Friday, January 30, 2015

መንግስት ከምርጫው በፊት አፈናውን ያቆማል የሚለው ተስፋ መሟጠጡን ሂውማን ራይተስ ወች አስታወቀ

ድርጅቱ ባወጣው የ2014 አለማቀፍ የሰብአዊ መብት አያያዝ ሪፖርት ላይ እንደጠቀሰው መንግስት ጋዜጠኞችን፣ ጸሃፊዎችን እና  የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎችን እንደፈለገ  ያስራል፣ በሰላም ተቃውሞአቸውን ለመግለጽ በወጡ ዜጎች ላይ ፖሊስ የሃይል እርምጃ ይወስዳል፤ እንዲሁም ለማፈኛነት እየዋሉ ያሉትን በአለማቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ የተወገዙትን አዋጆችን ለመለወጥ ምንም ምልክት አላሳየም ብሎአል።
ባለፈው አመት የኢትዮጵያ መንግስት ማንኛውንም ተቃውሞ ለማፈን መሞከሩን የገለጹት የሂውማን ራይትስ ወች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሌስሌ ሌፍኮው፣ ጋዜጠኞችና ተቃዋሚዎች ከሁሉም በባሰ እንደተሰቃዩና ከመጪው ምርጫ በፊት ሁኔታዎች ይሻሻላሉ የሚለው ተስፋ ሙሉ በሙሉ እንደተዳፈነ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እየፈጸመች ያለችው አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰትን የለጋሽ አጋራትን አለመተቸታቸውን  ሂውማን ራይትስ ወች በሪፖርቱ አመልክቷል።ሰማያዊ ፓርቲ የተቃውሞ ሰልፎችን እንዳያደረግ መከልከሉ፣ በኦሮምያ ክልል በሚያዚያና ግንቦት ወሮች የጸጥታ ሃይሎች ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸው፣ የግንቦት7 ዋና ጻሀፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ህገወጥ በሆነ መንገድ የመን ውስጥ ተይዘው መሰጠታቸውና የታሰሩበት ቦታ አለመታወቁንም ገልጿል።
ዞን 9 እየተባሉ የሚጠሩ ጸሃፊዎች በጸረ ሽብር ህግ መከሰሳቸውን፣ የ6 ጋዜጣ አሳተሚዎች በተመሳሳይ ወነጀል መከሰሳቸውን የጠቀሰው ሂማውን ራይትስ ወች፣ መንግስት ዌብሳይቶችን መዝጋቱን እንዲሁም ስልኮችን በመጥለፍ መረጃዎችን እንደሚያሰባሰብ አትቷል።
በኦሞ ሸለቆ አካባቢ በርካታ ዜጎች ያለፍላጎታቸውና ተገቢው ካሳ ሳይከፈላቸው እንደሚፈናቀሉም ድርጅቱ አስታውቋል። መንግስት ተደጋጋሚ ወቀሳና ትችት ቢደርስበትም የጸረ ሽብር ህጉንና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጀቶችን ለመቆጣጠር የወጣውን ህግ ለመቀየር ፈቃደና አለመሆኑን የጠቀሰው ሂውማን ራይትስ ወች፣ የመንግስትን የልማት እቅድ የተቹ ሰዎች እስራትና ወከባ እንደሚያጋጥማቸው አትቷል።
መንግስት ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ማፈኑ በመጪው ምርጫ ላይ አሉታዊ ተጽኖ እንደሚኖረው ሌስሌ ሌፍኮው ተናግረዋል። ሂማን ራይትስ ወች በ656 ገጽ ሪፖርቱ በአለም ዙሪያ ያሉ የ90 አገራት የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ቃኝቷል።
ኢሳት ዜና

Monday, January 26, 2015

ቢያጥቡት የማይጸዳ ዘረኛ ቡድንን ለማስወገድ ከአንድነት ጋር አንድ እንሁን !!

