ለከፍተኛ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት መኖሪያ የሚሆን ለእያንዳንዳቸው 25 ሚሊየን ብር የሚያወጡ፣ 6 ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች በአዲስ አበባ ሲኤምሲ አካባቢ ከፍተኛና ምቹ ቦታ ተመርጦ እየተገነቡላቸው መሆኑን የፌዴራል መንግሥት ቢሮዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተክለጻድቅ ተክለአረጋይን ለ ሸገር ኤፍ ኤም 102 ተናግረዋል።
የሕንጻ ግንባታ ስራቸው በመጠናቅ ላይ ያሉት እነዚህ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ከመሬት በታች አንድ ከመሬት በላይ ባለ ሁለት ፎቅ ሲሆኑ የመዋኛ ገንዳዎችን ጨምሮ የተለያዩ ዲዛይኖችን ( ቅርጻቅርጾችን) የሚያሟሉ አጠቃላይ ወጪያቸው ከ154 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ተናግረዋል። እነዚህ መኖሪያ ቤቶች የጡረተኛ ባለስልጣናቱ ዘላለማዊ የግል ንብረት ሆነው ያገለግላሉ ሲሉ ባለስልጣኑ ተናግረዋል።
ቀጣይ ሁለተኛ ዙር ምቹ የባለስልጣናት መንደር ግንባታም እንዲሁ በመንግስት ወጪ ይጀምራል። በትግራይ መቀሌ ለህወሃት ከፍተኛ ባለስልጣናት የተሰሩ መኖሪያ ቤቶች ሰፈር አፓርታይድ በመባል ይጠራል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ለሚኖሩበት ቤት መንግስት በወር 400 ሺህ ብር የቤት ኪራይ ወጪ ከታክስ ከፋዩ ሕዝብ እየወሰደ ይከፍላል።
ኢትዮጵያ 15 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጓቿ አሁንም በከፍተኛ ረሃብ እየተሰቃዩ ናቸው። ከግማሽ በላይ የሚሆነው ህዝብ ከአንድ ዶላር በታች ወይም ከ1 ዶላር እስከ 2 ዶላር ባለ የቀን ገቢ ይተዳደራል። አገሪቱ ከ30 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወይም ከ1 ትሪሊዮን 200 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ወይም እዳ አለባት።
ምንጭ ፤- ኢሳት
No comments:
Post a Comment