Thursday, October 29, 2015

መምህር ግርማ ዋስትና ተከለከሉ * የማታለል ክስ የቀረበባቸው መምህሩ “ሴራ ነው – ከሳሹን አይቼው አላውቅም” አሉ - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/47805#sthash.G6117g2V.dpuf

ትናንት ዘ-ሐበሻ በሰበር ዜና መምህር ግርማ ወንድሙ መታሰራቸውን መዘገቧ አይዘነጋም:: ፖሊስ ዛሬ መምህር ግርማን ፍርድ ቤት አቁሞ ጠርጥሮ ያሰረበትን ምክንያት አስረድቷል:: የፌደራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የወንጀል ችሎት በመምህር ግርማ ላይ ፖሊስ የፈጸመውን ክስ ከሰማ በኋላ ፖሊስ አቶ ግርማ ቢፈቱብኝ መረጃና ሰነዶችን ሊያሸሹ ይችላሉና 14 ቀን ይፈቀድልኝ ሲል ጠይቋል:: የመምህር ግርማ ጠበቃ የተጠረጠሩበት ክስ ዋስትና የሚያስከለክል አይደለም ሲል ሲል በዋስ እንዲለቀቁ ጠይቆ ነበር:: ሆኖም ፍርድ ቤቱ ፖሊስ አብዛኛውን ምርመራ በማጠናቀቁ የጠየቀውን 14 የምርመራ ቀን ሰርዞ በ7 ቀን ውስጥ አሉኝ የሚላቸውን ማስረጃዎች አሰባስቦ እንዲጨርስ ፈቅዶ ውጤቱን ለመስማትም ጥቅምት 25 2008 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል። መምህር ግርማ ወደ ማረፊያ ቤት ሄደዋል:: በመምህር ግርማ ወንድሙ ላይ የቀረበው ክስ የሚከተለው ነው:- (ከመንግስት ሚዲያዎች እንደወረደ የተገኘ ነው) የወንጀሉ ዝርዝር ፖሊስ መምህር ግርማ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ምክንያት የሆነው ወንጀል የተፈፀመው መስከረም 2006 ዓ.ም ነው ብሏል። በየካ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ወሰን ግሮሰሪ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩት አቶ በላይነህ ከበደ በመምህር ግርማ የማታለል ወንጀል የተፈጸመባቸው ግለሰብ ናቸው። እንደ ፖሊስ የምርመራ መዝገብ እኚህ ግለሰብ ከትዳር አጋራቸው ጋር 400 ካሬ ሜትር ላይ ባረፈ መኖሪያ ቤታቸው ይኖሩ ነበር። እንደ ምርመራ መዝገቡ መምህር ግርማ የግል ተበዳይን እምነት በመጠቀም የምትኖርበትን መኖሪያ ቤት እስከ ጥር 30 2006 ሽጠህ ካልወጣህ አስከሬንህ ይወጣል ይሏቸዋል። የፖሊስ የምርመራ መዝገብ እንደሚለው ልጅ ያልወለዱት ባልና ሚስት ከመሞት መሰንበት በማለት ይህንን ቤት በጣም በዝቅተኛ ዋጋ በ800 ሺህ ብር ይሸጡታል። ቤቱ በዚህ ዋጋ እንዲሸጥ መምህር ግርማ በራሳቸው ሰዎች አማካኝነት ብዙ ያልተገባ ስራ ሰርተዋል ነው የሚለው የምርመራ መዝገቡ። ከዚያም መምህር ግርማ በዚህ ብቻ ሳይመለሱ የግል ተበዳዩን ቦሌ አካባቢ በራዕይ ያየሁት ቦታ አለ እዚያ ነው ገዝተህ የምትኖረው ይሏቸውና ሌላ የማታለያ ዘዴ ቀየሱ ይላል ምርመራው። ቤቱ የተሸጠበትን 800 ሺህ ብር አምጣና እንዲበረክትልህ ልፀልይበት ብለው በመውሰድ በዚያው ውለው አደሩ፤ የግል ተበዳዩም በእርሳቸው ላይ ያላቸው እምነት ባለመጥፋቱ በትዕግስት ስልክ ቢደውሉላቸውም ስልካቸው ዝግ ሆነባቸው፤ ይባስ ብሎ ከሀገር ወጡ ተባለ የሚለውም ተጠቅሷል። የግል ተበዳይ ሁኔታው ማታለል መሆኑን ስለተረዱ 2007 መጋቢት ወር ገደማ ለፖሊስ ያመለከቱ ሲሆን፥ እርሳቸው ከሄዱበት እስኪመለሱ ፖሊስ የግል ተበዳዩን እና የምስክሮችን ቃል ተቀብሎ ቆይቶ ተጠርጣሪው መምህር ግርማ ወንድሙን ትናንት በቁጥጥር ስር አውሏቸው ነው ዛሬ ፍርድ ቤት ያቀረባቸው። ተጠርጣሪው መምህር ግርማ እኔ የተባለውን ሰው ቀይ ይሁን ጥቁር አይቼው አላውቅም፤ ሆን ተብሎ ከጀርባ የተጠነሰሰብኝ ሴራ አለ በማለት ለችሎቱ አስረድተዋል። - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/47805#sthash.G6117g2V.dpuf