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ከምስረታው እስካሁን ለወያኔ ህወሃት ቡድን ትልቅ የራስ ምታት ሆኖ ቆይቷል።በመሆኑም ድርጅቱን ለማፍረስ በተለያዩ ጊዜያት የድርጅቱን አመራሮች በማሰር፣ በመደብድብ፣ ከሀገር በማስደድ፣ በማስፈራራት እና በድርጅቱ ውስጥ ሰርጎ ገቦችን በማስረግ ያላደረገው ሙከራ አልነበረም። ሆኖም ግን አንድነት በቆራጥ አመራሮቹ ፣ አባላቶችና ደጋፊዎች ታጋድሎና መስዋእትነት እስካሁን ህልውናውን ጠብቆ ቆይቷል።
በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያችን የተከሰተው አገር አቀፍ ቀውስ ህዝቡ ብሶቱን ያለምንም ፍርሃት እንዲገልጽ እያስገደደው መሆኑን የተረዳው የህወሀት ቡድን ትግሉን መርተው ከስልጣን ማማ ያወርዱኛል ብሎ የሚፈራቸውን የፖሌቲካ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን ለማጥፋት ቆርጦ ተነስቷል። —

[ሙሉውን መግለጫ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ]—

zeHabesha.com

Friday, December 19, 2014

ሰበር ዜና (Update) – አምስት ሰዎች ሲቆስሉ ሁለት ሞተዋል፣ የባህርዳር ህዝብ አደባባይ በመውጣት ተቃውሞውን በማሰማት ላይ ነው

(ነገረ-ኢትዮጵያ) ዛሬ ጠዋት ባህርዳር ከተማ ላይ የተነሳውን የህዝብ ተቃውሞ ፖሊስ በኃይል ለመበተን ጥረት እያደረ ቢሆንም ህዝቡ በብዛት ተቃውሞውን እየተቀላቀለ መሆኑን ከቦታው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ ፖሊስ በተኮሰው ጥይት ሁለት ወጣቶች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን ሌሎች አምስት ያህል ወጣቶች እንደቆሰሉ ተገልጾአል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከቀበሌ 10 አባይ ማዶ ያለው መንገድ ተቃውሞውን በተቀላቀለው ህዝብ የተዘጋ ሲሆን ወደ ጎንደር የሚወስደው መንገድም መዘጋቱ ታውቋል፡፡ የቀበሌ 8፣ 10ና 11 ነዋሪዎች እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተቃውሞውን እየተቀላቀሉ ነው ተብሏል፡፡ የአፈ ጉባኤ ጽ/ቤት አካባቢም በርካታ ህዝብ የተገኘ ቢሆንም ርዕሰ መስተዳደሩን ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናት የሉም እንደተባሉ ገልጸውልናል፡፡
————————-
(ነገረ-ኢትዮጵያ) ባህርዳር ከተማ ውስጥ 04 ቀበሌ እየተባለ የሚጠራው አካባቢ የሚገኘውን የጥምቀት ታቦት ማደሪያ ለባለሀብት ይሰጣል መባሉን ተከትሎ ህዝቡ አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞውን በማሰማት ላይ መሆኑን የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ገለጸዋል፡፡Protest in Bahirdar, Ethiopia
ምንጮቹ እንደገለጹት እጅግ በርካታ ህዝብ አደባባይ የወጣ ሲሆን፣ ሰልፈኞቹ በእምነታቸው እየተደረገባቸው የሚገኙትን ጣልቃ ገብነቶችና ሌሎቹንም ስርዓቱ እየፈጠራቸው የሚገኙትን ችግሮች የሚቃወሙ መፈክሮች እያሰሙ ይገኛሉ፡፡
የአማራ ክልል አስተዳደር የቤተ ክርስቲያን ንብረት የሆነውን የታቦት ማደሪያ ለመንገድና ለጥቃቅንና አነስተኛ ሱቆች መስሪያ እንዲነጠቅ ማዘዙን ተከትሎ በቤተ ክርስቲያን የተጠራው ተቃውሞ አሁንም ድረስ እንደቀጠለ መሆኑን የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ከታቦት ማደሪያው 9 ሜትር ገብቶ መንገድ እንዲሰራ እንዲሁም ቀሪው ለጥቃቅንና አነስተኛ ሱቆች እንዲሰጥ አስተዳደሩ ማዘዙን ተከትሎ ታቦት ማደሪያውን ከነገ ህዳር 10/2007 ዓ.ም ጀምሮ ሊፈርስ እንደነበር መረጃው የደረሳት ቤተ ክርስቲያን ለህዝበ ክርስቲያኑ አስቸኳይ ጥሪ ማስተላለፏ ታውቋል፡፡
ህዝቡም ‹‹በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ተገናኝተን በእግዚያብሄር ስም በአስቸኳይ ጠርተንዎታል›› በሚል በቀረበለት ጥሪ መሰረት ዛሬ ጠዋት ተቃውሞውን የጀመረ ሲሆን አሁንም ድረስ እንደቀጠለ ተገልጾአል፡፡ ህዝቡ ቀበሌ 10 በሚገኘው አዲሱ ምክር ቤት እንዲሁም በዚሁ ቀበሌ በሚገኘው የቀድሞው ምክር ቤት በመገኘት ተቃውሞውን እየገለጸ ይገኛል፡፡ በተለይ በአዲሱ ምክር ቤት ተገኝቶ ተቃውሞውን እያሰማ የሚገኘውን ህዝብ በኃይል ለመበተን ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ከቦታው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

