Tuesday, November 26, 2013

በሳውዲ ለሚገኙ ወገኖቻችን በአፋጣኝ እንድረስ፤ በወያኔ ላይ በጋራ እንነሳ!!!


በሳውዲ አረቢያ በሚገኙ ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው መጠን የለሽ የመብት ጥሰት ለመቃወም በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በየአገራቱ የሚገኙ የሳውዲን ኢምባሲዎችን በተቃውሞ እያጨናነቁ ነው። በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ባለው ዘግኛኝ በደል የተሰማቸውን ጥልቅ የመጠቃት ስሜት ኢትዮጵያን በተቃውሞ ሰልፎቹ ላይ በሚያሰሟቸው መሪር የሐዘን እንጉሮችና የቁጭት ንግግሮች እየገለፁ ነው። ከሐዘንና ቁጭት ባለፈም ለበደል ለተጋለጡ ወገኖቻችን አስቸኳይ ሰብዓዊ ርዳታ ለማድረስ እና የዲፕሎማሲ ድጋፍን ለማሰባሰብ ዓለም ዓቀፍ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ሥራውን ጀምሯል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ይህንን ዓለም ዓቀፍ ጥረት ለመደገፍ በውጭ አገራት የሚገኙ አባላቱ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መመሪያ አስተላልፏል።
ይህ ሁሉ በውጭ አገራት እየተደረገ ያለ ጥረት ነው። ኢትዮጵያዊያን ባሉበት አገራትና ከተማዎች ሁሉ በዚህ ጉዳይ ላይ በአንድነት መንቀሳቀሳቸው የሚያስደስት ነገር ነው። ሌላው ቀርቶ በሳዉዲ ዋና ከተማ ሪያድ ውስጥ እንኳን ኢትዮጵያውያን የሳውዲን መንግሥት ተቃውመው ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተዋል።
የሳውዲ መንግሥት በኢትዮጵያ ስደተኞች ላይ የያዘውን ጨካኝ አቋም እና በመንግሥት እውቅና በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን በደል መቃወም ያልተቻለው በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ!!! ይህ እጅግ ያማል፣ ልብን ያደማል።
ወያኔ የሳውዲ የንግድ ሸሪኮቹን ለማስደሰት የፈንሳይን ግማሽ የሚያህል ለም መሬት በነፃ መስጠቱ በቂ አልመሰለውም። በአገራቸው ኢትዮጵያዊያንን ሲጨፈጭፉ፣ ሲገሉና ሲደፍሩ በቸልታ መመልከቱ በቂ የወዳጅነት ስጦታ መስሎ አልተሰማውም። እናም ሸሪኮቹ የበለጠ እንዲደሰቱና ከእስከዛሬ በበለጠ ገንዘብ እንዲደጉሙት ለማበረታታት አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲያቸው ፊት ለፊት ኢትዮጵያንን ደበደበላቸው።
ወያኔ ከሳውዲ ጋር ያለው ግኑኝነት “የቢዝነስ ሽርክና” ነው። ቢዝነሱም ኢትዮጵያዊያንን በቁማቸው መሸጥንም ያጠቃልላል። የወያኔ ሹማምንት እና የሳውዲም ቱጃሮች በዘመናዊ ባርነት ንግድ ውስጥ አቀባይና ተቀባይ ናቸው። ለዚህም ነው እየተነገደበት ያለው ምስኪን ኢትዮጵያዊ እጣ ፈንታ በአዲስ አበባና በሪያድ አንድ ዓይነት የሆነው። እዛ ዱላ፤ እዚህም ዱላ። እዛ እስር፤ እዚህም እስር። እዚያ ስድብ፤ እዚህም ስድብ። እዚያ ቶርቸር፤ እዚህም ቶርቸር። በባርያ ንግድ ውስጥ አቀባዩም ተቀባዩም ባርያዉን መግዛታቸው፣ መስበራቸው፣ መግደላቸው የማይቀር መሆኑ የታወቀ ነው። ginbot7.org

No comments:

Post a Comment