Wednesday, October 28, 2015

አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ ከውጭ ሚ/ር ደኤታነት ተነሱ

(ዘ-ሐበሻ) የሟቹ አምባገን የኢትዮጵያ መሪ የቅርብ ሰው የነበረውና በውጭ ሃገር በተለይም በአሜሪካ እና በብራሰልስ በቆየባቸው ጊዜያቶች የአምባሳደርነት ስም ይዞ የገዢውን ፓርቲ አምባገነን መሪዎችን ገንዘብ በማሸሽ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ቆይቷል እየተባለ በሰፊው የሚተቸው ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ደኤታነት ስልጣኑ ድንገት ተነሳ::   አንዳንድ የቅርብ ምንጮች ብርሃነ ስልጣኑን የለቀቀቀው በፈቃዱ ነው ይበሉ እንጂ ጉዳዩ በአዲስ አበባውና በመቀሌው የሕወሓት ቡድን ክፍፍል ጋር የተያያዘ ነው እየተባለ ነው:: በ2013 ዓ.ም ከደደቢት በረሃ ጀምሮ ለዓመታት ሕወሓት ውስጥ በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ያገለገሉት አምባሳደር ስዩም መስፍን፣ አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ ፣ አቶ አርከበ ዕቁባይና አቶ ዘርዓይ አስገዶም ባቀረቡት ጥያቄና ፓርቲው እየተገበረ ባለው የመተካካት ሂደት በሚል ሽፋን መሰረት ሥልጣናቸውን እንዲለቁ የተደረጉ ሲሆን አቶ መለስ ከሞቱ በኋላ እነዚሁ ባለስልጣናት ወደ ሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ለመግባት ጥረት አድርገው ነበር:: በተለይም ከአቶ አርከበ እቁባይ ጋር በጋብቻ ዝምድና እንዳላቸው የሚነገርላቸው አቶ ብርሃነ ገብረክርስቶስ አቶ አርከበን የሕወሓትና የኢትዮጵያ ጠ/ሚ/ር ለማድረግ ከሚሰራው ቡድን ጀርባ ሆነው ብዙ ሲንቀሳቀሱ ቆይተው በመቀሌው ቡድን በባለፈው የሕወሓት ጉባኤ ላይ መሸነፋቸው ይታወሳል:: አቶ ብርሃነ ከዚህ ቀደም በሕጋዊ ባለቤቱ ላይ ሲወሰልት በመያዙ የቀድሞ ሚስቱ ከዛሬ 12 ና 13 ዓመታት ገደማ በፊት ብርሃነን በዝሙት ጉዳይ ክስ መስርታበት በመረታቱ በርሱ ስም በኒውዮርክ ከተቀመጠው የሕወሃት ባለስልጣናት ገንዘብ ውስጥ ካሳ እንዲሆናት 5 ሚሊዮን ብር እንደተፈረደላት በተለያዩ ሚዲያዎች መዘገቡ አይዘነጋም:: በአቶ ብርሃነ ገብረክርስቶስ ቦታ ሌላ ሚ/ር ደኤታ መሾሙም ተሰምቷል:: ባለስልጣኑ ወደ ሌላ ቦታ ይዘዋወሩ/ አይዘዋወሩ ያገኘነው መረጃ የለም:: - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/47789#sthash.jB36S8wc.dpuf

