Monday, March 28, 2016

የሰማያዊ ፓርቲ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ሊቀመንበሩን ኢንጂነር ይልቃልን እና አቶ ወረታውን አባረርኩ አለ

(ምንሊክ ሳልሳዊ) – ጠንካራ ፓርቲዎችን ሰርጎ ገብ አስገብቶ በመበታተን ጠንካራ አመራሮችን በመወንጀል ፓርቲዎችን አዳክሞ ብመቃብራቸው ላይ ተለጣፊ ታማኝ ተቃዋሚዎችን የሚተክለው ኢሕኣዴግ በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ገብቶ እየበጠበጠ እንደሚገኝ ከተለያዩ ምንጮች የሚወጡ ዘገባዎችን ተመልክተናል::
Yilikal Getenet
ፓርቲውን ለመቆጣጠር ፍላጎት ያለው ኢሕኣዴግ በሚደጉባቸው ሪፖርተር እና አዲስ አድማስ ጋዜጦች በኩል የፓርቲ አመራሮችን ስም ካለማስረጃ እና የፍትህ ውሳኔ ሲያጠፉ ከርመዋል::
በዛሬው እለት የተሰማው ዜና ደግሞ የሰማያዊ ፓርቲ ልሳን የነገረ ኢትዮጵያ አዘጋጅ በትዊተር ገጹ በዚህ መሰረት የድርጅቱ ሊቀመንበር ይልቃል ጌትነት እና ወረታው ዋሴ ከፓርቲው ሲባረሩ ወይንሸት ሞላ እና ስለሺ ፈይሳ ለ2 አምት ከማነኛውም የአመራርነት ቦታ ታግደዋል።ሰማያዊፓርቲ ሊቀመንበሩንና የቀድሞው የፋይናንስ ኃላፊን ከፓርቲው አባረረ። ሆኖም የሊቀመንበሩ መባረር ተግባራዊ የሚሆነው ከጠቅላላ ጉባኤ በኁዋላ መሆኑን እርምጃውን የወሰድው የዲስፕሊን ኮሚቴ ገልጹዋል ሲል ጽፏል::

Wednesday, March 23, 2016

ቤተ አምሃራ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምትን ትግል በማስመለከት ብአዴንን አስጠነቀቀ – “የአማራ ህዝብ ቁጣ ለመትረፍ ከህዝባችሁ ጎን ቁሙ”


Share1  519  1 
 Share1

bete amhara
ቀን: መጋቢት 13 2008 ዓ. ም
ወቅታዊውን የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ የማንነት ትግልን በማስመልከት ከቤተ አማራ የተሰጠ መግለጫ ፦
የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ የትግሬ – ወያኔ ሽፍታ ስርዓት በጉልበት የጫነባቸውን ባዕድ ማንነት በመቃወም የተፈጥሮ ማንነታቸው የሆነውን አማራነት ጥያቄ ያቀረቡት እጅግ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንደነበር ይታወቃል::
ይህም የታላቁ አማራ ህዝብ ለዘመናት የኖረበትን ከፍተኛ የሞራል ደረጃ ማሳያ ሆኖ ተመዝግቧል:: ምንም እንኳ በወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ላይ የደረሰው እና አሁንም በመተግበር ላይ ያለው ግፍ እና የዘር ማጥፋት እርምጃ ለበቀል ሊያነሳሳ የሚችል የአረመኔዎች ተግባር ቢሆንም ሰፊው የአማራ ህዝብ በአስደናቂ ትዕግስት እና ሆደ ሰፊነት ለሁለት አስርት አመታት ጉዳዮን ታግሶት ቆይቷል::
ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ የመብት ጥያቄዎች የሚያስደነግጡት የትግሬ-ወያኔ አስተዳደር የእኛን ወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ የማንነት ጥያቄ ለማዳፈን ያልጎነጎነው ሴራ የለም:: እስራት፣ ማዋከብ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ማፈናቀል እና ግድያ በተለያዮ ጊዜያት በወገኖቻችን ላይ የተፈጸመ እና እየተፈጸመ ያለ ሲሆን በተቀነባበረ ወያኔያዊ ሰላማዊ ሰልፍም ያለምንም ሃፍረት በሃገሪቱ ቴሌቪዥንም በተዘገበ ፕሮግራም በወገኖቻችን ላይ የተለመደውን የጅምላ ግድያ እርምጃ ይወሰድ ዘንድ ሲለፍፉ ሰፊው የአማራ ህዝብ በአግራሞት ተከታትሎታል:: ከሶስት ቀናት በፊት በዳንሻ እና ሶሮቃ ተጠናክሮ የቀጠለው አፈና፣ እስር እና ግድያም የዚሁ በዕብሪት የተሞላው የፀረ – አማራ እቅዳቸው አካል ነው::
በመሆኑም የትግሬ-ወያኔ አስተዳደር ይህ ሁለቱን ህዝቦች ወደማይበርድ እልቂት ሊወስድ ከሚችለው ሰይጣናዊ ድርጊት ባስቸኳይ በመታቀብ የሚከተሉትን እርምጃዎች እንዲወስድ ቤተ አማራ በጥብቅ ያሳስባል::
1. በደህንነት አሽከሮቻችሁ ታፍነው የተወሰዱት የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ የማንነት ኮሚቴው አባል አቶ ሊላይ ብርሃኔ እና ሌሎች አማሮች ያለምንም ማንገላታት ባስቸኳይ እንዲፈቱ::
2. የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ የማንነት ጥያቄ የማይቀለበስ የመላው አማራ ጥያቄ መሆኑን ተገንዝባችሁ ከያዛችሁት እራስን የማጥፋት አካሄድ እንድትቆጠቡ::
3. በተለያዩ ቦታዎች በአማራ ወገኖቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ማንገላታት፣ እስር እና ግድያ ባስቸኳይ እንዲቆም::

ወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ሆይ ፦

የመላው ቤተ አማራ ወገኖቻችሁ ማንነታችሁ ማንነታችን፣ ጉዳታችሁ ጉዳታችን ፣ ጠላታችሁ ጠላታችን ብለን በተጠንቀቅ ከጎናችሁ የተሰለፍን መሆናችንን ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን::

መላው አማራ ሆይ ፦
የትግሬ – ወያኔ የደገሰልንን የዘር ማጥፋት ዘመቻ ለመመከት በጀግኖች አባቶቻችን መንፈስ በአማራነት ተደራጂተን በአንድነት እንድንቆም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን::
በዕርቅ ስም የህዝባችንን ትግል ለመቀልበስ ለምትንቀሳቀሱ ሃሳዊ ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ፦
ሰላማዊ የሆነውን የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራነት ጥያቄ ለማዳፈን እውነተኛ ባልሆነ የሽምግልና ስም እየተንቀሳቀሳችሁ ያላችሁ ግለሰቦች ከአንዴም ሁለት ጊዜ ድብቅ ማንነታችሁን ህዝባችን ስልተረዳ ከዚህ መጥፎ ግብራችሁ እንድትታቀቡ በጥብቅ እናስጠነቅቃለን::
እንዲሁም የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ለሃይማኖቱ ያለውን ቀናዒነት ተጠቅማችሁ የህዝባችንን የማይቀለበስ የማንነት ጥያቄ ለማዳከም እየጣራችሁ ያላችሁ የስርዓቱ ጥገኛ የሃይማኖት መሪዎች ከዚህ መሰሪ ተግባራችሁ እጃችሁን እንድትሰበስቡ በጥብቅ እናሳስባለን።
ለብአዴን ባለስልጣናት እና ካድሬዎች ፦
ከመጨረሻው የአማራ ህዝብ ቁጣ ለመትረፍ ከህዝባችሁ ጎን ከመቆም ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌላችሁ አውቃችሁ አስላለፋችሁን ታስተካክሉ ዘንድ በጥብቅ እናሳስባለን። ታላቁ የአማራ ህዝብ እንደ ንስር ሃይሉን ያድሳል ! ቤተ አማራ ወደፊት !