Thursday, December 18, 2014

ህወሃት በመንግስት ወጪ 40ኛ አመቱን ለማክበር ሸርጉድ እያለ ነው

በከፍተኛ ዝግጅት ይከበራል የተባለው የህወሃት 40ኛ አመት በአል ወጪ የሚሸፈነው ከመንግስት ካዝና መሆኑ በአባል ድርጅቶች መካከል መነጋገሪያ አጀንዳ እየሆነ መምጣቱን የሚናገሩት የኢህአዴግ ምንጮች፣ ከመንግስት ካዝና ለሚወጣው ገንዘብ የተሰጠው ሰበብ  ገጽታ ግንባታ የሚል መሆኑን ገልጸዋል።
ህወሃት በአሉን ከድርጅቱ ካዝና በተለይም የአገሪቱን ሲሶ ሃብት ከተቆጣጠረው ኢፈርት ካዝና መጠቀም እየቻለ፣ ወጪውን መንግስት እንዲሸፍነው ማስደረጉ ለብዙዎቹ አልተዋጠላቸውም። አጠቃላይ ዝግጀቱ ምን ያክል ገንዘብ እንደሚያስወጣ እስካሁን በግልጽ ባይታወቅም፣ እስካሁን እየተደረጉ ባሉ እንቅስቃሴዎች ወጪውን እየሸፈኑ ያሉት የክልሉ መንግስትና የፌደራሉ መንግስት በጋራ ነው።
የካቲት 11 ቀን የሚከበረውን የህወሃት ቀን አስመልክቶ የተመረጡ ጋዜጠኞችና አርቲስቶችን በመንግስት ወጪ  ታህሳስ 13 ቀን 2007 ዓ.ም ወደ ትግራይ ይጓዛሉ። ህወሃት ከበዓሉ አስቀድሞ የትግራይ ክልልን ለማስጎብኘት ያሰበው ከወዲሁ ሰፊ የፕሮፖጋንዳ ስራ ለማከናወን እንዲመቸው በማሰብ መሆኑን ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡
 ኢሳት ዜና 

Wednesday, December 17, 2014

ዓይን አጥፊው የዓይን “ማከሚያ ቤት”