Tuesday, October 6, 2015

የኃይለማርያም ካቤኔ አባላት ታወቁ * ሬድዋን ወደ ወጣቶች እና ስፖርት ሚ/ር ተገፉ * ሶፍያን አህመድ ተሰናበቱ * ሕወሓት አሁንም የአንበሳውን ድርሻ ይዟል

(ዘ-ሐበሻ) የሕዝብ ተወካዮች የሌሉበት የኢህ አዴግ ፓርላማ ዛሬ ተሰብስቦ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ያቀረቡትን የካቢኔ አባላት አጸደቀ:: በዚህ ካቢኔ ውስጥ አሁንም ሕወሓት ዋና ዋና የስልጣን ቦታዎችን ይዟል:: የውጭ ጉዳይ ሚኒስተርነቱ; ኢኮኖሚው በሕወሓት ስር እንዲቆይ ሲደረግ አሁን ደግሞ በተጨማሪም አቶ ሬድዋን ሁሴን ይመሩት የነበረውን የመንግስት ኮሙዩንኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሀላፊ ሚኒስትር ቦታም ወስዷል:: በዚህም ቦታ ላይ የሕወሓቶ አቶ ጌታቸው ረዳ ተሹመዋል:: ለረዥም ጊዜ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ሁነው ሲሰሩ የቆዩት አቶ ሶፍያን አህመድ በአቶ አብዱላዚዝ መሀመድ ተተክተዋል::
Hailemariam
የሕወሓቱን የካዛንቺሱን መንግስት የሚላላኩት የካቤኔ አባላቱ ዝርዝር እንደሚከተለው ቀርቧል::
አቶ ደመቀ መኮንን – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ
ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል – በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ እና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር
ወይዘሮ አስቴር ማሞ – በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ እና የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስትር
አቶ ሲራጅ ፈጌሳ – የመከላከያ ሚኒስትር
ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም – የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
አቶ ካሳ ተክለብርሃን – የፌደራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር አካባቢ ልማት ሚኒስትር
አቶ ጌታቸው አምባዬ – የፍትህ ሚኒስትር
አቶ አብዱላዚዝ መሀመድ – የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር
አቶ ተፈራ ደርበው – የእርሻ እና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሚኒስትር
አቶ ስለሺ ጌታሁን – የእንሰሳትና የዓሳ ሀብት ልማት ሚኒስትር
አቶ አህመድ አብተው – የኢንዱስትሪ ሚኒስትር
አቶ ያዕቆብ ያላ – የንግድ ሚኒስትር
አቶ አብይ አህመድ – የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር
አቶ ወርቅነህ ገበየሁ – የትራንስፖርት ሚኒስትር
አቶ ሙኩሪያ ሀይሌ – የከተማ ልማት እና ቤቶች ሚኒስትር
ዶክተር አምባቸው መኮንን – የኮንስትራክሽን ሚኒስትር
አቶ ሞቱማ መቃሳ – የውሃ፣ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር
አቶ ሽፈራው ሽጉጤ – የትምህርት ሚኒስትር
አቶ ቶሎሳ ሻጊ – የማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር
ዶክተር ከሰተብርሀን አድማሱ – የጤና ጥበቃ ሚኒስትር
አቶ አብዱልፈታህ አብዱላሂ – የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር
ኢንጂነር አይሻ መሀመድ – የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር
ወይዘሮ ዘነቡ ታደሰ -የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስትር
ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም – የአካባቢ ደን ልማት እና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር
አቶ ሬድዋን ሁሴን – የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትር
ወይዘሮ ደሚቱ ሀምቢሳ – የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚኒስትር ማዕረግ የካቢኒ አባል የሆኑ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ሹመትን ለምክር ቤቱ አቅርበው አስፀድቀዋል።
በዚህም መሰረት
አቶ በከር ሻሌ – የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬከተር
አቶ ጌታቸው ረዳ – የመንግስት ኮሙዩንኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሀላፊ ሚኒስትር
አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ – የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር
ዶክተር ይናገር ደሴ – የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ተሹመዋል።

- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/47173#sthash.3qtnVktv.dpuf

Wednesday, September 30, 2015

አርባ‬ ምንጭ የነበረው የአሜሪካ መንግስት የመከላከያ ኃይል ቡድን አካባቢውን ለቆ እየወጣ ነው - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/47004#sthash.gAOFFpsI.DSRAF3oP.dpuf

