Monday, November 30, 2015

ወያኔ ሰራሽ የርስበርስ ግጭት ድግሶችን እናምክን

November 28, 2015
def-thumbየወያኔ ስርዓት የኢትዮጵያን አስተዳደር ሲያዋቅር በህዝብ ታሪካዊ አብሮነትና ተዛምዶ ላይ ተመስርቶ ሳይሆን የብሔር ብሔረሰብ ልዩነቶችን በማጉላትና ልዩነቱም የርስበርስ ጥርጣሬና ግጭት ምንጭ እንዲሆን በማድረግ ነው። ልዩነቱ የእርስ በርስ ግጭትና የረጅም ጊዜ ቁርሾ እንዲፈጥር ተደርጎ ከመዋቀሩ በተጨማሪ፣ ግጭቱ በማንኛውም ጊዜ እንዲነሳ ፖለቲካዊ ግፊት ይደረግበታል ። አንዱ ብሔረሰብ በሌላው ብሔረሰብ ክልል ውስጥ ሲሆን ባዕድነት እንዲሰማውና እንዲሰጋ፣ አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ እንዲመለከተው ለማድረግ ላለፉት 24 አመታት ሲገፋ ቆይቷል፤ እየተገፋም ነው። በዘመነ ወያኔ በየቦታው በብሔር ወይም ብሔርሰብ ስም የተነሱ ግጭቶች በሙሉ የተቀሰቀሱት በራሱ በአገዛዙ ባለስልጣኖች እንጂ በህዝቡ አይደለም፤ ሆኖም አያውቅም። በተለያዩ የደቡብ የሀገሪቱ ክፍሎች የአማራ ተወላጆችን ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ ለማባረር የተወሰዱት እርምጃዎች በሙሉ ባለስልጣኖቹ ከፊትና ከጀርባ ሆነው የቀሰቀሱዋቸው ፣ ያቀነባበሩዋቸውና የመሩዋቸው ለመሆናቸው ተጎጂዎች በግልጽ ሲናገሩ ሰምተናል።
በቅርቡ በቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ በአስቃቂ ሁኔታ ተገድለውና ተጥለው የተገኙት የአማራ ተወላጆች የሥርዓቱን ባህሪይ ከሚያሳዩ መግለጫዎች አንዱ ነው ። እንዲህ አይነቱ አሰቃቂ ድርጊት ወያኔ ባስለጠናቸውና ባዘዛቸው ካድሬዎችና ባለስልጣኖች የተፈጸመ እንጂ በሕዝብ ተነሳሽነት የተፈጸመ አለመሆኑ ግልጽ ነው። በቅርብ የተፈጸመው ድርጊት ቀደም ሲል በመንግስት ደረጃ የተቀነባበረው አማሮችን የማፈናቀል ዘመቻ ተከታይ ስራ ነው። በወገኖቻችን ላይ በሚዘገንን መንገድ የተፈጸመው ይህ አሰቃቂ ግፍ ዘልቆ ይሰማናል። ቁጭታችንና ሀዘናችን ግን ወያኔ ወደሚፈልገው የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት መንስኤ እንዳይሆን ከፍተኛ ትዕግስትና ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል።
ሰሞኑን እንደገና በታሪክ ሊዘገብ ከሚችል ልዩነት ውጭ ባኗኗር፣ በባህልና ቋንቋ የማይለያዩትን የሰሜን ኢትዮጵያ ህዝቦች ቅማንትና አማራ በሚል ለማጋጨት ጥረት በማደረግ ላይ ይገኛል። ይህ ሰይጣናዊ አካሔድ በወያኔ የፖለቲካ ተንኮል እየተመራ እንዳለ የሚያሳዩ ብዙ መረጃዎች አሉ። አርበኞች ግንቦት 7 የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ካላንዳች መድሎና ልዩነት ሀገሪቱ ላይ መብታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ ሁሉም በየበኩላቸው የሚያደርጉትን ጥረትና ትግል ይደግፋል። በህዝባችን መካከል ያሉት ግንኙነቶች አንዱ አንዱን የሚያግዝና የሚደግፍ እንዲሆን እንጂ የእርስ በርስ የመጋጨትም ሆነ የመናቆር ምክንያት እንዳይሆን ተግቶ ይሠራል ።
ኢትዮጵያውያን ብሄርና ዘር ሳንለያይ ይህንን የወያኔ ተንኮል ችግሩ ወደባሰ ደረጃ ሳይሄድ መቋቋምና ማክሸፍ እንደሚኖርብን አርበኞች ግንቦት 7 ያሳስባል። ይህ ታሪክዊ መተሳሰራችንንና ታላቅ ሕዝብነታችንን የማይመጥን አሳፋሪ የወያኔ ፖለቲካ እንደሀገር እንዳያጠፋን ሁላችንም በንቃትና በቁርጠኝነት መቋቋም ይኖርብናል::
አርበኞች ግንቦት ፯ ልዩነት ጌጥ እንጂ የጠብና የግጭት ምክንያት የማይሆንባት ሀገር ፥ የየብሔረሰቡ መብት ሁሉ የይስሙላ ሳይሆን በተግባር የተረጋገጠባት ሀገር ፥ ከነልዩነታችን በጋራ ራዕይ የምንተሳሰርባትና የምንገነባት ሀገር እንድትኖረን የሚያደርገውን ትግል ይቀጥላል። የቻልክ በአካል ተቀላቀለን። ያልቻልክ በያለህበት የወያኔ ዘራፊዎች ያሰቡትን የተንኮል ጉንጉን በመበጣጠስ ተሳተፍ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !

መምህር ግርማ በተጠረጠሩበት የግድያ ክስ የሟች አስከሬን በድጋሚ እንዲመረመር ታዘዘ

ዘ-ሐበሻ) መምህር ግርማ ወንድሙ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ:: ፖሊስ በመምህሩ ላይ ከግድያ ወንጀል ጋር በተያያዘ ያቀረበው ክስ የተሰማ ሲሆን የተከሰሱበት አስከሬን ጉዳይንም ፍርድ ቤቱ ተመለከተው:: ፍርድ ቤቱ እንዳዘዘው መምህር ግርማ በተጠረጠሩበት የግድያ ክስ አስከሬኑ በድጋሚ እንዲመረመር ፍርድ ቤቱ ማዘዙን የዘ-ሐበሻ ምንጮች አስታውቀዋል:: የአስከሬን ምርመራው ተጠናቆም መምህር ግርማ ታህሳስ 4, 2008 ዓ.ም ፍርድ ቤት ተመልሰው እንዲቀርቡ ታዟል:: በመምህር ግርማ ላይ ከግድያ ወንጀል ጋር በተያያዘ ክስ ለመመስረት ዝግጅት እንዳለ ከአንድ ወር በፊት ዘ-ሐበሻ ቀድማ ምንጮቿን ጠቅሳ መዘገቧ አይዘነጋም:: - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48603#sthash.tGkwU6uf.dpuf

በበርካታ ኢትዮጵያውያን ብርቱ ትግል ቢቢሲ ራድዮ የኦሮሚኛ ቋንቋ ሥርጭት ለመጀመር ፈቃደኛ መሆኑ ተሰማ -

(ዘ-ሐበሻ) ቢቢሲ በመካከለኛና በአጭር ሞገድ የትግርኛና የአማርኛ ቋንቋ የራድዮ ስርጭቶችን ወደ ኤትዮጵያና ኤርትራ ለመጀመር እቅዱን ካወጣ በኋላ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከአማርኛ እና ከትግርኛ ቋንቋ በተጭማሪ የኦሮሚኛ ፕሮግራምም እንዲጀመር ባደረጉት ሰፊ ትግል የዓለማችን ትልቁ የመረጃ ተቋም የሕዝቡን ጥያቄ መቀበሉን ምንጮች አስታወቁ:: ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በዓለም አቀፍ ደረጃ የፊርማ ማሰባሰብ በማህበራዊ ድረገጾች በማድረግ ቢቢሲ የኦሮሚኛ ቋንቋ የራድዮ ስርጭትም እንዲጀምር ግፊት ያደረጉ ሲሆን ተቋሙም በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የሕዝብ ፊርማዎችን ከተመለከተ በኋላ ጥያቄውን ተቀብሏል ተብሏል:: ቢቢሲ በይፋ ይህንን ጥያቄ በቅርቡ ለሕዝብ ያቀርበዋል ያሉት ምንጮች በአማርኛ; በኦሮሚኛ እና በትግርኛ ቋንቋዎች የቢቢሲ ራድዮ ዝግጅቶች በመካከለኛውና በአጭር ሞገድ ለመቅረብ መወሰኑ እንደ ትልቅ ድል ይቆጠራል ብለዋል:: ቢቢሲ የኦሮሚኛ ቋንቋን እንዲጀምር ግፊት ለማድረግ በተደረገው የፊርማ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ ውስጥ በአንድነት የተንቀሳቀሱ ኃይሎች በሌሎች ሃገራዊ ጉዳዮች ላይም እንዲሁ በሕብረት ለውጥ የሚያመጡ ጥረቶችን በጋራ እንዲሰሩ ከሕዝብ ጥሪ ቀርቧል:: - 