Wednesday, March 2, 2016

የህወሃት ልዩ ነፍሰ ገዳይ ሠራዊት አመሰራረት። የገዳይ ቡድኑ አጋዚ እና የእናት እንባ


agazi
የህወሃት ልዩ ነፍሰ ገዳይ ሠራዊት አመሰራረት። የገዳይ ቡድኑ አጋዚ እና የእናት እንባ
የእግሊዝኛው ጽሁፍ አዘጋጅ ፡ዓለም ማሞ
የአማርኛው ተርጓሚ፡ቢላል አበጋዝ
“ፔንታጎን ያሰለጠናቸው የኢትዮጵያ ሠራዊት ፤ክፉውን አጋዚ የተሰኘውን ልዩ ኅይልም ይጨምራል።”
–ጄረሚ ስከሂል
ኢንተር- ሴፕት ኤንድ ናሽናል ሴኩሪቲ ለተባለው ጋዜጣ መስራችና ቃል አቀባይ ከአሜሪካ መንግስት ክፍተኛ ምክር ቤት የፍርድ ኮሚቴ ዘንድ ቀርቦ ከሰጠው የምስክርነት ቃል የተወሰደ ጥቅስ። ዲሴምበር 9 ፣2010
ታሪኩ እነሆ
ከእድሜዋ በላይ የጠናች መስላ ትታያለች።በአካል ያያት ስድሳ ዓመት ሞልቷታል ብሎ መገመት ይችላል።እውነቱ ግን አርባ ዓመትዋ ብቻ ነው።
“ወታደራዊው መንግስት ስልጣን ከመያዙ ሁለት ዓመት በፊት ነው የተወለድኩት” ትላለች ታሪክ እየጠቀሰች።የተጨማደደው ቆዳዋ፤ማዲያቷ እና ሽበትዋ መከራን ያሳለፈችን እናት ታሪክ ይናገራሉ።ያለፉት አስር ዓመታት በችግር የተሰቃየችባቸው ናቸው። “የበኩር ልጄን ከአስር ዓመት በፊት ቀበርኩ፤እኛ ተቃዋሚዎች አቸንፈን ድምጣችንን በቀሙን ጊዜ” አለች ወደ አድማሱ ቃኝታ ከተራሮቹ ሰው ብቅ የሚል እንደሁ ትጠብቅ ይመስል።
“እንዴት ሞተ?” ብዬ ጠየቅኋት ላለፉት አስራ አምስት ደቂቃዎች ከማታው ውርጭ ላይ ከቆየንበት ውጭ ወደቤት እየተከተልኳት።
“በጠራራ ጸሃይ ከሚወደው ጓደኛው ጋር ነው የገደሉት።አንዲት ቦታ፤ በአንዲት ቀን ነው አዲስ አበባ ላይ የተገደሉት።” አለች በተጎሳቀለው ፊትዋ ላይ እምባዋ እየወረደ።ምሬትዋንና ያለችበተን የከፋ ሃዘን ጥልቀት በቃላት ለመግለጥ ይከብዳል። ከተቀመጥኩበት ብድግ ብዬ እጆችዋን ይዤ ካጠገብዋ ቁጢጥ አልኩ። “ማን ገደላቸው ?” ብዬ ጠየቅኋት።ትክዝ ብላ ቆይታ ወደበሩ ራመድ፡ ራመድ ብላ በሩን ከዘጋችው በኋላ ሚስጥር እንደምትነግረኝ ሁሉ ዝቅ ባለ ድምጥ “አጋዚ። አጋዚ። ነው የገደላቸው” እያለች የሟች ልጆችዋን ፎቶግራፎች ሳም ሳም አድርጋ እንዳያቸው ሰጠችኝ።ለትምህርት ምረቃ ቀን የተነሷቸው ነበሩ።ምስላቸው በፈገግታ ተሞልቷል።ምኞትና ተሰፋ ይታይባቸዋል።ፎቶግራፎቹ በእምባዋ ርሰዋል የንባዋ ዘለላ በፎቶ የሚታየውን የልጆችዋን ፈገግታ ሲሸፍነው ሀዘንዋን የሚጋሯት መስሎ ታየኝ። ሙታንና ቁዋሚዎች አብረው የሚያለቅሱበት አገር። በምናቤ ልጆቹ ቤቱ ውስጥ ያሉ መሰለኝ።በናትና ልጅ መሃል ሞትም የማያስቀረው ውህደት በማህፅንና በእትበት መሃከል ያለው ቁርኝት ይሆን ? እንጃ። ብቻ የልጆቹ ውቃቢና የዓፍላ መንፈሳቸው ክቤቱ ውስጥ አለ።ካደጉበት።ከምዬ ቤት።ገና ባጭር ሳይቀጩ ከነበሩበት።ከኪሴ መሃረብ አውጥቼ እንባውን ከፎተግራፎቹ በዝግታ ጠረግሁ።በጥልቅ አዘኔታ ሳያቸው ወንድሞቼ፤የወንድሜ ልጆች፤ያጎት ያክስቶቸ እንዲያው የናቴ ልጆች መስለው ታዩኝ።በህይወት ባሉበት ጊዘ አግኝቻቸው ባላውቅም የማውቃቸው መሰሉኝ።የኔ የራሴን ያለፈ የልጅነቴንና የወጣትነት ዘመን ከፊቴ ደቀኑብኝ።ወጣትነቴን፤ፍርሃት አልባነቱን፤ለፍትህ፤ለነጻነት፤በቁርጠኝነት ተከራካሪነት መቆሙን።
ዲሞክራሲ! ለምእተ አመታት እውን ያልሆን ስንቀርበው የሚርቀን የኔ ትውልድ ህልም፤ያለፈው ትውልድም ህልም፤የዛሬው ትውልድም። “አዬ እርግማን” ብዬ ለራሴ አጉተመተምኩ።
ለመሄድ ስነሳ አዘንተኛዋ እናት እቅፍ አረገችኝና እባክህ ደግመህ መጥተህ ጠይቀኝ አለችኝ።እምባ እየተናነቀኝ ይሁን መጣለሁ። እጠይቅሻለሁ አልኳት።ስለያት ብቸኝነትዋን አሰብኩት።የሞቀ የደመቀ ሁለት ልጆችዋ ይቦረቁና ይጫወቱ የነበረበትን የዛሬውን ኦና ቤትዋን አሰብኩት።የናትን ሃዘን ጥልቀቱን እንድረዳው፤እንዲሰማኝ ሞከርኩ። የእናትን ሃዘን ፤የዘጠኝ ወር ቤትን ህመም ፤ ክናት ሌላ ማን ሊረዳው? አልኩ ለራሴ።
አጋዚ የሚለውን ስም በተደጋጋሚ ሰምቸዋለሁ።ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች ስለ አጋዚ የሚናገሩት ልክ እንደ ውጭ ወራሪ ሀይል አድርገው ነው።የዚህ ቡድን ሰለቦችና ተግባሩን ያዩት እንደሚናገሩት “ግኡዝ ገዳይ ሮቦቶች፤ ምንም ልዩነት የማያደርጉ ትንሽ ከትልቁ መለየት ህጻናት ከአዋቂ፤ወጣት ሽማግሌ፤ ሴት፤ ወንድ፤ የታጠቀ ወይ ጀሌ አንዱንም የማይመርጡ።ጨፍጫፊ።ግፍ መስራቱን ይወዱታል ቢባል ከውነት የራቀ አይሆንም።
አንድ የፋሺት ጣሊያ ወረራ ጊዜ የነበሩ አርበኛ አጋዚን ከጣሊያኑ ጊዜ ካራብኘሪ ጋር ያመሳስሉታል።
“ቋንቋቸው ግራ ነው።ባህልና ወግ ግዳቸውም አይደል።ባሻቸው ጊዜ መጥተው ወንዶችን፤ልጆችን መንጭቀው ይሄዳሉ።ሲሻቸው እዚው ረሽነው ይሄዳሉ። መንደር ቀበሌ ከተማ ይወርራሉ።አየህ አጋዚ ልክ እንደ ጣልያን ካራብኘሪዎች ነው።” የአረጋዊው የነጣው ረጅም ጢም፤የተሸበሸበው ግንባራቸው ብሩህ አይኖቻቸው ምስክርነት የቆሙ ይመስላሉ።
“ታውቃለህ እንዲህ ያለ በገዛ ህዝቡ ላይ የሚጨክን መንግስት ኖሮን በታሪካችን አያውቅም። ካራብኘሪዎችን ምን እንዳደረግናቸው ልንገርህ።” አሉ በኮራ ድምጻቸው “የእግዜርን እርዳታ ይዘን ከአርበኞች ጋር ሁነን ነቅለን ጣልናቸው።” የሚነደው ያገር ፍቅራቸው እንደ እሳት ወላፈን ሙቀቱ እየተሰማኝ። “አጋዚዎችንም ዋጋቸውን እንሰጣቸዋለን።አዲሱ ትውልድ የኛን አርበኝነት ተዋርሷል።የጊዜ ጉዳይ ነው።አገራችን ነጻ ትወጣለች።” አሉ ምርኩዛቸውን ጠበቅ አድርገው እየጨበጡ።የታሪክ ምጸት ቢሆንም የአጋዚን ከጣሊያን ካራብኘሪዎች ማነጻጸር አሁን ብቻ አይደለም የሰማሁት።በስልጣን ላለው መንግስት ተወዳዳሪ ለሌለው ጭካኔ ማመሳከሪያ በመሻት ነው።