Zehabesha News
(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ)
‪አርባ‬ ምንጭ የነበረው የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ መንግስት የመከላከያ ኃይል ቡድን ከባለፈው ሳምንት ሐሙስ ጀምሮ አካባቢውን ለቆ እየወጣ እንደሆነ ታወቀ፡፡
‪‎ህወሓት‬ በሁመራ የሚገኙ 40 የንግድ ቤቶችን ራሱ በስውር በእሳት አቃጥሎ በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የታጠቁ የነፃነት ድርጅቶች ለማላከክ እየሞከረ እንደሚገኝ ከውስጥ አዋቂ ምንጮቻችን የተገኘው መረጃ አጋለጠ፡፡
አርባ ምንጭ የነበረው የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ መንግስት የመከላከያ ኃይል ቡድን ከባለፈው ሳምንት ሐሙስ ጀምሮ አካባቢውን ለቆ እየወጣ እንደሆነ ታወቀ፡፡
በአርባ ምንጭ እና አካባቢው ሲንቀሳቀስ እና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ከዚያ እያስነሳ ወደ ሚፈልገው አቅጣጫ ለጥቃት ሲያሰማራ ለረጅም ጊዜ የቆየው የአሜሪካ የመከላከያ ኃይል ቡድን ከአገሪቱ መንግስት በተሰጠው መመሪያ የቆይታ ጊዜ ኮንትራቱን አቋርጦ ሀሙስ ዕለት አካባቢውን ለቆ መውጣት መጀመሩን በቦታው የሚገኙ ምንጮቻችን ገልፅዋል፡፡
ድሮን የታጠቀው የአሜሪካ የመከላከያ ኃይል ቡድን የአርባ ምንጭን መሬት ለቆ መንቀሳቀስ የጀመረበት ምክንያት ለጊዜው በውል ተለይቶ ባይታወቅም መንግስት ነኝ በሚለው በህወሓት አገዛዝ እና በአሜሪካ መንግስት መካከል አለመግባባት ተከስቶ ቅራኔ ሳይፈጠር እንዳልቀረ ውስጥ አዋቂ ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡
ቡድኑ ከአሁን በፊት ከአርባ ምንጭ በተጨማሪ በድሬ ደዋ ላይ ተቀምጦ በሰው አልባ አውሮፕላኖች በሶማሊያ በሚንቀሳቀሱ የአልሸባብ ተዋጊዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት መክፈቱ ይታወቃል፡፡
ህወሓት በሁመራ የሚገኙ 40 የንግድ ቤቶችን ራሱ በስውር በእሳት አቃጥሎ በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የታጠቁ የነፃነት ድርጅቶች ለማላከክ እየሞከረ እንደሚገኝ ከውስጥ አዋቂ ምንጮቻችን የተገኘው መረጃ አጋለጠ፡፡
የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ገና ከሽፍትነቱ ጀምሮ በህዝብ ላይ ሴራ በማቀነባበር የሚታወቀው ህወሓት ራሱ ግንብቶ ለግለሰቦች ያከራየውን የንግድ ማዕከል ነው በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ የነፃነት ድርጅቶች ድርጊቱን እንደፈፀሙት በማስመሰል ከህዝብ ለመነጠል ሲል ነው በተቀነባበረ ሂደት በእሳት የለቀቀው ፡፡
በህወሓት የተቀነባበረ ሴራ የተከሰተው ከባድ የእሳት አደጋ የደረሰው መስከረም 14 ቀን 2008 ዓ.ም ሲሆን ከ40 በላይ ሱቆች ተበልተው ወደ አመድነት ተቀይረዋል፤ በሚሊዮኖች ገንዘብ የሚገመት ንብረትም ወድሟል፡፡
ህወሓት በአዲስ አበባ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱት የቦንብ ፍንዳታዎች ትግራይ ሆቴልን ጨምሮ እጁ እንዳለበት የአሜሪካ ኤምባሲ ለስቴት ዲፓርትመንት የላከውን ደብዳቤ በዋቢነት ጠቅሶ ዊክሊክስ የተባለው ድረ-ገፅ ማጋለጡ የሚታውስ ነው፡፡
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/47004#sthash.gAOFFpsI.DSRAF3oP.dpuf