Saturday, November 28, 2015

የሕወሓት አስተዳደር አዲስ አበባን “እናሰፋለን” በሚል ሰበብ የሚሰራው ሸፍጥ ተጋለጠ (ምስጢራዊውን ደብዳቤው ይዘናል)

(ዘ-ሐበሻ) በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ሕዝቡ ሕወሓት የሚመራው መንግስት ያዘጋጀው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን በመቃወም አደባባይ በመውጣቱ ለበርካቶች ሕይወት መጥፋት እና ለበርካቶች መቁሰል ምክንያት እንደነበር ይታወሳል:: እነዚህ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ የሃገራችን ፍሬዎች ምክንያታቸው በአዲስ አበባን የማስፋፋት ምክንያት ምስኪን ገበሬዎችን በማፈናቀል መሬታቸውን ለባለሃብቶች ለመሸጥ ነው የሚል ነው:: ሕወሓት የሚመራው መንግስት “በልማት” ስም የተለያዩ የሃገራችንን መሬቶች ገበሬዎቹን በማሰናበት ለውጭ ባለሃብቶች በመሸጥ ይታወቃልና ወትሮም እነዚሁ በኦሮሚያ ክልል ያሉ ሕዝቦች አደባባይ ወጥተው ይህን በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ገበሬዎችን ያፈናቅላል ያሉትን አዲሱን ማስተር ፕላን ቢቃወሙ አይገርምም:: ዛሬ የተለቀቀው ምስጢራዊ ደብዳቤ በአዲስ አበባን የማስፋፋት ስም በሕወሓት መንግስት የሚደረገውን ጥልቅ ሴራ ያጋለጠ ነው:: ምስጢራዊው ደብዳቤ እንደሚያሳየው ‘ሆዜ ሂማንተሪያን ፋውንዴሽን” የተሰኘ ድርጅት የመለስ ዜናዊን መንደር በሰበታ አዋስ ወረዳ ያቀረበውን ጥያቄ ወረዳው መቀበሉን ያረጋገጠበት ነው:: ደብዳቤው እንደሚለው ለመለስ ዜናዊ መንደር ግንባታ ለሆዜ ፋውንዴሽን አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሄክታር ወረዳው እንዲያዘጋጅ መጠየቁን እና ይህንንም ማዘጋጀቱን ነው:: እንግዲህ አዲስ አበባን እናስፋፋለን የሚሉት ምስኪን ገበሬዎቹን አፈናቅሎ ምን ለመፍጠር እንደሆነ ከዚህ በታች ከቀረበው ደብዳቤ ይረዱና አስተያይትዎን ያስቀምጡ:: - 

Thursday, November 26, 2015

የህንዱ ካራቱሪ ኩባንያ ንብረት ጨረታ ወጣበት

 ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጋምቤላ ብሔራዊ ክልል በኑኤር ዞን ጂካዎ እና ኢታንግ ወረዳ የሚገኘውን የህንዱ ካራቱሪ አግሮ ፕሮዳክትስ ኃ/ተ/የግ/ማ ንብረት የሆነውን 100ሺህ ሄክታር የእርሻ መሬት ጨምሮ ሌሎች ንብረቶች ላይ የሐራጅ ጨረታ አውጥቷል። ባንኩ ህዳር 7ቀን 2008 በመንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ባወጣው የሐራጅ ማስታወቂያ መሠረት ተጨራቾች እስከ ታህሳስ 12 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ መጫረት እንደሚችሉ የገለጸ ሰሆን፣ በዚህ ጨረታ ለሽያጭ የቀረበው የካራቱሪ በሊዝ የተረከበው መሬት 100 ሺ ሔክታር ሲሆን ከዚህ ውስጥ 7ሺ 645 ሄክታር መሬት የለማ መሆኑን ገልጾአል፡፡ ኩባንያው ከመንግስት ለእርሻ ኢንቨስትመንት ከተረከበው መሬት በተጨማሪም መጋዘን፣ የሠራተኞች መኝታ ቤቶችንና ተገጣጣሚ ቤቶችን ባንኩ እንደሚሸጥ አስታውቆአል፡፡ ባንኩ ያስቀመጠው የጨረታ መነሻ ዋጋ 55 ሚሊየን 886 ሺህ 424 ብር ከ52 ሳንቲም ነው፡፡ ካራቱሪ ኩባንያ ከኢትዮጽያ ንግድ ባንክ ከ 4 አመት በፊት 62 ሚሊየን ብር የተበደረ ሲሆን ገንዘቡን ለተወሰነ ጊዜያት መክፈል ከጀመረ በሃላ ማቁዋረጡን ከባንኩ የተገኘ መረጃ ይጠቁማል፡፡ ኩባንያው ከስምንት ዓመት በፊት ወደኢትዮጵያ ገብቶ እጅግ ሰፊ መሬት በርካሽ ሊዝ ዋጋ ሲወስድ «ይህ ክስተት በርካታ ገበሬዎችን ያፈናቅላል፣ ለተፈጥሮ ሐብት ውድመትም ያጋልጣል» በማለት ሲቃወሙ የነበሩ ኢትዮጵያዊያንን«የጸረ ልማት ሃይሎች አጀንዳ ነው» በማለት መንግስት ሲያጣጥል ቆይቷል። ኩባንያው በሜካናይዜድ የግብርና ስራ ብዙ ውጤት ያመጣል በሚል እምነት በነጻ በሚል የሊዝ ዋጋ 300ሺህ ሄክታር መሬት በጋምቤላ ክልል ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት እንዲረከብ የተደረገ ሲሆን፣ ኩባንያው በፍጥነት ወደስራ እገባለሁ በሚል የተረከበው ቦታ ላይ ያሉትን ዛፎችና ሌሎች የተፈጥሮ ሐብቶች በማውደሙ ከአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቶች በወቅቱ ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶበታል፡፡ ይህም ሆኖ ኩባንያው ስራውን በይፋ እስካቆመበት ጊዜ ድረስ ከተሰጠው ቦታ ማልማት የቻለው 800 ሄክታር መሬት ብቻ ነው፡፡በዚህ ምክንያት ከአንድ ኣመት ተኩል በፊት የግብርና ሚኒስቴር 200 ሺ ሄክታር መሬት ከኩባንያው መልሶ ለመቀማት ተገዶኦል፡፡ ኩባንያው ከ150 በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞች የነበሩት ሲሆን የሀገሪቱን ሕግ አክብሮ የሠራተኛ መብት በማክበር መክፈል የነበረበትን የደመወዝ ገቢ ግብር ባለመክፈሉ ተጨማሪ ክሶች አሉበት፡፡በተጨማሪም በግብርና ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፈቃድ ወስዶ፣ ከባንክ በተበደረው ገንዘብ ከቀረጥ ነጻ ያስገባቸውን የእርሻ ማሽነሪዎችን ለሶስተኛ ወገን በማከራየትና በመሸጥ ያልተፈቀደለት ንግድ ስራ ውስጥ ገብቶም መገኘቱ ስለኩባንያው ብዙ ያወራውን መንግስት ጭምር ያሳፈረ ሕገወጥ ተግባር ሆኗል፡፡ ካራቱሪ ቦታውን የተረከበው ከፌዴራል መንግስት በመሆኑ የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት ብዙ ችግሮች መኖራቸውን ቢረዳም ምንም ማድረግ ሳይችል ቀርቷል።የኩባንያው ከፍተኛ ሃላፊዎች ከመንግስት በሊዝ ኪራይ ያገኙትን መሬት በማስያዝ ከንግድ ባንክ ከተበደሩና ሕገወጥ ስራ ሲያከናውኑ ከቆዩ በሁዋላ ጉዳዩ ሲታወቅባቸው ሀገር ለቀው መውጣታቸው ታውቆአል፡፡

Wednesday, November 25, 2015

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የፊታችን ማክሰኞ በአውሮፓ ፓርላማ ንግግር ያደርጋሉ ተባለ

(ዘ-ሐበሻ) የትጥቅ ትግሉን መንገድ መርጠው ታግዬ አታግላለው ብለው አስመራ የወረዱት የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የፊታችን ማክሰኞ ዲሴምበር 2 በአውሮፓ ፓርላማ ንግግር እንዲያደርጉ መጋበዛቸውን ለዘ-ሐበሻ የደረሱ መረጃዎች አመለከቱ:: ከአስመራ ወደ ብራሰልስ እንደበረሩ የሚነገርላቸው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለሕዝብ ክፍት በሆነው በዚሁ የአውሮፓ ፓርላማ ላይ ንግግር እንዲያደርጉ የተጋበዙት በወ/ሮ አና ጎሜዝ ነው ተብሏል:: በዚህ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ መገኘት ለሚፈልጉ – የአውሮፓ ነዋሪዎች በምርጫ 97 ወቅት የአውሮፓ የምርጫ ታዛቢ ለነበሩት ወ/ሮ አና ጎሜዝ ደብዳቤ ፕሮግራሙ ለሕዝብ ክፍትና ነፃ በመሆኑ አስቀድማችሁ ስማችሁን፣ የተወለዳችሁበትን ቀን/ ወር/ ዓ.ም፣ ዜግነታችሁን፣ እና የፓስፓርት ቁጥራችሁን በ Anamaria.gomes@europarl.europa.eu በመላክ መመዝገብ እንደሚቻል የደረሰን መረጃ ጠቁሟል::