ባገሪቱ የትኛውም ክፍል ህዝባዊ እምቢተኝነት ወይም አመጽ ሲነሳሳ ከየት መጣ ሳይባል አጋዚ ከቸች ብሎ የአፈናና የግድያ ተግባሩን ያከናውናል።ብዙ ተመሳሳይ የአጋዚን ዘግናኝ ተግባራት፤ኢሰባዊ ድርጊቶችም የሚገልጡ በርካታ ምስክርነቶች ሰምቻለሁ።ሁለት ወንዶች ልጆችዋን ለአጋዚ የገበረችውን እናት ካነጋገርኩ ወዲህ ግን አስተሳሰቤ ተለወጠ።ሀዘንም ዋጠኝ።ከዚህ ሌላስ ምን ግፍ ተሰርቷል?ምን ግፍስ ይሰራ ይሆን? እያለ አእምሮዬ ወተወተ።የዚህን የገዳይ፤አፋኝ ቡድን አሳዛኝ ድርጊት በሚቻለኝ መጠን ለማጋለጥ ቁርጠኛ አደረገኝ።
አጋዚ የሚለው ስም በኢትዮጵያ ፍራትና ሽብርን ይፈጥራል።ልክ ካራቫን ዴላ ሙኤርቴ (የሞት ቅፍለት) ተብሎ በቺሌ ላቲን አሜሪካ ይታወቅ እንደነበረው አይነት ነው።ይህ ቡድን አውጉስቶ ፒኖቼ የተባለው ወታደራዊ አምባ ገነን በ1973 ዓም መፈንቅለ መንግስት እንዳካሄደ ያቋቋመው ነው።ሌላው ተመሳሳይ ደግሞ ጄኔራል ሆዜ አልቤርቶ ሜድራኖ ያቋቋመው ኦርጋኒዛሲኦን ዴሞክራሲያ ናሺናሊስታ የተባለው የኤል ሳልቫዶር (ላቲን አሜሪካ) ገዳይ ሰራዊት ነው። ይህ ሰራዊት በስውር የሚያግት፤በህይወት ፈራጅ፤ሰቆቃ ፈጻሚ ነበር። ለማንም መንግስትን ለተቃወመ ወይንም ተቃውሙዋል ተብሎ ለሚጠረጠር ቡድን ወይም ግለ ሰብ ያለ ምህረትና ሰባዊነት የግፍ ቀንበሩን ያሰፈረ ቡድን ነበር።
አጋዚ ምስጢራዊ ራስ ገዝ ተጠያቂነቱ ቱባ ለሆኑት እፍኝ የማይሞሉ የህወሃት አመራሮች ነው።አጋዚ የተሰየመው ከህወሃት መስራቾች አንዱ በነበረው ዘሩ ገሰሰ የትግል ስሙ አጋዚ ነበርና።በውነተኛ ወታደራዊ አደረጃጀት ሲመዘን አጋዚ የግል ጦር፤ቅጥረኛ በጦር ቱጃሮች (war lordes) የግል ጥቅማቸውን ለመጠበቅ የሚቆሙትን ዓይነት ነው።የእዝ ሰንሰለቱ ከቋሚው ዘረኛና በዘር ከተዋቀረው የህወሃት መደበኛ መከላከያ መዋቅር ውጭ ነው።የአጋዚ መኖር ዋነኛ ምክንያት ወያኔ ኢሃዴግን በስልጣን ማሰንበት ነው።መንደርም በእሳት ተለኩሶ ይውደም፤ንጹሃን በጥይት ይፈጁ፤ ቀዬዎች የሽብር አምባ ይሆኑ፤ወያኔ ብቻ ይሰንብት። የአጋዚ መኖር ለዚህ ነው።አጋዚ ቀድሞ ሲመሰረት “ጸረ ዓለማቀፍ ሽብርተኛ” የሚል ጭንብል ነበረው። ይህ የሆነው የምእራብ አገር መንግስታትን ለማማለልና ደስ ለማሰኝት አልፎም ድጋፍ፤ስልጠና እና ትጥቅም ለማግኘት ነበር።ቍም ነገሩ ግን አገር በቀል የሆኑትንና ለዲሞክራሲ ፤ ለፍትህና ለነጻነት ራእይ የሚደረጉ ትግሎችንና እቢተኝነትን መደምሰስ ነው።
በዚህ ጉዳይ ላይ ጥቂት መርማሪ ጋዜጠኞች ስለ አጋዚና የውጭ ድጋፉ ጠይቀዋል።ይህን ግፈኛ ቡድን ማነው የሚያስታጥቀው ማንስ አሰለጠነው እያሉ።ከኒህ ጋዜጠኞች መካከል ጄረሚ ስከሂል ተቀዳሚው ነው።የዩ ኤስ አማሪካን ተመሳሳይ ሚና በአፍጋኒስታን፤ በማሊ፤ በሶማሊያ፤በየመን መርምሯል። በዲሴምበር 9 ቀን 2010 ዓም ለአሜሪካ ምክር ቤት በዝርዝር ምስክርነት ሰጥቷል።ምስክርነቱ ሰው አልባ የሚበር አውሮፕላንን እቅስቃሴ፤የዩ ኤስ አሜሪካንና የሶማሊያ ጎሳ ጦር አበጋዞች ጋር ግንኙነት አካትዋል። “ሽብርተኝነትን መዋጋት” በሚል ሰበብ እንዴት አሜሪካ እንደ አጋዚ ያሉ የገዛ አገራቸውን ዜጎቸ የሚያሸብሩ ወታደራዊ ተቋሞችን መደራጀት ልታግዝ እንዴት እንደቻለች ጠይቋል። እንደ ሚስተር ሺል ጥናት “የዩ ኤስ አሜሪካን ልዩ ወታደራዊ ቡድን ለረጅም ጊዜ የአጋዚን ሰራዊት ሲያሰለጥን ኖርዋል” የስከሂል የጥናት ጭብጥ እንደ ህውሃት ካሉት ጋር መቧደን የዘለቄታው ጉዳቱን ለአሜሪካና ለአገራችንም የሚያስከትለውን ጉዳት ማመላከት ነው።
ቃሌን ጠብቄ የሁለቱ ልጆች እናት የወላድ መሃንዋን ልጠይቃት ተመለስኩ።ጭጋጋማ ቀዝቃዛ ምሽት ነበር።ከጓሮዋ ካለችው ትንሽ ያትክልት ስፍራ እየቆፋፈረች ነበረ።”በልጆቼ ሃሳብ የተጨናነቀውን አእምሮየን ቢያስታግስልኝ ብዬ እማስናለሁ።” አለች እጅዋን እየጠራረገች። ክበሩ መግብያ ስደርስ ጠበቅ አድርጋ አቀፈችኝ። የናት ፍቅር ሙቀቱ እየተሰማኝ ወደቤቱ ውስጥ ተከተልኳት።
“እግዜር ይባርክህ ልትጠይቀኝ በመምጣትህ።” አለች ወደ ማድቤቱ እያመራች። “ሻይ አፈላልሃለሁ” አለች።
“አመሰግናለሁ” ብዬ መለስኩ።
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በእጅ በተሰራ ቅርጫት ብስኩት፤ ሻይ በፊንጃል ይዛልኝ መጣች።ስለ ብዙ ነገሮች አወራን።”ዛሬማ ብዙ እናቶች ለሞቱ ልጆቻችው ጥቁር ይለብሳሉ” አለችኝ አንዳንዶቹን በስም እየጠራች።
“ዛሬ እኮ ጨለማ ዘመን ነው።ጓደኞቸ፤መንደርተኞቸ፤የከተማውም ሰው አንድ ሰው ቢያንስ ተገሎባቸዋል” አለችኝ።
ደግሜ ልጠይቃት የመጣሁት ስለሟች ልጆችዋ ለመጠየቅ የሷንም መጽናናት ላውቅ ብዬ ነው።እንቅልፍ አጥታ እንደሰነበተች እንዲያው ድክም ብሏታል።ትንሽ ተኝታ ታድር እንደሁ ጠየቅኋት። “ሽለብ ሲያገኝ ልጆቼ ከፊቴ ድቅን ይላሉ።ከትምርት ቤት ሲመጡ፤ያዘዝኳቸውን ሲከውኑ፤የትምህርት ቤት የቤት ስራቸውን ሲሰሩ።እንቅልፍ የለኝም።ደህና እንቅልፍ የተኛሁበት ምሽት ይናፍቀኛል።” ጥልቁ ሃዘንዋ፤አንዱ በሌላው ላይ የተደራረበው መከራዋ ህወሃት የፈጸመውን በደሎች ያመለክታሉ።ፈተናዋ አድክሟታል።
“የት ነው ልጆችሽ የተቀበሩት ?” አልኳት
“ተዚህ ግድም።ሩቅ አይደለም። በግር ያስኬዳል።በሰንበት ሁሌ ልጆቼን ላጫውት እሄዳለሁ” አለች።
“ዛሬ ትወስጅኛለሽ?” አልኳት
“አዎ! እወስድሃለሁ” እያለች ጥቁር ጥለት ነጠላዋን ተከናንባ “ተከትለኝ” አለችኝ። “በዚህ ጋ” ስትል ተከትያት ለአስራ አምስት ደቂቃ በደረቀው ሳራማ ሜዳ ላይ የግር መንገዱን ተከትለን ተጓዝን።ከሩቁ የሚግጡ ከብቶች ይታዩኛል።ጥቂት ሄደን ቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ደረስን።ጥቂት ጸሎት አድራጊዎች ተውጭው ይታያሉ ሌሎችም እየመጡ ነበር።ተገረገራው ስትደርስ አማተበችና እየሰገደች ጸለየች። እኔም እንደስዋ አደረግሁ። ጥቂት ራመድ እንዳለች ከበተ- ክርስትያኑ ደቡባዊ ጠርዝ ልጆችዋ ካረፉበት ደረስን። ጠጋ ስንል ንግግርና ልቅሶ ተደባልቀው እንሰማለን።