Tuesday, September 15, 2015

ከአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ (ሞላ አስገዶምን አስመልክቶ)

September 14, 2015
Patriotic Ginbot 7 Movement for Unity and Democracyበኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ትግል ታሪክ ውስጥ ባጠቃላይና በተለይ ደግሞ ህወሓት/ኢህአዴግ የፖለቲካ ስልጣኑን በተቆጣጠረባቸው ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ውስጥ ህወሓት/ኢህአዴግን እንቃወማለን በሚለው ወገን ገንነው የመጡ ሁለት አፍራሽና ኋላቀር የፖለቲካ አዝማሚያዎች (trends ) አሉ። ከነኝህ ውስጥ አንደኛው ራስን በፖለቲካ አመለካከት ዙሪያ ከማሰባሰብ ይልቅ በጎጥና በዘውግ ደረጃ የመመልከትና ሀገራዊ ፖለቲካን በደም ቆጠራ የመመንዘር አባዜ ነው። ሁለተኛውና ከዚሁ ያልተናነሰው ችግር የፖለቲካ ድርጅት በመሰረታዊ ያመለካከት መርሆች ዙሪያ ሰፋ ያለ የማህበረሰብ ክፍልን የማሰባሰቢያ ድንኳን መሆኑ ቀርቶ፤ በስራ ሳይሆን ድንገተኛ አጋጣሚን በመጠበቅ ትርፍ ለማጋበስ በሚቋምጡ ሰነፍ “ነጋዴዎች“ የተቋቋሙ ሩቅ የማይሄዱ የንግድ ድርጅቶች ይመስልበ ተግባር ምንም የማይፈይዱ ”የፖለቲካ ድርጅቶች“ እንደ አሸን የመፍላታቸው ፈሊጥ ነው። እነኝህ ሁለቱም አዝማሚያዎች የህወሓት/ኢህአዴግን ህይወት ከማራዘም አልፈዉ ማህበረሰቡን ወደሚመኘው እውነተኛ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት አንድ ጋት እንኳን ፈቀቅ አላደረጉትም። ይልቁንም ዴሞክራሲን የሚናፍቁ ታጋዮች ተሰባስበውና ተጠናክረው ስርዓቱን ከመግፋት ይልቅ በግለሰብ ደረጃ ወይንም በትናንሽ ቡድኖች በመሰባሰብ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች በስርዓቱ በቀላሉ እየተመቱ ብዙ ታጋዮች ለሞት፤ ለስቃይና ለእስር ተዳርገዋል። አሁንም እየተዳረጉ ነው።
የዚህ አይነት የትግል አካሄድ ሩቅ እንደማያስኬድ የኢትዮጵያ ህዝብ ከተገነዘበው ቆይቷል። ይህ አካሄድ እንዲቀየርና የፖለቲካ ሀይሎች ተሰባስበው ይህንን በስልጣን ላይ ከሚገባው በላይ የቆየና አገሪቱን ለውርደት የዳረገ የጥቂት ዘራፊዎች ቡድን ከጫንቃው ላይ እንዲያነሱለት ሲማጠን ቆይቷል።ምንም እንኳን በመሪዎች ድክመት የሚመኘውን ዳር መድረስ ባይችልም ባጭር ጊዜ ልምዱ በትንሹም ቢሆን የተባበረ ትግል ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም በመጠኑም ቢሆን አይቶታል።
ይህ የህዝብ ፍላጎት መኖር ግን በራሱ ይህንን የተባበረ ሰፊ ማህበራዊ እንቅስቃሴ መፍጠርን ቀላል ያደርገዋል ማለት አይደለም። በብዙ ስራ፤ በብዙ ድካምና ያላሰለሰ ጥረት የሚፈጠር እልህ አስጨራሽ ሂደት ነው። ባንድ በኩል እንዲህ አይነት ሰፊ የህዝብ እንቅስቃሴ በስልጣኑ ለመቆየት የሚፈጥርበትን ችግር የሚረዳው በስልጣን ላይ ያለው የዘራፊዎች ቡድን ይህን እንቅስቃሴ ከወዲሁ ለማምከን ያለ የሌለ የገንዘብ፤ የስለላና የተንኮል ሀይሉን ይጠቀማል። በተቃዋሚ ድርጅቶች ውስጥ ሰርጎ በመግባትና ደካማ ሀይሎችን በገንዘብ በመግዛት ወይንም በማስፈራራት እንዲህ አይነት ትብብሮች እንዳይፈጠሩ ከውስጥ ለመቦርቦር ተግቶ ይሰራል። በሌላ በኩል ደግሞ የትም የማያደርሳቸውን “የራሳቸውን ድርጅት” የሙጢኝ ብለው ለትልቅና አገራዊ አላማ እራሳቸውን ላለማስገዛት የቆረጡ ደካማ “የድርጅት መሪዎች” እንዲህ አይነቱን የጋራ እንቅስቃሴ በራሳቸው ግብዝነትና ስግብግብነት ምክንያት ብቻ ሊያሰናክሉት መሞከራቸው አይቀርም።