“በአዛዙ የአፈና መዋቅር የኢትዮጵያ ህዝብ የነፃነትና የእኩልነት ትግል አይቀለበስም” – ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ -

ህወሓት/ኢህአዴግ በህገ መንግስቱና በሌሎች ራሱ ባወጣቸው ህጎች በርካታ መብቶችን ለይስሙላ ቢደነግግብ ቅሉ፤ በተግባር ግን እነዚህን መብቶች ሆነ ብሎ ባደራጀው የአፈና መዋቅሩ እየደፈቃቸው ይገኛል፡፡ ምንም እንኳን አገዛዙ የመደራጀት መብትን በወረቀት ቢያሰፍርም ‹‹እግር እስኪያወጡ እንጠብቃለን፤ እግር ሲያወጡ ግን እንቆርጣለን›› በሚል መርህ ፓርቲዎችን በዚሁ የአፈና መዋቅሩ በገሃድ እያፈረሰ ቀጥሏል፡፡ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ፈቅጃለሁ ቢልም ጋዜጠኞችን በማሰር፣ በማሳደድና ሚዲያዎችን በመዝጋት አማራጭ ሀሳብ እንዳይራመድ አድርጓል፡፡ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን ወረቀት ላይ ቢደነግግም በአስተዳደራዊ መዋቅሩ መሰረት ክርችም አድርጎ ዘግቶታል፡፡ የዜጎችን የመዘዋወር መብት ቢደነግግም ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ፓስፖርት በመንጠቅ ጉዟቸውን በማተጓጎል ላይ ይገኛል፡፡ የመንግስት አሰራር ግልፅና ተጠያቂነት አለበት ተብሎ ተደንግጓል፤ ነገር ግን በየ መስርያ ቤቱ ያለ እጅ-መንሻ ዜጎች አገልግሎት ማግኘት አይቻልም፡፡ ይህ ሁሉ አፈና ሆነ ተብሎ ታስቦበት፣ የአገዛዙን ስልጣን ለማራዘም የሚደረግ መዋቅራዊ ጫና መሆኑን ፓርቲያችን በጽኑ ያምናል፡፡ ዛሬ በሀገራችን ከፍተኛ ርሃብ፣ ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ስራ አጥነት፤ ስደት እና ሌሎችም ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውሶች በሰፊው ተንሰራፍተው ይገኛሉ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ እነዚህን ወቅታዊ ጉዳዮች ከህዝብ ጋር ተወያይቶ አቋም ለመውሰድና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለመሰንዘር ህዳር 18 ቀን 2008 ዓ.ም ህዝባዊ ስብሰባ እንደሚያደርግ ለአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት የእውቅና ደብዳቤ ለማስገባት በተደጋጋሚ ጥረት ያደረግን ቢሆንም የአፈና መዋቅሩ የእውቅና ደብዳቤውን መቀበል ባለ መፈለጉ ለ5 ጊዜ ተጉላልተን በ6ኛው በሪኮመንዴ(በፖስታ) ለመላክ ተገደናል፡፡ የእውቅና ደብዳቤው በሪኮመንዴ የደረሰው አስተዳደሩ ህዳር 6 ቀን 2008 ዓ.ም ላይ ሆኖ ‹‹ህዳር 18/2008 ዓ.ም አልፏል›› በሚል ለተጨማሪ ጊዜ ደብዳቤውን ሳያስተናግድ ቀርቷል፡፡ ህዳር 18 ያላለፈ መሆኑን ካስረዳን በኋላ ለሶስት ቀናት በተደጋጋሚ ብንመላለስም ‹‹ከደህንነትና ፖሊስ ጋር ካልተመካከርኩ እውቅና አልሰጥም›› ሲል እምቢታውን ገልጾአል፡፡ በዚህም ምክንያት ከአባላትና ደጋፊዎቻችን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ልናደርገው የነበረው ውይይት ሊደናቀፍ ችሏል፡፡ ከዓለም የነጻነት የትግል ታሪክ እንደምንገነዘበው በአገዛዝ አፈና የተገታ የህዝብ ጥያቄ ኖሮ አያውቅም፡፡ አፈናው የነጻነትን ጊዜ ቢያዘገይ እንጅ ፈጽሞ ሊያስቀርም አይችልም፡፡ ስለሆነም ጭቆናው ወደ ነፃነት የሚያስኬደውን ጉዞ እልህ አስጨራሽ ከማድረግ በቀር ዘላቂነት ኖሯቸው የነጻነት ጥያቄውን ፈጽሞ ማዳፈን እንደማይችሉ አገዛዙ ሊረዳ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ህዝብ ለማይቀረው የነፃነት ትግል ቆርጦ እንዲነሳና ከሰማያዊ ፓርቲ ጎን እንዲቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር! ህዳር 14 ቀን 2008 ዓ.ም አዲስ አበባ - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48484#sthash.UvtimX4X.dpuf

Thursday, November 19, 2015

የኢትዮጵያ ወጣቶች ክልል፣ ቋንቋም ሆነ ሀይማኖት ሳይገድባቸው በጋራ ይቁሙ!