“እዚህ ነው ትኝት ያሉት።ልክ ከቤታቸው አብረው በልጅነታቸው ተቃቅፈው ይተኙ እንደነበረው፤አበቦቼ፤ልጆቼ” እያለች ፊትዋ ላይ ያለውን እንባ ጠረገችው።የራሴን እንባ እየታገልኩ እሷን ላጽናናት ሞከርኩ።ትንሹ ሲገደል ገና አስራ ስድስት ዓመት እንደነበረና ሰላማዊ ሰልፍ ሲካፈል እንደተገደለ ነገረችኝ። “ልክ እንደኔው ልጆቻችው በአጋዚ ጥይት የረገፉባቸው እናቶች እጅግ ብዙ ናቸው።” አለች ጉዞአችንን ወደ መጣንበተ ማምራት ስንጀምር።
“እንደምሰማው አጋዚዎች የሰለጠኑት በአሜሪካኖች ነው።ይህ እውነት ነው?” ብላ ጠየቀችኝ።አጥብቃ ነው የጠየቀችው ድምጽዋ ንንዴትም ብሶትም የተቀላቀለበት ይመስላል።
“አዎን ተመሳሳይ ዜና ሰምቻለሁ” ብዬ መለስኩላት።
“ለምን ልጆቻችንን የሚገድል ታጣቂ ቡድን ያሰለጥናሉ? ሳስብ የነበረው አሜሪካኖች ደግ ሰዎች ናቸው ብዬ ነበር። አዛኞችም ናቸው ብዬ ነው።”
“የአሜሪካ ህዝብ አይደለም።ይህ የፖለቲከኞች ውሳኔ ነው።” ብዬ ተገቢውን መለስኩላት። ትንሽ ቢያጥናናት ብዬ።
“ምን አልባት እንዳንተ የተማሩ ሰዎች የኛን በደል ለአሜሪካ ፖለቲከኞች ማድረስ አለባቸው። አጋዚ የሚባለው ልጆቻችንን መግደል እንዲያቆም።” አለች።
ለአሜሪካ ፖለቲከኞች ፤ለአሜሪካም ህዝብ ለዓለምም ሁሉ መልክትዋን ለማድረስ ቃል ገባሁላት።
ለመሄድ ስነሳ እንደምትማጠነኝ ሁና ወዳይኔ ብረቱ እያየች፤
“እባክህ በደላችንን ዓለም እንዲያውቀው አድርግ።አጋዚን አሰልጥነው ማስታጠቃቸው፤ በጅምላ ገዳዮችን ማሰልጠናቸው መሆኑን ይወቁት።አንድ ብቻ ሳይሆን ሁለት ልጆችዋን የተቀማችዋን እናት ታሪክን ንገራቸው።የወላድ መካንን እናት ምን ይሏታል? መካን የሆንኩት ሁለቱን ባንዴ አጋዚ ሲቀማኝ ነው።” አለች።
እኔ ለዚህ ሁሉ ጥያቄዎችዋ መልስ የለኝም።መልስም የምትጠብቅ አይመስለኝም።እንደው ሀዘንዋ ይውጣላት ብላ እንጂ።ምናልባት ሁለቱንም።እኒህ እለት ተእለት የማብሰለስላቸው ጥያቄዋች ናቸው።እስተማውቀው ድረስ ጥያቄዎቹ በሺ የሚቆጠሩ እናቶች ባገሩ በሞላ የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ናቸው።
ምስኪንዋን እናት ተሰናብተን መንደሩን ለቀን ስንጓዝ አይኖቼ አካባቢውን አማተሩ።የሚጫወቱ ልጆች አይታዩም።በማሳው ላይም ገበሬዎች የሉም ።መንገደኛም አይታይም።ህይወት እርጭ ብሎ፤ታግቷል።ተሩቅ የተኩስ ድምጥ ይሰማኛል።ማን ይሆን ባለሳምንት? ሌላ ወጣት? ወንድ ?ሌላ ወጣት ሴት?ሽማግሌ ማን ይሆን? ማነው ባለተራ ? ማን ይሆን የአጋዚ እራት ብዬ ተከዝኩ።
ባልጋዬ ጋደም ብዬ ያን ማታ የዚህን ጭካኔ መነሻ ልደርስበት አሰብኩ።ዘመናዊ ስልጣኔና ተቋም አቀድ የሆነ አረመኔያዊ ጥፋት በንጹሀንና ባልታጠቁ ህዝቦች ላይ! ሃሳቤ ከቦታ ቦታ ተንክራተተ፤ከአንድዋ እናት እምባ ወደ ሌላዋ። ከአንዱ አባት ምሬት ወደ ሌላው።ሸለብ ያረገኝ ብዬ ባስብ አእምሮዬ እምቢ አለ።“ሽለብ ሲያደርገኝ ልጆቼ ድቅን ይላሉ” ብላ ያለችው ደግሞ ደጋግሞ ባሳቤ ይመጣል።ልጠይቃት መሄዴ ሃዘንዋን አባብሶት ይሆን? ብዙ ተገላብጨ እንቅልፍ እምቢ ሲለኝ ተስፋ ቆረጥሁ።አጣጥፌ ከደብተሬ ያኖርኩትን የተጣጠፈ ወረቀት ሳብ አደረግሁት።የጥንቱ ሮማዊ ገጣሚ ጋየስ ቫሌሪየስ ከታለስ (84᎔54 ከክርስቶስ ልደት በፊት)ግጥም ነበር። ለሟች ወንድሙ የገጠመው፤
“በባእድ ባህሮች ቀዘፋ፤ ባልታወቁ ወደቦች ለቀናት በባህር ስጓዝልህ
ከዚህ የመጣሁት ለሽኝት ነው የናቴ ልጅ ላንተው ስንብት፤
ለሞትከው የቋሚን የመጨረሻ ስጦታ ይዥልህ
ቃሌ ከንቱ ነው ትቢያ ለሆነው ሰው።
አይ ወንድምየ ይኸው አንተን ነጠቁኝ
አንተን አብሮ አደግ ወንድሚን ቀሙኝ!
በጨካኝ እጃቸው ቀጠፉህ እኔንም በሀዘን ወጉኝ።
ይሄው ተዝካርህ ድሮም ለሄደ ድንግጉ
ትዝካርህን እነሆ በማእርጉ
የወንድምህ እምባ ያራሰውን
ውሰድ አድናቆቴን በሞቴ የእምባየን ንዳድ ስንብቴን”
ግጥሙን በህወሃቱ አጋዚ ለተገደሉት ሁሉ ደጋግሜ አነበብኩት።ደጋግሜ ባነበብሁት ቁጥር አገሩን ማሰስ አማረኝ። እያንዳንድዋን አጋዚ ልጇን የቀማትን እናት ላናግር።ላዳምጣቸው፤ ሀዘናቸውን እካፈል ብዬ።ስሜቴና ፍላጎቴ ቢገፋፉኝም በተግባር ማዋሉ አቀበት መሆኑ አልጠፋኝም።የአጋዚ ግድያ ከመብዛቱ የተነሳ ቁጥሩ አያሌ ነውና በጥቂት ዓመታት ላዳርስ የምችለው ጥቂቶችን ብቻ ነው።ጥቂቶችን ብቻ።ጠዋት ሲነሱ ባዶ ወንበሮችን የሚያዩትን እናቶች። ከትምሀርት ቤት የቀሩባቸውን፤ለሰርጋቸው ያልበቁላቸውን፤አያቶች ያደርጉናል ብለው ይጓጉላቸው የነበሩትን።
ቆይቶ አእምሮዬ ተረጋግቶ አሰበ።አገሩን አስሼ የእናቶችን የሃዘን ህመም ሁሉ ማዳመጥ ወሰንኩ።የግል የምስጢር ፍላጎቴም ይሆናል የአባቴን አገር፤ውቡን አገር ያያት የቅማያቴን አገር ላይ።ቀኑ፤ቦታው፡ሰአቱ፡ምክኛቱ ወይ ሰውዬው የተለየ ይሆናል ወይ ጠመንጃውን የተኮሰው ሰውዬ አንድ አይሆን ይሆናል። የናቶች መሪር ሀዘን ግን ከሰሜን ተራሮች ይሁን ከምዕራብ ጥቅጥቅ ጫካ ፤ከሜዳማው አገር ይሁን ከደቡቡ ሳራማ መሬት፤ክምስራቅ፤ከከተማ ይሁን ባላገር የትም ቢሆን የእምዬ ሀዘን ያው ነው።እርር፤ድብን ነው።የዘጠኝ ወር ቤት ንዳድ።
ላሁኑ ስለማውቃት እናት መናገር መርጫለሁ።ስለተዋወቅኋት ደስታና ክብር ስለሚሰማኝ እናት።በስም ልጠራት የማልችለው እናት።የሁለት ልጆችዋ ምስል በአእምሮዬ ታትሞ የቀረው።ጀምበር በወጣች ቁጥር እኔን ወጥረው ይይዙኛል።ሁሌም ለፍትህ ቁም።ለስልጣን ለሹመት ሳይሆን እያሉ። ይህ ደግሞ ላደርግ ከምችለው ትንሹ ነገር ነው።
ደራሲውን ለማግኘት
alem6711@gmail.com