ይህ ግን ጊዜው ያለፈበት አዝማሚያ ነውና የሚሳካ ሙከራ አይሆንም። የተናጠል ትግል ሂደት ማብቂያው ጊዜ ተቃርቧል። የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የሚታገሉ ኃይሎች እንዲህ አይነቱን ፋይዳ ቢስ ሂደት የመቀበል ትዕግስታቸው ተሟጧል። በቅርብ ጊዜ የሞላ አስገዶምን መክዳት በማስመልከት የትህዴን አመራር ባወጣው መግለጫ“ኢትዮጵያን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊት ሀገር ለማድረግ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር አብሮ መስራት የድርጅታችን መሰረታዊ መርሆ ነው” እንዳለው ይህ መሰረታዊ መርሆ በሀገራችን የጸረ ህወሓት/ኢህአዴግ ትግል የበላይነት ይዞ እየመጣ ያለ እጅግ አስፈላጊና ለድሉም ወሳኝ የሆነ የጊዜው የፖለቲካ አዝማሚያ ነው። አርበኞች ግንቦት 7 ይህን መሰረታዊ መርሆ ከምር ወስዶ የሚንቀሳቀስ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ነው።
ይህ አዲስ የፖለቲካ አዝማሚያ ምቾት የማይሰጣቸው የፖለቲካ ኃይሎች መኖራቸው የሚጠበቅ ነው። የህወሓት/ኢህአዴግ የስለላ ድርጅት ከሰሞኑ ሞላ አስገዶምን በማስመልከት ባወጣው መግለጫ በግልጽ እንዳስቀመጠው ኢትዮጵያውያን የዴሞክራሲ ኃይሎች ተሰባስበው እንዳይታገሉና ስርዓቱን እንዳይፈታተኑ የማያደርገው ጥረት የለም። በዚህ በህወሓት/ኢህአዴግ መሰሪ እንቅስቃሴ ደግሞ በቀላሉ መጠቀሚያ የሚሆኑት በጋራ የሚደረግ ትግል በግለሰብ ደረጃ ያሳጣናል ብለው የሚፈሩት “የግል ጎጆና” ጥቅም የሚያስጨነቃቸው ደካማ የፖለቲካ መሪዎች ነን ባዮችን ነው። ባንጻሩ በየድርጅቶቹ ውስጥ በሚገኙት ብዙሀኑ ሩቅ አሳቢ መሪዎች ጥረትና በተለይም ደግሞ ይህን ትግል ለአላማ እንጂ ለሌላ ምንም አይነት የግል ጥቅም ያልተቀላቀሉና በትግሉ ሂደትም ትልቁን ሚና በሚጫወቱት ብዙሀን ታጋዮች አልበገር ባይነት እንዲህ አይነት ደካማ መሪዎች ተከታይ በማጣት ሲዳከሙና በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በድርጅታቸው ውስጥ የሚነሳባቸውን ተቃውሞ መቋቋም ባለመቻላቸው በቀላሉ እየተፍሸለሸሉ ከመራገፍ በስተቀር በድርጅቶቹ ላይ ከባድ ጉዳት ሳያደርሱ ይከስማሉ።
በህወሓት/ኢህአዴግ “የስለላ ድርጅት አቀናባሪነት” በሞላ አስገዶም መሪነት ከሰሞኑ የተሞከረው የማፍረስ ንቅናቄ ከሽፎ ወደ ተስፋ መቁረጥ የክህደት እንቅስቃሴ የተቀየረው የሰሞኑ ሙከራም የዚህ አጠቃላይ ሂደት አካል ነው። በዚህ የከሸፈ ሙከራ ውስጥ እጅግ የሚገርመውና የትህዴንን ብዙሀን አመራሮች ብስለት፤ የድርጅቱን መዋቅራዊና ድርጅታዊ ጥንካሬ፤ እንዲሁም ብዙሀኑ ታጋይ ለጋራ ትግል ያለውን ቆራጥ አቋም ያስመሰከረው፤ ይህንን የማፍረስ ሙከራ የመራውና ሳያሳካለት በመጨረሻም በጣም ጥቂት ተከታዮቹን ብቻ ይዞ የከዳው ለረጅም ጊዜ የድርጅቱ ሊቀመንበር የነበረው ሞላ አስገዶም መሆኑ ነው። እንዲህ አይነት የመክዳት ሂደት ባጭር ጊዜ በማህበረሰባችን ላይ የሚፈጥረውን አስጨናቂ ስሜት የምንረዳው ቢሆንም ከዚያ በላይ ልንረዳው የሚገባው ግን በእንዲህ አይነት ከፍተኛ ያመራር ቦታ የነበረ ሰው ሙከራ አለመሳካት በእርግጥም የሀገራችን ፖለቲካ እየበሰለ፤ ከግለሰብ አመራሮች ተጽእኖ እየተላቀቀ፤ አዲስ የተባብሮ መታገል አቅጣጫን እያበሰረ እየሄደ መሆኑንና በትናንሽ ሰዎች መግተርተር ይህ ሂደት የማይቀለበስ መሆኑን የሚያመለክት የረጅም ጊዜ ግኝት መሆኑን ነው።
አርበኞች ግንቦት 7 በዚህ አጋጣሚ ለትህዴን ብዙሀን አመራርና ለሰፊው ታጋይ በመርህ ላይ ለተመሰረተው አቋማቸውና መርሃቸውን ለማስጠበቅ ለሚያደርጉት ቆራጥ ትግል ያለውን ጓዳዊ አክብሮት ይገልጻል። በመግለጫቸው ላይ በግልጽ ያስቀመጡት መርሆአቸው የኛም መርሆ መሆኑን ስንገልጽላቸው በታላቅ ኩራት ነው። ድርጅታቸውን እያጸዱ የተመሰረቱበትን መርሆ ጠብቀው ለመጓዝ ባሳዩት ቁርጠኝነትና ወደፊትም በሚያደርጉት ትግል ምንጊዜም ከጎናቸው መሆናችንንና ጓዳዊ ድጋፋችን ምንጊዜም እንደማይለያቸው በዚህ አጋጣሚ ደግመን ልናረጋግጥላቸው እንወዳለን። በመግለጫቸው ላይ እንዳሉትም ይህ ትግል ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ሳያደርግ የማይቆምና እንዲያውም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ለኢትዮጵያ ህዝብም በየጊዜው በሚፈጠሩ እንቅፋቶች ላይ ሳያተኩር ትግሉን በሙሉ ልብ እንዲደግፍ ያደረጉት ጥሪ የኛም ጥሪ ነው።
አንድነት ኃይል ነው!!!
አርበኞች ግንቦት 7: ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ

Friday, August 7, 2015

የአርበኞች ግንቦት 7 አመራር ኤፍሬም ማዴቦ አስመራ ወርደው የትጥቅ ትግሉን ተቀላቀሉ


(ዘ-ሐበሻ) ከአርበኞች ግንቦት 7 ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ኤፍሬም ማዴቦ አስመራ ሄደው የትጥቅ ትግሉን መቀላቀላቸው ተሰማ::
የአርበኞች ግንቦት 7 መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንዲሁም አቶ ነአምን ዘለቀ አስመራ ወርደው ትግሉን ከተቀላቀሉ ሳምንታት የተቆጠረ ሲሆን አቶ ኤፍሬም ማዴቦም ከትናንት በስቲያ ትግሉን ተቀላቅለዋል::
አርበኞች ግንቦት 7 በሕወሓት መንግስት ሠራዊት ላይ በሰሜን በኩል ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ አፍቃሬ ወያኔ ሚዲያዎች በሰሜን በኩል ትግል የለም ለማለት “የኢትዮጵያ መንግስት ሰራዊቱን ወደ ሱማሊያ አሰማራ” የሚሉ ዜናዎችን በማስተጋባት ላይ ይገኛሉ::
ለዘ-ሐበሻ የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው ከአቶ ኤፍሬም በተጨማሪ ሌሎች ስማቸው ያልጠቀሰ የድርጅቱ አመራሮች ትልቅ ገቢ የሚያስገኝላቸው ሥራቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን በመተው የትጥቅ ትግሉን ተቀላቅለዋል::
የዛሬ 25 ዓመት ወደ ስደት ገብተው በሰሜን አሜሪካ የተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተማሩት አቶ ኤፍሬም ከጆርጅ ሜሰን ዩኒቨርሲቲ በማዕረግ የተመረቁ ታዋቂ የፖለቲካ ሰው ናቸው::