November 5, 2015
def-thumbከ1950ዎቹ ጀምሮ የተደረጉ ሕዝባዊ ንቅናቄዎች በሙሉ የተጠነሰሱትና የተመሩት እድሜያቸው ከሠላሳ አምስት ዓመት በታች በሆኑ ወጣቶች ነው። የ1997 ምርጫ ታሪካዊ እንዲሆን ያደረጉ፤ የሚያዝያ 30 ቀን 1997ን ታላቅ ሰልፍ ያደራጁ፤ ሕዝብን አደፈፍረው ለምርጫ በማሰለፍ ግንቦት 7 ቀን 1997 ታሪካዊ ዕለት እንድትሆን ያደረጉ፤ በኋላም “ድምፃችንን አናስነጥቅም” በማለት የአግዓዚ ፋሽስቶችን በድንጋይና ዱላ የገጠሙ የኢትዮጵያ ወጣቶች ናቸው። በዚህ ትግል ሽብሬ ደሳለኝን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች ሕይወታቸውን ሰውተዋል፤ በቁጥር የበዙት ደግሞ አካሎቻቸውን አጥተዋል፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች አሁንም በአገዛዙ እስር ቤቶች ሰቆቃ እየተፈፀመባቸው ነው። ጥቃቱ ቢበዛም ትግሉ ደግሞ የዚያኑ ያህል ተጠናክሮ ቀጥሏል። የኢትዮጵያ ወጣት ጥቃትን አሜን ብሎ አይቀበልም።
ህወሓትና ህወሓት የፈጠራቸው አድርባይ ድርጅቶች የዛሬው ወጣት ወኔው የላሸቀ፤ ኑሮው የተጎሳቆለ፤ የነገ ተስፋውም የጨለመ እንዲሆን ፓሊሲ ነድፈው እየተንቀሳቀሱ ነው። ህወሓት “መብት ተነፈግን” ብለው ብረት ባነሱ ወጣቶች መቋቋሙን ረስቶ የዛሬ ወጣቶች መብቶቻቸውን ተጠቅመው ሕይወታቸውን መምራት ቀርቶ መብቶቻቸው ምን እንደሆኑ እንዲጠይቁ እንኳን አይፈቅድላቸውም። በህወሓት አገዛዝ የትምህርት ተቋማት የሚሰጡት ትምህርት ጥራት እጅግ የወረደ በመሆኑ ወጣቶች የሕይወትን ፈተና ለመቋቋም የሚያስችል ክህሎት ሳይዙ እንዲመረቁ እየተደረገ የተመራቂ ሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ተደርጓል። ለወጣቱ የሥራ እድሎችን የመክፈት ጉዳይ አገዛዙን የሚያስጨንቀው አይደለም። ለም መሬታችን ለባዕዳን በመሸጡ የገጠሩ ወጣት የሚያርሰው ቁራሽ መሬት እያጣ መሰደድ ከጀመረ ውሎ አድሯል። በሀገር ውስጥ ተስፋ በመታጣቱ በገጠርም በከተማም የሚገኙ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ወደ ደቡብ አፍሪቃና አረብ አገራት ለመሄድ በረሃ ማቋረጥ፤ ባህርን በታንኳ መሻገር የጀመሩት በዚሁ የግፍ አገዛዝ ዘመን ነው። ዘመናዊ ትምህርት ያገኘው ወጣትም በተማረው ትምህርት አገሩንና ወገኑን የማገልገል ህልሙ ተጨናግፎ ስደት እጣ ፈንታው የሆነው በዚሁ በህወሓት የአገዛዝ ዘመን ነው። በጫትና ሌሎች ሱሶች አዕምሮው የደነዘዘው ወጣት ቁጥርም አስደንጋጭ ነው።
ከዚህ ሁሉ የከፋው ደግሞ ወጣቱን በዘር በማደራጀት እርስ በርሱ እንዲጣላ መደረጉ ነው። በየጊዜው በሚፈለፈሉ “የወጣቶች ፎረሞች” አማካይነት የወጣቱ ወኔ ተሰልቦ አድርባይነትን እንዲለማመድ ተደርጓል። የጎንደሩ ወጣት ለአሰላው፣ የመቀሌው ለባህርዳሩ፣ የጅማው ለአዋሳው ባዕድ እንዲሆን፤ በጥርጣሬም እንዲጠባበቅ፤ በሰበብ አስባቡም እንዲቆራቆስ ተደርጓል። ህወሓት ወጣቶችን በወጣቶች ላይ የሚያዘምት እርኩስ ኃይል ነው።
አገዛዙ ይኸ ሁሉ ቢያደርግም ዛሬም የኢትዮጵያ ወጣት፣ የነብር ጣት መሆኑን እያስመሰከረ ነው። አገሩን ከህወሓት ፋሽስቶች ለማዳን ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር በመቀላቀል ላይ ያለው የወጣት ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ነው፤ በያለበት ከተማና መንደር ሆኖ በመደራጀት ላይ ያለው ወጣት ቁጥር ደግሞ በጣም አበረታች ነው። ከዚህም በላይ የቴፒ፣ አርባምንጭ፣ ባህርዳርና ጎንደር ወጣቶች እያደረጉት እንዳለው በተደራጀ መንገድ አምባገነኑን ሥርዓት መጋፈጥ ጀምሯል። ጊዜው የአርበኖች ግንቦት 7ቱ አርበኛ አምሳሉ ተሾመን የመሰሉ ለጠላት እጅ ከመስጠት በራስ ላይ እርምጃ መውሰድን የሚመርጡ ቆራጦችን ፈጥሯል።
በእንዲህ ዓይነት ወቅት ክልልን፣ ቋንቋን፣ ዘርንና ሀይማኖትን የተሻገረ የወጣቶች ኅብረት መኖሩ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው። በቴፒ ወጣቶች ላይ በሚደርሰው ጥቃት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወጣት ሊቆጭና ድጋፍ ሊሰጣቸው ይገባል። የአርባምንጭ ወጣቶች ሲሳደዱ፣ ሲደበደቡና ሲገደሉ በመላ ኢትዮጵያ ያሉ ወጣቶች ሊንቀሳቀሱ ይገባል። በለቀምት ወጣቶች በደል ሲደርስ በመላው የኢትዮጵያ ወጣቶች ላይ የደረሰ ጥቃት ነውና ሁሉም ሊያመውና ከጎናቸው ሊቆም ይገባል። በባህርዳርና ጎንደር ወጣቶች ላይ በደል ሲደርስ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ወጣቶች ከጎናቸው ሊቆሙ ይገባል።
የህወወሓት “ወጣቱን ከፋፍለህ፣ አዳክመህ ግዛ” ፓሊሲ በራሱ በወጣቱ ቁርጠኝነትና የጋራ ስሜት ሊከሽፍ ይገባል። ህወሓትን ወደ መቃብሩ የሚገፋው በህወሓት የአገዛዝ ዘመን ተወልዶ ያደገ ወጣት መሆኑ የአገዛዙ ኋላቀርነትና የመጪው ጊዜ ብሩህነት ማረጋገጫ ነው።
አርበኞች ግንቦት 7 የወደፊቷ ኢትዮጵያ ለወጣቱ ምቹ አገር መሆን አለባት፤ መገንባት የሚኖርባትም በወጣቱ ትውልድ ነው ብሎ ያምናል። በዚህም የኢትዮጵያ ወጣቶች ክልል፣ ዘር፣ ቋንቋም ሆነ ሀይማኖት ሳይገድባቸው ለጋራ መብቶቻቸው በጋራ እንዲቆሙ፤ በአንድ አካባቢ ወጣቶች ለሚደርስ ጥቃት የሌላ አካባቢ ወጣቶች አፀፋዊ ምላሽ እንዲሰጡ ያበረታታል። ኢትዮጵያ በወጣቶቿ ያላሰለሰ ትግል ከወያኔ አምባገናዊ አገዛዝ ነፃ ትወጣለች።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