Thursday, February 18, 2016

ቻርል ዳርዊንና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ


Darwin-and-land-to-the-tiller
ቻርል ዳርዊንና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ
ቢላል አበጋዝ
ዋሽግቶን ዲ ሲ፣ሐሙስ ፣ ፌብሩወሪ 18 ቀን 2016
የታላቁ ሳይቲስት የቻርል ዳርዊን 207ተኛው ልደቱ በዚህ ወር ተከብሯል። እሱ ካልው አንዱ ነገር
“ከዝርያዎች መካከል ጠንካራው አይደለም ኗሪነቱ ቀጣይነት ያለው(እማይመክነው:እማይጠፋው)። እጅግ ብልሁም አይደለም። ለለውጥ ዝግጁ የሆነው እንጂ”
ቻርልስ ዳርዊን 1809
መግቢያ
ቻርል ዳርዊን የሳይንስ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካም ሰውም የነበረ ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ መረጃ ተሰብስቦ ቀርቦለት ምን ታስባለህ ቢባል በኦሮሞ ክፍለ አገር እየሆነ ያለው ዓመጽ የኢትዮጵያ ህዝቦችሁሉ የሚያደርጉት አገር አቀፍ ዴሞክራሲያዊ ትግል አካል ነው። ይህ እንዴት ይህ ተሰወራችሁ? ብሎን ይታዘበን ነበር እላለሁ። የሰውን ልጅ አስተሳሰብ፤ሳይንስን እንዳለ ቀየረው የሚባለውን መላምቱን ለመቅረጽ ዳርዊን የፈጀበት ጊዜ እኛ ወያኔን ስናስታምም የፈጀነውን ዘመን ያንሳል።
ለውጥ ሲመጣ እያየነው ለውጡን ወያኔ ሲያውገረግረው እኛ ግን አስተሳሰባችንንና መንገዳችንን መቀየር ካቃተን ለውጡን ወያኔ እንዲጠቀምበት አደረግን ማለት ነው።በዚህ እራሳችንንም አገራችን ኢትዮጵያንም እንበድላለን ማለት ነው። አዲስ ሁኔታ ሲከሰት ወዲያው ሁኔታውን አገናዝበን አስተሳሰባችንንም ቀይረን ዛሬ የሚጠይቀውን አቅጣጫ መቀየርን፤ማረምን፤ዝግጅትን ማድረግ እስካልቻልን ወያኔን መርታት ዳገት መሆኑ ግልጥ ነው።ጥንካሬም ብልሃትም እያለን እንዴት ወያኔ ሰነበተን? ካልጠየቅን ወያኔ አፍዝ አደንግዝ እንዳስደገመብን ያለ ነው። በኦሮሞ ክፍለ አገር እየሆነ ያለው ዓመጽ ልድገመው የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ የሚያደርጉት አገር አቀፍ ዴሞክራሲያዊ ትግል አካል ነው።
ትንታኔ
በዚህ ጽሁፍ የቻርል ዳርዊንን የአራዊትና እጽዋትን ዝርያ አመጣጥና ዝምድና ገላጭ መላምቱን የማቅረብ ዓላማ የለኝም።ከላይ የጠቀስኩት የዳርዊን አባባል የሚለግሰንን ብልሃት ለዲሞክራሲያዊ ትግላችንም ምን ይዘይድበታል ለማለት ብቻ ነው።
በወጣትነት ዘመኑ ቻርል ዳርዊን ለአምስት ዓመታት በመርከብ ዓለምን ዞሮ የጽዋትና የእንስሳትን መረጃና ናሙናም ሰብስቦ ለሃያ ዓመታት ከተመራመረ በኋላ ዝርያዎች በቀጣይነት ዘራቸው የማይጠፋው [survival] ተፈጥሮ ራሱ በደነገገው መሰረት የገጠማቸውን ነባራዊ ለውጥ ለመቀበል የተመቻቹትን ብቻ የሚመርጥ ስርዓት ስላለ መሆኑን በገናናው መላምቱ ሲያስረዳ፤ ለውጥ ለመቀበል ያቃታቸው፤መራባትም ያልሆነላቸው ዘራቸው መክሰሙንም በመላመቱ አካቶታል።
ህወሃት መሩ መንግስት ልክ እንደወታደራዊ ደርግ አዋጅ፤ህገ መንግስት፤ብሄር ገለመሌ እያለ ቀስ ብሎ ስልጣን ላይ ጉብ ሲል፤ፊቱ ለሚደቀኑ የነበሩ ተለዋጭ ሁኔታዎች መልስ እያዘጃጀ እራሱንም ለለውጥ እያመቻቸ ነበር። ዛሬም ይህንኑ ያደርጋል። እስታሁንም ለውጥ ሲመጣ ቢደናገጥም ተንገዳግዶ ይቆማል።ለለውጥ ዝግጁ መሆንና፤ፊታችን የሚከሰተውን ለውጥ ማየት እየተሳነን ህወሃትን አቸናፊ እናደርገዋለን። ይህንን ቀጥዬ ላስረዳ።
ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ወያኔ ገና ከተማ ሳይገባ ማን ብርቱ ተቃውሞ እንደሚያደርግበት በመረዳት የኅይልም የፕሮፓጋንዳውንም በትር አማራው ብሄር ላይ ያሳርፍ ነበር።ህወሃት ጋር የተደለሉ ኦሮሞዎች ሎሎችም እየተባበሩ።ከአማራውም ከሌሎች ብሄሮችም ተጨምረው አድር ባዮችን በጥቅም አሰልፎ ሲያበቃ የራሱን በፖለቲካ ስልጣን መደርጀትን የዝምድና ሀረግ በማድረግ ሰንብቶበታል። ይህ ዛሬም ያለ ዝምድና ነው።ይህን ዝምድና ስር ነቀል ለውጥ ብቻ የሚሽረው ነውና ህወሃት እስታለ ደግሞ ይቀጥላል።ህወሃትን ዲሞክራሲያዊው ትግል በድል ሲሽረው ወያኔ ጋር አብሮ ታሪክና ትዝብት ይሆናል። ባጭሩ ወያኔ ዝግጅት አድርጎ ሲገባ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሀይሎች አልተዘጋጁም ነበር።ይሄው ሃያ አምስት ዓመታ እየተቆጠሩ ነው።
እንዳአሁኑ የወጣት ተማሪዎች እንቅስቃሴ የኦሮሞ ብሄረሰብ በብዛት በሚኖርባቸው የኢትዮጵያ ክፍላተ አገር እንደሚካሄደው በሌሎቹም ቦታዎች እየተነሱ ተራ በተራ መመታታቸውን አይተናል።ህወሃት አገር አቀፍ እንዳይባልበት እጅግ ሲጥር የመጣውን ለው የሁላችን የጋራ ነው ለማለት ተስኖን በመደናገር ራሱ ህወሃት ያለው ደግመን [ትቀብለን] አመጹን “የኦሮሞ”፤ “የአማራ” እናደርገዋለን።ባጭሩ ቻርልስ ዳርዊን እንደሚለው ሀይል ቢኖረንም ለውጡን ለመጠቀም ራሱን ያመቻቸው ህወሃት ሆኖ እናገኘዋለን።
በኦሮሞ ክፍለ አገር ዛሬ ተቀጣጥሎ እየነደደ ያለው ዓመጽ እንዴት ተከሰተ?የህዝባዊ ብሶቱ መነሻ ምንድን ነው?በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍላተ አገራት ከተነሱት ዓመጾች በምን ይመሳሰላል?እንዴት ሊራመድ ይችላል?ወያኔን ለማንበርከክ ምን ቀጥሎ ምን ይደረግ እንደማለት ህወሃት ለመጣው ለውጥ የሰጠውን ስያሜ ውጠን “የኦሮሞ ክልል” የዚያ ክልል የሚል ታርጋ እንለጥፍበታለን።ለህወሃትም የሌለውን ብላተኛነት አክለንለት ከናካቴው አመጹን ወያኔ በውስጥ እጅ ሆን ብሎ በራሱ ሰዎች እንዳስነሳው የምናስብም አለን። የተንኮል ቅንብር (Conspiracy Theory) ድረስ የምንሄድና ወጣቱ በደሙ የከፈለበትን መና ለማድረግና ህወሃትም ለመርታት አስቸጋራ መስሎ እንዲታይ ያለማስተዋል እንናገራለን።ህወሃት ጠንካራ አይደለም።ብልሃትም የለውም።የለት ተለትዋን ለማድረግ ግን ጮሌ ነው። እስታሁን በራሱ ላይ ህዝባዊ አመጽ ሆን ብሎ የሚዶልት አምባገነን ታይቶ የሚታወቅ አይመስለኝም።ህወሃት ግን የተፈጠረውን ሁኔታ ሊጠቀምበት የማያደርገው የለም ማለት ይቻላል።በግልጹ ለመናገር አማራው ኦሮሞውን፤ኦሮሞው አማራውን እንዲጠላውና እንዲጠራጠረው በመሆኑ የህወሃት ፍላጎት እደተመኘው የምንሆንለት እራሳችኑ ነን።ተመቸነው ልበል ወጣቶች እንደሚሉት ?ለውጥን ፈርተን መለወጥ አቅቶን እንዴት ወያኔን ለማሰናበት እንችላለን?
ነገ የአማራው ህዝብ በብዛት በሚኖርበት ክፍለ አገር አመጽ ቢቀጣጠል።የጋምቤላውና የአፋሩ እንደቀድሞው ቦግ ሲል የህወሃት መሩን መንግስት መግለጫ ተቀብለን የምናስተጋባ ከሆነ ብልሃትም ጉልበትም የኛ ቢሆንም ወያኔ የለመደውን ግዜያዊ ድል አግኝቶ ቀጠለ ማለት ነውና፤ ሲሆን ለውጥ ሳይመጣ ቀድመን እናስላ ካልሆነ ለውጡ፤አመጽ ሲከሰት ሌላ ስም ሳይሆን አገር አቀፍ ዴሞክራሲያዊ ትግል መሆኑን ኢትዮጵያ አገሬ የምንል ይህን ስያሜ እንጂ የወያኔን አናስተጋባ።ሌላ ምሳሌ ”ኢትዮጵያ ትፈራርሳለች” ሲል የወያኔ ተረት ተረት “ወያኔ ስንት ቦታ ተሰንጥቆ ይፈርሳል ?” ብለን ይህን ሂደት ለማፋጠን ምን ይደረግ እንበል።ዛሬ ኢትዮጵያ ለለውጥ ዝግጁ ናት የምሁራንዋ ዝግመት እንጂ !” ይህን እናስብበት::
የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚያደርጉት አገር አቀፍ ዴሞክራሲያዊ ትግል ያቸንፋል!
የፖለቲካ መሪዎች አሁኑኑ ይፈቱ!
የሃይማኖት መሪዎች አሁኑኑ ይፈቱ!
የታሰሩ ጋዜጠኞች አሁኑኑ ይፈቱ!
ለወጣቶች ግድያ ህወሃት እንጂ ማንም ተጠያቂ አይደለም !
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

Thursday, February 4, 2016

የሀገር አድን ጥሪ ለወጣቱ!(ከአርበኞች ግንቦት7 ወጣቶች መምርያ )

