተር አምባቸው መኮንን – የኮንስትራክሽን ሚኒስትር
አቶ ሞቱማ መቃሳ – የውሃ፣ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር
አቶ ሽፈራው ሽጉጤ – የትምህርት ሚኒስትር
አቶ ቶሎሳ ሻጊ – የማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር
ዶክተር ከሰተብርሀን አድማሱ – የጤና ጥበቃ ሚኒስትር
አቶ አብዱልፈታህ አብዱላሂ – የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር
ኢንጂነር አይሻ መሀመድ – የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር
ወይዘሮ ዘነቡ ታደሰ -የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስትር
ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም – የአካባቢ ደን ልማት እና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር
አቶ ሬድዋን ሁሴን – የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትር
ወይዘሮ ደሚቱ ሀምቢሳ – የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚኒስትር ማዕረግ የካቢኒ አባል የሆኑ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ሹመትን ለምክር ቤቱ አቅርበው አስፀድቀዋል።
በዚህም መሰረት
አቶ በከር ሻሌ – የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬከተር
አቶ ጌታቸው ረዳ – የመንግስት ኮሙዩንኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሀላፊ ሚኒስትር
አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ – የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር
ዶክተር ይናገር ደሴ – የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ተሹመዋል።

- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/47173#sthash.3qtnVktv.dpuf