የኢትዮጵያ ወጣቶች ክልል፣ ቋንቋም ሆነ ሀይማኖት ሳይገድባቸው በጋራ ይቁሙ!

ከ1950ዎቹ ጀምሮ የተደረጉ ሕዝባዊ ንቅናቄዎች በሙሉ የተጠነሰሱትና የተመሩት እድሜያቸው ከሠላሳ አምስት ዓመት በታች በሆኑ ወጣቶች ነው። የ1997 ምርጫ ታሪካዊ እንዲሆን ያደረጉ፤ የሚያዝያ 30 ቀን 1997ን ታላቅ ሰልፍ ያደራጁ፤ ሕዝብን አደፈፍረው ለምርጫ በማሰለፍ ግንቦት 7 ቀን 1997 ታሪካዊ ዕለት እንድትሆን ያደረጉ፤ በኋላም “ድምፃችንን አናስነጥቅም” በማለት የአግዓዚ ፋሽስቶችን በድንጋይና ዱላ የገጠሙ የኢትዮጵያ ወጣቶች ናቸው። በዚህ ትግል ሽብሬ ደሳለኝን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች ሕይወታቸውን ሰውተዋል፤ በቁጥር የበዙት ደግሞ አካሎቻቸውን አጥተዋል፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች አሁንም በአገዛዙ እስር ቤቶች ሰቆቃ እየተፈፀመባቸው ነው። ጥቃቱ ቢበዛም ትግሉ ደግሞ የዚያኑ ያህል ተጠናክሮ ቀጥሏል። የኢትዮጵያ ወጣት ጥቃትን አሜን ብሎ አይቀበልም።
ህወሓትና ህወሓት የፈጠራቸው አድርባይ ድርጅቶች የዛሬው ወጣት ወኔው የላሸቀ፤ ኑሮው የተጎሳቆለ፤ የነገ ተስፋውም የጨለመ እንዲሆን ፓሊሲ ነድፈው እየተንቀሳቀሱ ነው። ህወሓት “መብት ተነፈግን” ብለው ብረት ባነሱ ወጣቶች መቋቋሙን ረስቶ የዛሬ ወጣቶች መብቶቻቸውን ተጠቅመው ሕይወታቸውን መምራት ቀርቶ መብቶቻቸው ምን እንደሆኑ እንዲጠይቁ እንኳን አይፈቅድላቸውም። በህወሓት አገዛዝ የትምህርት ተቋማት የሚሰጡት ትምህርት ጥራት እጅግ የወረደ በመሆኑ ወጣቶች የሕይወትን ፈተና ለመቋቋም የሚያስችል ክህሎት ሳይዙ እንዲመረቁ እየተደረገ የተመራቂ ሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ተደርጓል። ለወጣቱ የሥራ እድሎችን የመክፈት ጉዳይ አገዛዙን የሚያስጨንቀው አይደለም። ለም መሬታችን ለባዕዳን በመሸጡ የገጠሩ ወጣት የሚያርሰው ቁራሽ መሬት እያጣ መሰደድ ከጀመረ ውሎ አድሯል። በሀገር ውስጥ ተስፋ በመታጣቱ በገጠርም በከተማም የሚገኙ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ወደ ደቡብ አፍሪቃና አረብ አገራት ለመሄድ በረሃ ማቋረጥ፤ ባህርን በታንኳ መሻገር የጀመሩት በዚሁ የግፍ አገዛዝ ዘመን ነው። ዘመናዊ ትምህርት ያገኘው ወጣትም በተማረው ትምህርት አገሩንና ወገኑን የማገልገል ህልሙ ተጨናግፎ ስደት እጣ ፈንታው የሆነው በዚሁ በህወሓት የአገዛዝ ዘመን ነው። በጫትና ሌሎች ሱሶች አዕምሮው የደነዘዘው ወጣት ቁጥርም አስደንጋጭ ነው።
ከዚህ ሁሉ የከፋው ደግሞ ወጣቱን በዘር በማደራጀት እርስ በርሱ እንዲጣላ መደረጉ ነው። በየጊዜው በሚፈለፈሉ “የወጣቶች ፎረሞች” አማካይነት የወጣቱ ወኔ ተሰልቦ አድርባይነትን እንዲለማመድ ተደርጓል። የጎንደሩ ወጣት ለአሰላው፣ የመቀሌው ለባህርዳሩ፣ የጅማው ለአዋሳው ባዕድ እንዲሆን፤ በጥርጣሬም እንዲጠባበቅ፤ በሰበብ አስባቡም እንዲቆራቆስ ተደርጓል። ህወሓት ወጣቶችን በወጣቶች ላይ የሚያዘምት እርኩስ ኃይል ነው።
አገዛዙ ይኸ ሁሉ ቢያደርግም ዛሬም የኢትዮጵያ ወጣት፣ የነብር ጣት መሆኑን እያስመሰከረ ነው። አገሩን ከህወሓት ፋሽስቶች ለማዳን ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር በመቀላቀል ላይ ያለው የወጣት ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ነው፤ በያለበት ከተማና መንደር ሆኖ በመደራጀት ላይ ያለው ወጣት ቁጥር ደግሞ በጣም አበረታች ነው። ከዚህም በላይ የቴፒ፣ አርባምንጭ፣ ባህርዳርና ጎንደር ወጣቶች እያደረጉት እንዳለው በተደራጀ መንገድ አምባገነኑን ሥርዓት መጋፈጥ ጀምሯል። ጊዜው የአርበኖች ግንቦት 7ቱ አርበኛ አምሳሉ ተሾመን የመሰሉ ለጠላት እጅ ከመስጠት በራስ ላይ እርምጃ መውሰድን የሚመርጡ ቆራጦችን ፈጥሯል።
በእንዲህ ዓይነት ወቅት ክልልን፣ ቋንቋን፣ ዘርንና ሀይማኖትን የተሻገረ የወጣቶች ኅብረት መኖሩ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው። በቴፒ ወጣቶች ላይ በሚደርሰው ጥቃት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወጣት ሊቆጭና ድጋፍ ሊሰጣቸው ይገባል። የአርባምንጭ ወጣቶች ሲሳደዱ፣ ሲደበደቡና ሲገደሉ በመላ ኢትዮጵያ ያሉ ወጣቶች ሊንቀሳቀሱ ይገባል። በለቀምት ወጣቶች በደል ሲደርስ በመላው የኢትዮጵያ ወጣቶች ላይ የደረሰ ጥቃት ነውና ሁሉም ሊያመውና ከጎናቸው ሊቆም ይገባል። በባህርዳርና ጎንደር ወጣቶች ላይ በደል ሲደርስ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ወጣቶች ከጎናቸው ሊቆሙ ይገባል።
የህወወሓት “ወጣቱን ከፋፍለህ፣ አዳክመህ ግዛ” ፓሊሲ በራሱ በወጣቱ ቁርጠኝነትና የጋራ ስሜት ሊከሽፍ ይገባል። ህወሓትን ወደ መቃብሩ የሚገፋው በህወሓት የአገዛዝ ዘመን ተወልዶ ያደገ ወጣት መሆኑ የአገዛዙ ኋላቀርነትና የመጪው ጊዜ ብሩህነት ማረጋገጫ ነው።
አርበኞች ግንቦት 7 የወደፊቷ ኢትዮጵያ ለወጣቱ ምቹ አገር መሆን አለባት፤ መገንባት የሚኖርባትም በወጣቱ ትውልድ ነው ብሎ ያምናል። በዚህም የኢትዮጵያ ወጣቶች ክልል፣ ዘር፣ ቋንቋም ሆነ ሀይማኖት ሳይገድባቸው ለጋራ መብቶቻቸው በጋራ እንዲቆሙ፤ በአንድ አካባቢ ወጣቶች ለሚደርስ ጥቃት የሌላ አካባቢ ወጣቶች አፀፋዊ ምላሽ እንዲሰጡ ያበረታታል። ኢትዮጵያ በወጣቶቿ ያላሰለሰ ትግል ከወያኔ አምባገናዊ አገዛዝ ነፃ ትወጣለች።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

Monday, November 16, 2015

በረሀብ ለተጠቁ ወገኖቻችን እንድረስላቸው !!!

November 14, 2015
def-thumbበወቅታዊ ሁኔታ ላይ የአርበኞች ግንቦት 7 የአቋም መግለጫ
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዳግም ለአስከፊ ረሀብና ችጋር ተጋልጧል፤ ስፋት ጥልቀቱ በ70ዎቹና 80ዎቹ ከነበሩት ጋር ይስተካከላል ተብሎ ተፈርቷል። ከአሁኑ ሰው በረሀብ መሞት መጀመሩ ከአራትና አምስት ወራት በኋላ የሚመጣውን አደጋ ከባድነት መገመት ያስችላል።
ለአስር ተከታታይ ዓመታት ከአስር በመቶ በላይ ዓመታዊ የኢኮኖሚ እድገት በማምጣት ዓለምን እየመራን ነው የሚለው ዓይን ያወጣ ውሸት፤ “ድህነትን ተረት እናደርጋለን” የሚለው ጉረኛ መፈክር፤ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ራድዮ “የህዳሴ ብስራቶች”፣ የአባይ ግድብና የከተማ ባቡር ግንባታ ዜናዎች ለኢትዮጵያዊው አርሶ አደር ቁርስ፣ ምሳና እራት አልሆኑም።
“አድገናል”፣ “ተመንድገናል”፣ “በምግብ ራሳችንን ችለናል” ሲል የከረመው የህወሓት አገዛዝ የረሀቡ ዜና አፈትልኮ ሲወጣ እና የዓለም መገናኛ ብዙሀን መነጋገሪያ ሲሆን የተራበውን ወገናችንን ለማብላት ከመሯሯጥ ይልቅ ተፈጥሮ ላይ ማላከኩን ተያይዞታል። ከዚህ አልፎ ዓመታዊ ድግሶቹ እና ለባለሥልጣናቱ የሚሰጡ ጥቅማጥቅሞች ጉዳይ ከረሀብ በላይ አሳሳቢ በመሆኑ 15 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ በሞት አፋፍ ላይ እያለ የአገሪቱ ሀብት ለድግስና ፈንጠዚያ እንዲሁም ለእያንዳንዱ ባለሥልጣን ቤተመንግሥት አከል መኖሪያ ቤት ማሠሪያ እየዋለ ነው። መቀሌ ላይ ህወሃት 40ኛ ልደቱን ለማክበር ወደ ግማሽ ቢልዮን ብር ባወጣ ማግስት በአማራ ስም ለወያኔ ባርነት የገባው ብአዴን 300 ሚሊዮን ወጪ በማድረግ በረሃብተኛው ሕዝብ አናት ላይ እየጨፈረ ነው:: ይህ የኢትዮጵያን ሕዝብ መናቅ ብቻ ሳይሆን ደግሞ ደጋግሞ ከመግደል የሚቆጠር ወንጀል ነው።
ለመሆኑ የአየር ንብረት መዛባት እየተደጋገመ ለሚመጣ ችጋርና ቸነፈር በቂ ምክንያት ሆኖ ያውቃልን? ለምንድነው ፍትህና ነፃነት በሰፈነባቸው አገሮች ውስጥ ዝናብ ጠፍቶ የእርሻ ምርት ቢቀንስ እንኳን ሰው በረሀብ የማይሞተው? አስከፊ የረሀብ ዜናዎች የሚሰማባቸው አገሮች በሙሉ ነፃነት የታፈነባቸው አገሮች መሆናቸውስ የአጋጣሚ ጉዳይ ነው? ለምንድነው ተደጋግሞ ከሚመጣ የረሀብ አዙሪት መውጣት ያቃተን?
የእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልስ አጭርና ቀጥተኛ ነው። ለችግሮች መፍትሄ መሻት የሚቻለው በነፃነት ማሰብ የሚችል ጭንቅላት ሲኖር ነው። በባርነት ጨለማ ውስጥ ያለ ጭንቅላት ለችግሮች መፍትሄ የማፍለቅ አቅም የለውም። እንዲያውም እንዲህ ዓይነቱ ድኩም ጭንቅላት ችግሮችን ማሸነፍ ሳይሆን ተሸናፊነትን ተቀብሎ ከችግሮች ጋር ተስማምቶና ተወዳጅቶ መኖርን ይመርጣል። ለዚህም ነው የአስተዳደር በደልና ረሀብ ምክንያትና ውጤት ብቻ ሳይሆን እጅና ጓንትም ጭምር የሆኑት።
ነፃነት ያለው ሕዝብ ረሀብን እንደሚያሸነፍ ተደጋግሞ የታየ ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው ረሀብን የተፈጥሮ ሚዛን መዛባት ውጤት ብቻ አድርጎ ማቅረብ እውነትን መሸፈጥ የሚሆነው። ረሀብ የብልሹ አስተዳደር ውጤት መሆኑ ያፈጠጠ፣ ያገጠጠ ሀቅ ነው። ከረሀብ መገላገያ መንገድም የተበላሸ አስተዳደር ተወግዶ ኃላፊነት የሚሰማው፣ የዜጎች የማሰብ ነፃነት የሚያረጋግጥ ሕዝባዊ አስተዳደር ሲኖር ነው።
አገራችን ኢትዮጵያን የረሀብ ቀጠና ካደረጉ የ24 ዓመታት የወያኔ “የዘርፈህ ብላ” የኢኮኖሚ ፓሊሲ ውጤቶች መካከል አንዳንዱን ለአብነት ያህል መዘርዘር ይቻላል።
1.ገበሬና መሬት ተለያይተዋል። ኢትዮጵያዊያን አርሶ አደሮች መሬት አልባ ሆነዋል። ለም መሬቶች በኢንቨስትመንት ስም ለህወሓት ጉልተኞችና ምስለኔዎቻቸው ታድሏል፤ እነሱ ደግሞ በተራቸው ለባዕዳን ሽጠውታል። ኢትዮጵያዊው አርሶ አደር በሀገሩ ጭሰኝነት እንኳን አጥቶ ለቀን ሠራተኝነትና ልመና ተዳርጓል። በዚህም ምክንያት ገበሬው እንኳንስ ትልቁን የአየር መዛባት ትንሿንም የዋጋ ንረት መቋቋም እስከማይችልበት ደረጃ ተዳክሟል።
2.ዘርን መሠረተ ባደረገ ክልላዊ ድንበር ሳቢያ ኢትዮጵያዊው ጎበዝ አርሶ አደር አንዱ ቦታ ቢከፋ ወደ ተሻለ ቦታ ተዛውሮ ማረስ አልቻለም። ከሰሜን ወደ ደቡብ ከሄደ የአገራችን አርሶ አደር ይልቅ ባህር ተሻግሮ የመጣ ኤንቨርስተር ነኝ ባይ መሬት ማግኘት ይቀለዋል። እንዲያውም ኢትዮጵያዊው ገበሬ በዱላና በጥይት ሲባረር፤ ከባዕድ አገር የመጣው ብድርና ማበረታቻዎች ይሰጠዋል።
3.የህወሓት ባላሥልጣኖችና በየቦታው ያስቀመጧቸው ምስለኔዎቻቸው ራሳቸውን ባለሚሊዮኖች፣ ከፍ ሲልም ባለ ቢሊዮኖች አድርገዋል። እነዚህ በአንድ ጀምበር ከትቢያ የተነሱ ቱጃሮች ከገንዘብ በተጨማሪም የጄኔራልነት፣ የሚኒስቴርነት፣ የክልል ገዢነት፣ እጅግ ቢያንስ የቢሮ ኃላፊነት ሥልጣንን ኪሳቸው ውሰጥ ከተዋል። የመንግሥት ሥልጣንና ሃብት ይኸን ያህል የተቆራኙበት ሥርዓት በኢትዮጵያ ኖሮ አያውቅም። የጥቂቶች ያለአገባብና ያለቅጥ መክበር በአንፃሩ ደግሞ የብሃኑን ሕዝብ መደህየት ረሀብ እጣ ፈንታችን እንዲሆን አድርጓል።
4.በአቋራጭና በፍጥነት ለመክበር አስተማማኙ መንገድ የገዛ ራስ ጥረትና ታታሪነት ሳይሆን ቅጥፈት፣ አጭበርባሪነትና ሎሌነት ማደር መሆኑን የህወሓት አበጋዞች በተግባር እያሳዩ ሠርቶ፣ ለፍቶ ማደግ ሞኝነት እንዲሆን አድርገውታል። በዚህም ምክንያት በባህላችን ውስጥ ኮትኩተው ያሳደጓቸው አድርባይነት፣ ስንፍናና እና ልመና ችግርን የመጋፈጥ አቅማችንን ሰልበውታል።
5.ደኖቻችን ተጨፍጭፈው፣ ለም መሬታችን ተሸርሽሮ በማለቁ የግብርናችን ምርታማነት በእጅጉ ቀንሷል። በህወሓት የአገዛዝ ዘመን የደን ጭፍጨፋና የመሬት መሸርሸር በአስደንጋጭ ሁኔታ ጨምሯል። አገሪቷ በፍጥነት ወደ ምድረበዳነት እየተቀየረች ነው።
6.ኢትዮጵያዊያን ገበሬዎች ድርቅን መቋቋም ስለሚችሉ ሰብሎች ወይም የአስተራረስ ዘዴዎች ማሰብ፣ መመራመርና መፈተሽ አይችሉም። አዲስ ነገር መሞከር “የኢህአዴግ የግብርና ፓሊሲን“ በመቃወም ወንጀል የሚያስቀጣ ተግባር ሆኗል። በዚህም ምክንያት ገበሬው ድርቅን መቋቋሚያ አዳዲስ ዘዴዎች መፈለግ ቀርቶ በተለምዶ የሚያውቃቸውንም መጠቀም አልቻለም።
7.የህወሓት አገዛዝ፣ እንደ ኢኮኖሚው ሁሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ ብዛት ሊቆጣጠር የሚሞክረው ቢሮ ውስጥ ቁጭ ተብሎ በሚደረግ የቁጥር ጨዋታ ነው። አገዛዙ ውጤታማ የስነ ሕዝብ ፓሊሲ የለውም፤ እንኳንስ የቀጣይ ዓመታት የሕዝብ እድገት ምጣኔን ሊቆጣጠር አሁን ያለነው ቁጥራችን ስንት እንደሆነ እንኳን በትክክል ሊነግረን አልቻለም፤ ረሀብ ነው መብዛታችንን እየነገረን ያለው።
አርበኞች ግንቦት 7፡ የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ እነዚህና የመሳሰሉት ጭብጦችን በማንሳት የረሀቡ መሠረታዊ ምክንያት የህወሓት አገዛዝ ያሰፈነው ብልሹ አስተዳደር መሆኑን በአንጽዖት ይናገራል። ሕዝባችን በነፃነት ማሰብ፣ መመራመር፣ መፈተሽ ቢችል ኖሮ ረሀብን መከላከያ ብልሃት ማግኘት ባላቃተውም ነበር ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 ያምናል። ረሀብን ለማጥፋት ህወሓትን ከሥልጣን ማስወገድ ከምንጊዜውም በላይ ወሳኝ የሆነ ጊዜ ላይ ተደርሶአል ብሎ አርበኖች ግንቦት 7 ያምናል።
ነገር ግን ረሀብ ጊዜ አይሰጥም። የፓለቲካ ሥርዓት ለውጥ በሞት አፋፍ ላይ ላለ ወገናችን መፍትሄ አይሆንም። ስለሆነም ለረሀቡ መሠረታዊ መፍትሄ የሆነውን ትግላችንን ሳንዘነጋ የወገኖቻችንን ሕይወት ለመታገድ የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል። ሲቪክ ማኅበራት የተራበው ወገናችን የወያኔ መጠቀሚያ ሳይሆን የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የሚያገኝበት መንገድ እንዲያፈላልጉ እና ወገን ለወገን የሚቆምበትን ዘመቻ እንዲያስተባብሩ ጥሪ ያደርጋል። ለወገኖቻችን የሚላከው እርዳታ ከዚህ በፊት እንደነበረው ሁሉ ወደአገዛዙ ባለሥልጣኖች የግል ኪስ እንዳይፈስ ጥንቃቄ እንዲደረግ ያሳስባል። ለወገኖቻችን ለመድረስ እያንዳንዳችን በግል፤ እንዲሁም በቡድን የተቻለንን ሁሉ እናድርግ።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
ኅዳር 3 ቀን 2008 ዓ.ም.

Sunday, November 15, 2015

ጋዜጠኞችና የረድኤት ድርጅቶች ረሃቡ ወደተከሰተበት ቦታ እንዳይሄዱ ተከለከለ * መንግስት ረሃቡን ለመደበቅ ከፍተኛ መመሪያ አስተላለፈ -