ማክሰኞ ፣2 ፌብሩወሪ 2016
12042873_868355303254893_5731700769108826326_nወጣቶች በሃገራችን ላይ የተጫነብን የወያኔ የመርገምት አገዛዝ ያጎሳቆለን፤ በኑሮ የተበደልንና በሰላም ለመኖር ያልታደልን ፍጡሮች ብንሆንም ህዝባችን ነጻነቱን ሲቀማ፣ መብቱ ሲደፈር፣ ክብሩ ሲዋረድ ከዳር ቁመን የምንመለከትበት አንዳች ምክንያት ሊኖረን አይገባም። ወቅቱ ለነፃነታችንና ለመብታችን ባላንጣ የሆነውን አምባገነን የወያኔን ስርዓት ፊት ለፊት ተጋፍጠን፣ በትግላችን ደቁስን ማንነታችንን የምናስመስክርበት ወቅት እንጂ በፍርሃትና በዝምታ ተውጠን ወደኋላ የምንልበት ስዓት አይደለም። ደግሞም እኛ ወጣቶች ለመብት እና ነፃነታችን ተፈጥሮ የለገሰችንን እምቅ ኃይልና ጉልበት ተጠቅመን በቁርጠኝነት ተነስተን ካልታገልን የሥርዓቱን አምባገነናዊ የጭቆና አገዛዝ በፍርሃትና በዝምታ እንደተቀበልን ተደርጎ መወስዱ የማይቀር ነው።
ከምንግዜውም በላይ እኛ ወጣቶችን ዛሬ ሁለት አበይት ጉዳዮች በጉልህ ያሳስቡናል፤ ሊያሳስቡንም ይገባል። እነዚህም ሃገራችን ያለችበት አሳሳቢ ሁኔታና የኛ የተተኪው ትውልድ የወደፊት ተስፋ ምን ሊሆን ይችላል? የሚሉት ናችው። በቀደመው ጊዜ በሃገራችን የተፈራረቁት አምባገነን ገዥዎች ለወጣቱ ተስፋና የተሻለ ነገር ከመስጠት ይልቅ በጠላትነት ፈርጀው በሽብር እየገደሉና ጥቃት እየፈጸሙበት ሲያሳድዱት ኖረዋል። የወጣቱ ሰቆቃ አሁን በወያኔ ዘመን ደግሞ እጅግ በጣም በከፋ ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሏል።
የወያኔ መሪዎች ለኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ማዕከላዊን፡ ቃሊቲን፤ ሽዋሮቢትን፣ ዝዋይን እና የመሳስሉ የሰቆቃ እስር ቤቶችን ሲያሰፉ እንጂ የሥልጠናና የምርምር ተቋም ሲያድሱና ሲገነቡ ለማየት አልታደልንም። የሚገነቡ የትምህርት ተቋማትም ለሥርዓቱ የእድሜ ማራዘሚያ እንጂ የእውቀት ማስጨበጫ ተቋም እንዳልሆኑ ተግባራቸውንና ውጤታቸውን መመልከት ይቻላል። በአደባባይ ያለፍትህ የሚገደለው ወጣት ባንክ ሲዘርፍ ተገኘ፣ ወንጀል ሲሰራ ተያዘ የሚሉ የሀሰት ምክንያቶች እየተለጠፉበት ያለኃጢአቱ የሀሰት ስም በመቀባት ዳግም ይገሉታል።
የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ከሚፈራበት የትምህርት ተቋም ድረስ በመግባት የአማራ ህንጻ፣ የኦሮሞ ህንጻ፣ የትግሬ ህንጻ…ወዘተ እያሉ የትምህርት ሥርዓቱን ከጠባቡ የፓለቲካ ግባቸው ጋር በማያያዝ በነገ ተስፋችን ላይ ዘምተው የልዩነት ግድግዳ ባሳፋሪ መልክ እየገነቡ ቀጥለዋል። አላማው ደግሞ በጎስኝነት በሽታ ተውጠን ከእህቶቻችንና ከወንድሞቻችን ጋር እየተባላንና እየተገዳደልን የምንኖርበት ሲኦል ለመፍጠር መሆኑ አያጠያይቅም። በዚህም ሳቢያ ብሔራዊ ሰሜታችን እየደበዘዘ ሄዷል። ብሔራዊ ሰሜት ከሌለን ደግሞ አገር አለን ማለት ጨርሶ የሚታስብ እንደማይሆን ግልጽ ነው።
በነገራችን ላይ ዛሬም ድረስ ወያኔዎች ለእድገትና ለልማት መዘጋጀታችውን እየደሰኮሩ ህዝብን በማታለል የስልጣን ዘመናቸውን ለማርዘም መውተርተራቸውን አላቆሙም። በየጊዜው ኢትዮጵያ ተመነደገች፤ ልማቱ ተፋጥኗል እያሉ በሃሰት ህዝብን ለማወናበድ ይሞክራሉ።እውነታው ግን በእጅጉ ተቃራኒ መሆኑን የህዝቡን የኑሮ ሁኔታን በመመልከት መረዳት ይቻላል። ዛሬ የፋሽስቱ ወያኔ አገዛዝ በፈጠረው የተወሳሰበ ችግር በሀገሪቱ የወጣት ሥራ ፈትና ተጧሪ ሞልቶና ተትረፍርፎ በሚታይበት፤ ሥራ የማግኘት እድል በፓለቲካ ታማኝነት ብቻ በሆነባት ሃገርና ወያኔ የፓለቲካ ሥልጣኑንና ወታደራዊ ኃይሉን ተጠቅሞ የሀገሪቷን ሀብት እያጋበስ በሚዘርፍበት ሁኔታ ላይ ቆመን ልማትና እድገት ማለት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ተራ ማጭበርበሪያና ዲስኩር ካልሆኑ በስተቀር ፈጽሞ ትርጉም የሚሰጥ አይደለም።
ለነገሩ ወያኔ ከመጀመሪያው ጀምሮ ያዘጋጀልን ቃሊቲ፤ ማዕከላዊ፤ ሁርሶን፤ ሽዋሮቢትንና የመሳሰሉትን የማሰቃያ ማጎሪያዎች መሆኑን የተረዳን ስለሆነ በዚህ የምንደናገር አይደለም። ለዚህም ነው በአሁኑ ወቅት እኛ ወጣቶች ተሰባስበንና ተደራጅተን ከመታገል ውጪ ሌላ ምርጫ የለንም ብለን በድፍረት የምንናገረው።
አምባገነንነት ስርዓት ካልተገታ የአገር ሰላም ሆነ የህዝብ ህልውና እና አንድነት ዋስትና አያገኝም። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሥልጣን የጨበጡት ወንበዴ ግለሰቦች የኢትዮጵያ ህዝብን ሀብት እየተቀራመቱ ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉ፣ ህዝቡን የሚገሉ፤ የሚረግጡና የሚበድሉ በተለይ ደግሞ ለባእድ ጥቅም የተገዙ ናቸው። እነዚህ ግለስቦች ብሔራዊ ስሜታችውን አሽቀንጥረው የጣሉ፤ የራሳችውን ባህል፤ ወግ፤ ታሪክና ሕዝብ አምርረው የሚጠሉ ከራሳቸውና ሥልጣን ላይ ካስቀመጧቸው መንግሥታት ጥቅም ውጪ ሌላ ምንም የማይታያቸው ናችው።