የህንድ የአይን ህክምና ማዕከል (OIA) በታካሚዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተገለፀ
indian eye center
* “ብዙ ብር ከፍለን የዓይን ብርሃናችንን አጥተን ተመልሰናል” – ታካሚዎች 
* ከመነሻው የማዕከሉ አደረጃጀት አዋጁን የሚቃረን ነው – የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ
* ማዕከሉ በየዓመቱ የሚታደስ የህክምና አገልግሎት ፈቃድ አልተሰጠውም
ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት የተሻለ የአይን ህክምና ለመስጠት፣ ለኢትዮጵያውያን ሀኪሞች የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርግና በዘርፉ ምርምርና ጥናት እንዲያካሂድ ታስቦ በዘውዲቱ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ የተገነባው የህንድ የአይን ህክምና ማዕከል በታካሚዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተገለፀ፡፡
ጉዳት የደረሰባቸው ታካሚዎች እንደተናገሩት በማዕከሉ በተሰጣቸው ህክምና ሳቢያ የዓይን ብርሃናቸውን አጥተዋል፡፡ በማዕከሉ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት የተሟላ የህክምና ቁሳቁስ፣ በዘርፉ በቂ እውቀት ያላቸው ባለሙያዎችና ደረጃውን የጠበቀ ግንባታ ሳያሟላ የሚሰጠው ጥራቱን ያልጠበቀ አገልግሎት ዜጎችን ለአይነ ስውርነት፣ ለተጋነነ ወጪና ለእንግልት እየዳረገ ነው፡፡
ማዕከሉ ለኢትዮጵያውያን ሃኪሞች የቴክኖሎጂ ሽግግር ያደርጋል ቢባልም ሁሉም የህክምና ቁልፍ ቦታዎች በህንዳዊያን በመያዛቸው እቅዱ እንዳልተሳካና ከስምምነት ውጪ በተጋነነ የደሞዝ ክፍያ ምዝበራ እንደሚፈፀም ተገልጿል፡፡
የአይን ህክምና ማዕከሉ ከተለያዩ ተቋማት ገምጋሚ ተመድቦለት የአንድ ዓመት ተኩል የስራ አፈፃፀሙ በተገመገመበት ወቅት ከግንባታው ጀምሮ ችግር እንዳለበት በመግለፅ ችግሩ ሳይቀረፍ የትኛውም የመንግስት አካል ለማዕከሉ ድጋፍ እንዳያደርግ ገምጋሚዎቹ ቢያስጠነቅቁም ፈቃድ አግኝቶ ደረጃ ሳይወጣለት፣ ጥራቱን ሳይጠብቅና ባለሙያና መሳሪያ ሳያሟላ ወደ ስራመግባቱ ተገቢ አልነበረም ተብሏል፡፡ መንግስት በተቋሙ ላይ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም ገምጋሚዎችና የማዕከሉ ሰራተኞች አሳስበዋል፡፡
ከመነሻው የኢትዮጵያ ነዋሪዎች በጎ አድራጎት ድርጅት መሆኑ እየታወቀ የጤና ማዕከሉ፣ ሜዲካል ዳይሬክተር፣ ስራ አስኪያጁ፣ የሃብት ማፈላለጉና ሌሎች ከፍተኛ ኃላፊነቶች በውጭ ዜጎች መያዛቸው የፌደራል በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ አዋጅን ፍፁም የሚቃረን ነው ያሉት በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የጤና ፕሮጀክት ክትትል እና ድጋፍ ባለሙያ አቶ ጥላሁን አለሙ፤ ማዕከሉ በርካታ  ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያሉበት መሆኑንና የተጠቃሚን አቅም ያላገናዘበ፣ ባለሙያ ያልተሳተፈበትና በከተማ አስተዳደሩ ስልጣን በተሰጠው አካል ያልፀደቀ የክፍያ ተመን በማውጣት የተጋነነ ክፍያ የሚያስከፍል፣ በጤና ንግድ ስራ ላይ የተሰማራ ድርጅት ነው ብለዋል፡፡