ሕወሓት የሚመራው የኢትዮጵያ ገዢ በኢትዮጵያ የተከሰተውን እና 15 ሚሊዮን ሕዝብን ለረሃብ ያጋለጠውን አደጋ ለመሸፋፈን ከፍተኛ የሆነ የፕሮፓጋዳ ሥራዎችን ከመስራት በተጨማሪ መረጃዎች እንዳይወጡ እስከማፈን ደረጃ መድረሱን ምንጮች ለዘ-ሐበሻ አስታውቀዋል::
ፎቶ ፋይል
ፎቶ ፋይል
የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር መስሪያ ቤት; የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስተርና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት በአንድ ላይ ተቀናጅተው እየሰሩት የሚገኘው የመረጃዎችን የማፈን ሥራ ታች ድረስ ወርዶ እስከ ፓርቲ አባላትና “ደጋፊ” የተባሉ ሰዎች ጭምር እንዲሰራበት እየተደረገ ነው:: “ረሃቡን አስታከው ለውጭ መንግስታት ሊያሳጡን የሚሞክሩትን መታገል አለብን” በሚል እነዚህ ሶስት መስሪያ ቤቶች ባወጡት መመሪያ መሠረት የውጭ ጋዜጠኞችም ሆነ የረድኤት ድርጅቶች ረሃቡ ወዳለበት ቦታ ሄደው ፎቶ እንዳያነሱ; ቭዲዮ እንዳይቀርጹ; ማንኛውንም ቃለምልልስ እንዳያደረጉ ተከልክሏል:: በተለይ ቢቢሲ በቅርቡ በኢትዮጵያ በአንድ ትንሽ ክልል ስፍራ ብቻ በቀን 2 ህፃናት በረሃቡ እየሞቱ እንደሆነ መዘገቡን ተከትሎ አለም አቀፍ ሚዲያዎች እና የአፍቃሬ ሕወሓት መንግስት ደጋፊ የሆኑ ሃገራት ሳይቀር ከዚህ ቀደም “ልማታዊ መንግስት” እያሉ ሲያሞካሹ የነበረውን አፋቸውን በመጠራረግ ረሃቡን እና መንግስት የሚከተለውን ፖሊሲ እንደገና እየመረመሩ እንደሚገኙ ዲፕሎማቲክ ምንጮች ይናገራሉ::
እንደ ዘ-ሐበሻ ምንጮች ዘገባ በቅርቡ በቢቢሲ የቀረበችውን እናት የአማራ ክልል ጋዜጠኞች አስገድደው ቃለምልልስ ያደረጓት ሲሆን በቅርቡም በመንግስት ሚዲያዎች ላይ “አልራበኝም” ዓይነት ንግግር በማስደረግ የቢቢሲን ዘገባ ለማስተባበል ሥራ እየተሰራ ይገኛል::
ከሥስቱ መስሪያ ቤቶች በተላለፈው መመሪያ መሠረት የመንግስት ሃላፊዎች ከላይ እስከታች በየሶሻል ሚዲያው በመውጣት ችግሩን መንግስት ተቆጣጥሮታል እያሉ መጻፍ እና መናገር አለባቸው:: “ተቃዋሚዎች የመንግስታችንን መልካም ገጽታ ለማጠልሸት ሆን ብለው የሚያደርጉት ሤራ ነው” እያሉም በውጭ ያሉ ኤምባሲዎችና ተላላኪዎች እንዲያነገሩ ትዕዛዝ ከመተላለፉም በላይ መንግስትን ይደግፋሉ ለተባሉ የውጭ ጋዜጠኞች ወደ ሃገር ቤት እንዲገቡና መልካሙን ነገር ብቻ እንዲዘግቡ ኢምባሲዎች መሥራት እንዳለባቸውም የወጣው መመሪያ ሲያመለክት ስለመንግስት መጥፎ ነገር ሊናገሩ ይችላሉ የተባሉ ጋዜጠኞች ግን ረሃቡ ወዳለበት ቦታ እንዳይሄዱ/ ምስል መቅረጽና ቃለምልልስ ማድረግ እንዳይችሉ የኮምዩኒኬሽን መስሪያ ቤት ፈቃድ እንዳይሰጥ ት ዕዛዝ ወርዷል::
በስልጣን ላይ ያለው መንግስት 15 ሚሊዮን ሕዝብ በመራቡ የተነሳ በወዳጅ ሃገሮቹ ሳይቀር በመጥፎ አይን እየታየመምጣቱ በስርዓቱ ውስጥ “ገጽታችን ተበላሸ” በሚል ራሱን የቻለ ሽብር ፈጥሯል:: (ዘ-ሐበሻ)
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48271#sthash.STvv23Es.dpuf

Wednesday, November 11, 2015

ለ6 ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ከ150 ሚሊዮን ብር ባላነሰ ገንዘብ የግል መኖሪያ ቤት እየተሰራላቸው ነው፡

ለከፍተኛ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት መኖሪያ የሚሆን ለእያንዳንዳቸው 25 ሚሊየን ብር የሚያወጡ፣ 6 ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች በአዲስ አበባ ሲኤምሲ አካባቢ ከፍተኛና ምቹ ቦታ ተመርጦ እየተገነቡላቸው መሆኑን የፌዴራል መንግሥት ቢሮዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተክለጻድቅ ተክለአረጋይን ለ ሸገር ኤፍ ኤም 102 ተናግረዋል።
የሕንጻ ግንባታ ስራቸው በመጠናቅ ላይ ያሉት እነዚህ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ከመሬት በታች አንድ ከመሬት በላይ ባለ ሁለት ፎቅ ሲሆኑ የመዋኛ ገንዳዎችን ጨምሮ የተለያዩ ዲዛይኖችን ( ቅርጻቅርጾችን) የሚያሟሉ አጠቃላይ ወጪያቸው ከ154 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ተናግረዋል። እነዚህ መኖሪያ ቤቶች የጡረተኛ ባለስልጣናቱ ዘላለማዊ የግል ንብረት ሆነው ያገለግላሉ ሲሉ ባለስልጣኑ ተናግረዋል።
ቀጣይ ሁለተኛ ዙር ምቹ የባለስልጣናት መንደር ግንባታም እንዲሁ በመንግስት ወጪ ይጀምራል። በትግራይ መቀሌ ለህወሃት ከፍተኛ ባለስልጣናት የተሰሩ መኖሪያ ቤቶች ሰፈር አፓርታይድ በመባል ይጠራል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ለሚኖሩበት ቤት መንግስት በወር 400 ሺህ ብር የቤት ኪራይ ወጪ ከታክስ ከፋዩ ሕዝብ እየወሰደ ይከፍላል።
ኢትዮጵያ 15 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጓቿ አሁንም በከፍተኛ ረሃብ እየተሰቃዩ ናቸው። ከግማሽ በላይ የሚሆነው ህዝብ ከአንድ ዶላር በታች ወይም ከ1 ዶላር እስከ 2 ዶላር ባለ የቀን ገቢ ይተዳደራል። አገሪቱ ከ30 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወይም ከ1 ትሪሊዮን 200 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ወይም እዳ አለባት።
ምንጭ ፤- ኢሳት

ሰማያዊ ፓርቲ ህዳር 18 ህዝባዊ ስብሰባ ጠራ • መስተዳደሩ ለ5ኛ ጊዜ ማሳወቂያ ደብዳቤውን አልቀበልም ብሏል • ‹‹መልካም አስተዳደር የሚባለው ከወሬ ያለፈ እንዳልሆነ ያሳያል›› ኢ/ር ይልቃል ጌትነት -

ሰማያዊ ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከአባላቱና ደጋፊዎቹ ጋር ውይይት ለማድረግ ህዳር 18/2008 ዓ.ም በመብራት ኃይል አዳራሽ ህዝባዊ ሰብሰባ እንደሚያደርግ ሊቀመንበሩ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ይሁንና የማሳወቂያ ደብዳቤውን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት በአካል ለማድረስ ጥረት ቢደረግም በሰራተኞቹ ዘንድ ለአምስተኛ ጊዜ ‹‹ኃላፊዎቹ የሉም፡፡ እኛ አንቀበልም›› መባላቸውን ም/ሊቀመንበሩ አቶ ነገሰ ተፋረደኝ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ‹‹ጠዋት ስንሄድ፣ ከሰዓት ኑ፣ ከሰዓት ስንሄድ፣ ስብሰባ ላይ ናቸው ጠዋት ኑ እያሉ 5 ጊዜ አንቀበልም ብለውናል፡፡›› ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ‹‹ለአንድ መስሪያ ቤት ደብዳቤ ለማድረስ በመዝገብ ቤት አሊያም በፀኃፊ በኩል መቀበል በቂ ነው፡፡ ኃላፊውን የግድ መጠበቅ አያስፈልግም ነበር፡፡›› ያሉት ኢ/ር ይልቃል ‹‹ይህ አስተዳደራዊ በሆነ መንገድ ህገ መንግስታዊ መብትን የሚያግዱበት ስልት ነው›› ብለዋል፡፡ ሊቀመንበሩ አክለውም ‹‹ስለመልካም አስተዳደር በሚያወሩበት በአሁኑ ወቅት አስተዳደራዊ በሆነ መንገድ መብትን እያገዱ መቀጠላቸው መልካም አስተዳደር የሚባለው ከወሬ ያለፈ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው›› ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት ለ5ኛ ጊዜ የሰማያዊ ፓርቲን የስብሰባ ማሳወቂያ ደብዳቤ በአካል መቀበል ባለመፈለጉ ፓርቲው ደብዳቤውን በሪኮመንዴ ለመላክ መገደዱን ፓርቲው ለፅ/ቤቱ በላከው ደብዳቤ ላይ አመላክቷል፡፡ በዚህም መሰረት ዛሬ ህዳር 1/2008 ዓ.ም ፓርቲው ማሳወቂያውን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት በሪኮመንዴ መላኩን ሊቀመንበሩ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48184#sthash.cioSnkrv.dpuf

Tuesday, November 10, 2015

በሰሜን ጎንደር ዞን በርካታ የልዩ ሃየል አባላትና ሰላማዊ ዜጎች ተገደሉ

ኢሳት ዜና :-ከቅማንት ብሄረሰብ ጥያቄ ጋር በተያያዘ በአርሶ አደሩና በክልሉ ልዩ ሃይል መካከል ከማውራ 15 ኪሜ ርቃ በምትገኘዋ ሮቢት አካባቢ እንዲሁም በላይ አርማጭሆ ዋና ከተማ ትክል ድንጋይ ከፍተኛ ውጥረት ነግሶአል። እስከትናንት ድረስ በአርሰዶ አደሩና በልዩ ሃይል መካከል በተደረገ የተኩስ ለውጥጥ ከ100 በላይ የልዩ ሃይል አባላት ሲገደሉ፣ ከ36 ያላነሱ ንጹሃን ዜጎች ደግሞ በልዩ ሃይል አባላት ተገድለዋል። ዛሬ በበርካታ መኪኖች የተጫኑ የመከላከያ ሰራዊት አባላትና የልዩ ሃይል አባላት ከባድ መሳሪያዎችን ሳይቀር ወደ ትክል ድንጋይ በማስገባቱ ህዝቡ ቤቶቹን ዘግቶ ከመቀመጡም በላይ፣ ትምህርት ቤቶች የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የንግድ ድርጅቶች በሙሉ ተዘግተዋል። የልዩ ሃይል አባላት የተገደሉባቸውን ባልደረቦቻቸውንሊበቀሉ ነው በሚል የቻለው ወደ ጫካ መውጣቱንም ያካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ተናግረዋል። በርካታ የተገዱ የልዩ ሃይል አባላት በአዘዞ የመከላከያ ካምፕ እና በጎንደር ሪፈራል ሆስፒታል መወሰዳቸውን የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። የልዩ ሃይል አባላት እህትማማች ሴቶችን በጩቤ ገድለው መገኘታቸውን የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ አስነዋሪ በሆነ መልኩ ባለትዳር ሴቶችን ሳይቀር መድፈራቸው የህዝቡን ቁጣ አባብሶታል በማለት ነዋሪዎች ተናግረዋል። ጥያቄውን ከሚያስተባብሩ ወገኖች መካከል አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ሰው ለኢሳት እንደተናገሩት በህዝቡ በኩል ከልዩ ሃይል አባላት መካከል 102 ከህዝቡ ደግሞ 33 ሰዎች ተገድለዋል ይላሉ።

Monday, November 9, 2015

በጎንደር ጭልጋና ትክል ድንጋይ መካከል በሚገኝ ማውራ የተባለ ቦታ በገበሬዎችና በህወሓት ልዩ ኃይል ጦር መካከል ውጊያ ተካሄደ - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48081#sthash.FOzLOtJp.dpuf

በጎንደር ጭልጋና ትክል ድንጋይ መካከል በሚገኝ ማውራ የተባለ ቦታ ላይ በአካባቢው ገበሬዎችና በህወሓት ልዩ ኃይል ጦር መካከል ከፍተኛ ግጭት ተቀስቅሶ ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ፍልሚያው የተጀመረው ትናንት ረፋድ ላይ ሲሆን አሁንም ተባብሶ እንደቀጠለ ነው፡፡ አካባቢው ትንሽ እንኳን ፋታ በሌለው ተከታታይ የጦር መሳሪያ ፍንዳታ ድምፅ እየተናጠ ይገኛል፡፡
እስካሁን ድረስ በደረሰን መረጃ መሰረት በትንሹ 5 የልዩ ኃይሉ ጦር አባላት ተገድለዋል ከ9 በላይ ደግሞ ቆስለዋል፡፡ ነገር ግን በማውራ ገበሬዎች በኩል የደረሰ ጉዳት ይኑር አይኑር ምንም የታወቀ ነገር የለም፡፡
የጎንደር-ጭልጋ ማውራ ገበሬዎችንና የህወሓትን ልዩ ኃይል ለመዋጋት ያበቃቸው ምክንያት ምን እንደሆነ በውል ተለይቶ አልታወቀም፤ ነገር ግን በጭልጋና አካባቢው ቀደም ሲል የተነሳው የብሄር ጥያቄ ሳይሆን እንዳልቀረ ምንጮቻችን ያላቸውን ግምት አስቀምጠዋል፡፡
በተጨማሪም በጭልጋና አካባቢው የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከግጭቱ አንድ ሳምንት ቀደም ብለው መዘጋታቸውና ሙሉ በሙሉ ማስተማር ማቆማቸው ተገልጿል፡፡
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48081#sthash.FOzLOtJp.dpuf

Monday, November 2, 2015

የአዲስ አበባና አካባቢዋ ወተት ከፍተኛ መርዛማ ህፃናትን የሚያቀጭጭ እና የሚያሳጥር ኬሚካል አለው ተባለ -

ነገሩ፣ ለዘመናት ከምናውቀው እውቀት የተለየ በመሆኑ ግራ ማጋባቱ አይቀርም፡፡ እስካሁን ለሕፃናት ዕድገትና ጥንካሬ ጥሩ ነው በማለት ሕፃናትን ስንመግብ የኖርነው ወተት፤ በተቃራኒው ለሕፃናት ዕድገት ጥሩ አይደለም፤ ያቀጭጫቸዋል ቢባሉ ምን ይላሉ? የሚገርም ነው!ሰሞኑን በሂልተን ሆቴል ሲካሄድ በቆየው 4ኛ የአፍሪካ የምግብና የኑትሪሽን ፎረም ላይ አንድ ተመራማሪ፤ በመርዛማ ኬሚካሎች (አልፋ ቶክሲን) ላይ ያደረጉትን የምርምር ውጤት ሲያቀርቡ፤ እግረ መንገዳቸውን የአዲስ አበባና አካባቢዋ ወተት ከመጠን በላይ መርዛማ ኬሚካል (አልፋ ቶክሲን) እንዳለው ገልፀዋል፡፡ ተመራማሪው ዶ/ር አሻግረ ዘውዱ፤ ዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት (ILRI) ባወጣው ሪፖርት፤ በ2016 በአዲስ አበባና አካባቢዋ ባደረገው ጥናት፣ ከተሰበሰቡት 140 ናሙና ከ90 በመቶ በላይ ዓለምአቀፍ ሕግ ከሚፈቅደው በላይ መርዛማ ኬሚካል (አፍላቶክሲን M1) እንዳለው ማስታወቁን ተናግረዋል፡፡ አልፋ ቶክሲን በሻጋታ ምክንያት የሚፈጠር መርዛማ ኬሚካል ነው ያሉት ተመራማሪው፤ መርዛማ ኬሚካሉ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ቢጐዳም በሕፃናት ላይ የበለጠ ጉዳት ያደርሳል፣ መቀጨጭና መጫጫት ያስከትላል፡፡ በዕድሜያቸው ልክ ቁመታቸው አያድግም፡፡ በኢትዮጵያ 40 በመቶ ሕፃናት ቀጫጫ ናቸው፡፡ መርዛማ ኬሚካሉ ከማጫጨት በተጨማሪ ረዥም ዕድሜ ሲቆይ የጉበት ካንሰር ያስከትላል ብለዋል፡፡ አልፋ ቶክሲኖች የተለያዩ ናቸው፡፡ እህል ላይ የሚገኙትና በይበልጥ የሚታወቁት 4 ናቸው፡፡ እነሱም B1 B2 G1 G2 ይባላሉ ያሉት ዶ/ር አሻግሬ፤ እህሉ ላይ የሚገኘውን B1 አልፋ ቶክሲን የበላ ከብት በሰውነቱ ውስጥ በሚካሄደው ሜታቦሊዝም፣ B1 መርዛማ ኬሚካል ወደ M1 ይቀየራል፡፡ ኤች አይ ቪ ከእናት ወደ ልጅ እንደምታስተላልፍ እናት ለልጇ ጡት ስታጠባ መርዛማውን ኬሚካል ወደ ሕፃኑ ታስተላልፋለች፡፡ ከብትም እንደዚሁ፡፡ ሕፃኑ በአልፋ ቶክሲን የሚጠቃው፣ ጡት መጥባት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡ ወተት ለሕፃናት ዕድገት ጥንካሬና ውፍረት ጥሩ ነው ስለሚባል ወተት እየጠጡ ያድጋሉ፤ ለአልፋ ቶክሲን እየተጋለጡ ናቸው ያሉት ተመራማሪው፤ “በወሎ ድርቅ ጊዜ የእርጐ ፈንገስ የሚባል ነገር ተፈጥሮ ነበር፡፡ የሚበላ ነገር ሲጠፋ ፈንገስ የተቀላቀለበት ምግብ በልተው፤ ጋንግሪን ተፈጥሮባቸው እግራቸው የተቆረጠ ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡” ብለዋል፡፡ ዓለምአቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ያወጣውን መረጃ በተመለከተ፤ መንግስት ከኢትዮጵያ ፐብሊክ ኢንስቲትዩት፣ የደረጃዎች ምዘናና ተስማሚነት፣ የምግብ ሳይንስና ኑትሪሽን ማዕከል እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ ባለሙያዎች ጥናት እንዲያደርጉበት ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡ ውጤቱ ልክ እንደተባለው ከሆነ ምን እናድርግ? በማለት ምክክር ይደረጋል ያሉት ዶ/ር አሻግሬ፤ ልክ ካልሆነ ደግሞ ኅብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ ይደረጋል ብለዋል::   ምንጭ አዲስ አድማስ ጋዜጣ (ዛሬ በአዲስ አበባ ታትሞ የወጣ) - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/47909#sthash.9lxCGAJc.dpuf