ታዲያ የሃገራችን ህልውና ከመቼውም በላይ ለከፋ አደጋ ተጋልጦ ባለበት በአሁኑ ወቅት በተለይ የእኛ የወጣቶች ግዴታና ድርሻ ምን መሆን አለበት ብለን ራሳችንን መጠየቅና ብሎም መልስ ለመስጠት መዘጋጀት ሀገራዊ ግዴታንና ኃላፊነትን ለመወጣት የመጀመሪያው እርምጃ መሆን ይኖርበታል።
ጭቆናንና በደልን በመታገል ረገድ ደግሞ የቀደምት የታላላቅ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አኩሪ ገድል ለዛሬው ትግላችን ትልቅ የትምህርት ማእከል ሆኖ ያገለግለናል። ሀገራችን ከኋላቀር ሥርዓትና ከብልሹ አገዛዝ ተላቅቃ፤ ድህነትን አሸንቀጥራ ጥላ በልማት ጎዳና እንድትራመድ፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን እንዲሆን፤ ማህበራዊ ፍትህ እንዲስፍን ባጠቃላይም ተጨባጭና ዘላቂ ለውጥ በሃገራችን እንዲመጣ ጽኑ እምነት ሰንቀው ለሕዝባዊ ትግሉ ሕይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ሲታገሉ የነበሩ ጀግና ወጣቶች እንዳሉ ታሪክ ያስገነዝበናል።
ዛሬም ጭምር ግንባራችውን ሳያጥፉ መስዋእትነትን በመክፈል እያስመስከሩ ያሉ መኖራቸውን ስንመለከት ጀግና የሚያፈራው ጀግናን ነውና እኛም ወጣቶች አንገታችንን ቀና አድርገን ዛሬም እንደ ትናንቱ ለሃገራችንና ለህዝባችን ነፃነት መታገል ብሔራዊ ግዳጃችን ብቻም ሳይሆን ታላቅ ክብርም ጭምር መሆኑን ተገንዝበን ለሞት ሽረቱ ትግል በቁርጠኝነት መነሳት ይኖርብናል። ከፊታችን ለሚጠብቀንና ሃገራችን እያሰማች ላለው የሀገር አድን ጥሪ መልስ ለመስጠት እኛ የኢትዮጵያ ወጣቶች ከሃገር ቤት እስከ ውጪው አለም ድረስ የተቀናጀና የተቀነባበረ ንቅናቄ በመፍጠር ምላሽ ልንሰጥ ይገባል።
በኅብረትና በጽናት ከታገልን ደግሞ የወያኔን የሰቆቃ አገዛዝ አሰወግደን የሕዝባችንን ሮሮ የማናስቆምበት እና ተጨባጭ ለውጥ በሀገራችን ለማምጣት የማያስችለን አንዳች ምድራዊ ሃይል እንደማይኖር በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል። ዛሬ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንዳለ ብልጭ ብልጭ እንደሚል ኮኮብ ብንመስልም በርግጠኝነት ነገ ከፀሐይ ደምቀን ከአሽዋ በርከትን የምንታይበት ጊዜ ይመጣል፤ እየመጣም ነው።
በመጨረሻም የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ወጣቱን ትውልድ መብቱንና የዜግነት ክብሩን ለመጎናጸፍ እንዲችል ብሎም የሀገር እና የወገን ነፃነትን ለማምጣት ወያኔን ታግሎ ማሸነፍና ከስልጣኑ ማውረድ ግድ ነው ብሎ በጽኑ ያምናል። በአገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም ተበታትኖ የሚገኘውን ወጣት በአገሩ ተከብሮ እንዲኖር የተለየና የተቀደሰ አማራጭ አለው። ይኸውም እየተደራጁ መታገል፣ እየታገሉ መደራጀት ነው ብሎ ንቅናቄያችን ያምናል።
የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ የነደፈውን ጊዜ የማይሽረውን ሁለገብ የመታገያ ስልትና አላማን ከግብ ለማድረስ ትግልን በጽናት መቀጠል የሚለው መርሁ ሲሆን ተደራጅቶ በጽናት መታገልን በተግባር ለማዋል ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወጣት ንቅናቄውን እንዲቀላቀል ጥሪ ያደርጋል። ተደራጅቶ ሊያጠፋን የተነሳን ጠላት በተደራጀ ሃይል ማንበርከክና ከስር መሰረቱ ማስወገድ ይቻላልና። ስለዚህ የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ በአረመኔው የወያኔ አገዛዝ ላይ የሚካሄደውን ትግል አጠናክሮ በመቀጠል በአገር ውስጥ ወጣቱን በህቡዕ ከማደራጀት ጀምሮ በውጭው ዓለም በየአህጉሩ በተዋቀሩ የንቅናቄው መዋቅሮች አማካኝነት ወጣቱን አደራጅቶ በማንቀሳቀስ አስፈሪ የሆነ የነፃነት ማዕበል ፈጥሯል። አሁንም የንቅናቄውን ዓላማ የሚደግፉና በነፃነት ትግሉ ለመሳተፍ የቆረጡ ወጣቶች እንዲቀላቀሉ የአርበኞች ግንቦት7 ወጣቶች መምርያ በድጋሚ ሃገራዊ ጥሪ ያቀርባል!
ፈሪዎችንና ባንዳዎችን ወደ ጎን በመተው እውነተኛ ታጋዮችን ይዘን ትግላችንን እንቀጥላለን!!!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