የጤና ማዕከሉ ካሉበት ችግሮች ውስጥ የማዕከሉ የውጭ ሞያተኞች የጤና የስራ ፈቃድ ከመውሰዳቸው በፊት ከኦፕሬሽን ጀምሮ ሌሎች የህክምና አገልግሎቶችን እየሰጡ እንደሆኑ የገምጋሚዎቹ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ በተጨማሪም ማዕከሉ በየዓመቱ የሚታደስ የህክምና አገልግሎት ፈቃድ ያልተሰጠው ህገ-ወጥ ተቋም ነው ሲልም ሪፖርቱ ገልጿል፡፡
አቶ ወ/ፃዲቅ ማናዬ ይባላሉ፤ የ62 ዓመት አዛውንት ናቸው፡፡
አዲስ አበባ ቂርቆስ ክ/ከተማ ኦሎምፒያ አካባቢ ይኖራሉ፡፡ “አምና መጋቢት ወር ላይ ዓይኔን ታምሜ ወደ OIA የሄድኩት ህንዶቹ ጥሩ ህክምና ይሰጣሉ ተብዬ ነው ያሉት አዛውንቱ፤ በመጀመሪያ የሞራ ግርዶሽ ነው ተብለው 4250 ብር ከፍለው የቀዶ ህክምና ማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡ “በመጨረሻ እራሳቸው በፈጠሩት ስህተት ከአንድም ሶስት ጊዜ ኦፕራሲዮን ተደርጌ ሬቲናዬን አበላሹት” የሚሉት አዛውንቱ፤ ከዚያም በኋላ ያለ ምንም መድሃኒትና እርዳታ ዝም ብለው እንዲጠብቁ በመደረጋቸው ቀኝ አይናቸው ሙሉ ለሙሉ ከጥቅም ውጭ ሆኖ ማየት እንደተሳናቸው በምሬት ገልፀዋል፡፡
ያለ ምንም መድሃኒት ለሁለት ወር ቀጠሮ ሰጥተውኝ ስመለስ “ያንተ የሬቲና ችግር ነው አሉኝ” የሚሉት አቶ ወ/ፃዲቅ፤ “የሬቲና ችግር ከሆነ ለምን ሶስት ጊዜ አደንዝዛችሁ ሞራ ነው በማለት ኦፕሬሽን አደረጋችሁኝ” በማለት ህንዳዊ ሀኪሞቹን መጠየቃቸውን፤ ነገር ግን ከማመናጨቅ ውጭ ቀና ምላሽ ማጣታቸውን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ “ወደ ሌላ ህክምና ለመሄድ ሪፈር ፃፉልኝ፤ አለበለዚያም እናንተ ጋር ያደረግሁትን አጠቃላይ የህክምና መረጃ ስጡኝ” ብለው መጠየቃቸውን የሚናገሩት አዛውንቱ፤ የምናውቀው ነገር የለም የፈለጋችሁበት ሄዳችሁ ክሰሱን፤ ምላሽ እንሰጣለን” በማለት አመናጭቀው እንደሸኟቸውና እይታቸውን አጥተው ቤት ውስጥ ከተቀመጡ 10 ወር እንዳለፋቸው ገልፀው፤ ማንበብና መፃፍ ሁሉ እንደተሳናቸው ተናግረዋል፡፡
በዚሁ የአይን ህክምና ማዕከል የህክምና ስህተት ተፈጽሞብኛል ያሉት የ65 ዓመቱ አዛውንት አቶ ኮሬ ወ/ማርያም፤ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ለህክምና ሲሄዱ የሞራ ግርዶሽ ነው ተብለው አምስት ሺህ ብር ከፍለው ኦፕሬሽን መደረጋቸውን አስታውሰው፣ በ15ኛው ቀን አይናቸው ሙሉ በሙሉ ጠፍቶ ወደ ማዕከሉ ተመልሰው መሄዳቸውን ይናገራሉ፡፡
“አይኔ መጥፋቱን እያወቁ አንድም ጠብታ ሳያዙልኝ ወደ ምኒልክ ሆስፒታል እንድሄድ ነገሩኝ” የሚሉት አዛውንቱ፤ ምኒልክ ሆስፒታል ሁለት ሶስት ጊዜ ቢመላለሱም ምንም እርዳታ ሳያገኙ ሲኤምሲ አትሌቲክስ ህንፃ ላይ በሚገኘው “ብሩህ ቪዥን” ክሊኒክ እንዲታከሙ እንደተነገራቸው ገልፀዋል፡፡
India-Eye-Care-Center
ማዕከሉ በመጋቢት ወር በኢህአዴግ ባለሥልጣናት ተመርቆ ሲከፈት
“ብሩህ ቪዥን አንዴ በመርፌ፣ ሌላ ጊዜ በመሳሪያ ይታይ እያሉ ለተጨማሪ 7ሺህ ብር ወጪ ተዳርጌያለሁ” ያሉት እኚህ ታካሚ፤ አራት ወር እንደሆናቸውና አይናቸውንም አጥተው፣ 12 ሺህ ብራቸውን በማፍሰስ ለተጨማሪ ችግር በመዳረጋቸው ተጨማሪ ወጪ እንደሚጠብቃቸው ተናግረዋል፡፡
“የተሟላ መሳሪያ ሳይኖር፣ በዘርፉ የሰለጠነ በቂ ሀኪም በሌለበት የህክምና ማዕከሉ እንዴት ፈቃድ ተሰጠው?” ሲሉ የሚጠይቁት አቶ ኮሬ፤ “መንግስት ለዜጎቹ የሚጨነቅ ከሆነ እንዲህ አይነቶቹን ተቋማትና ሰራተኞች ለፍርድ ማቅረብና ኢንሹራንስ ለተጎጂዎች እንዲከፍሉ፣ ከዚያም በአስቸኳይ ማዕከሉን ዘግቶ ከጥፋታቸው ማስቆም ያስፈልጋል” በማለት ብለዋል፡፡
ወደ ህክምና ማዕከሉ ከመሄዳቸው አስቀድሞ መኪና መንዳት ይችሉ እንደነበር የተናገሩት  የ66 ዓመቱ አዛውንት፤ ከአንድ ዓመት በፊት ህክምና መጀመራቸውን ይናገራሉ፡፡ “ችግሩ የሞራ ግርዶሽ ነው፤ ይህን በቀላሉ እንገፍልሃለን ብለው ኦፕሬሽን ካደረጉኝ በኋላ ጭራሽ አይኔ ማየት አቁሞ ቤት ተቀምጫለሁ” ሲሉ በምሬት የገጠማቸውን ችግር ገልፀዋል፡፡
“ከዚያ በኋላ አይኔ ጠፋ ብዬ በተከታታይ ብመላለስም ምንም መፍትሄ ሳላገኝ እስካሁን አለሁ” ያሉት አዛውንቱ፤ “እርግጥ እኔ የካርድ 40 ብር ከመክፈል በስተቀር ያወጣሁት ወጪ የለም፤ ምክንያቱም የነፃ ህክምና ወረቀት አፅፌ ነበር የሄድኩት” ብለዋል፡፡ እሳቸው ደግሞ የጨረር ህክምና ተደርጐላቸውም መሻሻል እንዳላሳየ ገልፀው ወደ ምኒልክ ሆስፒታል ሪፈር እንደተፃፈላቸው ይናገራሉ፡፡ “ሚኒልክ ሆስፒታል ሄጄ ስመረመር አይንህ ተበላሽቷል፤ የማየትም ተስፋ የለውም ብለው መለሱኝ” የሚሉት ተጎጂው፤ ተስፋ ቆርጠውና እይታቸውን ተነጥቀው ቤት መቀመጣቸውን ጠቅሰው ወዴት አቤት እንደሚባል ግራ እንደገባቸው፤ ይህን ላድርግ ቢሉም አቅምና የእይታ ችግር እንደማይፈቅድላቸው ተናግረዋል – “እግዜር ይክሰሳቸው” ሲሉም በምሬት ተናግረዋል፡፡
በአንድ የመንግስት የሚዲያ ተቋም ውስጥ የሚሰራ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ለህክምና ወደ ማዕከሉ መሄዱንና መቶ ብር ከፍሎ ካርድ ማውጣቱን ይናገራል፡፡ እንደ ሌሎቹ የሞራ ግርዶሽ ችግር ሳይሆን ረጅም ርቀት እይታ ችግር እንዳለበት ተነግሮት፤ ለህክምናው መዘጋጀቱን ነገር ግን በመሃል ወረፋ ሲጠብቅ ስለ ማዕከሉ መጥፎ መጥፎ ነገሮች ሲነገሩ በመስማቱ ህክምናውን እንዳቋረጠ ይናገራል፡፡ “ችግሬን ከድጡ ወደ ማጡ አላደርግም ብዬ ህክምናውን አቁሜ ይልቁንም ክሊኒኩ ውስጥ አለ የተባለውን አሻጥር እየመረመርኩ ነው” ያለው ጋዜጠኛው፤ በማዕከሉ ከሚሰሩ ኢትዮጵያውያን የህክምና ባለሙያዎች የሰማው እጅግ የሚዘገንን ህገ-ወጥ አሰራር አይነ ስውር ከመሆን ያተረፈውን አምላኩን እንዲያመሰግን እንዳደረገው አጫውቶኛል፡፡
ማዕከሉ ከዚህ በተጨማሪም በብልሹ አሰራሮች መተብተቡን የግምገማ ሪፖርቶቹ ይጠቁማሉ፡፡ በሪፖርቱ ከተጠቀሱት ችግሮች መካከል የፋይናንስ፣ የግዢና የሰው ሃብት አስተዳደር ማኑዋሎች የሌሉትና ለምዝበራ የተመቻቸ መሆኑ፣ ማዕከሉ በአዋጅ ኃላፊነትና ስልጣን በተሰጠው ደረጃ መዳቢ አካል ደረጃ ያልወጣለት መሆኑና በምስራቅ አፍሪካ አንደኛ የተባለው ማዕከል ምንም አይነት የላብራቶሪ፣ የጠቅላላ ሰመመን፣ የድንገተኛና መሰል የአገልግሎት ክፍሎች ያልተሟሉለት መሆኑ ይገኙበታል፡፡
በሃገር ውስጥ ሊሟሉ የሚችሉ የቢሮ ቁሳቁሶች በከፍተኛና ወጪ ከውጭ ከመግባታቸው በተጨማሪ ተፈራራሚ አካላት ቢያንስ በፅሁፍ እንዲያውቁት አለመደረጉ የተጠቆመ ሲሆን የፕሮጀክት ክለሳ ሳይደረግ ከእቅድ ውጭ ለሆነ ግንባታ 634ሺ 986 ዶላር እንዲሁም ለህክምና መሳሪያና ለቢሮ ቁሳቁስ 315ሺ 171 ከ37 ሳንቲም በድምሩ 950ሺ 157 ከ37 ዶላር ያለ አግባብ ወጪ መደረጉን የገምጋሚው ኤክስፐርት ሪፖርት አመልክቷል፡፡ ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ማዕከሉ ሄደን የተለያዩ ህንዳዊያን ሃኪሞችን ለማነጋገር የሞከርን ሲሆን የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ወደ ህንድ በመሄዳቸው መረጃ ማግኘት የምንችለው እሳቸው ሲመለሱ ብቻ እንደሆነ ተገልፆልን ተመልሰናል፡፡ (ምንጭ: አዲስ አድማስ)

ቤኒሻንጉል ጉሙዝን ለመገንጠል የሽብርተኝነት ድርጊት ፈጽመዋል በሚል የተጠረጠሩ ተከሰሱ

-የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ለማስተጓጐል ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው ተጠቁሟል በታምሩ ጽጌ
በኤርትራ መንግሥት ድጋፍ ኤርትራ ውስጥ የተለያዩ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሥልጠናዎችን በመውሰድ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም በማቀድና በመዘጋጀት፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ለመገንጠል የሽብርተኝነት ድርጊት ፈጽመዋል በሚል በተጠረጠሩ አሥር የክልሉ ነዋሪዎች ላይ ታኅሳስ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተ፡፡
በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ተሰናድቶ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች አብዱልዋሀብ መኸዲ (በሌለበት)፣ አብዱራህማን ናስር (በሌለበት)፣ ኩርፊል ጅማ፣ ያሲር ጃባላ፣ ኢማም አብዱራዛቅ፣ ደፈአላ መሐመድ፣ አደም በደዊ፣ ሙድወኪል ከማል፣ አልፋዮድ በዳናና አዜን አህመድ ናቸው፡፡ 
ተጠርጣሪዎቹ በሰው ሕይወት፣ በአካልና በንብረት ላይ የተለያዩ ጉዳቶች ማድረሳቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ኅብረተሰቡን ለማስፈራራት፣ የአገሪቱን መሠረታዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ ሕገ መንግሥታዊና ማኅበራዊ ተቋማትን ለማናጋትና ለማፈራረስ ራሱን የቤኒሻንጉል ሕዝቦች ነፃ አውጭ ንቅናቄ (ቤሕነን) ብሎ በሚጠራው በሽብር ተግባር ላይ በተሰማራ ድርጅት ውስጥ ሆነው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ክሱ ያብራራል፡፡ 
አብዱልዋሀብ መሀዲ የተባለው ተጠርጣሪ ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ቤሕነን የሚባለውን ሕገወጥ ድርጅት በማቋቋምና በሊቀመንበርነት ከመምራቱም በተጨማሪ፣ ኤርትራ ውስጥ ሆኖ የተለያዩ የፖለቲካ ሥልጠናዎችንና የሽብር ተልዕኮዎችን ሲሰጥ መቆየቱ በክሱ ተጠቅሷል፡፡
ተጠርጣሪው ከሌሎች ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ኤርትራ ውስጥ በሚገኘውና ‹‹ሀሆና›› በሚባለው ወታደራዊ ማሠልጠኛ በመግባት፣ ከሁለት እስከ ስድስት ወራት ሥልጠና መውሰዳቸው በክሱ ተገልጿል፡፡ የመሣሪያዎች አጠቃቀም፣ የወታደራዊ አካል ብቃትና የፀረ ተሽከርካሪ ፈንጂ ማጥመድ ሥልጠናዎችን መውሰዳቸውንም ክሱ አክሏል፡፡ 
ተጠርጣሪዎቹ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጥቅምት 15 ቀን 2006 ዓ.ም. ሸርቆሌና አልቤሮ በተባሉ አካባቢዎች በሚገኘው፣ ዱምድ አቤ ተብሎ በሚጠራ መንገድ ላይ ፀረ ተሽከርካሪ ፈንጂዎችን በማጥመዳቸው፣ ጥቅምት 26 ቀን 2006 ዓ.ም. 12 ሰዎችን ጭኖ ከሸርቆሌ ወደ አስቢሮ ይጓዝ የነበረ ሚኒባስ ላይ የፍንዳታ ጉዳት በማድረስ ሦስት ሰዎች ወዲያውኑ እንዲሞቱና በዘጠኝ ተሳፋሪዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡
የክልሉን መንገዶች በማጥናትና ፈንጂዎችን በማጥመድ ከፍተኛ አደጋ እንዲደርስና የንፁኃን ሰዎች ሕይወት እንዲጠፋ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ፣ ተጠርጣሪዎቹ ወደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚሄዱ ተሽከርካሪዎችን በማስቆም፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላትንና ሌሎች ሲቪል ሰዎችን መግደላቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ 
ተጠርጣሪዎቹ ከሁለተኛው ተጠርጣሪ አብዱራህማን ናስር ከሚኖርበት ሰሜን ሱዳን በኩል በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር ደማዚን አሻራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በመገናኘት፣ የተለያዩ የሽብር ተልዕኮ ማስፈጸሚያ የጦር መሣሪያዎችን፣ ለምግብና የተለያዩ ወጪዎች የሚሆን ገንዘብ ይቀባበሉ እንደነበር ክሱ ያስረዳል፡፡ 
ተጠርጣሪዎቹ በሚያዚያ ወር 2006 ዓ.ም. ወደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚወሰደውን መንገድ በድንጋይ በመዝጋት፣ ከአሶሳ ከተማ ወደ ግድቡ 28 ሰዎችን ጭኖ ይጓዝ የነበረ የመከላከያ ሠራዊት ተሽከርካሪን በማስቆምና በማስወረድ፣ በአካባቢው በነበረ ጫካ ውስጥ በማስገባት፣ ሦስተኛው ተጠርጣሪ በጥይት ደብድቦ እንደገደላቸውና የያዙትን ገንዘብ እንደወሰዱ ክሱ ይገልጻል፡፡ ተሽከርካሪውንም ከራሱ ቤንዚን ስበው በማርከፍከፍ እንዳቃጠሉት ክሱ ያብራራል፡፡ 
ተጠርጣሪዎቹ የሽብር ተልዕኮ ለመፈጸም ቆርጠው በመነሳታቸው በተለያዩ ጊዜያት መንገድ በመዝጋትና ተሽከርካሪዎችን በማስቆም፣ ተሳፋሪዎችን በጥይት ደብድበው በመግደል፣ እንዲሁም የተወሰኑ ሰዎችን እጃቸውን ወደኋላ በማሰር፣ በድንጋይና በዱላ በመደብደብና አንገታቸውን በመቆልመም የግድያ ወንጀል መፈጸማቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ 
የመከላከያ ሠራዊት በደረሰው ጥቆማ መሠረት ባደረገው ከበባ ለ30 ደቂቃ ያህል ተኩስ ከተለዋወጡ በኋላ ሁለት ተጠርጣሪዎች ተገድለው፣ ሌሎቹ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ ሁሉም ተጠርጣሪዎች በተጠረጠሩበት የሽብርተኝነት ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡    

