Wednesday, December 4, 2013

እውነተኛ ታሪክ እና ምክር ለወንዶች!

እውነተኛ ታሪክ እና ምክር ለወንዶች! 

የዛሬ ስንት አመት እንደሆነ ረሳሁት ግን ቆይቷል፡፡ እኔ እና ዮ ቲጂ ለራዲዮ ፕሮግራሟ ቃለ ምልልስ አደረገችልን፡፡ (በቅንፍም ዮ የተባለውን ግለሰብ እንዳታውቁት በመስጋት ስሙን ከሚገባው በላይ ከምችለው እኩል አሳጥሬዋለሁ፡፡ (በሌላ ቅንፍ ታዋቂ ነበርን እኮ "አሉ" የተባሉ ሬድዮ ፕሮግራም አዘጋጆች ቃለ ምልልስ ላይ የማንጠፋ… (በሶስተኛ ቅንፍ እርጅና መጣና ድቅን አለ ፊቴ… በአራተኛ ቅንፍ. (ሃሃ)))) 

እናላችሁ ቃለ ምልልሳችን የሚያተኩረው በሴቶች ጥቃት ላይ ነበር፡፡ እኔ ጉዳዩ በሬዲዮ ስለሚተላለፍ ብቻ ሳይሆን ልምዱም ስላልነበረኝ "ሴት ልጅ የሚደባበስ እንጂ የሚመታ አካል ያላት አይመስለኝም" ብዬ ለሴት እህቶቼ እና "ወንድሞቼ" ያለኝን ወገንታዊነት አንፀባቅኁ… (መለኛ እኮ ነኝ…) 

ዮ ነፍሴ ግን ገርል ፍሬንዱ ካልደበደባት እንደምታኮርፈው ገለፀ እኛ ስቱዲዮውን በሳቅ ሞላነው… ዮ አዩን ፈጠጥ አድርጎ "የምሬን ነው የምላችሁ ከልመታኋት ታኮርፈኛለች፡፡ እኔ ደግሞ ኩርፊያ አልወድም ደህና አአድርጌ እደበድባታለሁ" አለ፡፡ ዮ ሌላም ሌላም ቺኩን ከመደብደብ ጋር ተያይዞ ያለውን ልምድ ምንም ሳይደብቅ ሞቅ አድርጎ ነገረን፡፡ ቲጂ ሆዬ ሁሉንም ቅድት አደረገችው፡፡ ያ ፕሮግራም በነጭ ሪባን ቀን የሚተላለፍ ነበር፡፡ ቲጂ አሪፍ ፕሮግራም እንደሚወጣው እየቋመጠች፡፡ ሁለታችንንም በጣም አመስግና ሸኘችን፡፡ 

ዮ እንቅልፍ አልወስደው አለ፡፡ "ምን ነካኝ" ሲልም አብዝቶ ተፀፀተ፡፡ የተፀፀተው ገርል ፍሬንዱን ስለደበደባት አይደለም፡፡ ለህዝብ በሚተላለፍ ራድዮ ፕሮግራም ላይ ይሄንን ጉዱን በማስቀረፁ እንጂ፡፡ በሌሊት ደውሎ ቲጂን ይሄንን ፕሮግራም ባለማስተላለፍ ህይወቱን ከአደጋ እንድትታደገው ለመናት፡፡ "ምን ሆነሃል" ብላ ብትጠይቀው ይሄ ፕሮግራም ከተላለፈ ራሱን እንደሚያጠፋ ነገራት፡፡

ነጭ ሪባን ቀን የሴቶች ጥቃትን ለመቃወም የተሰየመ ቀን ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ MahiFantish Wube ተጨማሪ አላት

መደምደሚያ

መፀፀት ካለብን ሚስቶቻችንን፣ ገርል ፍሬንዶቻችንን ወይም ቺኮቻችንን ስንደበድብ እንጂ ጉዳችን ሲሰማ መሆን የለበትም፡፡ ወንዶች ሆይ እውነት እውነት እላችኋለሁ ሴቶቻችን ቢፈልጉ እንኳ አትምቷቸው፡፡ ቢከሱን እስር ቤት ባይከሱን ሃኪም ቤት መመላለሱ ምን ይጠቅመናል! (በውቄ ቶን አለች እዚጋ… ሃሃ) 
"ፍቅር ያሸንፋን" ብለን ደግሞ ቴዲ ቶን እንጨምርባት እና አማን ያድርገን እንበል... 

መልካም ነጭ ሪባን ቀን!

Source -Abe Tokichaw

No comments:

Post a Comment