Monday, July 20, 2015

ሊቀመንበራችን ትግል ሜዳ ውስጥ ነው!- መግለጫ

ሐምሌ 12 2007 ዓ.ም.
ህወሓት በኢትዮጵያዊያን እና በኢትዮጵያ ላይ ያሰፈነው ዘረኛና ፋሽስታዊ አገዛዝ እንዲያበቃ፤ በምትኩም ፍትህ፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ዲሞክራሲ የሰፈኑበት የፓለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት እንዲመሠረት እና የሀገራችን አንድነት በጠንካራ መሠረት ላይ ለማኖር አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ተገዶ የገባበት የመረረ የአመጽ ትግል መጀመሩን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል። በዚህም መሠረት ኢትዮጵያዊያን የነፃነት አርበኞች በጀግነትና በጽናት እየታገሉ ነው።
ይህ ትግል በባርነትና በነፃነት መካከል የሚደረግ ወሳኝ ትግል ነው። የዚህ ትግል ውጤት የእኛ የዚህ ዘመን ትውልድ ሕይወት ብቻ ሳይሆን የአገራችንን የወደፊት ታሪክ፤ የልጅ ልጆቻችንን ሕይወት ይወስናል። በዚህም ምክንያት ይህንን ትግል በድል መወጣት ግዴታችን ነው። በዚህ ወሳኝ ወቅት ለነፃነት ግድ ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከጎናችን ሊቆም ይገባል።
አርበኞች ግንቦት 7 አመራሩን ሁኔታዎች በፈቀዱ መጠን እና ትግሉ በሚጠይቀው ቦታ እንዲገኙ የሚያደርግ መሆኑ ሲገልጽ ቆይቷል። አሁን ትግሉ በደረሰበት ደረጃ የአመራሩ በትግሉ ሜዳ ውስጥ መገኘት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ሊቀመንበሩን ጨምሮ አመራሩን ወደ ትግሉ ሜዳ አንቀሳቅሷል። በዚህም መሠረት የንቅናቄው ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ወደ ትግል ሜዳ ወርዷል።
ትግሉ መሯል። ወሳኝ የሆነ ትግል ውስጥ ገብተናል። የትግሉ መሪዎች የሕይወት መስዋዕትነት እሚከፈልበት ቦታ ይገኛሉ። በአሁኑ ሰዓት የንቅናቄው አመራር በተሟላ ሁኔታ በትግሉ ሜዳ ውስጥ እንዲገኝ ማድረግ ተችሏል። ኢትዮጵያዊያን እጅ ለእጅ ተያይዘን ዘረኛው የህወሓት አገዛዝን ከጫንቃችን ለማስወገድ ቆርጠን እንድንነሳ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል።
ኢትዮጵያን ከህወሓት አገዛዝ ነፃ የሚያወጣው አርበኞች ግንቦት 7 ብቻ አይደለም። ስለሆነም ከሌሎች ድርጅቶች ጋር የሚደረገው ትብብር ቀዳሚ ትኩረት ከተሰጣቸው ሥራዎች አንዱ ነው። አርበኞች ግንቦት 7 ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተቀጣጠለው ሕዝባዊ አመጽ ለድል እንዲበቃ ይታገላል። ኢትዮጵያዊያንም በያሉበትም በተመሳሳይ ልዩነቶቻቸውን አቻችለው በህወሓት ፋሽስታዊ አገዛዝ ላይ ክንዳቸውን እንዲያነሱ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል።
እነሆ የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በአካል ትግል ሜዳ ውስጥ ይገኛል። የሚችል ሁሉ እንዲከተል፤ መከተል የማይችል በያለበት ሁኖ ሁለገብ ትግሉን እንዲያጧጥፍ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