Monday, December 15, 2014

ጀግኖችን እያሰብን የበኩላችንን እንወጣ!! በመስዋዕትነት ነፃነት ይረጋገጣል፤ ሰላም ይሰፍናል። (በስደት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አባላት አስተባባሪ)

መምሀር የኔሰው ገብሬ በዳውሮ ከተማ ነዋሪና ትጉህ መምህር ነበር። እንደማንኛውም አገር ወዳድና የወገን ተቆርቋሪ እርሱም የወያኔ/ኢህአዴግ ሥርዓተ መንግሥት በሕዝብ ላይ የሚያደርሰውን ገደብ የለሽ ሰቆቃ መቀበል ባለመቻሉ ፣ በአንፃሩ በተቃውሞ አቋሙን በአደባባይ የሚገልጽና ይህ እኩይ ድርጊት እንዲቆም ታግሎ ለማታገል በጽናት ስለቆመ የሥርዓቱ ሰለባ ሆነ። እስራቱና እንግልቱ አልበቃ ብሎ ከሥራ መደቡም ተገለለ ። በዚያው ላይ ፍትህ ለማግኘት የሚያስብ ሕሊናና የሚሰማ ጆሮ እንደሌለ ተረድቶ ለአሰቃዩትም ለአጠቃላይ ሕዝቡም መራር መልእክት ያስታላልፋል ብሎ ያሰበውን መስዋዕትነት መርጦ ራሱን በጋዝ አንድዶ ሕዳር 1 ቀን 2004 ዓ.ም መስዋዕት ሆነ። ይህ ተግባሩ ቀደም ሲል ለአገር አንድነትና ለሕዝብ ሉዓላዊነት ፣ ለመምህሩ መብትና ጥቅም መከበር ሲታገሉ መስዋዕት የሆኑትን፣ በእስራት የማቀቁትን፣ ከእናት አገራቸው ተሰድደው በባዕድ አገር ያለውዴታቸው የእንግልትና የናፍቆት ኑሮ የሚገፉትን መምህራን፣ የሙያ ማህበሩ የኢመማ መሪዎችን፣ ደጋፊዎቻቸውንና ተባባሪዎቻቸውንም የሚያስመካ አንጸባራቂ መስዋዕትነት ሆኖ አልፏል። መቼም ቢሆን ነፃነት ያለመስዋዕትነት ተገኝቶ አያውቅም። በሕዝቡ ጫንቃ ላይ ተፈናጦ የሚገኘውን ጨካኙን፣ ዘረኛውን፣ ግፈኛውን፣ —-  [ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ]—–