Tuesday, December 29, 2015

በድርቁ ምክንያት 400ሺ ህጻናት አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መሆናቸው፣ አንድ ሚሊዮን ትምህርት ማቋረጣቸው ተገለጸ

ኢሳት (ታህሳስ 18 ፣ 2008)
በኢትዮጵያ ስድስት ክልሎች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ ከ 400ሺ የሚበልጡ ህጻናትን ለአሳሳቢ የጤናና የአካል ችግር አጋልጦ እንደሚገኝና ጉዳት የሚደርስባቸው ህጻናት ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) አስታወቀ።
ለተረጂዎች የሚያስፈልገው ድጋፍ በበቂ ሁኔታ በመቅረብ ላይ አለመሆኑ ችግሩን እያባባሰው እንደሆነም ድርጅቱ ገልጿል። ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለተጋለጡ ከ10 ሚሊዮን ሰዎች መካከል ወደ ግማሽ የሚጠጉት ህጻናት መሆናቸውን ያስታወቀው ዩኒሴፍ ከእነዚሁ መካከል ከ 400ሺ የሚበልጡት ለከፋ የጤናና የአካል ጉዳይት ተዳርገው እንደሚገኙ አመልክቷል።
የህጻናቱ ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ሲገልፅ የቆየው ይኸው ተቋም፥ አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች የህጻናቱን ህይወት ለመታደግ ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቋል። በቀጣዩ ጥቂት ወራቶች ውስጥ የተረጂዎች ቁጥር ወደ15 ሚሊዮን ያሻቅባል ተብሎ በመጠበቁም ለጉዳት የሚጋለጡ ህጻናት ቁጥርም አብሮ እንደሚጨምር ዩኒሴፍ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በድርቁ ምክንያት ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ህጻናት ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ መድረሱን ያወሳው ድርጅቱ በሀገሪቱ ያለዉ የድርቅ አደጋ ከተገመተዉ በላይ መሆኑንም አመልክቷል።
የህጻናት አድን ድርጅቶች ጥምረት በበኩሉም ልዩ ድጋፍና ክትትልን የሚፈልጉ ህጻናት በቂ ድጋፍ እያገኙ አለመሆኑ ስጋት መፍጠሩን ገልጿል።
ይኸዉ ከ180 በሚሆኑ ወረዳዎች ዉስጥ ተከስቶ ያለዉ የድርቅ አደጋ እስከቀጣዩ አመት መጋቢት ወር ድርስ ቀጣይ በመሆኑም አስከፊ የጤናና የአካል ጉዳት የሚደርስባቸዉ ህጻናት ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል ጥምረቱ አሳስቧል።
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ የአለም አቀፉ ማህብረሰብ የገባዉን ቃል ባለመጠበቁ ሳቢያ ቸግሩ እየተባባሰና የተረጂዎች ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱን በደጋሚ አስታዉቋል።

Tuesday, December 15, 2015

ሰማያዊ እና ኦፌኮ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

ሰማያዊ ፓርቲና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ነገሰ ተፋረደኝ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ሁለቱ ፓርቲዎች ዛሬ ታህሳስ 5/2008 ዓ.ም ባደረጉት ስብሰባ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግለጫ በመስጠት፣ መንግስት የሚፈፅመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በመከታተል ለማጋለጥ እንዲሁም ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባዎችን በጋራ ለማካሄድ እንደተስማሙ ምክትል ሊቀመንበሩ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ከመድረክ ጋር እንዲሰራ በወሰነው መሰረት ዛሬ ከኦፌኮ ጋር በተደረገው ውይይት በሰማያዊ ፓርቲ በኩል ሊቀመንበሩ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፣ ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ነገሰ ተፋረደኝ፣ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊው አቶ ጋሻው መርሻና የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ ወ/ሮ መዓዛ መሃመድ ተገኝተዋል፡፡ በኦፌኮ በኩልም ሊቀመንበሩ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ሙላቱ ገመቹ እና ፀኃፊው አቶ በቀለ ነገአ ተገኝተዋል፡፡ ሁለቱ ፓርቲዎች በቅርቡ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግለጫ እንደሚሰጡና የጋራ ግብረ ኃይል አቋቁመው የፖለቲካ ትግል እንደሚያደርጉም አቶ ነገሰ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል